Tuesday, January 26, 2016

መልእክት ኀበ ፊልሞና፡፡(3)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


ማክሰኞ ጥር 17 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

(መልእክት ወደ ፊልሞና)

‹‹እምጳውሎስ ሙቁሐ ለኢየሱስ ክርስቶስ፡ (ኤፌ. 3፡1)››!

·  ጸሐፊው፡- ሐዋርያው ጳውሎስ ሲሆን፤ መልእክታቱን በአገልግሎት አጠገቡ ሆነው በሚረዱት እርሱ እየተናገረ ያጽፍ እንደ ነበር (ሮሜ 16፡22፤ 1 ቆሮ. 16፡21፤ ገላ. 6፡11፤ ቆላ. 4፡18፤ 2 ተሰ. 3፡17)፤ ነገር ግን ለፊልሞና የተላከውን ይህንን መልእክት በገዛ እጁ እንደ ጻፈው ይነግረናል (ፊል. 19)፡፡
·  የተጻፈበት ጊዜ፡- የፊልሞና መልእክት የቆላስይስ መልእክት በተጻፈና በተላከ ጊዜ በተመሳሳይ ከሮም (ሐዋርያው በእስር ቤት ሳለ) አብሮ የተላከ መልእክት ሲሆን፤ ጊዜውም ከ61 – 63 ዓ/ም ባለው ወቅት እንደ ሆነ ይታሰባል፡፡
· የመልእክቱ ጭብጥ ፡- ሁላችንም ባሮች የነበርን ሲሆን፤ ነገር ግን በክርስቶስ ወንድሞችና እህቶች ነን የሚል ነው፡፡

     ‹‹የተወደደ፤ የሚለው አገላለጽ ሙገሣን አልያም ልዩ መሆንን የሚያሳይ ሳይሆን፤ ጥልቅ የሆነ ፍቅርን ለማሳየት የተነገረ ነው፡፡ . . . አብሮን ለሚሠራ፤ የሚለው ደግሞ ወንጌልን ከማስፋትና ሌሎችን ወደ እምነት ከማምጣት ጋር በተያያዘ ያለውን አገልግሎት በተመለከተ የተነገረ ነው፡፡›› /ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ/

       ሌሎችን መውደድ በሌለበት፤ በትክክል እግዚአብሔርን ማመን አይኖርም፡፡ በክርስትና ውስጥ አብሮ መሥራት ከመዋደድ ባነሰ ነገር ላይ ሊመሠረት አይችልም፡፡ ጌታ ለጴጥሮስ ትልቅ ኃላፊነት ሲሰጠው፤ አስቀድሞ የጠየቀው ‹‹ትወደኛለህን?›› (ዮሐ. 21፡15-17) በማለት ነበር፡፡ ፊልሞና በሌሎች ወንድሞች ልብ ውስጥ የተወደደ መሆኑ ጌታን ከመውደዱ የተነሣ እንደ ሆነ ልንረዳ እንችላለን፡፡

       በእምነት እንደሚገባ ለመኖር ከፍቅር የበለጠና የተለየ ምንም ኃይል የለም፡፡ በዓለም ሥርዓት አብሮ ለመሥራት የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች ይኖሩ ይሆናል፤ በእኛ ዘንድ ግን በክርስቶስ የሆነ ‹‹የእርስ በርስ መዋደድ››ን የሚተካ ምንም ነገር የለም (1 ቆሮ. 13)፡፡ ክርስትና ባሮች ወደ ‹‹ተወደደ ወንድምነት›› የሚለወጡበት፤ ከነገድ፣ ቋንቋና ዘር የተዋጀንበት (ራእ. 5፡9) ሰማያዊ ጥሪ ነው (ዕብ. 3፡1)፡፡ ከሁሉ በላይ በጌታ የተወደድን እንደ ሆንን ልናስተውል ያስፈልጋል፡፡


‹‹በቤትህ ላለች ቤተ፡ ክርስቲያን››


       የቆላስይስ ምዕመናን በፊልሞና ቤት ውስጥ ይሰበሰቡ ነበር፡፡ አፍብያ የፊልሞና ሚስት እንደ ነበረች፤ አርክጳ ደግሞ ልጃቸው እንደ ሆነ ይታሰባል (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)፡፡ አርክጳን በተመለከተ ሐዋርያው ‹‹ለአርክጳም፡- በጌታ የተቀበልከውን አገልግሎት እንድትፈጽመው ተጠንቀቅ በሉልኝ›› (ቆላ. 4፡17) ብሎ ስለ ጻፈ፤ አገልጋይ ወታደር እንደ ሆነ እንገነዘባለን (ፊል. 2፡25)፡፡

       በፊልሞና ቤተሰብ ውስጥ ሕያው እግዚአብሔር በመንፈስና በእውነት (ዮሐ. 4፡24) የሚመለክበት፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም (ማቴ. 18፡20) ማኅበር ነበር፡፡ በክርስትናው ጅማሬ ከመንፈስ ቅዱስ መውረድ ጀምሮ ቤተ፡ ክርስቲያን (የክርስቲያን ወገን) በግለሰቦች ቤት ውስጥ የነበረ መሰባሰብ እንደ ሆነ እናውቃለን (ሐዋ. 1፡13፤ 2፡1)፡፡ ሐዋርያው ‹‹በክርስቶስም ያሉት የይሁዳ ማኅበሮች . . ›› (ገላ. 1፡22) እንዳለ፤ በየስፍራው ያለው መሰባሰብ በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት (2 ቆሮ. 5፡17) የሆኑ ምእመናን አንድነት ነበር፡፡

