Monday, November 30, 2015

እድል ፈንታችን



ሰኞ ሕዳር 20 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት
ከወንድም እሸቱ

      ጥያቄ፡ - ‹‹ለብዙ  ጊዜ ነገሮች  ላይ እድለኛ  እንደሆንኩ ይሠማኝ ነበረ አሁን ነገሮች በተቃራኒዉ ሆኑብኝ ቀላል ሙከራየ ሁሉ ይከሽፋሉ ምን ይሻለኛል››፡፡

        ወንድም እሸቱ በሙሉ ፈቃደኝነት ችግርህን በጋራ መፍትሔ እንድንፈልግበት ልታካፍለን ስለወደድክ አስቀድሜ ላመሰግንህ እወዳለሁ፡፡ በማስከተል ችግርን በፍጹም ግልጽነት መናገር መቻል የመፍትሔው ትልቅ አካል እንደሆነ እያስታወስኩህ፤ መፍትሔ ልናገኝባቸው እንችላለን ወደምላቸው አሳቦች ከመሄዴ አስቀድሞ ጥቂት ጥያቄዎችን ልጠይቅህ (ለእሸቱ)፡፡

·        እድልና እድለኛነት ለአንተ ያላቸው ትርጉም ምንድነው?
·        ለአንተ እድለኛ የመሆንና ያለመሆን መለኪያው (መገለጫው) ምንድነው?
·        እድለኛ እንደነበርክ በተሰማህ ጊዜና አሁን እንዳልሆንክ በሚሰማህ ጊዜ በኑሮህ ላይ ያለው ተግባራዊ ልዩነት ምን ይመስላል? (ብትችል በዝርዝር ለመጻፍ ሞክር)
·        ሙከራዎችህ በምን ላይ ያተኮሩ ነበሩ? ትክክለኛነታቸውንስ እንዴት ትመዝነዋለህ?
·        ሙከራዎችህ ለሚያስከፍሉት ዋጋ አንተ ጋር ያለው ዝግጅት በቂ እንደ ነበር ታስባለህ? ክንውናቸውንስ የምትመዝንበት መንገድ ምን ይመስላል?
·        እንደከሸፉብህ በምታስባቸው ነገሮች፤ ምክንያቱ ምን እንደ ሆነ አጥርተህ ለማወቅ ሙከራ አድርገሃል? ላልተሳኩልህ ነገሮች የአንተ ድርሻ የቱ ጋር? እና ምን ያህል? እንደሆነ ለመረዳት ሞክረሃልን? ሌሎች ነገሮች በዚህ ውስጥ ያላቸውንስ ድርሻ መለየት ችለሃልን?

           ከላይ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት ጥያቄዎቹ በአንተ ውስጥ ያለውን ትክክለኛ ምልከታ እንድታስተውል ይረዱሃል፡፡ ክፍተቶችህ የቱ ጋር እንደሆኑም ለመለየት ይጠቅሙሃል፡፡ ከጥያቄህ እንደምረዳው በእድል የምታምን ይመስላል፡፡ ‹‹እድል›› የብዙ ሰዎች የመከራከሪያ አሳብ ነው፡፡ አንዳንዶች እድል የሚባል ነገር የለም ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ እድል ከሌለህ ምንም የለህም ይላሉ፡፡ ለዚህም የተለያዩ ምክንያታዊ አሳቦች ሲቀርቡ እንመለከታለን፡፡ ነቢዩ ግን እንዲህ ብሏል (መዝ. 15)፡ -
      



        ችግር ብለህ ወዳካፈልከን ስንመጣ፤ የምንኖርበት ዓለም ማግኘትና ማጣት፤ ክብርና ነቀፋ፤ ብርታትና ድካም በፈረቃ የሚስተናገዱባት መሆኗን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ በደስታ ውስጥ የሰነበተ አያዝንም ማለት አይደለም፡፡ በመከራ የሚያልፍም ወደ ዕረፍት አይመጣም ማለት አይደለም፡፡ ሐዋርያው ‹‹መዋረድንም አውቃለሁ፤ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ›› /ፊል. 4፡12/ እንዳለ፤ በዚህ ዓለም ላይ ያለውን ቋሚ ትምህርት ልብ እንድትል እንመክርሃለን፡፡
    
        ተወዳጅ ሆይ፤ ከዚህ በፊት በማታውቀው አሁን ግን እንግዳ እንደሆነብህ በምትነግረን አጋጣሚ ውስጥ ያለውን ትምህርት በቸልታ አትለፈው፡፡ ‹‹ይሠማኝ ነበረ›› ስትል ምን አልባት ስሜትህና በሕይወትህ እየሆነ ያለው ነገር ምናልባት የተራራቀ እንደሆነ ለማጤን ሞክር፡፡ አሁንም ከሚመጣው ምላሽ መማርህን ቀጥል፡፡ ተግባራዊ ኑሮ ትልቅ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ቀለም ከወረቀት አስማምተን ከምንማረው የበለጠ የምናልፍባቸው መንገዶች የሚያስተምሩን ነገር ወደ ጥንካሬ እንድናመራ ይረዳናል፡፡
      
