Thursday, December 17, 2015

ድልና ምክር (2)

                          በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!



‹‹ድልም ብዙ ምክር ባለበት ዘንድ ነው›› /ምሳ. 24፡6/፤ ‹‹እርስ በርሳችን እንመካከር›› /ዕብ. 10፡25/!

                              ሐሙስ ታህሳስ 7 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

         ፈተና የምንኖርበት የአሁኑ ዓለም አንደኛው መልክ ነው፡፡ የኖረ ይቸገራል፤ የሚራመድን እንቅፋት ይመታዋል፡፡ መኖር ባይኖር መቸገር ከወዴት አለ? መንቀሳቀስስ ባይኖር እንቅፋት ከወዴት አለ? በዓለም ሳለን መከራ እንዳለብን ይህ አስቀድሞ የተባለ አይደለምን? (ዮሐ. 16፡33)፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ችግርን ብርቱ ዓይን ሲመለከተውና ደካማ ሲያየው የተለያየ ነው፤ ፈተና በሚያስተውል ሰው ጆሮና በማያስተውል ዘንድ ሲሰማ ሁለቱም ጋር አንድ አይደለም፡፡

       ለችግሮች ጊዜያዊ መፍትሔ ስለ መፈለግ ከምትደክሙ ራሳችሁን በጥንካሬ መገንባት ላይ ጊዜ ውሰዱ፡፡ ፈተና በማንኛውም ጊዜ ሊመጣ ይችላል፡፡ ዳሩ ግን ዛሬ ያልተሠራ ማንነታችሁን በቅጽበት አልያም ውስን በሆነ ጊዜ ውስጥ አትገነቡትም፤ ሁኔታዎችን ለመቀየር ከመድከም ራስን መቀየር ላይ ትኩረት ማድረግ ይበልጣል፡፡ በዚህም ችግር የማይጠጋው ሰው ሳይሆን ችግርን በትክክለኛው መንገድ የሚፈታ ሰው ትሆናላችሁ፡፡  

·        በየእለቱ የክርስቶስን ፍቅር አስቡ፡ ‹‹ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት ወይስ ራብ ወይስ ራቁትነት ወይስ ፍርሃት ወይስ ሰይፍ ነውን? . . ›› /ሮሜ 8፡35/ ተብሎ እንደተጻፈ፤ በሚገጥማችሁ ልዩ ልዩ ፈተና የክርስቶስ ፍቅር በልባችሁ ሊገዛ ያስፈልጋል፡፡ ሁኔታዎች የተለያየ መልክና ቅርጽ ይኖራቸዋል፤ ነገር ግን በክርስቶስ የተወደድንበትን የፍቅር መሰረት ቸል ልንል አይገባም፡፡ ‹‹. . የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው›› /ዮሐ. 13፡1/ ተብሎ እንደተጻፈ፤ በምትጋጠሟቸው ፈተናዎች ውስጥ የተወደዳችሁበት የክርስቶስ ፍቅር አእምሮአችሁን ሊሞላው ይገባል፡፡
        የመከራ አንዱ ስሜት ‹‹አለመፈለግ›› ነው፡፡ በምንኖርበት መልክዓ ምድር እንደማይፈለጉ የሚሰማቸው ብዙ ወገኖች በልዩ ልዩ ስፍራ አሉ፡፡ በቤተ ሰዎቻቸው፤ በጓደኞቻቸው፤ በሥራ ባልደረቦቻቸው፤ በእጮኝነትና በትዳር አጋሮቻቸው፤ በአካባቢያቸው፤ በቅርብና በሩቅ ዘመዶቻቸው ያለመፈለግን በረሃ በብዙ ምሬት የሚጓዙ በዙሪያችን የምናስተውላቸው ናቸው፡፡
         የተወደዳችሁ እናንተ፤ ራሱን ብቻ ምክንያት አድርጎ የወደዳችሁን ጌታ አስቡ፡፡ ‹‹. . እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ በሕዝብ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው›› /ሐዋ. 2፡47/ እንደተባለ፤ በሌሎች ዘንድ ሞገስ የሚሆናችሁን፤ መፈለግ መወደድ የሚሰጣችሁን ክርስቶስ ወዳችሁት ኑሮ፤ ‹‹ማን ይለየኛል?›› በተባለው በዚያው መጠን መጠጋት ይሁንላችሁ፡፡ በሚለዋወጥ ሁኔታ ውስጥ የማይለዋወጥ ፍቅር ክርስቶስ ኢየሱስ ነው!
·        ትክክል ካልሆነ የበደለኝነት ስሜት ራሳችሁን ነፃ አድርጉ፡ ኑሮአችን በብዙ ግንኙነቶች የተከበበ እንደመሆኑ፤ መግባባት ብቻ ሳይሆን አለመግባባትም ይኖራል፡፡ አስደሳች በሆኑ ነገሮች መካከል ብቻ የምናልፍ አይደለንም፡፡ እኛ ሌሎችን የምንወቅስባቸው ርእሶች እንዳሉ ሁሉ የምንወቀስባቸውም እንዲሁ ይኖራሉ፡፡ ሕይወት እንደ ሥጋ ዓይናችን ወደ ውጪ እያየን ብቻ የምንኖርበት አይደለም፤ ወደ ውስጣችን መመልከትና ራሳችንን መፈተሽም ይገባል፡፡
        የበደለኝነት ስሜት በበደልንበት ነገር ላይ በጊዜው ካልሆነም ሰንብቶ አግባብ ሲሆን፤ ይህም በቀጣይ ልናስተካክለውና ልንወስድ የሚገባንን ትክክለኛ እርምጃ የሚጠቁም ነው፡፡ መጽሐፍ ‹‹ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን እውነትም በእኛ ውስጥ የለም›› /1 ዮሐ. 1፡8/ እንደሚል፤ በእግዚአብሔርና በሰዎች ፊት ለሠራነው ኃጢአት ንስሐ መግባትና በልጁ ደም መንጻት ያስፈልጋል፡፡ አስቀድሞ በተናዘዝንበት በደል ወይም የበደልነውን ሰው ይቅርታ በጠየቅንበት በዚያው ነገር የ‹‹በደለኝነት ስሜት›› ማስተናገድ አግባብ አይደለም፡፡
         በምክክር ክፍለ ጊዜ ከማውቃቸው ጉዳዮች የወደዳትን ሰው ልትወደው ባለመቻሏ ምክንያት ራሱን አጥፍቶ ዛሬ ድረስ በደለኝነት የሚወቅሳትና ለቀጣይ ግንኙነት ዝግ የሆነች ወጣት፤ በድህነት ያሳደጉት እናቱ እሱ ዛሬ ባለ ሀብት ሲሆን በሕይወት ባለመኖራቸውና በጉስቁልናቸው ላሳደጉት እናቱ ምንም ባለማድረጉ በደለኝነት የሚሰማው ወጣት፤ ራሷን ልትከላከልና ልታመልጥ በማትችልበት ሁኔታ ውስጥ በመደፈሯ የበደለኝነት ስሜት የምታስተናግድ ወጣት፤ በተቀጣጠሩበት ሰዓት ሳይመቸው ቀርቶ ከቀጠሮው አራት ሰዓታት በኋላ ታንቆ በሞተ ጓደኛው ምክንያት የበደለኝነት ስሜት ውስጡን ክፉኛ የሚወቅሰው ወጣት . . . ተወዳጆች ሆይ፤ ትክክል ካልሆነ የበደለኝነት ስሜት እራሳችሁን ነጻ አድርጉ፡፡
