(መልእክት ወደ ፊልሞና)
‹‹እምጳውሎስ ሙቁሐ ለኢየሱስ ክርስቶስ፡ (ኤፌ. 3፡1)››!
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመንፈሳዊ ሕይወት ትክክለኛ እድገት መሰረታዊ ነገር
ነው፡፡ በስብከትና በንባብ የምናዘወትረውን የእግዚአብሔር ቃል በጥናት መልክ ለመረዳት መሞከር፤ ጊዜ መድቦ መመርመር ከክፍሉ የበለጠ
እንድንጠቀም ይረዳናል፡፡ በክርስትና ኑሮአችን ቋሚ የሆነ፤ አማራጭ የማናስቀምጥበት ‹‹ቃሉን የማጥናት ጊዜ›› ቢኖረን እራሳችንን፤
እንዲሁም በዙሪያችን ያሉትን እንጠቅማለን፡፡
ተወዳጆች ሆይ፤ ያለ እግዚአብሔር ቃል በማንሻገረው የአሁኑ ዓለም ቋሚ ውጊያ
እንዲሁም በዲያብሎስ ሽንገላ መካከል እንደምንመላለስ ላስታውሳችሁ
እወዳለሁ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ . . . የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው›› /ኤፌ. 6፡17/ ይለናል፡፡
በሚታየው ዓለም የማይታየውን መንፈሳዊ ውጊያ በመንፈስ ሰይፍ ካልሆነ በቀር ድል ልናገኝ አንችልም፡፡
ቃሉ ሕያው የሚሠራ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ
ነው፤ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፤ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል (ዕብ. 4፡12)፡፡
የእግዚአብሔርን ቃል ብርታት የምንረዳው ወደ ሕያው ቃሉ ስንጠጋ፤ እንደተጻፈልን እንደዚያው ስንጠቀምበት ነው፡፡ ‹‹የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው›› /2 ቆሮ. 4፡3/ እንደተባለ፤
የቃሉ ፍቺ እንዲያበራልን (መዝ. 118፡130)፤ አስተዋዮችና ጥበበኞችም እንዲያደርገን በመንፈስ ሆነን ጊዜ ሰጥተን ቃሉን ልንመረምር
ይገባል፡፡
‹‹አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና›› /ሮሜ 15፡4/ እንደተባለ፤
ቅዱስ ቃሉ ትምህርታዊ ይዘት ያለው እንደመሆኑ ከቅዱሱ ቃል መርጠን አንድ ክፍል እናጠናለን፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም ክፍሎች የእግዚአብሔር
መንፈስ ያለባቸው እንደ መሆናቸው አንዱን ከሌላው ልናበላልጥ አይገባም፡፡ ነገር ግን እድገታችንን በጠበቀ መልኩ ልናጠናው ይገባል፡፡
‹‹መስማትም በሚችሉበት መጠን . . . ቃሉን ይነግራቸው ነበር›› /ማር. 4፡33/ ተብሎ እንደተጻፈ፤ ልንረዳው በምንችለው አቀራረብ
ቃሉን ለማጥናት መወሰን በእጅጉ ተገቢ ነው፡፡
እግዚአብሔር
በፊታችን በሚሰጠን ጊዜ ከአዲስ ኪዳን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የ‹‹ፊልሞና መልእክት››ን እናጠናለን፡፡ መልእክቱ ፊልሞና ለተባለ
ግለሰብ፤ የቆላስይስ ቤተክርስቲያን በቤቱ የነበረች፤ ጠቃሚ የሚል ትርጉም ያለው አናሲሞስ የተባለ ባሪያ የነበረው፤ ወንጌል ከሐዋርያው
ጳውሎስ ሰምቶ በክርስቶስ ክርስቲያን ለሆነው ለእርሱ የተጻፈ ነው፡፡ መልእክቱ አንድ ምእራፍና ሃያ አምስት ቁጥሮች ያሉት ሲሆን፤
በ61-63 ዓ.ም ባለው ጊዜ እንደተጻፈ ይታሰባል፡፡ ጸሐፊው ሐዋርያው ጳውሎስ ሲሆን፤ የመልእክቱ ይዘት ‹‹በክርስቶስ ያለን ወንድማማችነት››
የሚል ይሆናል፡፡ በፍቅር ቤታችን (ቤተ ፍቅር) መልእክቱን እንድናጠናው የሆነበትም ምክንያት ይህ ነው፡፡ መልእክቱ እርስ በርሳችን
የምንተያይበትን ትክክለኛ የፍቅር ልኬት ይሰጠናል፡፡
የፊልሞና መልእክት ከሌሎች መልእክታት በበለጠ ሐዋርያው በራሱ እጅ እንደጻፈው
ይታመናል፡፡ ለምሳሌ የሮሜ መልእክት ላይ ‹‹ይህን መልእክት የጻፍሁ እኔ ጤርጥዮስ›› /ሮሜ 16፡22/፤ እንደሚል፤ ሐዋርያው መልእክቱን
በረዳቱ አማካኝነት እንደጻፈው እናውቃለን፡፡ ተወዳጅ የሚል የስም ትርጉም ያለው ፊልሞና የባሪያው የአናሲሞስ አሳዳሪው ሳለ፤ ባልተገለጸልን
ምክንያት አናሲሞስ ከጌታው ኮብልሎ ወደ ሮም በመሄድ በዚያ ሐዋርያው ጳውሎስን ያገኘዋል፡፡ በዚያም ከሐዋርያው ወንጌልን ሰምቶ በማመን
እውነተኛ ክርስቲያንና የሐዋርያው የጳውሎስ ቅርብ ረዳት አገልጋይ (የልቤ ሰው) ይሆናል፡፡
ሐዋርያው ከፊልሞና አምልጦ ወደ ሮም የመጣውን ባሪያ አናሲሞስን ይህንን
መልእክት በመጻፍ ወደ ፊልሞና መልሶ ይልከዋል፡፡ በመልእክቱም ‹‹ተቀብለህ ለዘላለም እንድትይዘው . . ›› /ቁ. 15/ በማለት
በፍቅር ይጠይቀዋል፡፡ በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ውስጥ ያለው ዋና አሳብ ይህ ነው፤ ለዘላለም መቀባበልና መያያዝ፡፡ ጌታችን
‹‹እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ››
/ዮሐ. 13፡ 34/ እንዳለን፤ በክርስትና ውስጥ የመቀባበልና የመያያዝ መሰረቱ ‹‹እንደ ወደድኋችሁ›› የሆነበት መሠረት ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ አዲስን ትእዛዝ በሰጠበት በዚህ ክፍል ‹‹እርስ
በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ›› የሚለው እንደተደገመ ልብ በሉ፡፡ ሐዋርያው ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ‹‹ከሌለኝ ከንቱ ነኝ›› /1 ቆሮ.
13፡2/ ያላቸው ፍቅርን ነው፡፡ አናሲሞስንም በተመለከተ ፊልሞና ይቅርታ እንዲያደርግለት፤ በክርስቶስ የተወደደ ወንድሙ አድርጎ
እንዲቀበለው፤ በሮማውያን ሕግ መሠረት ሊገደል የሚገባውን፤ የሕግ ሁሉ ፍጻሜ በሆነው ክርስቶስ (ሮሜ 10፡4) እንዲቀበለው በመልእክቱ
ተጠይቋል፡፡
ማሳሰቢያ፡ መልእክቱን በማጥናት የምትከታተሉ
መጽሐፍ ቅዱስ እና የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት (በመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የተዘጋጀ) እንዲኖራችሁ እመክራለሁ፡፡ ለቀጣዩ የመልእክቱን ክፍል በማስተዋል አንብቡ!
‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!
No comments:
Post a Comment