Tuesday, February 16, 2016

መልእክት ኀበ ፊልሞና፡፡(4)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


ማክሰኞ የካቲት 8 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

(መልእክት ወደ ፊልሞና)

‹‹እምጳውሎስ ሙቁሐ ለኢየሱስ ክርስቶስ፡ (ኤፌ. 3፡1)!››

‹‹ሐዋርያው ጳውሎስ በተገኘበት ቦታ ሁሉ በጥልቅ ትህትና የተመላለሰ፤ ባሮችን ነጻ የሚያወጣውን እና ከጌቶቻቸው ጋር የሚያስተካክላቸውን፤ እንዲሁም የእግዚአብሔር ልጆች የሚያደርገውን የወንጌል ኃይል የገለጠ ነው›› /ከቀደሙት፡ - ቲዎዶሬት/

‹‹የእምነት ኅብረት›› /ቁ. 6/

          ከሞት በኋላ የሚቀጥል አብሮነት ከእምነታችን ኅብረት የሚመጣ ነው (1 ዮሐ. 1፡3)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹እምነት ከመስማት ነው፤ መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው›› (ሮሜ 10፡17) እንዲል፤ እውነተኛ እምነት በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ላይ የቆመ ነው፡፡ ፊልሞናን በተመለከተ ‹‹የእምነትህም ኅብረት›› ተብሎአል፡፡

         በቀደመው ጥናታችን በፊልሞና ቤት ውስጥ ክርስቲያኖች በኅብረት ይሰባሰቡ እንደነበር አይተናል፡፡ ይህም ኅብረት ‹‹ሁለት ወይም ሦስት በስሜ›› (ማቴ. 18፡20) የሚለውን እውነት ማእከል ያደረገ ነው፡፡ ‹‹ለተወደደውና አብሮን ለሚሠራ›› በተባለለት በፊልሞና አገልግሎትም የክርስቲያኖቹ (ቅዱሳን) ልብ አርፎአል፡፡

          ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ስፍራ ፊልሞና የእምነቱ ኅብረት ‹‹ለክርስቶስ ኢየሱስ ፍሬ እንዲያፈራ›› ይለምነዋል፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ በክርስቶስ የሆነው የክርስትና ኅብረት በዋጋ ለገዛን (1 ቆሮ. 6፡20፤ 7፡23) ለክርስቶስ ፍሬ እያፈራ ነውን? ክርስትናው ከፀሐይ በታች ላለው ነገር ፍሬ የሚለቀምበት የደምና የሥጋ ማሳ ሆኖ ማየት እጅጉን አሳዛኝ ነው፡፡ ሐዋርያው እየለመነ ያለው ለምን እንደሆነ ልብ በሉ፤ ለክርስቶስ ኢየሱስ ፍሬ እንዲያፈራ ብቻ ነው፡፡

         የንግዳችሁ ኅብረት ለዚህ ዓለምና ለእናንተ ፍሬ የሚያስገኝ መስክ ይሆናል፤ ዳሩ ግን በክርስቶስ ላይ ባለን እምነት የሆነው ኅብረት ፍሬው ‹‹ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል›› (ኢሳ. 53፡10) ተብሎ ለተተነበየለት ጌታ ፍጻሜ ሊሆን ይገባል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ምንም ያገለገለ ቢሆን የፍሬውን አድራሻ በስሙ ስለ ማድረግ ግን አልከጀለም፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ደምና ስም የተመሠረተውን ክርስትና ጭምር በስማቸው ስላደረጉት ብዙዎች መንበርከክ ይገባናል፡፡

        በእውነት እምነት የሆነ ኅብረት ለኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ፍሬን ያስገኛል፡፡ ፊልሞና እንደ ክርስቶስ ባሪያ በማገልገል ይደክማል፤ ፍሬውንም ለጌታ በአድራሻው አሳልፎ ይሰጣል፡፡ እንዲህ ያለው ወንድም በፍቅር የተሞላ ነበር፡፡ ‹‹ወንድሜ ሆይ፤›› ላለውም ሐዋርያ ብዙ ደስታና መጽናናትን አስገኝቶአል፡፡ ከሐዋርያው ጳውሎስ ምስክርነት እንደምንረዳው ፊልሞና በጌታና ባመኑት ወንድሞች ፊት ግብዝነት የሌለበት ንጹሕ ፍቅር የነበረው አገልጋይ ነበር፡፡

‹‹ስለ ፍቅር እለምናለሁ›› /ቁ. 9/

        አግባብ የሆነውን ለማዘዝ በክርስቶስ ብዙ ድፍረት የነበረው፤ የኢየሱስ ክርስቶስ እስር የሆነው፤ ሽማግሌው ሐዋርያ ጳውሎስ ይህንን መብቱን በመተው ‹‹ስለ ፍቅር›› ይለምናል፡፡ ለአንድ ሰው መብቶቹን እንደ መተው ያለ ጭንቅ የለም፡፡ ይቅርታ ተጠያቂዎች ስንሆን ሳለ ይቅርታ መጠየቅ፤ ልንቀበል ተገብቶ ሳለ እንዲሁ መተው፤ የምናስተዳድር ሆነን ሳለ እንደ ባሪያ ዝቅ ማለት ብርቱ ፈተናዎች ናቸው፡፡

       ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ‹‹በእናንተስ እንዲህ አይደለም›› ብሎ በተናገረበት ክፍል ‹‹ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን›› (ማቴ. 20፡26) አላቸው፡፡ በክርስትና የትልቅነት ምንጩ የባሪያን ስፍራ መያዝ መሆኑ መቼም አይቀየርም (ፊል. 2፡7-11)፡፡ ስለ ፍቅር ዝቅ ብሎ መለመንን፤ እንዲሁም መለመንን (ይጠብቃል) ባለመማራችን ምክንያት በጅምር የቀሩ፤ ደርጅተው የፈረሱ የሚያስቀኑ ግንኙነቶችን ልንፈትሽ አግባብ ነው፡፡

       በሐዋርያነት ሥልጣን የሚያገለግለው ጳውሎስ ‹‹እለምናችኋለሁ›› የሚለውን ቃል ብዙ ጊዜ ይጠቀማል (ሮሜ 16፡17፤ 1 ቆሮ. 1፡10፤ 2 ቆሮ. 2፡8፤ ገላ. 4፡12፤ ኤፌ. 4፡1፤ ዕብ. 13፡19)፡፡ ፊልሞናንም በእስራቱ በወንጌል ስለ ወለደው ስለ ልጁ ስለ አናሲሞስ በፍቅር ይለምነዋል፡፡ እንዲህ ያለው አቀራረብ ለዛሬው ክርስትና የማንቂያ ደወል ነው፡፡ የአንድ ጥሩ ሰብእና ባለቤት የሆነን ሰው የአቀራረብ ደረጃ እንኳ የማይተካከል የምን ቸገረኝ ክርስቲያናዊ ግንኙነት በተበራከተበት ዘመናችን፤ በዚህ መጽሐፍ የመጣው ይህ ቃል የምንገሠጽበትም ጭምር ነው፡፡

       ‹‹አስቀድሞ ስላልጠቀመህ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም ስለሚጠቅም›› የሚለው አገላለጽ ‹‹በእውነትህ ቀድሳቸው ቃልህ እውነት ነው›› (ዮሐ. 17፡17) የሚለውን ያስታውሰናል፡፡ አናሲሞስ ምንም እንኳ ጠቃሚ በሚል የስም ትርጉም እየተጠራ የኖረ ቢሆንም ዳሩ ግን ከእግዚአብሔር ያልተወለደ ባሪያ (በሥጋ ባርነቱ እንዳለ ሆኖ) ነበር፡፡ በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት ዋጋችንን የሚያስወድደው ስለ እኛ የሞተልን ክርስቶስ ነው፡፡ አናሲሞስ እንደ ስሙ ጠቃሚ የሆነው ለሰማው የእውነት ቃል በእምነት ትክክለኛ ምላሽ በመስጠቱ ነው፡፡

       የእግዚአብሔር ልጆቹ ተብላችሁ የተጠራችሁ ሆይ፤ በክርስቶስ ያላችሁን ሰማያዊና መንፈሳዊ ስፍራ ልብ እንድትሉ እመክራችኋለሁ (ኤፌ. 1፡3)፡፡ ቃሉ ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም›› (ገላ. 4፡7) ይላልና፡፡ ለፍጥረቱ የበኩራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ የወለደን (ያዕ. 1፡18) የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ክብር ይግባውና በዚህ እውነት አስረጅነት እኛ ሁላችን ‹‹ጠቃሚ›› ነን፡፡

         ራሳችሁን እንደ ማይጠቅም፤ ዋጋ እንደ ሌለው ሰው አድርጋችሁ የምታስቡ አተያያችሁን እንድታስተካክሉ መንፈስ ቅዱስ ይጠይቃችኋል፡፡ የእናንተን ውበት የምትጠይቁበትን መስታወት ለውጡ፡፡ ነቢዩ ‹‹ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች›› (መዝ. 138፡14) እንዳለ፤ ደግሞ ‹‹ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው›› (2 ቆሮ. 5፡17) እንደተባለ፤ ራሳችሁን ሕያው የሚሠራ በሆነው የእግዚአብሔር ቃል ተመልከቱ፡፡


         ሐዋርያው ጳውሎስ አናሲሞስን እንደ ተወደደ ወንድም እንዲቀበለው ፊልሞናን ይጠይቀዋል፡፡ ‹‹ልቤ እንደሚሆን›› የሚለው አገላለጽ አናሲሞስ በጳውሎስ ዘንድ ያለውን ስፍራና ምስክርነት ያስረዳናል፡፡ አሁን ጠቃሚ እንደ ሆነ የተመሰከረለት የቀድሞው ባሪያ ተግባራዊ የሕይወት ለውጥ በዚህ መልእክት ውስጥ ግልጽ ነው፡፡ ወደ አሳዳሪው ለመመለስ፤ ይቅርታ ለመጠየቅና ለማገልገል በነበረው ፈቃደኝነት ውስጥ ለእውነት መሸነፉን እንመለከታለን፡፡ ‹‹እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል›› (ዮሐ. 8፡31)!       
                                                ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!  

No comments:

Post a Comment