       ብዙ ሰዎች በእግዚአብሔርም በሕሊናም ፊት ፍትሃዊ ባልሆኑ ነገሮች ሲወቀሱና ሲከሰሱ ይኖራሉ፡፡ አግባብ በሆነ መንገድ ራሳችሁንና ኑሮአችሁን ፈትሹ ሊስተካከል የሚገባው ነገር ካለ የሚጠይቀውን ሁሉ ጤናማ በሆነ እርምጃ አድርጉ፤ ልታስተካክሉ እድል ያጣችሁበትን (ለምሳሌ፡- ሞት) ከእግዚአብሔርና ከራሳችሁ ጋር ጨርሱ፡፡ አግባብ የሆነውን የበደለኝነት ስሜታችሁን እንኳን ቶሎ ወደ መፍትሔ አምጡት፡፡ ክፉኛ የሚወቀሱና ሕሊናቸው የሚከሰስ ሰዎች የሚንቀሳቀሱ የአካል ክፍሎቻቸው እስከማይታዘዟቸው ድረስ ድንዛዜና መጨበጥ ሊሆንባቸው ይችላል፡፡
          ይራመዳሉ ግን ሊራመዱ በሚችሉበት አቅም መጠን አይደለም፡፡ ያስባሉ ግን ማሰብ በሚችሉት ጉልበት ያህል አይሆንም፡፡ የሚያዩት የሚሰሙትና የሚገኙበት ሁሉ ወቃሽ ይሆንባቸዋል፡፡ ተወዳጆች ወዳጆቼ፤ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ለበደል ሁሉ ስርየት ነው፤ ‹‹በውድ ልጁም እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት›› /ኤፌ. 1፡7/፡፡ በእርግጥም ሕሊናችሁ ውስጥ የሞተ ሥራ (በደል) ካለ፤ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ባቀረበ በክርስቶስ ደም ፍጹም መንጻትን አግኝታችኋል (ዕብ. 9፡14)፡፡  
·        ራሳችሁን የማግለል መፍትሔ አይኑራችሁ፡ ብቸኝነት ጠላት ነጥሎ እኛን የሚያገኝበት የእሱ ምቹ ስፍራ ነው፡፡ መገለል የአካል ብቻ አይደለም፡፡ በስልክ ምክክር ከማውቀው የትዳር ችግር ተሞክሮ ብናነሣ አንድ ቤት ይኖራሉ፤ አንድ መኝታ ይጋራሉ፤ ዳሩ ግን እሷ ብቻዋን ናት፡፡ ለሚመለከታቸው፤ ቤታቸው ለሚመጣ፤ ስለ እነርሱም ለሚሰማ ትዳሩ የቆመ ነው፡፡ ከኃያሉ ከእግዚአብሔር እና በተወሰነ ሁኔታ ከጉዳዩ ባለቤት በቀር የማንም ማስተዋል በማይደርስበት ስፍራ ግን ትዳሩ ፍቺ ላይ ነው፡፡
         ችግር ታቅዶ አይመጣም፡፡ ለመጡ ችግሮች ግን መፍትሔ እናቅዳለን፡፡ ከመፍትሔ አሳቦቻችሁ ቀዳሚው እግዚአብሔር መሆን እናዳለበት ሁሉ እራሳችሁን የማግለል መፍትሔ ደግሞ ፈጽሞ (ግድ የምንልበት አስገዳጅ ሁኔታ እንዳለ ሆኖ) ሊኖር አይገባም፡፡ ቤተሰብና ትዳር በእያንዳንዱ ነገር ላይ ተሳትፎአችንን የሚጠይቁ ግንኙነቶች ናቸው፡፡ በእነዚህ ውስጥ የሚኖረው መኮራረፍ የአገር መኮራረፍ፤ የሚፈጠረውም ትርምስ የሕዝብ ሁሉ ትርምስ ነው፡፡
         ብቸኝነትን አልያም ራሳቸውን ማግለልን እንደ መደበቂያ የሚቆጥሩት፤ በማወቅም ባለ ማወቅም በዚህ ውስጥ የሚያልፉ ብዙ ናቸው፡፡ መረሳት የሌለበት ነገር ቢኖር ብዙ ግንኙነቶች በተለይ ትዳርና ቤተሰብ አካላችን ካልሆነ በቀር አሳባችንን የማናርቅባቸው ናቸው፡፡ ኮሽ ሲል እህ ማለት አይቀርም፡፡ ሸሽተን የሚመጡ መፍትሔዎች እንዳሉ ሁሉ ቀርበን፤ ዋጋ ከፍለን የሚመጡ መፍትሔዎችም አሉ፡፡ ሁለቱን መለየት አለመቀላቀል፤ ለትክክለኛው ለአንዱ ተግባራዊ መታዘዝ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡
       ችግሮች ላይ ማውራትን፤ ተደጋጋሚ ግን አሰልቺ ባልሆነ መንገድ ውይይት ማድረግን፤ አግባብ የሆነ ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛ መሆንን አዳብሩ፡፡ ራሳችሁን በቀላሉ ማግለል ግን አይቅለላችሁ፡፡ ችግር የበለጠ እናንተን የሚያደቅና የሚጥልበት አንዱ ምቹ ስፍራ ነውና፡፡ መነጋገርን፤ ለትክክለኛው ሰው ችግር ማካፈልን፤ እውነተኛ ስሜትን መግለጽ መቻልን፤ የችግሩን ዝርዝር ነገር መለየትን ተለማመዱ፡፡