       ሐዋርያው ጵርስቅላና አቂላን በተመለከተ ‹‹. . በቤታቸውም ላለች ቤተ፡ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ›› (ሮሜ 16፡5) ይላል፤ ንምፉንን በተመለከተም ‹‹. . በቤቱም ላለች ቤተ፡ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ›› (ቆላ. 4፡15) በማለት ይናገራል፡፡ ‹‹ . . በየጸሎቱም ይተጉ ነበር›› (ሐዋ. 2፡42) ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ያመልኩ ነበር፡፡

        ቤተ፡ ክርስቲያን፤ 1. የትንሣኤው ምስክሮች (ሐዋ. 1፡8፤ 2፡40፤ 17፡18) 2. ደቀ መዛሙርት (ሐዋ. 6፡1፤ 6፡7፤ 9፡1፤ 9፡26)፤ 3. ክርስቲያን (ሐዋ. 11፡26፤ 26፡27፤ 1 ጴጥ. 4፡16)፤ 4. ምእመናን (ሐዋ. 10፡45)፤ 5. ወንድሞች (ማቴ. 23፡8፤ ሐዋ. 11፡1፤ 28፡14) እና 6. ቅዱሳን (ሐዋ. 9፡13፤ ሮሜ 1፡7፤ 1 ቆሮ. 1፡1) በመባል በታወቁ የእግዚአብሔር ልጆች ኅብረትነቷ መጽሐፍ ቅዱሳችን ይገልጣታል፡፡ ቤተ፡ ክርስቲያን እንደ ሙሽሪት ክርስቶስ ሙሽራዋ (ኤፌ. 5፡30-32)፤ እንደ አካል ክርስቶስ ራስዋ (ቆላ. 1፡18)፤ እንደ ሕያው እግዚአብሔር ቤት ክርስቶስ ሊቀ ካህናቷ (1 ጢሞ. 3፡15) ነው፡፡

        የቀደመችይቱ ቤተ፡ ክርስቲያን እንዲህ ያለው መንፈሳዊ አኗኗር ለዛሬው ክርስትና በእጅጉ ትምህርት ሰጪ ነው፡፡ ምእመናን በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ካልሆነ በቀር በቤታቸው መንፈሳዊ ልምምድ የሌላቸው መሆኑ፤ ክርስትናውን ጉልበት ያሳጣና ለክርስቲያኖች ምስክርነት አፈና ሆኖ የኖረ የሰው መንገድ ነው፡፡ በአደባባይ አንቱ የተባሉ፤ በቤትና በቅርቦቻቸው ‹‹አንተን /ቺን ብሎ . . ›› የሚባሉ ወገኖች፤ በሰው ፊት ብቻ ሳይሆን በመለኮት ዘንድም እንዲህ የሆነባቸው ተወቃሾች፤ ውስን የሆነው የክርስትና ልምምዳቸው ያመጣባቸው ነው፡፡  

        በቤተሰብ መካከል አብሮ መጸለይ አለመለመዱ፤ መጽሐፍ ቅዱስን በቤት ውስጥ የማንበብና የማጥናት ልማድ አለመዳበሩ፤ እንዲህ ያለው ተግባር ከኦርቶዶክስ ቤተ እምነት ያሸሻል ተብሎ መታሰቡ ክርስትናውን ያደባባይና የፈረቃ ብቻ አድርጎታል፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ በቤታችሁና በቤተ ሰዎቻችሁ አልያም አብረዋችሁ በሚኖሩ መካከል ያላችሁን መንፈሳዊ ኑሮ መለስ ብላችሁ ለመመልከት ሞክሩ፡፡ እንደ ቃሉ ለመኖር ትተጋላችሁን? በቅርባችሁ ያሉትን የሚያሸንፍ መንፈሳዊ ትጋት አላችሁን?   

        ሐዋርያው ጳውሎስ አናሲሞስን በክርስቶስ ክርስቲያን እንደ ሆነ ወንድም አድርገው የፊልሞና ቤተ ሰዎችና በቤቱ ያለው ጉባኤም ጭምር እንዲቀበለው መልእክቱን እንዲህ ባለ አቀራረብ ይጀምራል፡፡ አቀራረቡን ያሰረበት ሰላምታ ‹‹ከእግዚአብሔር ከአባታችን፤ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ፤ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን››  የሚል ነው፤ ከአብ (ቲቶ 2፡11) በወልድ (ገላ. 1፡6) በኩል የተገለጠው ጸጋ ለሰው ልጆች ሰላምን ያመጣ ነው፡፡

