Tuesday, March 1, 2016

መልእክት ኀበ ፊልሞና፡፡(5)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


ማክሰኞ የካቲት 22 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

(መልእክት ወደ ፊልሞና)

‹‹እምጳውሎስ ሙቁሐ ለኢየሱስ ክርስቶስ፡ (ኤፌ. 3፡1)!››

v ‹‹ሳልማከርህ ምንም እንኳ ላደርግ አልወደድሁም ›› /ቁ. 14/

          ባለፈው ጥናት ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹ሐዋርያዊ ሥልጣኑን›› መሰረት ባደረገ መንገድ ሳይሆን፤ 
1. እድሜውን (እኔ ሽማግሌው)፤ 
2. የኢየሱስ ክርስቶስ እስር መሆኑን፤ 
3. የፊልሞና ሕሊና በጎነት፤        
4. በመካከላቸው ያለውን የእምነትና ፍቅር አንድነት ማእከል በማድረግ 
          የሁሉም ነገር ማሠሪያ በሆነው ‹‹ስለ ፍቅር›› ለምኖታል፡፡ (ዮሐንስ አፈወርቅ)         

        አናሲሞስን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ እርሱ ጋር በመሆን እንዲያገለግለው ሊያስቀረው ፈቅዶ ነበር፡፡ ዳሩ ግን አሳዳሪው ከነበረው አሁን ደግሞ በክርስቶስ ወንድሙ ከሆነው ከፊልሞና ጋር መመካከርን እንደ ወደደ ይገልጻል፡፡ በዚህ መልእክት ውስጥ ከምናየው የክርስቶስን ፍቅር ማዕከል ያደረገ እውነተኛ ግንኙነት አንጻር፤ በኋላ ፊልሞና አናሲሞስን ያገለግለው ዘንድ ወደ ሐዋርያው ጳውሎስ መልሶ ሊልከው እንደሚችል ልናስብ እንችላለን፡፡ ዳሩ ግን ሐዋርያው ምንም ሥልጣን ያለው ቢሆንም እንኳ የፊልሞና በጎነት በፈቃዱ እንጂ በማስገደድ እንዳይሆን ተጠንቅቋል፡፡

        ተወዳጆች ሆይ፤ እውነተኛ በጎነት ፈቃደኝነትን የተከተለ መሆን አለበት፡፡ ሰዎች በተለያየ አስገዳጅ ምክንያት መልካምነታቸውን ሊገልጹልን፤ በስሌትም ሊወዱን ይችላሉ፡፡ ከፍቅር የሚመነጨውን በጎነት ግን ምንም ደግናችሁ አታገኙትም፡፡ ፍቅር የሚገራውን ልብ ኃይል አይገራውም፡፡ ሐዋርያው ፊልሞናን (አሳዳሪው) እና አናሲሞስን (ባሪያው) ለማገናኘት ያሳየው አቀራረብ ይህንን በሚመስል መደብ ለሚፈጠሩ ልዩነቶች ሁሉ ቋሚ ትምህርት ነው፡፡

       መመካከር በክርስትና ሕይወት ትልቅ ስፍራ አለው (1 ተሰ. 5፡11)፡፡ ሐዋርያው በክርስቶስ ብዙ ድፍረት እያለው ከፊልሞና ጋር መመካከርን መርጧል፡፡ ይህም ጎዳና የሂደቱን ውጤት በእጅጉ ይወስናል፡፡ ሐዋርያው ፊልሞናን ‹‹አብሮን ለሚሠራ›› ካለ ‹‹ሳልማከርህ›› ማለቱ ትክክል ነው፡፡ ምክክር አብሮ የመሥራት ብዙ አካል ነው፡፡ በተለይ ለአገልጋዮች  ጠቃሚ  አቅጣጫን እናይበታለን፡፡ ያለ ምክክር ሥራ የሚፋረስ እንጂ ጠላትን (ዲያብሎስ) የሚያፈርስ ሊሆን አይችልም፡፡

v ‹‹ተቀብለህ ለዘላለም እንድትይዘው››  
                          
        በምንኖርበት የአሁኑ ዓለም ቋሚ ነገር ብርቅ ነው፡፡ አዎን የሆነው በምናስነጥስበት ፍጥነት አይደለም ይሆናል፡፡ አይደለም ደግሞ እንዲሁ፡፡ ወዳጅነት አልዘልቅ፤ የጨበጥነው አልበረክት፤ ያሞገስነው አልጸና ይለናል፡፡ የማይሰብረኝ ካልነው ውስጥ እንክትክት የሚያደርግ ይወጣል፡፡ የፍቅርን ጥማት የሚቆርጥ ኢየሱስ ብቻ ነው (ጥሜን ቆረጠልኝ እንዲሉ)፡፡

        ‹‹ሰው በታናሽነቱ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው›› (ሰቆ. ኤር. 3፡27) ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ እግዚአብሔር በቀላልም በከባድም ሁኔታ ውስጥ ብዙ አስተምሮኛል፡፡ እኔና አብ አንድ ነን (ዮሐ. 10፡30) ካለው ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ በቀር ምድሪቱ ላይ የዓይንም የልብም ማረፊያ የሚሆን እንደሌለ ይህን አንድ ነገር ተረድቻለሁ፡፡