        ‹‹በደረቅ ምድር እንደሚያልፉ በኤርትራ ባሕር በእምነት ተሻገሩ፤ የግብፅ ሰዎች ግን ሲሞክሩ ተዋጡ›› /ዕብ. 11፡29/ ተብሎ እንደተጻፈ፤ በእምነት መኖርን ተለማመድ፡፡ ነገሮችን እምነት ላይ ሆኖ ማድረግና፤ ሙከራዎቻችንን ማመን ፍጹም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ እምነት ወደ መሻገር ሲያመጣን፤ የሥጋና የደም ሙከራ ግን የምድር በሆነው ነገር መዋጥን ያስከትላል፡፡ ጠንካራ እምነት በውስጥህ እንዲኖር ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ያለህን ግንኙነት ለማጠንከር ትጋ፡፡

         መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ በሳምንት ምን ያህል ጊዜ ትመድባለህ? በውስጡ የምታገኘውን ቅዱስ አሳብ ለማሰላሰልስ ምን ያህል ጊዜ ትወስዳለህ? አስታውስ! እምነት ከመስማት ነው፤ መስማትም በእግዚአብሔር ቃል /ሮሜ 10፡17/፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በምትናገረውና በምትሠራው ነገር ትክክለኛ ምሪት ይሰጥሃል፡፡ አንድ ነገር ለመሥራት (አንተ እንዳልከው ለመሞከር) ስትዘጋጅ ወደ ተግባር ከመሄድህ አስቀድሞ ከእግዚአብሔር ቃል ጥቂት የማንበብ ልማድ ይኑርህ፡፡

         በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ብትሆን የገባህ ብቻ ሳይሆን ያልገባህም ነገር በዙሪያህ እንዳለ ልትረዳ ያስፈልጋል፡፡ ጸሎት በድንግዝግዝ ውስጥ አጥርተን እንድናይ ያስችለናል፡፡ ዕይታችን ውስን የሆነ እኛ የሚሰወረው አንዳች ነገር ከሌለ ከእግዚአብሔር ጋር ዘወትር መነጋገርን ልምዳችን ልናደርግ ግድ ያስፈልጋል፡፡ ከምታየው አልፎ ከሚያይልህ ጌታ ጋር ሁልጊዜ በጸሎት ፊቱ ተመላለስ፡፡

        አይተንና ዳሰን ከምንረዳው ያለፈ መንፈሳዊ ውጊያ ባለባት ዓለም ውስጥ እንዳለን መረዳታችን በእጅጉ ጠቃሚ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ወደ ውስጥና ወደ ውጪ አጥርተህ እንድትመለከት እመክርሃለሁ፡፡ የተገለጠ ነገር ካለ እንድታስተካክ፤ ለተሰወረው ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት እንድትንበረከክ እመክርሃለሁ፡፡ ዘጠኝ ዳቦ ከመላስ . . እንዲሉ፤ የሙከራ መንገዶችህን ቆም ብለህ ብትገመግማቸውና አንድ ነገር ላይ ጉልበትህን ብታውል ትርፍ ከሚመስል ኪሳራ ራስህን ታድናለህ፡፡

        ያልኩህን አስታውስ! ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ፍጠር፤ ቅዱሱን ቃል መሰረት አድርገህ በጸሎት ትጋ (ለምሳሌ፡ በእምነት፤ በመንፈስ፤ እንደ ፈቃዱ፤ በኢየሱስ ስም ጸልይ)፤ ብዙ ከመሞከርና እድለኝነት ላይ ከመደገፍ ይልቅ ልትሠራ በምትችለው ጥቂት ተግባር ላይ ትኩረትህን አድርግ፡፡ ችግሩ ላይ ሳይሆን መፍትሔው ላይ ብዙ ጊዜ ውሰድ፡፡ በትክክል ሊረዱህና በተሻለ ሊያግዙህ የሚችሉትን ሰዎች (በቅርብህ ካሉት) ለመለየትና ለመመካከር ፈቃደኛ ሁን፡፡

        እንግዲህ የቤተ ፍቅር ቤተ ሰዎች ሁሉ ችግር ባልከን ነገር ላይ መፍትሔ ሆኖልህ ‹‹እግዚአብሔርን አመስግኑልኝ›› የምትልበትን ጊዜ በእምነት አብረንህ እንጠባበቃለን፡፡ በክርስቶስ በሆነው ፍቅር እጅግ እንደምንወድህም አንሸሽግህም፡፡ ወንድማችን፤ የእግዚአብሔር ኃይል በሥራህ ሁሉ ክንድና መከናወን እንዲሆንልህ እየጸለይን አንተንም የአንተንም ለታመነው እግዚአብሔር እጅ አሳልፈን እንሰጣለን፡፡//
   
        /የቤተ ፍቅር ቤተ ሰዎች፤ በኢ-ሜል ከተላከልን ጥያቄ የተወሰደ መሆኑን እንገልጻለን/ 
                                             ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment