Friday, December 25, 2015

‹‹ጽኑዕ ኃያል ለምጻም››

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


አርብ ታኅሣሥ 15 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

        እግዚአብሔር የሌለበት ጀግንነት፤ እርሱ ሞገስ ያልሆነለት ከፍታ፤ ቅዱሱን አምላክ የማያሳይ መክበር፤ ለእርሱም የማይገዛ ሥልጣንና ባለ ጠግነት እጅግ ከንቱ ነው (ሉቃ. 12፡21)፡፡ ጌታችን ‹‹ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል።›› (ማቴ. 12፡30) ብሎ እንደተናገረ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም ማድረግ ከየትኛውም ብልጥግና የላቀ ነው (ኢሳ. 27፡5-6)፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል?›› /ማቴ. 16፡26/ እንዳለን፤ ለሰው ወደ እግዚአብሔር እንደመድረስ ያለ ስኬት፤ ብልጥግናም የለም፡፡

         የሶሪያ ንጉሥ ሠራዊት አለቃ ንዕማን፤ በጌታው (በንጉሡ) ዘንድ ታላቅ ክቡር ሰው ነበረ፤ ደግሞም ጽኑዕ ኃያል ነበረ (2 ነገ. 5፡1-4)፤ ነገር ግን ለምጻም ነበረ፡፡ የሠራዊት አለቃ ለምጻም፤ ታላቅ ክቡር ሰው ለምጻም፤ ጽኑ ኃያል ለምጻም ነበረ፡፡ ከአህዛብ የሆነውን ይህን ሰው ከእግዚአብሔር ቃል በቀር ማን እንዲህ ሊለው ይችል ነበር? ከስሩ የሚታዘዙ ሎሌዎቹ ታሪኩን ቢጽፉት ኖሮ እንዲህ ተጽፎ አናነብም፡፡ የአለቆቻቸውን ግብር እየበሉ ታሪክ አምታተው ስለጻፉ ተወቃሾች ብዙ የሚባልባት አገር ላይ እንዳለን አንስተውም፡፡ እግዚአብሔር ብቻ ልካችሁን ይናገራል፡፡

         ዘመን ማስቆጠራቸውን፤ ብዙ ወዳጅ ማፍራታቸውን፤ ስለራሳቸው ያወሩትንና አብልተው ጭምር ያስወሩትን አይቶ የዋህ ልባችን ‹‹አንቱ›› ያላቸው በእውነት ፊት ቀለው አይተናል፡፡ ለሰው ከተያዘበት ምድራዊ ነገር በላይ ውርደት የለም፡፡ ‹‹ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?›› /ኢሳ. 6፡8/ የሚለው የእግዚአብሔር ድምጽ ከመቼውም ጊዜ በላይ የገባኝ አሁን ነው፡፡ በምታልፈው ዓለም ላይ ያለው ባለ ጠግነት ፍለጋ የሌለውን የክርስቶስን ባለ ጠግነት (ኤፌ. 3፡8) ካስጣለን፤ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን (1 ቆሮ. 15፡19)፡፡

         ተወዳጆች ሆይ፤ ዓለሙን በሞላው ጌታ እንደሚያየው ማየት ለክርስቲያኖች በእጅጉ የተገባ ነው፡፡ የምድር ጨውና የዓለም ብርሃን (ማቴ. 5፡13-14) የሆኑት ክርስቲያኖች ለምድሪቱ መፍትሔ ናቸው፡፡ ችግርን በችግሩ በኩል ካላያችሁት መፍትሔ መሆን አይቻላችሁም፡፡ ንዕማንን አስቡት፤ በቤተ መንግሥት ያሉቱ እንዴት የሚመለከቱት ይመስላችኋል?፤ ውለታ የዋሉልንን መገሠጽ፤ ወገኔ የምንላቸውን ማረም፤ የከበቡንን ወዳጆች ማስተካከል፤ ጌታ ልቡ ከሌለበት ረብ መለየት የብዙ ክርስቲያኖች ፈተና ነው፡፡ በዚህም የአሁኑን ዓለም ወድደው የሚኖሩ ብዙ ናቸው፡፡

        ንዕማንን በዙሪያው ያሉ በሠራዊት አለቅነቱ በኩል፤ በታላቅ ክቡር ሰውነቱ በኩል፤ በጽኑዕ ኃያልነቱ በኩል በታማኝነት ጭምር እንደሚመለከቱት መረዳት ከባድ አይሆንም፡፡ ዛሬም እኛ ‹‹ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና›› የተባልን በምድር ያለውን እንዴት እያየነው ነው? የአሁኑ ዓለም ብልጥግናው፤ የሰዎች የሰው መካከል ክብራቸው፤ ሀብትና ንብረታቸው፤ የሥጋና የደም ጥበብ ብልሃታቸው፤ የጊዜው ማስፈራራት የስብ ሞገሳቸው . . . በየት በኩል ነው የምንመለከታቸው? እግዚአብሔር ጥሪው ቅዱስ ነውና (2 ጢሞ. 1፡9) ለዚህ አልተጠራንም፡፡

        ከክፉ መንገዱ እንዳይመለስ የኃጢአተኛውን እጅ ማበርታት ከእግዚአብሔር ቅጣትን ይቀበላል፡፡ እግዚአብሔር ኃጢአተኛውን በእርግጥ ትሞታለህ ባለ ጊዜ በደለኛው ከመንገዱ እንዲመለስ እናስጠነቅቀው ዘንድ ባንናገር ኃጢአተኛው ይሞታል፤ ደሙን ግን እግዚአብሔር ከእጃችን እንደሚፈልግ (ሕዝ. 33፡8) ተጽፎአል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ወደ ዓለም የመጣው ኃጢአተኞችን ሊያድን ነው (1 ጢሞ. 1፡15)፡፡ ቤተ ሰዎቻችን ቢሆኑ አልያም ወዳጆቻችን እውነት በሆነው የእግዚአብሔር ቃል በኩል ብናያቸው ወደ መፍትሔው እናደርሳቸዋለን (ዮሐ. 4፡41-42)፡፡ ‹‹ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው›› /1 ጢሞ. 2፡3/፡፡

       በሶርያውያን አደጋ ጣዮች ከእስራኤል ምድር ተማርካ በንዕማን ቤት አገልጋይ የነበረች ታናሽ ብላቴና በዚያ ነበረች፡፡ ለንዕማንም ሚስት ‹‹ጌታዬ በሰማርያ ካለው ከነቢዩ ፊት ቢደርስ ኖሮ ከለምጹ በፈወሰው ነበር›› በማለት አስረዳቻት (2 ነገ. 5፡3)፡፡ በዚህች ብላቴና ውስጥ የነበረውን እምነትና ድፍረት መመልከቱ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ የእግዚአብሔር መፍትሔ የሚገኝበት ታናሽነት እጅግ ትልቅነት ነው፡፡ ሐዋርያው ጢሞቴዎስን ‹‹ . . ማንም ታናሽነትህን አይናቀው›› /1 ጢሞ. 4፡11-12/ እንዳለው፤ በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ በመሆን ወደምንኖርበት ከፍታ መምጣትን መለማመድ ያስፈልጋል፡፡

       ብላቴናይቱ ንዕማንን በለምጹ በኩል አስተዋለችው፡፡ በአገር ደረጃ ጀግና፤ ታላቅ ክቡር ሰው፤ ጽኑዕ ኃያል የሆነው ሰው መፍትሔ እንደሚፈልግ፤ ያውም የሕያው እግዚአብሔርን መፍትሔ ተረዳች፡፡ ለሚያልፈው መፍትሔ የሆኑ በማያልፈው (በዘላለሙ) ተቸግረዋል፡፡ በሚታየው የደመቁብን፤ በማይታየው ግን ምስኪኖች ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ በመንፈስ፤ በሥጋ፤ በነፍስ የተጎሳቆሉ ብዙ ናቸው፡፡ በእግዚአብሔር በኩል ወደ ሰዎች መድረስ፤ የእግዚአብሔርን የልቡን ምክርና የዘላለም አሳቡን ለሥጋ ለባሽ ሁሉ መግለጥ ጽድቅ ነው፡፡

       ለምጽ የኃጢአት ማሳያ ሆኖ በቅዱሱ መጽሐፋችን ተገልጾአል፡፡ ‹‹ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል . . ›› /ሮሜ 3፡23/ እንደተባለ፤ ኃጢአተኛው ዓለም መድኃኒት ያስፈልገዋል፡፡ የንዕማን ሥጋ እንደ ትንሽ ብላቴና ሥጋ ንጹሕ የሆነበት ውኃ ሳይሆን፤ ለዓለሙ ሁሉ የፈሰሰ የሥርየት ደም (ይቅርታ ማግኛ) ያሻዋል፡፡ ከነቢይ የሚበልጥ (ማቴ. 11፡9)፤ ኃጢአታችንን በራሱ ደም ያነጻ (ዕብ. 1፡3)፤ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን እርሱም የበደላችንን ስርየት ወዳገኘንበት (ኤፌ. 1፡7) ወደ ፍቅሩ ልጅ (ቆላ. 1፡13) ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ መድረስ ያስፈልጋል፡፡

       ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት አድርጎ ‹‹የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ ይህንን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግናለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፤ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና›› /ሉቃ. 10፡21/ በማለት የጸለየውን ጸሎት ስንመለከት፤ እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ ያስቀመጠው መፍትሔ ከዚህ ዓለም ጥበበኞችና አስተዋዮች የተሰወረ እንደሆነ እንረዳለን፡፡

       ‹‹እግዚአብሔር አምላክ ነው፤ ለእኛም በራልን›› እንደተባለ፤ ደግሞ ‹‹በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ፡- በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና›› /2 ቆሮ. 4፡6/ ተብሎ እንደተጻፈ፤ ‹‹የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ የሆነ›› (ቆላ. 2፡3) ኢየሱስ ክርስቶስን መረዳት ከዚህች ዓለም ጥበብና እውቀት የተነሣ ሊሆን አይችልም፡፡ ጌታ ‹‹ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና›› (ማቴ. 16፡17) እንዳለ፤ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ የመሆኑ ነገር በሰማያት ያለው አባት የሚገልጠው እውነት ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ‹‹ሰውረህ . . . ስለገለጥህላቸው›› በማለት ስለ ሁለት ነገር አመሰገነ፤ ጥበበኛና አስተዋይ ነን ለሚሉት ስለመሰወሩ፤ ሕጻናት ለሆኑት ጥበብና ማስተዋል ለማይገኝባቸው (ለማይጠበቅባቸው) ደግሞ ስለተገለጠ፡፡

        ተወዳጆች ወዳጆቼ ሆይ፤ ንዕማን ፊት ክብር ሕጻን መሆን ነው፡፡ መፍትሔው ያለው ታናሽ ብላቴና ውስጥ ነው፡፡ የንዕማን የችግሩ እንቆቅልሽ በአንዲት ምርኮኛ የቤት ውስጥ ባሪያና ሕጻን በኩል ይፈታል ብሎ ማን ሊጠብቅ ይችላል? ጌታ እግዚአብሔር ከሰው እሳቤና ግምት ባለፈ ይሠራል፡፡ ከጠበቃችሁት አቅጣጫ ሳይሆን መፍትሔያችሁ ካልጠበቃችሁበት በኩል ይሆናል፡፡ እናንተ የጨከናችሁበት፤ ልባችሁም በገፋው ውስጥ የመለኮት መፍትሔ ይቀመጣል፡፡ ዮሴፍ የሸጡት ወንድሞቹ እንደ በረከት ሊፈልጉት ተሰደዋል፡፡ አስቀድሞ የሸጡት እርሱ እንጀራቸው ነበር፡፡ በኋላ ግን ፍለጋው ቀላል አልነበረም፡፡ ዋጋ ከፍለውበታል፡፡

        በንጉሥ ግብዣ፤ በሹማምንት መካከል፤ በብዙ ሎሌዎች ፊት በሞገስና በክብር የሚቀመጠው ሰው ከተማረከች የቤቱ ሠራተኛ አፍ ደኅንነት ይወጣል ብሎ አይጠብቅ ይሆናል፤ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ምክር በሰው የማይጠበቀው ሆነ፡፡ እግዚአብሔርን ማን እንዲህና እንደዚያ አድርግ ሊለው ይችላል? መርዶክዮስን እያከበረ ሲያዞር የነበረው ሐማ ነገሮች እንደዚያ ይሆናሉ ብሎ መቼ አሰበ? ‹‹በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ፤ የእግዚአብሔር ምክር ግን እርሱ ይጸናል›› /ምሳ. 19፡21/ ተብሎ እንደተጻፈ፤ ከእግዚአብሔር የሆነውን ማንም አያቆምም፡፡ ከሰው ልብ ብዙ አሳብ ይልቅ ለታላቅነቱ ፍጻሜ የሌለው የሕያው እግዚአብሔር ምክር ይጸናል፡፡

        እግዚአብሔር እውነትና መፍትሔ ሆኖ ከማይገለጥበት ምቾት፤ ጌታን የሚያከብር ጉስቁልና በእጅጉ ይበልጣል፡፡ ለእግዚአብሔር ከማይመች ከፍታ፤ የእርሱ ክንድ የሚሠራበት ዝቅታ ይልቃል፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ በእናንተ ስላለው መድኃኒት ኢየሱስ በፍጹም ግልጥነት መስክሩ (ሐዋ. 4፡29-30)፡፡ ንዕማን ፊት ተናገሩ፤ የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና (ሮሜ 6፡23)፤ የምዋቹን ሞት በማይፈቅድ (ሕዝ. 18፡32) በእግዚአብሔር ፊት ሕይወት የሚገኝበትን (ቲቶ 2፡1) ክርስቶስ ኢየሱስን አውሩ፡፡ ሁኔታው በሶሪያ እንደነበረችው ብላቴና ባይመች እንኳ እውነትን ተናገሩ፤ አትፍሩ፡፡ ንዕማን የሠራዊት አለቃ፤ ታላቅ ክቡር ሰው፤ ጽኑዕ ኃያል ቢሆንም ዳሩ ግን ለምጻም ነው፤ የእናንተ መፍትሔ ያሻዋል፤ በእምነት ድፈሩ፡፡
                          ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!
        

No comments:

Post a Comment