በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንጌል ያስተማርኳትን አንዲት ሴት በቢሮዬ መንገድ ላይ አግኝቻት፤
በፀጉሯ መንጣት፤ በሰውነቷ መግዘፍ፤ በፊቷ መሸብሸብ ስገረም፤ ‹‹የነገርከኝ ቃል ግን አላረጀም›› አለችኝ፡፡ ታዲያ ስለ ባለቤቷና
ልጆቿ እየጠየኳት፤ በመሐል ‹‹ምን ሆነህ ነው? ፊትህ ደህና አይደለም›› እያለች ምራቋን እጇ ላይ እንትፍ ብላ ለእኔ የማይታየኝን
እሷ የምታየውን ከፊቴ ላይ ታብሳለች፡፡
በእርግጥ በጊዜው ያዘንኩበት ነገር ቢኖርም፤ ያ ከአሳቤ በስተ ውስጥ የነበረ ነው፡፡ ሴቲቱ ፊቴ ላይ ምን ታይቷት እየደጋገመች ምራቅ
እንዳጠገበችው ባላውቅም፤ በጊዜው ግን ቅንነቷን እንዳደነቅሁ አስታውሳለሁ፡፡ ምንም እንኳን ለጭርት ወጪ ብታስወጣኝም ማለት ነው፡፡
ሴቲቱ እንደ ከፋኝ እያወራች በምራቅ ጉንጬን አራሰችው፡፡ በጊዜው እኔ ያዘንኩበት ነገር እድሜው አጭር፤ ክብደቱ ቀሊል፤
መፍትሔው ግልጽ ነበር፡፡ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን።›› የሚለው የታመነ ቃል ልቤን ሞልቶት ነበር፡፡ የከፋኝን ለማስወገድ
/በእርሷ ግንዛቤ/ ከከፋኝ የከፋ ነገር አደረገች፡፡ እንግዲህ ይህ ከሁለት አመታት በፊት የሆነ አጋጣሚ፤ በዚህ ርዕስ ዙሪያ ልጽፍ
ሳስብ ትዝ አለኝ፡፡ ለመነሻም እንዲሆን አሰብኩ፡፡
በኑሮ ውስጥ ጥሩም መጥፎም አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ፡፡ ሰው የሆነ ሁሉ ደግሞ እነዚህን በጸጋ ተቀብሎ ጤናማ ምላሽ የመስጠት
ኃላፊነት አለበት፡፡ በተለይ በክርስቶስ እውነተኛ የልብ አማኝ ከሆኑ ክርስቲያኖች ይህ አብዝቶ ይጠበቃል፡፡ ደስታና ሀዘን፤ ማግኘትና
ማጣት፤ ፍቅርና ጥላቻ ፈረቃቸው የከረረበት ዘመን ቢኖር ይህ ይመስለኛል፡፡ ሰዎች ብዙ ነገር አልዘልቅላቸው እያሉ ተቸግረዋል፡፡
አስቤዛ ብቻ ሳይሆን አመልም የማይበረክትበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ‹‹ዘጠኝ ዳቦ ከመላስ አንዱን መብላት›› የሚለው አባባል እርጅና
ተጫጭኖታል፡፡ ብዙዎች የቻሉትን ያህል ብዙ ነገር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ስለቀጣጠነብን፤ ከሕይወት ያነሰ ነገር ስናወራ ሕይወት የሆነውን
ነገር ቸል እንዳንለውም ብዬ እፈራለሁ፡፡ ያልተባረኩ ሰዎች ጣራና ግድግዳቸውን፤ መኪናና ግቢያቸውን፤ ማሰሮና ቦሀቃቸውን /ምፀትም
ጭምር/ ሲያስባርኩ ታዝቤያለሁ፡፡ ጠላት ዲያብሎስ ትኩረታቸውን ከቁስ ጋር አያይዞ፤ ሰዎችን በነፍስ አስጨንቆ መግዛቱ ግርም ይለኛል፡፡
ጌታ ይግለጥላችሁ!
የገጠመንን የምናይበት አተያይ፤ ለዚያም የምንወስደው እርምጃ የውስጥ ሰላማችንን መወሰኑ አይጠፋንም፡፡ ሰዎች የከፋቸውን
ነገር መነሻ አድርገው በከፋ ነገር ውስጥ ሲገኙ፤ እንደ ባለ አእምሮ ልብን ያሳዝናል፡፡ ከሌሎች መከፋትና ጊዜያዊ ችግር አልፈውም
መንፈሳዊ ተግዳሮታቸውን አለማስተዋላቸው መገረምን ያጭራል፡፡ እንደ ሰው ጭንቅ የሆኑ ቀኖችን አልፌአለሁ፡፡ ሞት አፍጥቶ በጌታ ተርፌአለሁ፡፡
ያለ ሽንገላ፤ በግልጽ በሚገባኝ ሁኔታ በተጨመረ እድሜ እየኖርኩ ነው፡፡ እየገቡኝ የተፈተንኩባቸው፤ ሳይገቡኝ አልፈው ዘግይቼ የተረዳኋቸውን
ውጊያዎች አስተውላለሁ፡፡ ምርጫዬ ያመጣውንም፤ ተመርጦ ወደ እኔ የመጣውንም መራራ ጌታዬ አጣፍጦት አውቃለሁ፡፡ ዳሩ ግን ‹‹ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም
በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን።›› /1 ዮሐ 5÷19/ አልተባለምን? የተከፋንበት እርሱ ምንድ ነው?
