Monday, June 29, 2015

ስፍራችሁን ያዙ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!



ሰኞ ሰኔ 22 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

በዚህ ምድር ላይ እጅግ አስፈሪው ሰው ክርስቶስ የሌለውን ማንነት የያዘ ነው፡፡ ለምድሪቱ እግዚአብሔር እንደሌለው ሰው ያለ ሥጋትና ሽብር፤ የሁከት ርዕስና የክፋት ሥር የለም፡፡ ለአመፃ ጉልበት በሚሆኑ፤ ለከንቱ ኑሮ አቅም በሚፈጥሩ፤ ሰውን ከባህርዩ ውጪ ነውርን በሚያለማምዱ ብዙ ነገሮች መሐል በምንመላለስበት የዚህ ዓለም ስርአት፤ ማምለጥ የደኅንነት አምላክ በሆነው በእግዚአብሔር ነው፡፡
‹‹አምላካችንስ የደኅንነት አምላክ ነው፤ ከሞት መውጣትም ከእግዚአብሔር ነው።›› /መዝ. 67፡20/ እንደተባለ፤ ደኅንነት ከእግዚአብሔር፤ ከሞት ማምለጥም ሁሉን ከሚችል አምላክ ነው፡፡ ነቢዩ በሌላ ስፍራ ‹‹እግዚአብሔር ከመቅደሱ ከፍታ ሆኖ ተመልክቶአልና፥ ከሰማይ ሆኖ ምድርን አይቶአልና የእስረኞችን ጩኸት ይሰማ ዘንድ፥ ሊገደሉ የተፈረደባቸውን ያድን ዘንድ›› /መዝ. 101፡19-20/ እንዳለ፤ መዳን በእርሱና ከእርሱ ካልሆነ በቀር ሥጋ ለባሽ ሁሉ ከዘላለም ፍርድና ኩነኔ ሊያመልጥ አይችልም፡፡

