Tuesday, December 30, 2014

ዕድሜህ ስንት ነው?

              በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ማክሰኞ ታህሳስ 21 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

     የሰው የተሰፈረ ዕድሜ የዘላለም እግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ ሰው ስለተዋደደ የማይጨምረውና የማያዝበት ልዩ በረከት ልንኖርበት የተሰጠን ዘመናችን ነው፡፡ የሥጋ አባታችን አልያም እናታችን የቱንም ያህል ቢወዱን ከዕድሜያቸው ቀንሰው በእኛ ላይ አይጨምሩልንም፡፡ እየኖርን እንደሆነ በተሰማን ጊዜ ሁሉ እያኖረን ያለውን አምላክ ቸል ማለት በደል ነው፡፡ በዚህ መንገድ ለተባረክንበት መባረክ የመጀመሪያው ምላሽ ይህንን እውቅና መስጠት ነውና፡፡ ስለ ስጦታው በቂ ማስተዋል በውስጣችን ከሌለ፤ ለሰጪውም ሆነ ለስጦታው ክብር አይኖረንም፡፡ ተቀብለን ሰጪውን ልብ አለማለት መንፈሳዊ ድንዛዜ ነው!

      ከእግዚአብሔር የተሰጠንን ዕድሜ ሰዎች ‹‹ስንት ነው?›› ጥያቄ ሲያስጨንቃቸው፤ አሳንሰው ሲናገሩ አልያም ባልሰማ ሲያልፉ ብዙ ጊዜ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች ልኩን ለመናገር የሚቸገሩበትን የስነ ልቦና ትንታኔ ለጊዜው እንተወውና፤ በጀመርንበት መንፈሳዊ ቅኝት ወደ ፊት ለማየት እንሞክር፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ረጅም ዕድሜ የኖሩ፤ እንዲሁም አጭር ዘመን ኖረው ያለፉ ሰዎችን እናገኛለን፡፡ ለዚህ አሳብ በዘፍጥረት ምዕራፍ አምስት ላይ የምናገኛቸውን አባትና ልጅ እንይ፡፡

      ‹‹ሄኖክም የኖረበት ዘመን ሁሉ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ሆነ፡፡ ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም፤ እግዚአብሔር ወስዶታልና›› /ዘፍ. 5፡23/፤ ‹‹ማቱሳላም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ዘጠኝ ዓመት ሆነ ሞተም›› /ዘፍ. 5፡27/፡፡

      ተወዳጆች ሆይ፤ በዚህ ክፍል ሰዎች በዕድሜያቸው መጨመር የሚሸማቀቁበትን ሀቅ እናገኘዋለን፡፡ በተቀበሉት ዘመን እንደሚፈልጉት ኖረው ቀኖቹ አለማለፋቸው፤ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አለመመላለሳቸው እንደ ትልቅ ምክንያት ነው፡፡ ኑሮ ትክክለኛ ነዋሪ ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር እንደ ፈቃዱ በሰጠን ዘመን ላለማፈር ‹‹አካሄድን ከእግዚአብሔር ጋር›› ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በምንኖርበት በእያንዳንዱ ቀን ምድሪቱ ከእኛ ከክርስቲያኖች ብዙ ትጠብቃለች፡፡ በዙሪያችን ላለው ችግር እኛ ውስጥ ‹‹ክርስቶስ›› /ዮሐ. 3፡16/ የሚባል ትልቅ መፍትሔ አለ፡፡

       ከማቱሳላ አንፃር ሄኖክ ትንሽ ኖሮ ትልቅ የተወራለት ‹‹አካሄዱ ከእግዚአብሔር ጋር›› ሲሆን፤ ብዙ የኖረው ማቱሳላ ግን ‹‹ኖረ፤ ሞተ›› ተብሎለታል፡፡ እግዚአብሔር ትልቅን ነገር በትልቅ ውስጥ አለማኖሩ ይደንቃል፡፡ የተናቀውን ወደ ክብር የሚያመጣ፤ የተገፋውን አስታውሶ ወደ ከፍታ የሚያመጣ፤ በብላቴኖች ውስጥ ትልቅን እምነት የሚያደርግ እግዚአብሔር ነው፡፡ በጥቂቱ ውስጥ ብዙን የሚሠራ እርሱ ነው፡፡ በትንሹ ዘንድ ትልቅን ነገር የሚያከናውን የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነው!

       በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ዕድሜያቸው፤ ስማቸው፤ ክብራቸው፤ ዘራቸው ያልተጠቀሰ ግን ኃያሉ እግዚአብሔር ድንቅን በእነርሱ ያደረገባቸውን ሰዎች ልናስተውል እንችላለን፡፡ ለሚታመኑት እግዚአብሔር ዛሬም እንደዚያው ነው፡፡ ከጊዜ ለውጥ ጋር አብሮ የማይለወጥ እግዚአብሔር ታሪካችሁን ሊለውጠው፤ ኪሳራ ያላችሁትን ዘመን ሊክሰው የታመነ ነው፡፡ በእርግጥም በእናንተ ውስጥ እምነትን ሊያገኝ ይወዳል፡፡

       የእግዚአብሔር ቃል ያለ ክርስቶስ የኖርንበትን ዘመን ከንቱ ብሎ ሲጠራው፤ ከክርስቶስ ጋር ያለውን ደግሞ ዕድሜያችሁ ይለናል፡፡ ክርስቲያን በክርስቶስ በማመኑ ቢሞት እንኳ ሕያው ነውና /ዮሐ. 11፡25/፤ ኑሮው የዘላለም ነው፡፡ ሄኖክስ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገው በእምነት አይደለምን? /ዕብ. 11፡6/፡፡ እምነት ከመስማት ነውና /ሮሜ 10፡17/ ሰው ከቃሉ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ከሌለው ትክክለኛ እምነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልምና፤ እውነተኛ እምነት /የአፍ ሳይሆን የልብ/ የሌለው ሰው የዘላለም እግዚአብሔርን ማስደሰት አይሆንለትም፡፡ 

       ሐዋርያው ‹‹ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው።›› /ገላ. 2፡20/ ይለናል፡፡ እውነተኛ ክርስቲያን የትክክለኛ ዕድሜው ቁጥር የሚጀምረው በክርስቶስ ክርስቲያን ከሆነበት ጊዜ ነው፡፡ ለኃጢአት የሞትን እኛ በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆነን ለእግዚአብሔር ሕያዋን ነን /ሮሜ 6፡11/፡፡    

      እንደ ሰው ኖረን በምናልፍበት የሥጋ ልደት ‹‹እነሆ፥ በዓመፃ ተፀነስሁ፥ እናቴም በኃጢአት ወለደችኝ።›› /መዝ. 50፡5/ ተብሎአል፡፡ ዳሩ ግን ‹‹በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና።›› /ሮሜ 8፡2/ እንደተባለ፤ በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። ተወዳጆች ሆይ፤ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል።

      የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና /ሮሜ 6፡23/ በሥጋ ልደት ወደዚህ ዓለም የመጣንበት ኑሮ አድራሻው መቃብር ነው፡፡ ከዚያ አሮጌ ሰው ጋር በሞት ተቆራርጠናል፡፡ ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ /ቆላ. 3፡3/ እንደተባለ፤ አሁን የያዝነው ሕይወት በክርስቶስ ኢየሱስ በመድኃኒታችን የሆነ ነው፡፡ ማንነታችንን እንደ ዳቦ ቆርሰን፤ ልባችንን እንደ ሻማ ለኩሰን የምናከብረው የጌቶች ጌታ እርሱ ነው፡፡  
       
በእንግድነቴ አገር፡

      ‹‹በእንግድነቴ አገር ሥርዓትህ መዝሙር ሆነችኝ›› /መዝ. 118፡54/፡፡ በዚህ ምድር ላይ የምንኖረው በእንግድነት ነው፡፡ እንግዳ የቱንም ያህል ቀን ቢያስቆጥር ርዕሱ እንግዳ ነው፡፡ ሻንጣው የተሰናዳ መንገደኛ! ቢበላ ቢጠጣ፤ ቢገባ ቢወጣ፤ ቢለብስ ቢከበር . . . እንግዳ ሁሌም እንግዳ ነው፡፡ የምንኖርባት ዓለም አንድ ቀን እንደመጎናጸፊያ ለመጠቅለል በአስገኚዋ እግዚአብሔር ቃል የተቀጠረች ናት፡፡ ዓለሙም ንብረቱም ያልፋል ይጠፋል፡፡ እንዲህ ባለው ምልክዓ ምድር ላይ ሁላችን አንዴ ኖረን የምናልፍ ነን፡፡ እንግዳ የሚያሰኙንን ብዙ መገለጫዎች በኑሮአችን ውስጥ በግልጥ እናስተውላቸዋለን፡፡

