(መልእክት ወደ
ፊልሞና)
‹‹እምጳውሎስ ሙቁሐ ለኢየሱስ ክርስቶስ፡ (ኤፌ. 3፡1)››!
· ጸሐፊው፡- ሐዋርያው ጳውሎስ ሲሆን፤ መልእክታቱን
በአገልግሎት አጠገቡ ሆነው በሚረዱት እርሱ እየተናገረ ያጽፍ እንደ ነበር (ሮሜ 16፡22፤ 1 ቆሮ. 16፡21፤ ገላ. 6፡11፤
ቆላ. 4፡18፤ 2 ተሰ. 3፡17)፤ ነገር ግን ለፊልሞና የተላከውን ይህንን መልእክት በገዛ እጁ እንደ ጻፈው ይነግረናል (ፊል.
19)፡፡
· የተጻፈበት ጊዜ፡- የፊልሞና መልእክት የቆላስይስ መልእክት
በተጻፈና በተላከ ጊዜ በተመሳሳይ ከሮም (ሐዋርያው በእስር ቤት ሳለ) አብሮ የተላከ መልእክት ሲሆን፤ ጊዜውም ከ61 – 63 ዓ/ም
ባለው ወቅት እንደ ሆነ ይታሰባል፡፡
· የመልእክቱ ጭብጥ ፡- ሁላችንም ባሮች የነበርን ሲሆን፤
ነገር ግን በክርስቶስ ወንድሞችና እህቶች ነን የሚል ነው፡፡
‹‹የተወደደ፤ የሚለው አገላለጽ ሙገሣን አልያም ልዩ መሆንን የሚያሳይ
ሳይሆን፤ ጥልቅ የሆነ ፍቅርን ለማሳየት የተነገረ ነው፡፡ . . . አብሮን ለሚሠራ፤ የሚለው ደግሞ ወንጌልን ከማስፋትና ሌሎችን
ወደ እምነት ከማምጣት ጋር በተያያዘ ያለውን አገልግሎት በተመለከተ የተነገረ ነው፡፡›› /ቅዱስ
ዮሐንስ አፈወርቅ/
ሌሎችን መውደድ በሌለበት፤ በትክክል እግዚአብሔርን ማመን አይኖርም፡፡
በክርስትና ውስጥ አብሮ መሥራት ከመዋደድ ባነሰ ነገር ላይ ሊመሠረት አይችልም፡፡ ጌታ ለጴጥሮስ ትልቅ ኃላፊነት ሲሰጠው፤ አስቀድሞ
የጠየቀው ‹‹ትወደኛለህን?›› (ዮሐ. 21፡15-17) በማለት ነበር፡፡ ፊልሞና በሌሎች ወንድሞች ልብ ውስጥ የተወደደ መሆኑ ጌታን
ከመውደዱ የተነሣ እንደ ሆነ ልንረዳ እንችላለን፡፡