        ሐዋርያው ‹‹ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው›› (1 ዮሐ. 1፡3) እንዳለ፤ በመንፈስ ትስስር (መንፈስ ቅዱስ) የሆነው የክርስትና ኅብረት እውነተኛ ሰላም ምንጩ ከሰማይ ነው፡፡ ሰላምታውም በመጀመሪያይቱ ቤተ፡ ክርስቲያን ‹‹እንዴት አደርክ? . . እንዴት ዋልክ?›› የመባባልን ያህል የተለመደ ነበር፡፡ ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እያጠናችሁ ያላችሁ እንዲህ ያለውን ሰላምታ በግላችሁ ብትለማመዱ እመክራችኋለሁ፡፡

‹‹ስለ ፍቅርህና ስለ እምነትህ . . ››

         Love and faith go together. As true faith includes works, so true faith includes love. We cannot believe in God without loving others. /The Orthodox Study Bible/.

          በጌታ በኢየሱስ ዘንድ እና በቅዱሳን (ክርስቲያኖች፤ ሐዋ. 9፡13፤ 1 ቆሮ. 1፡2) ሁሉ ዘንድ ፊልሞና ስላለው ‹‹ፍቅርና እምነት›› ሐዋርያው ጳውሎስ መስማቱንና እግዚአብሔርን ማመስገኑን ይነግረዋል፡፡ በእግዚአብሔር ፊት የሆነ መንፈሳዊ ልምምድ፤ በሰዎችም ፊት ሲሆን (ከውዳሴ ከንቱ የፀዳ)፤ ለእግዚአብሔር ብዙ ክብርና ምስጋናን ያመጣል፡፡ ሐዋርያው በፊልሞና ዘንድ ያለውን መልካም ነገር ይጠቅሳል፡፡ በሌሎች መልእክታቱ እንደሚያደርገው በዚህም መልእክት ከፊልሞና ሕይወት ለማመስገን ምክንያት የሚሆነውን ነገር ይጠቅሳል፡፡

          በሌሎች ዘንድ ያለውን መልካሙን ነገር በቸልታ አለመመልከት ለመልካም ግንኙነት ወሳኝ ነው፡፡ እንዲሁም በጎውን ለማስቀጠል እውነታውን መሰረት አድርጎ ለተግባራቸው እውቅና መስጠት ተገቢ ነው፡፡ በፊልሞና ሕይወት ያለው እምነትና ፍቅር ለሐዋርያው ጳውሎስ የሁልጊዜ የምስጋና ርዕስ ሆኖ አምላኩን ያመሰግን ነበር፡፡ ይህም በእስር (ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር) ላለው ሐዋርያ ብዙ ደስታና መጽናናትን ሰጥቶታል፡፡

         እምነትና ፍቅር በክርስትና ውስጥ እጅግ ቁልፍ የሆኑ የማንነጣጥላቸው ነገሮች ናቸው፡፡ እምነት እግዚአብሔርን የምንረዳበት (የምንቀበልበት) ሲሆን፤ ፍቅር ደግሞ ያመነውን አምላክ የምንገልጥበት የበለጠው መንገድ ነው፡፡ ስለ እምነት ‹‹እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው›› (ዕብ. 11፡1) ተብሎ ተጽፎአል፤ ደግሞ ይህ እምነት ከመስማት ነው፤ መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው (ሮሜ 10፡17)፡፡

         እምነታችን ተስፋ የተደረገለትን ነገር እርግጥ ሲያደርግልን፤ በተስፋ የምንጠባበቀውንም ነገር እውን ያደርግልናል፡፡ በተስፋ የዳንን (ሮሜ 8፡24)፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፤ እድፈትም ለሌለበት ለማያልፍም ርስት ሁለተኛ የተወለድን እኛ (1 ጴጥ. 1፡3-5)፤ የተባረከው ተስፋችንን (ቲቶ 2፡12) በእምነትና በትእግሥት ልንጠባበቅ ያስፈልገናል፡፡ እምነት ያላየነውን አምነን በጽናት መዝለቅን ይሰጠናል፡፡

‹‹ተፈሣሕኩ ወተሐሠይኩ በእንተ ተፋቅሮትከ››

         ስለ ፍቅር ‹‹እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፤ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ›› (ዮሐ. 13፡35) በማለት አንዱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሯል፡፡ ተግባራዊ እምነት መገለጫው ፍቅር ነው፡፡ ወደ እግዚአብሔር የደረስነው ከእግዚአብሔር ለእኛ በተገለጠው ፍቅር (ዮሐ. 3፡16፤ 1 ዮሐ. 4፡10) በኩል እንደ መሆኑ ለሌሎች፤ በተለይ እንደ እኛ ላመኑቱ የፍቅር እዳ (ሮሜ 13፡8) አለብን፡፡ እግዚአብሔር ልጆቹ ተብለን የምንጠራበትን ፍቅር (1 ዮሐ. 3፡1) እንደ ሰጠን፤ እኛ ሌሎችን እንደ ተወደዱ ወንድሞችና እህቶች የምንቀበልበት ፍቅር ሊኖረን ይገባል፡፡ በእግዚአብሔር ማመናችን ሌሎችን መውደድን ይጠቀልላል፡፡
                                     ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!
     

No comments:

Post a Comment