የእግዚአብሔር ቃል ከሚለን የተረፈስ ምን አለ?
የምንኖረው ከከፋን ይልቅ በከፋ ዓለም ላይ ነው፡፡ ‹‹ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም›› /ዮሐ 10÷10/ ተብሎ እንደ ተነገረን፤ የምንመላለሰው የዚህ
ዓለም አምላክ ዲያብሎስ በሚገዛበት ሥርዓት መካከል ነው፡፡ ለብዙዎች ከገጠማቸው የባሰ ምንም ነገር የለም፡፡ ዳሩ ግን ዓለሙ በሙሉ
ለዘላለም ሞት በሚቀጥር በብርቱ ቀንበር ስር ነው፡፡ እንደ ሰው ከሰው ጋር በሚኖረን ዕለታዊ ኑሮ ውስጥ የሚገጥሙን አላፊ መከራዎች
የዘላለሙን መከራ፤ ልባችንን የሚያንኳኩ ደስታዎችም ዘለቄታውን ተድላ እንዳይሸፍኑብን አብዝተን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል፡፡ እግዚአብሔር
በክርስቶስ ያደረገውን የመስቀል ሥራ የገፉ፤ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ያሉ ብዙ ሰዎች በዙሪያችን ያሉበት መልክአ ምድር
ላይ ነን፡፡ ከዚህም በላይ በእግዚአብሔር ስም መሽገው ለጥልቁ የጨለማ ገዢ
አምባሳደር የሆኑ የስም ክርስቲያኖችን በግልጽ የምናይበት ሁኔታ ውስጥ እያለፍን ነው፡፡
ተወዳጆች ሆይ፤ በሰማይ ያለችይቱ የእግዚአብሔር ፈቃድ በምድሪቱ ላይ የምትሆነው በቤተክርስቲያን፤ በእውነተኛ ምዕመናን
ሕይወት ተግባራዊነት ነው፡፡ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን /2 ቆሮ 4÷4/ ለሌሎች እንዲያበራ እኛ ለተረዳነው እውነት መሰጠት
አለብን፡፡ ከሚታየው አልፈን የምናይ፤ ከሚሰማው ዘልቀን የምንረዳ፤ ለጨለምተኛው ዓለም ብርሃን፤ ለመረረ ልቡና ማጣፈጫ ጨው፤ ለድፍርሱም
መጥራትን የምንሰጥ ልንሆን የሚገባ ነው፡፡ ከዘላለም ያነሰ ነገር መናገር ለሰሚዎቹ፤ ከዘላለም ያነሰ ነገር መስማት ለተናጋሪው ዕረፍትን
አይሰጥም፡፡ የፍቅር ሐዋርያው ‹‹ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን
ሕይወት እናወራላችኋለን›› /1 ዮሐ
1÷2/ ይለናል፡፡ ዝቅ ብላችሁ ስታነቡ ‹‹እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ›› ይላል፡፡ ሰዎችን መንፈሳዊ ወዳጅ የምናደርግበት መንገድ ከዘላለም
ያነሰ ሊሆን ጽድቅ አይደለም፡፡ በመንፈሳዊ ዓይን የምድሪቱ ትልቅ ሸክም ‹‹ክርስቶስ›› /ኤፌ 2÷12/ የሌለው ሰው ነው፡፡ እንደነዚህ
ያሉቱ የጽድቅ ጠላት፤ የቀናውንም የጌታን መንገድ የሚያጣምሙ የዲያብሎስ ልጆች ናቸው፡፡
ወዳጆች ሆይ፤ እንግዲህ የሕይወትን ቃል፤ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ፤ ለሰዎች ሁሉ በመግለጥ እንደ ብርሃን ልጆች መታየት
ይሁንልን፡፡ እውነትን በፍቅር እንያዝ፤ የቃልና የኑሮ ምስክርነት ይብዛልን፡፡ ለሰዎች ከዘላለም ያነሰ ነገር እንዳንመኝላቸው እመኛለሁ፡፡
በውስጣችሁ ያለውን የሕይወት ውኃ ምንጭ ወደ ሌሎች በረሃ ማንነት አፍስሱት፡፡ በዚያም ልምላሜ ይሆናል፡፡ መብቀልና ማደግ፤ አበባና
ፍሬ፡ ሠላሳ፤ ስልሣ፤ መቶም ያማረ ፍሬ፡፡ እነሆ ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን ያወጣው እንዲህ ይላል፡ - ‹‹እኔ ሕይወት
እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ።››፤ እርስዎ ከዚህ ላነሰ ኑሮ አልተጠሩም፡፡
‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!
wow its so good
ReplyDeleteጸጋህ ይብዛ ጌታ መከፋቴን ኮንኖታል ለካ ከሰፊው ውስኑን እያሁ ነበር፡፡ እውነትም ብዙ ይጠበቅብናል አምላክ ይርዳን
ReplyDeleteትላንት ጉባኤው እጅግ መንፈስና ኃይልን የተሞላ ነበር፤ ወዳጄ በምንችለው ሁሉ ከጎንህ ነን እግዚአብሔር ያበርታህ
ReplyDelete‹‹እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ።››፤ እርስዎ ከዚህ ላነሰ ኑሮ አልተጠሩም፡፡ meteratachenen endenastewel yeredan!
ReplyDelete