በባርነት ያሉትን ጩኸት የሚሰማ፤ በኃጢአታቸው ምክንያት ሞት የተፈረደባቸውን የሚያድን፤ የሰው እጅ ካልሠራው መቅደሱ ከሰማያት ከፍታ ሆኖ የሚመለከተው፤ የሰውን የበደል ፅዋ በልኩ የሚያውቀው የዘላለም አምላክ ጌታ እግዚአብሔር ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስም መጽሐፉን በተረተረ ጊዜ ‹‹የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል›› /ሉቃ. 4፡19/ ብሏል፡፡    
‹‹እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፥ እኔ አምላክ ነኝና፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ።›› /ኢሳ. 45፡22/ እንደተባለ፤ በራሳችን መንገድና ስሌት፤ ከሰውም በሆነ ጥበብና እውቀት ሊመጣ እንደሚችል ከምናስበው ደኅንነት፤ ወደ እግዚአብሔር ዘወር ማለት ሥጋ ለለበሰ ሁሉ ያስፈልጋል፡፡ ምሕረት ከሚምር ከእግዚአብሔር፤ የወጥመድ መሰበርም ከሰባሪው ጌታ የተነሣ ነው፡፡ ሰው ለኃጢአቱ ስርየት፤ ለመተላለፉም ይቅርታን ከእግዚአብሔር ዘንድ ካላገኘ የማንነቱ ማብራሪያ የከፋ ነው፡፡
ተወዳጆች ሆይ፤ ደኅንነት በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ትልቅ አጀንዳ ነው፡፡ በጠላት ዲያብሎስ ዘንድም የሚያሸብረው ትልቅ ርዕስ መዳናችንና ከሞት ማምለጣችን ነው፡፡ የክርስትናው ቀዳሚ ጥሪ መዳን ነው፡፡ በዘፀአት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከባርነት ነጻ የወጣው የእስራኤል ሕዝብ፤ በዘሌዋውያን መጽሐፍ አምላኩን ሲያመልክ እንደምናስተውል፤ ክርስቶስ ነጻነት ያላወጣው ሰው እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆነውን እግዚአብሔር የማምለክ ነጻነት ሊኖረው አይችልም /ገላ. 5፡1/፡፡  
አንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ስለ ሁሉ የሞተው ሁሉ መዳንን ያገኙ ዘንድ ነው /2 ቆሮ. 5፡14/፤ ‹‹ . . . ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ፤ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?›› /ዕብ. 1፡14/ ተብሎ እንደተፃፈ፤ የቅዱሳን መላእክት የአገልግሎት ማዕከልም በክርስቶስ ኢየሱስ የሰዎች መዳን ነው፡፡ በሰዎች መዳን በላይ በሰማይ ደስታ እንደሚሆን ሁሉ፤ በሚጠፉትም እንዲሁ ሀዘን ይሆናል፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ከእግዚአብሔር የሆኑቱ ሁሉ ደስ የሚሰኙት በሰው አጀንዳ ሳይሆን በእግዚአብሔር አሳብ ነው፡፡  
‹‹እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል።›› /ሉቃ. 15፡10/ ተብለናልና፡፡ ሰማያት ሐሴትን የሚያደርጉበት ርዕስ ‹‹መዳናችን›› ነው፡፡ ሰው ይህንን እውነት ተረድቶ ለተገለጠው እውነት አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጥና በእምነት ሲታዘዝ ከእግዚአብሔር አሳብ ጋር ይስማማል፡፡ የጠፋው ሲመለስ፤ የወደቀው ሲነሣ፤ የተሸሸገው ሲገኝ በመለኮት ጉባኤ ደስታው እጅግ ጥልቅና ትልቅ ነው፡፡
የኤፌሶንን መልእክት ስናጠና በስድስቱ ምእራፎች ውስጥ ሦስት ጭብጥ እናገኛለን፡፡ የመጀመሪያው፤ ስፍራን ማወቅና ስፍራን መያዝ ነው፡፡ እውነተኛ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ኅብረት በእግዚአብሔር የተሰጠውን ስፍራ በመያዝ ይጀምራል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ እግዚአብሔር በልጁ ሞት ለእኛ ያደረገውን በአግባቡ ማወቅና ማመን፤ ለዚያም መታዘዝ ይጠበቅብናል፡፡ ከዘላለም እስከ ዘላለም መለወጥ በእርሱ ዘንድ፤ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ የሌለበትን እግዚአብሔር /ያዕ. 1፡17/፤ ልጅ ልንሆነው የምንችለው ስፍራችንን ስንይዝ ነው፡፡
እውነታው በሚጠይቀው መንገድ ቦታቸውን በአግባቡ ባልያዙ ሰዎች መካከል የምናስተውለው መተራመስን ነው፡፡ እኛም እግዚአብሔር የሰጠንን ትክክለኛ ስፍራ ባልያዝንበት ሁኔታ መግባባት የቻልን፤ ግንኙነት ያደረግን፤ ሊመስለን ቢችልም መንፈስና እውነት የሆነውን እግዚአብሔር በተሰጠን መንፈሳዊ መብት ልክ አንቀርበውም፡፡ ከእርሱ የሆነውንም አንቀበልም፡፡ እንደ ቃሉ ለማያምኑ ምናብና ግምት ሕያውን እግዚአብሔር በስሙ ተጠርቶ ለማምለክ እውነት አይፈቅድላቸውም፡፡ ለዚህ ነው ክርስትና ነን የምንለው ሳይሆን ቅዱስ ቃሉ ናችሁ የሚለን የሚሆነው፡፡   
እግዚአብሔር የሰጠንን ከሰው አልተቀበልነውምና በሰው ፊት መጥቆር አንቀማም፡፡ በሰዎች መናጥም አንናወጥም፡፡ እርሱ በጠራን እየተጠራን፤ እርሱ ባስቀመጠን ስፍራችንን ይዘን መኖር ከመለኮት ዙፋን የተሰጠን መንፈሳዊ መብት ነው፡፡ እንዲህ ያለውን እኛ ለእኛ፤ ሌሎች ለእኛ፤ እኛም ለሌሎች አናደርገውም፡፡ ለዚህም የሚበቃ አቅም በሰው ውስጥ የለም /ገላ. 3፡22/፡፡ እውነቱን ባልተረዳንበት መልኩ ተባርከን እንደ ርጉም፤ ምሕረት ተደርጎልን እንደ በደለኛ፤ አርነት ወጥተን እንደ ባሪያ፤ ተቀብለን እንደ ምንደኛ ልንኖር፤ የተሰፈረልንም እድሜ እንዲሁ ሊፈፀም ይችላል፡፡
ሐዋርያው ‹‹በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።›› /ኤፌ. 1፡3/፤ የባረከን ይባረክ ይለናል፡፡ ክፍሉ ስለተባረከ ሰው እንጂ ገና ስለሚባረክ ማንነት አይናገርም፡፡ የተፈፀመን ነገር እናምነዋለን እንጂ ተስፋ አናደርገውም፡፡ ሰው በሆነው የእግዚአብሔር ልጅ ባለን እምነት ስፍራችን በሰማይ፤ በረከታችን መንፈሳዊ፤ ምንጩም የዘላለም አባት እግዚአብሔር ነው፡፡
ምድር ላይ መኖራችን የሰማዩን፤ እንደ ሰው ልማድ መመገባችን መንፈሳዊውን፤ ከሰዎች ጋር መቀባበላችን የዘላለሙን አያስረሳንም፡፡ ዓለም እናንተን ማን እንደሆናችሁ ከሚለው ይልቅ እናንተ በእግዚአብሔር ዘንድ ማን እንደ ሆናችሁ አለማወቅ ለሞት ያደርሳል፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ፤ ስፍራችሁን አስተውላችሁታልን?
‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!
- ይቀጥላል -

No comments:

Post a Comment