Monday, November 9, 2015

የሕይወት አቅርቦት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


ጥቅምት 29 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት
 /ፊል. 2፡14-15/

         በምጣኔ ሀብት ባለ ሙያዎች ዘንድ የፍላጎትና የአቅርቦት መጣጣም ጉዳይ የሁል ጊዜ ርዕስ ነው፡፡ የሰዎች ፍላጎት ሰፊ በሆነበት ሁኔታ ለዚያ አሳማኝ መሻት በቂ የሆነ ምላሽ መስጠት የሚጠበቅ እንደ መሆኑ የምድር መንግሥታት ለዜጎቻቸው ይሠራሉ፡፡ እግዚአብሔር የሰማያትና የምድር ገዥ ነው፡፡ የሁሉ ዓይን ተስፋ የሚያደርገው እርሱ (መዝ. 144፡15) በተለየ ሁኔታ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ልጁ ለሆኑት (ዮሐ. 1፡12) በሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ያስባል፤ ያደርጋልም (ፊል. 4፡19)፡፡

         የእግዚአብሔርን የዘላለም አሳብና የልብ ምክር በመስማትና በማስተዋል፤ ደግሞም በመታዘዝ ወደ እምነት የመጡትን (ሮሜ 10፡17) በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ የሚሰየምበት (ኤፌ. 3፡14) እግዚአብሔር እንደ አባት ይመግባል፤ ይንከባከባል፤ ያሳድጋል (1 ቆሮ. 3፡6)፡፡ እርሱ ጌታ ሕይወትን የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን የሚያበዛም ነው (ዮሐ. 10፡10)፡፡ የዘላለምን ሕይወት ከእግዚአብሔር ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ ያገኙ ሁሉ (ሮሜ 6፡23) ለዚህ ሕይወት አስፈላጊ የሆነውን ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት በመቅረብ ያገኛሉ (ዕብ. 4፡16)፡፡     

        ተወዳጆች ሆይ፤ እግዚአብሔር ሰውን ከመፍጠሩ አስቀድሞ ለሚፈጥረው ሰው አስፈላጊው የሆኑትን ነገሮች ሁሉ እንዳዘጋጀ (ዘፍ. 1)፤ በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት መሆናችንን (2 ቆሮ. 5፡17) ተከትሎ ያለን ኑሮም እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ማድረግ ነው (ኤፌ. 2፡10)፡፡ እግዚአብሔር ታላቅና ድንቅ አምላክ ነው (መዝ. 85፡10)፡፡ የእርሱ እጅ ሥራ የሆነው ሰው ለቀጣዩ አሁን የሚያቅድ፤ ያውም ይድረስ አይድረስ በማያውቀው ጊዜ ላይ አስቀድሞ የሚዘጋጅ ሆኖ ሳለ እጅግ ኃያል የሆነው እግዚአብሔር እርሱ እንዴታ?

        እግዚአብሔር የትኛውም ነገራችን መጠኑ አይደለም፡፡ ሰማይ ያንጠለጠለውን ምድር የተሸከመችውን መባ ብናደርግለት እንኳ እርሱ ‹‹ይህ ሁሉ የእኔ ነው›› አይለንምን? ቀድሞ ያልቆጠረው የምንቆጥርለት፤ አስቀድሞ የማያውቀው የምናሳብቅለት፤ የምንዘረጋለት እጁ እምታጥርበት፤ የሚሰወረው የምንገኝለት ከወዴት አለ? ሰው እግዚአብሔርን አውቆ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ክብርን ባይሰጠውና ባያመሰግነው በሚመጣበት ከንቱነት ምክንያት የለውም (ሮሜ 1፡20)፡፡ 

        በእምነት በኩል ሁላችን በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ነን (ገላ. 3፡26)፡፡ ታዲያ ሐዋርያው በዚህ በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋና ነውር የሌለብን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን እንድንመላለስ ማንጎራጎርና ክፉ ማሰብን አስወግደን ሁሉን እንድናደርግ እየመከረ፤ ‹‹በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ . . ›› (ፊል. 2፡14-15) ይለናል፡፡

        እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጆች በእውነተኛው የሕይወት ቃል አቅርቦት በኩል መገለጥን ትጋት ያደረጉ ናቸው፡፡ ጌታችን ‹‹እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ›› (ማቴ. 5፡14)፤ ደግሞም ‹‹በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም›› እንዳለ፤ ያለ መሰወር በግልጥ ‹‹እንደ ብርሃን የእግዚአብሔር ልጆች›› የምንታየው የማይጠፋውን ሕይወት (ሮሜ 2፡7) ለጠፋው የሰው ዘር በወንጌል ስናቀርብ (ማር. 16፡15) ነው፡፡

        እጅግ በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ ሆይ፤ መስጠት ፈልጋችሁ የምትሰጡት ያጣችሁበት አጋጣሚ ሁል ጊዜ በሕሊናችሁ መጥፎ ትዝታ ሆኖ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ቢኖራችሁ ልትሰጡ የነበረው ያ ምንድነው? ከጊዜያዊ መፍትሔ ያለፈ ነበርን? ተቀባዩን ከቀጣይ ፈተና፤ ደግሞ ቀን ጠብቆ ከሚደርስ መከራ ይታደገው ነበርን? የዘላለም ሞት ፍርድ በትከሻው የተሸከመውን ምስኪን ያሳርፈው ነበርን? የሁልጊዜ ደስታ፤ አእምሮን የሚያልፍ ሰላም፤ ከበረሃ ኑሮ የሚሰውር ጥላ ይሆን ዘንድ ይችል ነበርን? እንዲህ አይደለም፡፡

       የፍቅር ሐዋርያው ‹‹ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤ እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው።›› (1 ዮሐ. 1፡1-3) ይለናል፡፡ ክርስቲያን ከሚያልፈው የዚህ ዓለም ንዋይ ያለፈ ነገር በዙሪያው ላሉ ሁሉ አለው፡፡ ሰዎች የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበት እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል!

       የእግዚአብሔር ልጆች በመንፈስ የሆነ ቋሚ ትጋት ሊያሳዩበት የሚገባው ነገር ‹‹ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት›› (ቲቶ 2፡1) ለሰዎች ሁሉ ማድረስ ነው፡፡ ቃሉ ወደ ሌሎች ቀርበን ሕይወትን እንድናቀርብ በብርቱ ይነግረናል፡፡ ሰዎች የሚፈወሱበትን ይዘን ሊማቅቁ፤ የሚያርፉበትን ይዘን ሊሸከሙ፤ የሚድኑበትን ይዘን ሊሞቱ አይገባም፡፡ ቤተክርስቲያን በየዘመናቱ በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ወደ ክርስቶስ ሰዎችን የምታደርስ ናት፡፡

        ሐዋርያው ጴጥሮስ በበዓለ ኀምሳ ‹‹እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ›› ብሎ በሰበከ ጊዜ ይህን ሰምተው ልባቸው የተነካውን እና ንስሐ ገብተው የኃጢአታቸውን ስርየት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተቀበሉትን አይሁድ ‹‹ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ ብሎ መከራቸው›› (ሐዋ. 2፡40) የሚል ቃል እናነባለን፡፡ መጥፎና ጠማማ ትውልድ ጌታም ክርስቶስም በሆነው ኢየሱስ ያላመነ ነው፡፡

       እንዲህ ካለው ትውልድ እንኳን ስድብና ነቀፋ ሞትም ይጠበቃል (ሐዋ. 21፡13)፡፡ በሰማዕቱ እስጢፋኖስ ላይ ልቡ የተቆጣው፤ ጥርሱን ያፋጨው፤ በጩኸት እየተናገረ ለእውነት ጆሮውን የደፈነው፤ በአንድ ክፉ አሳብ ውስጥ በመሆን እስከ ሞት የወገረው መጥፎና ጠማማ ትውልድ ነው (ሐዋ. 7፡54-60)፡፡ እንዲህ ካሉቱ እንዲህ ያለው አመጽ የማይጠበቅ አይደለም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊሞት የመጣው ገዳዮች መካከል ነው፡፡ ሰው በዘላለሙ ካላመለጠ በጊዜው ነገር ቢበረታ ይህ የሚያስደንቅ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ለተያዘበት ለዚያ ባሪያ ነውና፡፡

