Saturday, March 26, 2016

ምኩራብ፡ የተፈታ ቤት


ቅዳሜ መጋቢት 17 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

‹‹እነሆ፤ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል፡፡›› /ማቴ. 23፡38/!

Saturday, March 19, 2016

ቅድስት፡ ከዳተኛይቱ ጸደቀች



ቅዳሜ መጋቢት 10 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

‹‹እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፡- ከአታላይቱ ከይሁዳ ይልቅ ከዳተኛይቱ እስራኤል ጸደቀች›› /ኤር. 3፡11/፡፡

               ማታለል መክዳት፤ መከዳት መታለል ከአሁኑ ዓለም መልክ መካከል ናቸው፡፡

Monday, March 14, 2016

መልእክት ኀበ ፊልሞና፡፡(6)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


 ሰኞ መጋቢት 5 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት


(መልእክት ወደ ፊልሞና)

‹‹እምጳውሎስ ሙቁሐ ለኢየሱስ ክርስቶስ፡ (ኤፌ. 3፡1)!››

‹‹ወእመሰ እኁየ አንተ ተወከፎ ከማየ፤ ለእኔስ ወንድሜ ከኾንህ እኔ እንደ ተቀበልሁት ተቀበለው፡፡ አንድም ለእኔ ወንድሜ ከኾነ እኔን እንደ ተቀበልህ ተቀበለው››፡፡

‹‹ . . እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው ›› /ቁ. 17/

        ሐዋርያው ጳውሎስ አናሲሞስን ‹‹እንደ እኔ›› ተቀበለው በማለት ይጠይቀዋል፡፡ ፊልሞና ጳውሎስን ተቀብሎ ለዘላለም እንደያዘው እናውቃለን፡፡ አሁንም በወንጌል እውነት በማመን ወደ ክርስትና የተቀላቀለውን አናሲሞስን ፊልሞና ጳውሎስን በተቀበለበት በዚያው መቀበል ሊቀበለው የተገባ ነው፡፡ ‹‹እንደ ባልንጀራ ብትቆጥረኝ›› ሲል በሁለቱ መካከል ያለውን የቀረበ ወዳጅነት ማስተዋል እንችላለን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹ባልንጀራህን እንደ ራስህ›› (ማቴ. 19፡19) የሚለውን ቅዱስ ትእዛዝ እንዴት ተግባራዊ እንዳደረገ በዚህ አጻጻፉ ልብ እንላለን፡፡

        አስቀድመን ባየናቸው ቁጥሮች ውስጥ ‹‹ስለ ልጄ›› ‹‹ልቤ እንደሚሆን›› በማለት ፊልሞና አናሲሞስን ይቀበለው ዘንድ ለምኖአል፡፡ እውነተኛ ልጅ ደግሞ አባቱን መምሰሉ እውነታ ነው፤ እንደ እኔ ተቀበለው ማለቱም የአናሲሞስን እውነተኛ መለወጥ፤ የጳውሎስንም እውነተኛ መውደድ እናይበታለን፡፡ እንዲህና እንደዚያ ነው ልንል በማንችልበት ሁኔታ በጳውሎስና በፊልሞና መካከል ልዩ የሆነ መቀራረብና ጥብቅ ወዳጅነት እንደ ነበር ከመልእክቱ መረዳት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ክርስትና መልክ ክርስቶስን ማሳየቱ ዛሬ ላለነው ወቀሳም ጭምር ነው፡፡

Saturday, March 12, 2016

ዘወረደ፡ ‹‹የአቤሴሎም ውበት››


ቅዳሜ መጋቢት 3 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት
‹‹በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ እንደ አቤሴሎም በውበቱ የተመሰገነ ሰው አልነበረም ከእግሩ እስከ ራሱ ድረስ ነውር አልነበረበትም።›› (2 ሳሙ. 14፡25)፤ ‹‹ . . አቤሴሎምም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ።›› (2 ሳሙ. 15፡6)!

           ውበት የሰውን ልብ የመግዛት ከፍተኛ አቅም አለው፡፡ ውበት በተለያየ መንገድ እንደ መስፈርት ጥቅም ላይ ሲውልም እናያለን፡፡ ሰዎች ለውበታቸው ስፍራ እንደሚሰጡ፤ ብዙ ወጪ እንደሚመድቡ ልናስተውልም እንችላለን፡፡ ውበት ልብን ይሰርቃል፤ ውበት አቋም ያስለውጣል፤ ውበት ለሰዎች ዓይን ርሀብ ጥጋብ ይሆናል፤ ውበት ምኞት በረሃ ላደረገው አእምሮ እንደ ጥሩ ምንጭ ነው፡፡ ይስሐቅ በርብቃ ውበት ከእናቱ ሞት ተጽናንቷል (ዘፍ. 24፡27)፤ ያዕቆብ ስለ ራሔል ውበት ለአጎቱ ለላባ አሥራ አራት ዓመት ተገዝቶአል (ዘፍ. 29፡17)፤ ንጉሥ አርጤክስስ በአመፀኛይቱ አስጢን ፈንታ ለአስቴር ውበት እጅ ሰጥቶአል (መጽሐፈ አስቴር 2፡17)፡፡

          ውበት ሰዎችን ከእውነት ፈቀቅ፤ ከሕሊና ዝቅ ያደርጋል፡፡ ንጉሡ ዳዊት በቤርሳቤህ ውበት ሚዛን ስቶ ነፍስ እስከ ማስጠፋት ደርሶአል (2 ሳሙ. 11፡2-4፤ 14-17)፤ ውስጡ በኢየሩሳሌም ቆነጃጅት ፍቅር የተለበጠው ንጉሡ ሰሎሞን የአህዛብን ጣዖታት ወደ ማምለክ የነዳው የአህዛብ ሴቶች ውበት ፍቅር ነው (1 ነገ. 11፡1)፤ ሳሙኤልን በዓይኑ ፊት ‹‹እግዚአብሔር እንደሚያይ እንዳያይ›› ያደረገው የኤልያብ ውበት ነው (1 ሳሙ. 16፡6)፡፡

Tuesday, March 1, 2016

መልእክት ኀበ ፊልሞና፡፡(5)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


ማክሰኞ የካቲት 22 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

(መልእክት ወደ ፊልሞና)

‹‹እምጳውሎስ ሙቁሐ ለኢየሱስ ክርስቶስ፡ (ኤፌ. 3፡1)!››

v ‹‹ሳልማከርህ ምንም እንኳ ላደርግ አልወደድሁም ›› /ቁ. 14/

          ባለፈው ጥናት ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹ሐዋርያዊ ሥልጣኑን›› መሰረት ባደረገ መንገድ ሳይሆን፤ 
1. እድሜውን (እኔ ሽማግሌው)፤ 
2. የኢየሱስ ክርስቶስ እስር መሆኑን፤ 
3. የፊልሞና ሕሊና በጎነት፤        
4. በመካከላቸው ያለውን የእምነትና ፍቅር አንድነት ማእከል በማድረግ 
          የሁሉም ነገር ማሠሪያ በሆነው ‹‹ስለ ፍቅር›› ለምኖታል፡፡ (ዮሐንስ አፈወርቅ)         

        አናሲሞስን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ እርሱ ጋር በመሆን እንዲያገለግለው ሊያስቀረው ፈቅዶ ነበር፡፡ ዳሩ ግን አሳዳሪው ከነበረው አሁን ደግሞ በክርስቶስ ወንድሙ ከሆነው ከፊልሞና ጋር መመካከርን እንደ ወደደ ይገልጻል፡፡ በዚህ መልእክት ውስጥ ከምናየው የክርስቶስን ፍቅር ማዕከል ያደረገ እውነተኛ ግንኙነት አንጻር፤ በኋላ ፊልሞና አናሲሞስን ያገለግለው ዘንድ ወደ ሐዋርያው ጳውሎስ መልሶ ሊልከው እንደሚችል ልናስብ እንችላለን፡፡ ዳሩ ግን ሐዋርያው ምንም ሥልጣን ያለው ቢሆንም እንኳ የፊልሞና በጎነት በፈቃዱ እንጂ በማስገደድ እንዳይሆን ተጠንቅቋል፡፡