Sunday, May 25, 2014

ቀላል ነው (ካለፈው የቀጠለ)

                   Please Read in PDF: Kelal new (yeketele)
                        እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት

     ‹‹ታላላቆችም ብላቴኖቻቸውን ወደ ውኃ ሰደዱ፤ ወደ ጕድጓድ መጡ፤ ውኃም አላገኙም፥ ዕቃቸውንም ባዶውን ይዘው ተመለሱ፡፡ አፈሩም ተዋረዱም ራሳቸውንም ተከናነቡ።›› (ኤር. 14÷3)፡፡

        አቤት ምድረ በዳ፤ አቤት ቃጠሎ፤ አቤት የውኃ ጥም፤ አቤት አቅም ማጣት፤ አቤት ሥጋት፤ አቤት መጨካከን፤ አቤት መጣደፍ፤ አቤት መተራመስ፤ አቤት አዙሪት፤ አቤት መዛል፤ አቤት እፍረት፤ አቤት መዋረድ፤ አቤት መደበቅ፤ አቤት አለመፈናፈን፤ አቤት ማለክለክ፤ አቤት የዕንባ ጅረት፤ አቤት የዓይን መጠውለግ፤ አቤት የማይቆጠር በድን፤ አቤት የተማሱ ጉድጓዶች፤ አቤት አፉን የከፈተ መቃብር፤ አቤት የሕፃናት ጩኸት፤ የአዛውንቶች ሲቃ፤ አቤት ሰይፍ፤ አቤት ቸነፈር፤ አቤት መበተን፤ አቤት ክሳት፤ አቤት መከራና ሰቆቃ!

        የተነሣንበት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ወደ ኤርምያስ ስለ ድርቅ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ አፈሩ . . . ተዋረዱ . . . ራሳቸውንም ተከናነቡ፤ የሚሉትን ቃላት ስናነብ፤ ልክ በዚያ ዘመን እንደ ነበረ ትኩስ ሀዘንተኛ የከበዱብን ነገሮች ወደ ፊታችን ይመጣሉ፡፡ ማንም ሰው በሕይወቱ እንዲህ ያሉ ውርደቶች ባይሆኑ ጽኑ መሻቱ ነው፡፡ ይሁዳ ያለቀሰችበት፤ ደጆችዋም ባዶ የሆኑበት፤ ብርሃኗን የተነጠቀችበት፤ ጩኸቷን አብዝታ ያሰማችበት የጭንቅ ጊዜ፤ የኑሮ በረሃዎቻችንን ግልጥልጥ አድርጎ ያሳየናል፡፡

       እግዚአብሔር የከለከለንን ማንም እንደማይሰጠን፤ የዘላለም አምላክ ያላሰበንን ማንም እንደማያስበን፤ የአማልክት አምላክ ያልራራልንን ማንም እንደማይራራልን፤ የጌቶች ጌታ ያልሰበሰበንን ማንም እንደማይሰበስበን፤ የነገሥታት ንጉሥ ያልሞላውን ጉድለት ማንም እንደማይሞላው፤ እርሱ ከጨከነብን የማንም ፊት እንደማይበራልን የምንረዳበት ክፍል ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የእግዚአብሔርን ቁጣ በአንድ መንገድ ብቻ እንደምናየው ይሰማኛል፡፡ ከቅጣትና ከጥፋት መልእክቱ አንፃር! ዳሩ ግን እንደዚያ ብቻ መልእክት እንዳለው እንዳናስብ የሚረዱን የእግዚአብሔር ትምህርቶች በቃሉ ውስጥ አሉልን፡፡ በዚሁ በነቢዩ በኤርምያስ የተግሣጽ ክፍል ውስጥ ውሸተኛ ነቢያት በእግዚአብሔር ስም ያልተላኩትን፤ ያላዘዛቸውን፤ ያልተናገራቸውን ግን የልባቸውን ሽንገላ ለሕዝቡ ሲናገሩ እናያለን፡፡ ሰላምን ለሕዝቡ ቢናገሩም፤ በረከትን ለሕዝቡ ቢተነብዩም እንደዚያ ግን አልሆነም፡፡


       የእግዚአብሔር እጅ በሕዝቡ ላይ ከብዳ ነበር፡፡ በዚህ ቁጣ ውስጥ እግዚአብሔር ምን እያለ ነው? እግዚአብሔር ያለንን ካልሰማነው፤ ሌሎች ያሉንን እርሱ ፉርሽ ያደርገዋል፡፡ እሰጣችኋለሁ ያለንን ለመቀበል እጆቻችንን ወደ እርሱ ካልዘረጋን፤ ከሌላ ልንቀበል የምንከጅለውን ይሰበስበዋል፡፡ እግዚአብሔርን ስለ አማራጭ ካወራነው፤ እራሱን ከመካከል ያወጣና ምርጫ ያልናቸውን አቅም ያሳየናል (አምላኬ ሆይ፤ ከልቤ በዕንባ እለምንሃለሁ እንዲህ ያለ ቅሌት ውስጥ አታግኘኝ)፡፡ ማንም የተናገረውን እግዚአብሔር ይገለብጠዋል፡፡ እርሱ ያለው ብቻ ይጸናል፡፡ ታላላቆች እግዚአብሔር የሚለውን ትተው፤ ሐሰተኞች ነቢያት የተናገሩትን አምነው፤ ልጆቻቸውን መቅጃ ዕቃ አስይዘው ወደ ውኃ ጉድጓድ ላኳቸው ግን ውጤቱ ‹‹ባዶ›› ነበር፡፡ ሰው እንዴት ሰውን አምኖ ይሰማራል?     

       ከእግዚአብሔር የሚገኘውን ከማን እንፈልገዋለን፡፡ እርሱ ያልሰጠንን መልአክቱ አይሰጡንም፡፡ ሰው በራሱ መንገድ ሲሄድ ነገሮች ቀላል አይሆኑም፡፡ መላላጥ፤ መጋጋጥ፤ ማዘን መሸማቀቅ ሰው ሲዘራ ሲያጭድ የሚኖረው ነው፡፡ እግዚአብሔር ያቀለለውን ማን ያከብደዋል? እርሱ የጨከነበትንስ ማን ሊያቀለው ይችላል? ‹‹ሙሴና ሳሙኤል በፊቴ ቢቆሙም፤ ልቤ ወደዚህ ሕዝብ አይዘነብልም፤ ከፊቴ ጣላቸው ይውጡ›› (ኤር. 15÷1) ብሎ እግዚአብሔር የተናገረው ለሕዝቡ የአማራጮቻቸው አቅም በተግባር እንዲታወቅ ነው፡፡ ታዲያ ስለት የበላውን፤ ቸነፈር ያከሳውን፤ ሬሳው አፈር ላይ የተጎተተውን ያንን ሕዝብ ማን ሊታደገው መጣ? በእግዚአብሔር ላይ ለምንሠራው አመጽ፤ ራሱ እግዚአብሔር መፍትሔ መሆኑ አምላክነቱን እናስተውል ዘንድ ትምህርት አይደለምን? የሸሸነው እግዚአብሔር ውስጥ የሚያቀርብ፤ ያሳዘነው እርሱ ውስጥ የሚያስደስት፤ ቸል ያለው እግዚአብሔር ውስጥ እረፍት መኖሩ ስንፍናችንን ምን ያህል ይወቅሰው?

      ተወዳጆች ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ሙሴና ሳሙኤል እንኳን አማራጭ ሆነው አይቀርቡም፡፡ እራሳቸውን እያታለሉ፤ የገዛ ስብከታቸው ከእግዚአብሔር አሳብ ጋር መናቆሪያ ለሆናቸው ሰዎች ይህ እውነት በልባቸው እንዲበራ ጽኑ ጸሎቴ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቁጣዎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስንመለከት ከትክክለኛው መልእክቱ ጋር ለመገናኘት መጠንቀቅ አለብን፡፡ እርሱ ብቻውን አምላክ ነው፡፡ የእግዚአብሔር እጅ በሌለበት ሁኔታ ጉድጓዶችም፤ መቅጃዎችም፤ እጆችም ባዶ ናቸው፡፡ ዳሩ ግን ‹‹እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፡- ነፋስ አታዩም፤ ዝናብም አታዩም፡፡ ይህ ሸለቆ ግን ውኃ ይሞላል፤ እናንተም ከብቶቻችሁም እንስሶቻችሁም ትጠጣላችሁ፡፡ ይህም በእግዚአብሔር ዓይን ቀላል ነገር ነው››  (2 ነገ. 3÷17)፡፡ ከእግዚአብሔር ቃል ከወጣ የኤዶምያስ መንገድ ይታዘዛል፤ ምድሪቱም በውኃ ትሞላለች፡፡ ያን ጊዜ መቅጃዎች ሁሉ በውኃ ይሞላሉ፡፡ ጉድጓዶች ሁሉ ይረካሉ፡፡ በእግዚአብሔር ዓይን ነገሮች ቀላል ናቸው፡፡ የሰው ዓይን ከዚህ ዓይን ላይ ሊነቀል ይገባልን? የኔ ጌታ በአንተ ዓይኖች ውስጥ ብዙ ጉዳዮችን፤ አሁንም እንኳ አይቻቸው ቀለዋል፡፡ ምስጋናህ ይብዛ፤ መመለክህ ይጨምር፤ ክብር ላንተ ብቻ ነው፡፡

      በጉዳዮቻችሁ ላይ ምልክትንና አቅጣጫን ትፈልጉ ይሆናል፡፡ ጉድለታችሁ እንዲሞላ፤ ዕንባችሁ እንዲታበስ፤ ቋጠሯችሁ እንዲፈታ፤ መለወጣችሁ እንዲመጣ ምንም አይነት ምልክት አጥታችሁ ይሆናል፡፡ ዙሪያ ወጣ ገባው ምንም ነገር አያሰማችሁ ይሆናል፡፡ ነፋስ የለም፤ ዝናብም የለም፤ እግዚአብሔር ግን አለ፡፡ አደርጋለሁ ያሉ የሉም፡፡ እመጣለሁ ያሉ ቀርተዋል፡፡ የታመናቸው ከድተዋል፡፡ እንኳን ለሀዘናችን ለደስታችንም ታዳሚ ጠፍቶ ይሆናል፡፡ ባዶ ወንበሮች በዝተው አያችሁን? ጌታ ይሞላዋል፡፡ አሻግራችሁ ማዶ ማዶ አትዩ፡፡ ጥሩ የለበሰ፤ በደንብ የተጫማ፤ ስጦታ የታቀፈ፤ ፊታችሁን ለማየት የተቻኮለ በእናንተ አቅጣጫ አልታይ አላችሁን? ይኼው የሾህ አክሊል የደፋ፤ ይኼው የተራቆተ፤ ይኼው የደምላብ ወዝ የሆነው፤ ደም ግባት ያጣ፤ የሕማም ሰው፤ ደዌንም የሚያውቅ፤ ችንካር እጁን የሸፈነው ይኼው መድኃኒት፤ ወዳጅ፤ ፈውስ፤ እንጀራ፤ ውኃ፤ ብርሃን፤ እረኛ፤ ትንሣኤና ሕይወት ክርስቶስ ኢየሱስ!

      ክርስቶስ ላላቸው አፈሩም፤ ተዋረዱም፤ ራሳቸውንም ተከናነቡ አይሆንም፡፡ በእግዚአብሔር ልጅ ላይ የጸና እምነት ላለው ሰው ‹‹እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል›› (መዝ. 1÷3) ነው፡፡ በእፍረትና በውርደት በተሞላው ዓለም ውስጥ ክርስቲያን በእግዚአብሔር የታመኑ የእውነት ቃላት ላይ ልቡን ይጥላል፡፡ እግዚአብሔር የነገረውንም በጽናት ይጠብቃል፡፡ ብርሃኑን በሰው ሁሉ ፊት እየገለጠ ይኖራል እንጂ ራሱን በጉድለት አይከናነብም፡፡ ወደ ጉድጓዶች መቅጃ ይዞ የሚሄድ ሳይሆን የሕይወት ውኃ ከሆዱ የሚፈልቅበት (ዮሐ. 7÷38)፤ ለሌሎች የሚተርፍ ምንጭ ነው፡፡

       የተነሣንበትን ርዕስ የምንፈጽመው፤ በአዲስ ኪዳን የጥላውን አካል በሚያሳየን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው፡፡ ‹‹አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል። ለአምላካችንና ለአባታችንም እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን›› (ፊል. 4÷19-20)፡፡

1. ባለ ጠጋ አምላክ

        ምድሪቱ ላይ የብዙ ሀብታሞች የሀብት ልክ ታውቆ ደረጃ ወጥቶለታል፡፡ በዚህ አመት አንዱ ከፍ ሌላው ዝቅ ሊል፤ በቀጣይ ዝቅ ያለው ከፍ፤ የበለጠው ደግሞ ሊያንስ ይችላል፡፡ አንድ የአንደኛ ብቻ አይደለችም፡፡ ሰው ፈረቃው ብዙ ነው፡፡ በሽፍት ቀዳሚ፤ በሽፍት ተከታይ ሆነን የምንገፋፋበት የኑሮ ስርዓት ውስጥ ነን፡፡ አምላካችን ባለ ጠጋ አምላክ ነው፡፡ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፡፡ ሐዋርያው አምላኩን ባለ ጠጋ ይለዋል፡፡ ለእኛም እግዚአብሔር እንደዚያው ነው፡፡ የእግዚአብሔር የባለ ጠግነቱ መጠን ስንት ነው? የምድሩ ቢሰፈር፤ የሰማዩ ቢለካ ዋጋው ስንት ነው? በገንዘብ ቢተመን እግዚአብሔር ስንት ያወጣል? ፀሐይ ብቻ ስንት ብር ትሆናለች? እነ ማርስ፤ እነ ጁፒተር ሌሎቹም ፕላኔቶች፤ አዲስ ግኝቶቹን ጨምሮ ገበያ ላይ ስንት ይገመታሉ? ተመስገን ባለ ጠጋው እግዚአብሔር! 

2. ያልተተመነ መጠን

       ባለ ጠግነት ልክ ቢኖረውም፤ ተግባር ላይ የሚውለው ግን እየተመጠነ ነው፡፡ ያለን ሁሉ አይወድምም፡፡ ምክንያቱም የእኛ ነገር ላይ ማለቅ አለብን፡፡ ስንሰጥ አስቀርተንም ነው፡፡ ስናደርግ ሰስተንም ነው፡፡ ለበኋላ እና ለነገ የእጃችን ፍሬኖች ናቸው፡፡ አንዱ ሲያፍስ ሌላው እጅ ይቆነጥራል፡፡ እንደ ባለ ጠግነቱ ቢያደርግ የማይጎድለው፤ ነገዎች የማያሠጉት እግዚአብሔር ነው፡፡ መጠኖች ተመን አላቸው፡፡ በመጠኑ ልክ ይተመናል፡፡ ከእግዚአብሔር የተቀበልነው፤ ባለ ጠግነቱ ያደረገልንን በምንም አንተምነውም፡፡ እግዚአብሔር ያለውን ሳይሆን ካለው የሰፈረልንንም ገና ተረድተን አልጨረስነውም፡፡    

3. በክብር መሞላት

       ክብራቸው ተገፎ፤ ስማቸው ተነቅፎ፤ ሞራላቸው ተነክቶ ጉድለታቸውን የሚሞሉ፤ ኑሮአቸውን የሚያሸንፉ ብዙ ሰዎችን እናውቃለን፡፡ እንጀራ ነው! በሚል ርዕስ ነፍሳቸውን ሳይቀር የተነጠቁ ብዙ ወገኖች አሉ፡፡ አዎ በውርደትና በእፍረት ውስጥም ማግኘት ይኖራል፡፡ አምላካችን በክብር የሚሞላ ነው፡፡ እያዋረደ፤ እያንቋሸሸ፤ እያመመ የሚሞላ እግዚአብሔር የለንም፡፡ በክብር ጉድለታችን ይሞላል፡፡ ማጣታችን ያገኛል፡፡ ሕመማችን ይፈወሳል፡፡ ታሪካችን ይቀየራል፡፡

4. በክርስቶስ ኢየሱስ

         ሙላታችን ምንጩ ምን እንደ ሆነ መረዳታችን ብቻውን በቂ ሊሆን አይችልም፡፡ ምንጩን ወደ እኛ የሚያመጣውን ማወቅም በዚያው ልክ አስፈላጊ ነው፡፡ በክርስቶስ ካልሆነ በክብር መሞላት ከወዴት ይሆናል? ሐዋርያው በመልእክቱ ውስጥ ‹‹በ . . . ›› የሚለውን ቃል አብዝቶ ይጠቀማል፡፡ በተለይ ኤፌሶን አንድን ስናነብ ይህ እውነት ግልጥልጥ ይላል፡፡ እስቲ ማስታወሻችሁ ላይ ‹‹በ›› ብላችሁ ጎኑ ላይ ዳሽ አስምሩ፡፡ እናም ደስ ያላችሁን ፃፉ፡፡ በቃሉ መሰረት ያ እናንተ የፃፋችሁት ነገር ክርስቶስ የማይል ከሆነ ከክርስቶስ ጋር እኩል የሚሆን ሌላ ነገር አላችሁ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሰረት ደግሞ ክርስቶስ እንግዲህ በከንቱ ሞቷል ማለት ሊሆን ነው፡፡ እንዲህ ካለው መንፈሳዊ መሰል አመጽ ራሳችሁን ጠብቁ፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ አምላካችን እግዚአብሔር በክብር ይሞላብናል፡፡ ይህ ቃል ተግባራዊ የሚሆነው በእምነት በተቀበልነው ሁኔታ ነው፡፡  

5. የሚያስፈልገን ሁሉ

        ተወዳጆች ሆይ፤ ቃሉን ልብ በሉ፡፡ እያለ ያለው የፈለጋችሁትን ሁሉ አይደለም፡፡ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ነው፡፡ የእኛ ፍላጎት የሚያስፈልገንን በቅጡ ገና ያልተረዳ ግን ስግብግብ ነው፡፡ ስለ ትርፍ እየተጨነቀ ዋናው ያልገባው፤ መሰረታዊውን ከስሮ ለማጀቢያው የሚጋፋ ተላላ ነው፡፡ በእርግጥም እግዚአብሔር ጻድቅ ስለ ሆነ የሚያስፈልገን ልኩን ለመሙላት የታመነ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች እግዚአብሔር እንዳስቀረባቸው የሚሰማቸው ብዙ ነገር እንዳለ ይወቅሳሉ፡፡ እግዚአብሔር የራሱ አሠራርና ፈቃድ ያለው አምላክ ነው፡፡ እኛ በመዘነው የሚሠራ ሳይሆን፤ ሁሉን የሚመዝን ነው፡፡ እኛ የጠየቅነውን ሁሉ የሚመልስ፤ ያዘዝነውን ሁሉ የሚያደርግ እኛ እንጂ እግዚአብሔር ሊሆን አይችልም፡፡ ለሚያስፈልገን ለዚያ ለእውነቱ የሚተጋልን እግዚአብሔር ስሙ ብሩክ ይሁን፡፡

     የእግዚአብሔር መቻል መጽናኛችን ነው፡፡ ዳሩ ግን መጠንቀቅ ያለብን እግዚአብሔር የሚችለው እውነቱን ሳይጥስ፤ ከጽድቁ ሳይጣረስ ነው፡፡ የእኛ አምላክ ልዩ ነው ብለን የምንናገረው ከዚህም የተነሣ ነው፡፡ አይሳነውም በሚል ብዙ የሰው ብልሃትና ተረቶች ክብሩን ጋርደውብናል፡፡ እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ መረዳት ለእርሱ ክብርን የመስጠት የመጀመሪያው ተግባር ነው፡፡ አንሶ የተረዳነውን አሳንሰን ብናከብረው፤ ደብዝዞብን ያየነውን በስንፍና ብንሸፍነው ይህ የመጀመሪያው ውጤት ነው፡፡ ምንጩ ከጠራ የምንጠጣው ድፍርስ አይሆንም፡፡ የምንጠጣው ድፍርስ ካልሆነ ደግሞ ጤና አይቃወስም፡፡
     . . . ለአምላካችንና ለአባታችንም እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን›› (ፊል. 4÷19-20)፡፡


3 comments:

  1. ምንጩ ከጠራ የምንጠጣው ድፍርስ አይሆንም፡፡ የምንጠጣው ድፍርስ ካልሆነ ደግሞ ጤና አይቃወስም፡፡

    ReplyDelete
  2. ለአምላካችንና ለአባታችንም እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን›› (ፊል. 4÷19-20) Amen!

    ReplyDelete
  3. የእግዚአብሔር መቻል መጽናኛችን ነው፡፡ ዳሩ ግን መጠንቀቅ ያለብን እግዚአብሔር የሚችለው እውነቱን ሳይጥስ፤ ከጽድቁ ሳይጣረስ ነው፡፡ Ewenet new!

    ReplyDelete