         በሰው መካከል ላለ ሰው ‹‹ስለዚህ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እንደ ተቀበላችሁ እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ›› (ሮሜ 15፡7) የሚለው ቃል ፈታኝ እንደ ሆነ ሥጋና ደም ሊያስብ ይችላል፡፡ በእርግጥ ስለ መንፈስ ማሰብ ካልሆነ በቀር ሕይወትና ሰላም ሊሆን እንዳይችል ቃሉ ያስረዳናል (ሮሜ 8፡6)፡፡ ተዋዳጆች ሆይ፤ ሐዋርያው ፊልሞናን እየጠየቀው ያለው ‹‹ለዘላለም መቀበልን›› ነው፡፡

         የኮበለለ ሎሌን (ባሪያ) ቀርቶ ባል ሚስቱን ለዘላለም እንዳገባት በፊርማ ሥነ ስርዓቱ እድምተኛ ፊት ቢታወጅ ፍቅሬ አውጭኝ (እግሬ አውጪኝ እንዲሉ) እንደሚል አይጠረጠርም (ያውም የዘመናችን አብዛኛው ትዳር)፡፡ ጊዜያው መቀባበል፤ የኮትራት አብሮነት እያጋጋጠ ባለበት እድሜያችን እንዲህ ያለው መቀባበል ጊዜው እንዳለፈ ሊቆጠር ይችላል፡፡  የቃሉን እውነት መሆነ ለሚቀበል ልብ ሁሉ ግን ይህም እንታዘዘው ዘንድ የተገባ ነው፡፡

        እናት የወለደችውን በምትክድበት ምድር እግዚአብሔር የወለደውን በክርስቶስም ልጄ ያለውን እንደ ወንድም እንድንቀበለው ተነግሮናል፡፡ ዘላለማዊ መዛመድ በክርስቶስ ወንድማማቾች የሆንበት ነው፡፡ በሥጋ የሆኑ መዛመዶች ሞት ይፈታቸዋል፤ ‹‹የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ነው›› (ዮሐ. 11፡25) ባለን በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነው አንድነት ግን ሁል ጊዜ ከጌታ ጋር በመሆን ለዘላለም ይዘልቃል፡፡

         አናሲሞስ ለጊዜው የተለየውን ለዘላለም ሊገናኘው ወደ ፊልሞና ተመለሰ፡፡ በዘላለም ያወቅናቸው በጊዜው ሊጎዱን አሳብ ሲቁነጠነጥባቸው ማየት ምንኛ አሳዛኝ ነው? ‹‹በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን›› (ፊል. 2፡5)፡፡ አናሲሞስ ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባሪያ አይሆንም››፤ ከፊልሞና በኮበለለበት ማንነት ወደ እርሱ አልተመለሰምና፡፡ ፊልሞና አናሲሞስን ተቀብሎ ለዘላለም እንዲይዘው የፍቅር ግዴታ አለበት፡፡

v ‹‹ከባሪያ የሚሻል የተወደደ ወንድም››

        መሻላችን ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ትስስር የሚለካ ነው፡፡ ሰዎች በሀብት፤ በእውቀት፤ በዝና፤ በሥልጣን ለመበላለጥ ተግተው ሲሮጡ እናያለን፤ እኔ ግን እላችኋለሁ በክርስቶስ አትበለጡ፡፡ በእርሱ መሆን አይቅርባችሁ! ‹‹ሁሉን የሚችል አምላክ ወርቅና የሚብለጨለጭ ብር ይሆንልሃል›› (ኢዮ. 22፡25) ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ ሕያው እግዚአብሔር በክርስቶስ ሁሉን የሚያስንቅ ብልጥግናችን ነው!

         ከባሪያ የሚሻል ሕይወት በክርስቶስ ካልሆነ በቀር በሌላ እንዳይገኝ የተወደደው ወንድም አናሲሞስ ምስክር ነው፡፡ ‹‹በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን›› (ገላ. 5፡1) እንደ ተባለ፤ እውነተኛው ነጻነት በነጻ አውጪው በክርስቶስ በኩል የሚሆን ነው፡፡ አናሲሞስ ወደ አሳዳሪው ሲመለስ በሥጋውም ጭምር ሊያገለግል ነው፤ ዳሩ ግን እርሱ በሥጋ ሊሆን አይችልም፤ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቅሎታልና (ገላ. 5፡24)፡፡

       አናሲሞስ ለሐዋርያው ጳውሎስ በተለየ የተወደደ ወንድም ነው፡፡ እርሱ የክርስቶስ ሎሌና የእግዚአብሔር ምስጢር መጋቢ (1 ቆሮ. 4፡1) በሆነው ጳውሎስ ልብ ውስጥ ካለው ስፍራ በበለጠ ለፊልሞና ከባሪያ የሚሻል የተወደደ ወንድም መሆኑ አሳማኝ ነው፡፡ አናሲሞስ በፊልሞና ዘንድ በሥጋው እንደ ባሪያ (አገልጋይ) ሲሆንለት፤ በጌታ ዘንድ ደግሞ የተወደደ ወንድሙ ነው፡፡ ሐዋርያው ‹‹ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ›› (2 ቆሮ. 12፡2) እንዳለ፤ ቅዱስ መተዋወቅ፤ ለዘላለም የሆነም መያያዝ ከዚህ ውጪ ሊሆን እንዴት ይቻላል? እናስተውል!  

                                               ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!


No comments:

Post a Comment