     ለዘላለም የማይኖረውን፤ ይኑር ስላልን አናኖረውም፡፡ በጊዜው ላይ ደክመንም ወደ ዘለቄታ አናሻግረውም፡፡ በሚያልፈው መካከል ከማያልፈው እግዚአብሔር ጋር ከኖርን ዕድሜያችን በድፍረት የምናወራው የዘላለም ይሆንልናል፡፡ ሰዎች ያለ እግዚአብሔር ኖረው ሽበት ካስመካቸው፤ አንቱታ ካዝናናቸው፤ እኛ ከእግዚአብሔር ጋር ሆነን ደቂቃዋ የዘላለም በሆነችበት በእርሱ እንዴት አንመካ? የሚመካ በጌታ ይመካ ነውና ጌታ ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ! የሥጋ ወላጆች አቅደው ለመለመኛ፤ ይጦረኛል ብለው በስሌት ልጅ በሚወልዱበት በዚህ ክፉ ዓለም አንተ ለፍጥረቱ የበኩራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስበህ ወለድከን /ያዕ. 1፡18/፡፡ ኦ! ተመስገን፡፡

     ተወለደ ሞተን የምናልፍበት ትልቁ ልደት ክርስቶስ ነው፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን የሆንን አሁን የምንኖረው ኑሮ በወደደንና ስለ እኛ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምንኖረው ነው። ነብዩ ‹‹ሥርዓትህ መዝሙር ሆነኝ›› እንዳለ፤ ከፀሐይ በታች በወጣን በገባን ቁጥር ዜማችን ሰማያዊው ስርዓት ነው፡፡ ልብ በሉ! ነቢዩ በእንግድነቱ አገር ላይ እንግድነቱን አልዘመረም፡፡ የሚያልፈውን፤ የሚቀረውን፤ አላቃዊን አልተናገረም፡፡ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርን ስርዓት ዝማሬው አደረገ፡፡

     ተወዳጆች ሆይ፤ እግዚአብሔርን ከእያንዳንዱ ኑሮአችሁ ጋር ማያያዝን ልመዱ፡፡ እንደ ሰው ከሆነው ደስታ ባለፈ ያለውን ደስታ ተጠሙ፡፡ ባነሰው ከመርካት ከፍ ብላችሁ በበለጠው ዕረፉ፡፡ በሥጋ የተወለድኩበትን ቀን አስቦ ስጦታ ይዞልኝ የመጣውን ወንድም ‹‹ዕድሜህ ስንት ነው?›› አልኩት፡፡ እርሱም ‹‹ተወው እስቲ! እኔ ለወላጆቼ እንጂ ለራሴ ኖሬ አላወቅም፤ እነርሱን ጠይቃቸው›› አለኝ፡፡ እኔ ግን እናንተን እላችኋለሁ! በእውነት ቃል አስቦ ለዘላለም ክብር ለወለዳችሁ ለእርሱ ለእግዚአብሔር ኑሩ፤ ያም አይቆጫችሁም!

ባራህ፡

      አባቴ እግዚአብሔር ሁል ጊዜ እባርክሃለሁ፤ ምስጋናህም ዘወትር በአፌ ነው፡፡ በተወደደው ልጅህ በላይ በሰማያት በታች በምድር ክብር ይሁንልህ፡፡ በሥጋ መወለድ ቋንቋ ነው! ተብዬ ከሰው ተግባብቻለሁ፡፡ ይህ ግን ካንተ አላግባባኝም፡፡ በዚህም ቀልጣፎች የሆኑቱ አንተን አላወቁህም፡፡ በስብከት ሞኝነት፤ በእምነት በሆነው በኩል ግን አግኝቼሃለሁና ተመስገን፡፡ ከዚህ ዓለም ጥበበኞችና አስተዋዮች ሰውረህ ለታናናሾቹ የገለጥከውን ለእኔም ስለገለጥክልኝ ስምህ ብሩክ ይሁን፡፡ አሜን!    
                                               ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

1 comment:

  1. Interesting,good understanding and
    Blessed article.PS keep doing what you doing .Great job.Don't take long to
    Posting your teachings.Thanks,be blessed and l am thankful about u guys.Happy new year.Blessed.

    ReplyDelete