        በእግዚአብሔር አሳብ ላይ ጠላት የሆኑ የእግዚአብሔር መውደድ እንደሚያስፈልጋቸው እየተናገሩ ነው፡፡ እውነት ዕረፍት የነሳቸው አርነት መውጫቸው እርሱ እንደሆነ እየመሰከሩ ነው፡፡ ጽድቅ ላይ ዘመቻ የሚከፍቱ እርሱ እንደሚያሸንፍ እየታገላቸው ነው፡፡ ሰዎች በአመጽ እርካታን ካገኙ አድራሻቸውን እያጋለጡ ነው፡፡ እርሱም ነፍሰ ገዳይ የሆነው ዲያብሎስ ነው (ዮሐ. 8፡44)፡፡ በእውነት እርዳታችን ያስፈልጋቸዋል፡፡

       የእግዚአብሔር ቃል እንደሚነግረን ኖኅ ‹‹የጽድቅ ሰባኪ›› ነበር (2 ጴጥ. 2፡5)፡፡ እርሱ ጽድቅን የሰበከው እንዴት ባለ ትውልድ መካከል እንደ ሆነ ደግሞ ቃሉ ‹‹በውኑ ኃጢአተኞች ሰዎች የረገጡአትን የዱሮይቱን መንገድ ትጠብቃለህን? ጊዜያቸው ሳይደርስ ተነጠቁ መሠረታቸውም እንደ ፈሳሽ ውኃ ፈሰሰ። እግዚአብሔርንም። ከእኛ ዘንድ ራቅ ሁሉንም የሚችል አምላክ ምን ሊያደርግልን ይችላል? አሉት።›› (ኢዮ. 22፡15-17) በማለት ይነግረናል፡፡

       መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሳውልን ‹‹ስለ ምን ታሳድደኛለህ?›› (ሐዋ. 9፡4) ሲለው፤ ሳውል  ከሚያሳድዳቸው አልፎ ማየት አለመቻሉን እንረዳለን፡፡ ኖኅ ላይ የተዘባበተው (2 ጴጥ. 3፡3) የያኔው ትውልድ ከኖኅ አልፎ ማየት ያልቻለ ነበር፡፡ እነርሱም በቃልና በተግባር የእግዚአብሔርን የሕይወት ጥሪ ገፉ፡፡ ሕያው እግዚአብሔር የመርከቢቱን በር እስኪዘጋው ድረስ በከንቱ ኑሮአቸው ተደላድለው ነበር፡፡

       አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ላደረገ ለዚያ የእግዚአብሔር ሰው ምን ያህል ጭንቅ እንደሚሆን አስተውሉ፡፡ ‹‹ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና›› (2 ጴጥ. 2፡7-8) እንዲል ቃሉ፤ ‹‹በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።›› (2 ጢሞ. 3፡12)፡፡ እናንተ ዛሬም እንዲሁ የምታዩና የምትሰሙ ሆይ ልባችሁ ይጽና፤ ለማያልፈው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ታመኑ፡፡

        ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት የሆነውን የኖኅን ዘመን ሁኔታ ካለንበት አዲስ ኪዳን ጋር ሲያያይዘው ‹‹በኖኅ ዘመንም እንደ ሆነ፥ በሰው ልጅ ዘመን ደግሞ እንዲሁ ይሆናል።›› (ሉቃ. 17፡26) ብሎናል፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ መፍትሔው ግን ‹‹የሕይወትን ቃሉ›› ማቅረብ ነው፡፡ ለተመገበው (ላመነ) የዘላለም ሕይወት ይሆንለታል፤ ልቡ ይህን ጸጋ ለገፋው ደግሞ የዘላለም ጠኔ ይሆንበታል፡፡   
                                                                                     - ይቀጥላል -            
                                               ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!   

No comments:

Post a Comment