ü ስሜታችሁን በትክክል መረዳት፡፡
ü የተረዳችኋቸውን ስሜቶች በትክክል መያዝ መቻል፡፡
ü የቤተሰቦቻችሁን ወይም የትዳር አጋራችሁን ስሜት ለይቶ መረዳት፡፡
ü አሁንም ከተረዳችኋቸው የሌሎች ስሜት ጋር በትክክል ግንኙነትን መጠበቅ፡፡
ü በአግባቡ መለየት፤ መቆጣጠር እና ትክክለኛ እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡
·        መልካም አጋጣሚዎችን ቸል አትበሉ፡ በጨለማው አቅጣጫ የምታፈጡ ከሆነ ከብርሃኑ ጋር ተላልፋችኋል፡፡ ብዙ ሰዎች ጥሩ የሚባልን ሁኔታ መፍጠር ቀርቶ የተገኘውንም ለጥቅማቸው ለማድረግ ይፈተናሉ፡፡ ከዚህም የተነሣ ምሬት ልባቸውን ይሞላል፡፡ ልንሠራ የማንችልባቸውን ምክንያቶች ከመደርደር ይልቅ ልንሠራ የምንችልበትን አንድ እድል መጠቀሙ ላይ ጊዜን ማዋል ውጤታማ ያደርገናል፡፡
    አጋጣሚዎችን በአግባቡ አለመለየት ችግር መሆኑ እንዳለ ሆኖ፤ እንደሚገባ ልንሠራባቸው ያሉ ምቹ ጊዜዎችን ግን ማባከን አልፎ ቁጭቱ ያማል፡፡ ፈተናና መጥፎ አጋጣሚዎች ካላቸው ተጽእኖ መካከል፤ ከመልካም አጋጣሚዎች ጋር እንድንተላለፍ ማድረግ አንዱ ነው፡፡ አብዛኛው ችግርተኛ ችግሩ ተጨማሪ ችግር እንዲፈለፍል በማድረግ እነዚያን የሚያሳድግ ነው፡፡  
          ከተዘጉ በሮች ላይ ዓይናችሁን አንሡ፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ ፍጥሞ በምትባል ደሴት ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር ታስሮ የነበረበትን ሁኔታ ስንመለከት አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም እንኳ፤ በዚያ ውስጥም ትልቅ እድል ነበረ (ራእ. 1፡9)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ከጻፋቸው መልእክታት ጥቂት የማይባሉ የተጻፉት በእስር ቤት ነበር (ፊል. 1፡12)፡፡ ሊሰብክ ያልቻለባቸው ሁኔታዎች ሊጽፍ ግን ችሎባቸዋል፡፡
       በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ መልካም የሆኑ አጋጣሚዎችን መመልከት መቻል አትራፊ ያደርጋል፡፡ ብዙ ትልልቅ ነገሮች የተከናወኑት ደስ በማያሰኙ መራራ ሁኔታዎች ውስጥ ነው፡፡ በክርስትና ሕይወት እንዳገኘን ስናወራ፤ ሕይወቱ የተገኘበት መንገድ እየተዘነጋን ነው እንጂ ‹‹መስቀል›› ነው፡፡ ትንሣኤ የተበሰረው ከሞት መርዶ በኋላ ነው፡፡ ቤተመንግሥት የተደረሰው ከብዙ ትግልና ውጣውረድ በኋላ ነው፡፡ ከሕጻንነት ወደ እድገት የሚመጣው ከብዙ መጋጋጥና መላላጥ በኋላ ነው፡፡
         ተወዳጆች ሆይ፤ ችግሩን ቁም ነገር አድርጋችሁት፤ ትልቁን ቁምነገር እንዳትጥሉ ተጠንቀቁ፡፡ ፈተናን በተመለከተ ‹‹ . . ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል›› /1 ቆሮ. 10፡13/ ተብሎ ተጽፍአል፡፡ ሰው ፈተናው ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ፤ መውጫውን ቸል ብሎ ባያስተውል፤ ደግሞ ለመውጣት ባይንቀሳቀስ መከራውን ያራዝማል፡፡ ችግሩን ብቻ አትመልከቱ፤ ከችግሩ ጋር ያለውን መፍትሔ ልብ በሉ፡፡  
v    ችግርዎን እንካፈልዎ፡- ፖ.ሳ.ቁ፡ 31106 አዲስ አበባ፤ ኢ-ሜል፡ bfb.tube@gmail.com  ወይም የእርስዎን አድራሻ ይላኩልን፡፡
                         ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment