Wednesday, January 6, 2016

‹‹ይህ አሳርፎናል››

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


ረቡዕ ታኅሣሥ 27 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

          ‹‹ላሜሕም መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ልጅንም ወለደ። ስሙንም፦ እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከተግባራችንና ከእጅ ሥራችን ‹‹ይህ ያሳርፈናል›› ሲል ኖኅ ብሎ ጠራው።›› /ዘፍ. 5፡28-29/!

          ‹‹በተረገመች ምድር፡ ረፍታችን!›› በሚል ርእስ የጀመርነው ጽሑፍ ቀጣይ ንባብ ነው፡፡ ላሜሕ ‹‹ይህ ያሳርፈናል›› በማለት ተስፋውን በሚገልጥ መልኩ ከእረፍት ጋር በተያያዘ የልጁን ስም አውጥቷል፡፡ ዳሩ ግን ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ /ዘፍ. 3፡17/ ተብሎ የተረገመውን ላሜሕ (እኛንም ጨምሮ) ከወገቡ ፍሬ፤ ከእጁ ሥራ፤ ጽድቄ ከሚለው ተግባር እረፍትን ሊያገኝ አልቻለም፡፡


         ‹‹ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፤ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፤ አንድ ስንኳ የለም›› /ሮሜ 3፡11-12/ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ ‹‹አንድ ስንኳ›› ቤዛ ለሰው ከሰው መካከል ባለ መኖሩ ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአል›› /ዮሐ. 3፡16/፡፡ እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጅ ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥና ኃጢአተኞችን ሊያድን ወደ ዓለም መጥቶአል /ማቴ. 20፡28፤ 1 ጢሞ. 1፡15/፡፡


          የሰው ልጆች እንቆቅልሽ፤ የዚህችም ምድር ቋጠሮ ፍቺ በበረት በተወለደው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ውስጥ ነው (ዕብ. 1፡1-3)፡፡ ምቾትና እረፍትን ለሚፈልግ ልብ ‹‹ቃል ሥጋ ሆኗል›› /ዮሐ. 1፡14/፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ከድንግል ማርያም ተወልዶአል (ሉቃ. 2፡8-14)፡፡ በእውነት! ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፤ ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ፤ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች ኢየሱስ ብቻ ነው (2 ቆሮ. 5፡14)፡፡ ይህ አሳርፎናል!

         በመጀመሪያዎቹ የማቴዎስና የሉቃስ ወንጌላት የትውልድ ቆጠራን እንመለከታለን፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ፤ ‹‹የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ›› /ማቴ. 1፡18/ ካለ ወዲያ ግን ሌላ ትውልድ አይቆጥርልንም፡፡ ለዘመናት ክፉው ዲያብሎስ ሲያሳድድና ሲዋጋው የኖረው ዘር ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ›› /ማቴ. 4፡3/ በሚል ግራ መጋባቱ ፊት ሥራውን ሊያፈርስ ኢየሱስ በሥጋ ተገለጠ (1 ዮሐ. 3፡8)፡፡ እርሱ ከጨለማው ሥልጣን ያዳነን (ቆላ. 1፡13)፤ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራን (1 ጴጥ. 2፡9)፤ ከሞት ወደ ሕይወት ያሻገረን (ዮሐ. 5፡24)፤ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች ያደረገን (ዕብ. 3፡1)፤ እውነትና ሕይወት መንገድም የሆነን (ዮሐ. 14፡6) . . ነው፡፡ ይህ አሳርፎናል!

        ወንጌላቱ በእግዚአብሔር በአባቱ ስም የወጣለትን ‹‹ኢየሱስ›› /ማቴ. 1፡21/ እንደ ብቸኛ እረፍት ያቀርቡልናል፡፡ መልእክታቱም ይህንኑ በጥንቃቄ ያጠናክሩልናል፡፡ እርሱ ለድሆች ወንጌልን፤ ለታሰሩትም መፈታትን፤ ለዕውሮች ማየትን፤ ለተጠቁት ነጻ መውጣትን የሰበከ ነው (ሉቃ. 4፡17-19)፡፡

         እርሱ የሕይወት ራስ (ሐዋ. 3፡15)፤ የማዕዘን ራስ (ሐዋ. 4፡11)፤ የወንድ ሁሉ ራስ (1 ቆሮ. 11፡3)፤ የቤተክርስቲያን ራስ (ቆላ. 1፡18)፤ የአለቅነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ (ቆላ. 2፡10)፤ የመዳን ራስ (ዕብ. 2፡10)፤ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ (ዕብ. 12፡2)፤ የሃይማኖታችን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት (ዕብ. 3፡1)፤ . . ነው፡፡ ይህ አሳርፎናል!

         እንደ ቃሉ በክርስቶስ ክርስቲያን ለሆኑ ሁሉ በአሁኑ ዓለም ኢየሱስ እረፍት ከሆነን በላይ ደግሞ ፍጹም እረፍት ወደ ፊት ተጠብቆልናል (ፊል. 3፡20)፡፡ በተስፋ እንደ መዳናችን (ሮሜ 8፡24)፤ የተባረከው ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እንጠብቃለን (ቲቶ. 2፡11)፡፡ ስፍራ ላዘጋጅላችሁ ብሎ ስለ እኛ የቀደመው ጌታ እንደ ቃሉ ይመጣል (ዮሐ. 14፡2)፡፡ የማይጨረስ እረፍት በክርስቶስ!

        ሕይወታችን የሆነ ክርስቶስ በክብር ሲገለጥ እኛ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር እንገለጣለን (ቆላ. 3፡4)፤ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ እድፈትም ለሌለበት ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ›› /1 ጴጥ. 1፡3/፡፡ የምስጋና ትልቅ ርእስ!     

        ኢየሱስ ክርስቶስ በጌርጌሴኖን አገር አጋንንት ያደረባቸውን ሁለት ሰዎች አግኝቶ ‹‹ኢየሱስ ሆይ፤ የእግዚአብሔር ልጅ ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን ወደዚህ መጣህን?›› እያለ የሚጮኸውን ክፉ ከእነርሱ ወጥቶ ወደ እርያዎች መንጋ እንዲሰደድ አደረገው፡፡ ይህን ተከትሎ እረኞቹ ወደ ከተማ ሄደው የሆነውን ተናገሩ፡፡ ከተማው ሁሉ ኢየሱስን ሊገናኝ እንደ መጣ፤ ባዩትም ጊዜ ከአገራቸው እንዲሄድላቸው እንደ ለመኑት (ማቴ. 8፡28-34) ወንጌላዊው ጽፎልን እናነባለን፡፡

        ‹‹እግዚአብሔርንም፡- ከእኛ ዘንድ ራቅ፤ ሁሉንም የሚችል አምላክ ምን ሊያደርግልን ይችላል? አሉት›› /ኢዮ. 22፡17/ ተብሎ በቀደመው ኪዳን የተነገረው በአዲሱም ኪዳን በበለጠ ሲደገም እናስተውላለን፡፡ ዓለማችን ከመለኮት የሆነውን እረፍት በእሽታ መንፈስ በሚቀበሉ ሰዎች ብቻ የተሞላች አይደለችም፡፡ ‹‹እርሱ ሰላማችን ነው›› (ኤፌ. 2፡14) የተባለውን ጌታ የገፋች ምድርም እንደ ሆነች ልብ እንላለን፡፡ ደስታ የሆነውን አዝነውበት፤ ሰላም የሆነውን ታውከውበት፤ ጤና የሆነውን ታመውበት፤ እረፍት የሆነውን ተቅበዝብዘውበት፤ መፍትሔ የሆነውን ኢየሱስ ታውከውበት ‹‹ከአገራችን ሂድ›› አሉት፡፡

        መፍትሔዋን ስለገፋችና ሰቅላ ስለገደለች ዓለም እንደነቅ ይሆናል፤ ዳሩ ግን ለክርስቶስ ጀርባውን ስለ ሰጠ ክርስትና (ሃይማኖትና ሥርዓት) የእግዚአብሔር ቃል የሚለውን ማስተዋል በእጅጉ አስፈላጊ ነው (ራእ. 3፡15-22)፡፡ የሎዶቅያ (የሰው አገዛዝ) ቤተክርስቲያን፤ ራስ የሆነው ክርስቶስ በስተውጪ ተጥሎ ‹‹እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ . . ›› የሚልባት የማኅበረ ምእመናን ስብስብ ናት፡፡ ‹‹በስሜ›› /ማቴ. 18፡20/ ያለው ጌታ፤ ስሙ ኢየሱስ ነው፡፡

        የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ፤ እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከተግባራችንና ከእጅ ሥራችን ያሳረፈን ነው፡፡ ነቢዩ በቅኔው ‹‹እግዚአብሔርን፡- አንተ ጌታዬ ነህ አልሁ፤ ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም›› /መዝ. 15፡2/ እንዳለ፤ ሰው ከክፉ ሥራው ብቻ ሳይሆን በጎነቴ ከሚለውም ማረፍ አለበት፡፡ ደኅንነትን እንዳገኘ፤ ወደ ጽድቅም እንደ ደረሰ ሰው በበጎ ሥራና በፍሬ ልንገለጥ የሚያስፈልግ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፤ ያንንም ልንደገፍበትና ከእግዚአብሔር ጋር ሒሳብ ልንተሳሰብበት ግን ፍጹም አይቻልም፡፡ ሰው ጽድቁም የመርገም ጨርቅ የሆነበት ምስኪን ነው፡፡

       ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእኛ የሚሠራ እግዚአብሔር ነው (ፊል. 2፡13)፡፡ ለዘላለም ሕይወት ሰው ለእግዚአብሔር የሚሠራለት ምንም ነገር የለም፡፡ የኃጢአታችን ደመወዝ ሞት እንደ ሆነ ሁሉ፤ የዘላለም ሕይወት ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ነው (ሮሜ 6፡23)፡፡ ሰዎች ሁሉ የሚድኑበት የእግዚአብሔር ጸጋ፤ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት የሚያስክድ ጸጋ ከእግዚአብሔር ለእኛ ተገልጦአል፡፡

       ክርስቲያን ስላመነ እንዳመነ ሰው በእምነት ይኖራል (ሮሜ 1፡17) እንጂ ለዘላለም ደኅንነት እግዚአብሔር ከተግባሩና ከእጅ ሥራው (ከሰው) የሚፈልገው ምንም ነገር የለም፡፡ ጌታችን ‹‹እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ . . ›› /ዮሐ. 17፡4/ እንዳለ፤ ‹‹ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ፡- ተፈፀመ አለ፤ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ›› (ዮሐ. 19፡30)፡፡ የፈፀመው ጌታ አሳርፎናል!    
      
       በሰማርያ የተሰበከውን የምስራች ተከትሎ ከከተማው ብዙ ሕዝብ ወደ ኢየሱስ መጣ (ዮሐ. 4፡39)፡፡ ብዙዎችም በእርሱ አመኑበት፤ በእነርሱም ዘንድ እንዲኖር ለመኑት፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ አንዱ ኢየሱስ ጌርጌሴኖን ላይ ሂድልን ተብሎ ሲለመን፤ ሰማርያ ላይ ደግሞ ከእኛ ጋር ኑር ተብሎ ሲለመን እንመለከታለን፡፡ በእናንተ ልብ ውስጥ ኢየሱስ እንዴት ነው? በሰማርያ ያሉቱ ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ በማወቅና በማመን አረፉበት፤ ‹‹እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና›› /ሉቃ. 2፡10/፡፡ በእውነት! እርሱ ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስ አሳርፎናል!!
                                      ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

1 comment:

  1. ቤተ ፍቅሮች እግዚአብሔር አምላክ ይባርካችሁ። በፌስ ቡክ የምትለቁትም ስለፍቅር የተጻፉት ጥቅሶች እጅግ መልካም ናቸው። በርቱ... እንዳይቆም። የእግዚአብሔር ጸጋ ይብዛ !!

    ReplyDelete