Saturday, March 12, 2016

ዘወረደ፡ ‹‹የአቤሴሎም ውበት››


ቅዳሜ መጋቢት 3 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት
‹‹በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ እንደ አቤሴሎም በውበቱ የተመሰገነ ሰው አልነበረም ከእግሩ እስከ ራሱ ድረስ ነውር አልነበረበትም።›› (2 ሳሙ. 14፡25)፤ ‹‹ . . አቤሴሎምም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ።›› (2 ሳሙ. 15፡6)!

           ውበት የሰውን ልብ የመግዛት ከፍተኛ አቅም አለው፡፡ ውበት በተለያየ መንገድ እንደ መስፈርት ጥቅም ላይ ሲውልም እናያለን፡፡ ሰዎች ለውበታቸው ስፍራ እንደሚሰጡ፤ ብዙ ወጪ እንደሚመድቡ ልናስተውልም እንችላለን፡፡ ውበት ልብን ይሰርቃል፤ ውበት አቋም ያስለውጣል፤ ውበት ለሰዎች ዓይን ርሀብ ጥጋብ ይሆናል፤ ውበት ምኞት በረሃ ላደረገው አእምሮ እንደ ጥሩ ምንጭ ነው፡፡ ይስሐቅ በርብቃ ውበት ከእናቱ ሞት ተጽናንቷል (ዘፍ. 24፡27)፤ ያዕቆብ ስለ ራሔል ውበት ለአጎቱ ለላባ አሥራ አራት ዓመት ተገዝቶአል (ዘፍ. 29፡17)፤ ንጉሥ አርጤክስስ በአመፀኛይቱ አስጢን ፈንታ ለአስቴር ውበት እጅ ሰጥቶአል (መጽሐፈ አስቴር 2፡17)፡፡

          ውበት ሰዎችን ከእውነት ፈቀቅ፤ ከሕሊና ዝቅ ያደርጋል፡፡ ንጉሡ ዳዊት በቤርሳቤህ ውበት ሚዛን ስቶ ነፍስ እስከ ማስጠፋት ደርሶአል (2 ሳሙ. 11፡2-4፤ 14-17)፤ ውስጡ በኢየሩሳሌም ቆነጃጅት ፍቅር የተለበጠው ንጉሡ ሰሎሞን የአህዛብን ጣዖታት ወደ ማምለክ የነዳው የአህዛብ ሴቶች ውበት ፍቅር ነው (1 ነገ. 11፡1)፤ ሳሙኤልን በዓይኑ ፊት ‹‹እግዚአብሔር እንደሚያይ እንዳያይ›› ያደረገው የኤልያብ ውበት ነው (1 ሳሙ. 16፡6)፡፡

          ሶምሶንን ለጥፋቱ የልቡን ሁሉ እንዲገልጥ ያስገደደው የደሊላ ውበት ፍቅር ነው (መሳ. 16፡18)፤ ሕዝቅኤልን የዓይን አምሮት የሆነበት፤ ለተቀሰፈችው ሚስቱ በደረቁ ሀዘን ያስቀመጠው የገዛ አጋሩ ውበት ነው (ሕዝ. 24፡16)፤ አምኖንን ያስተከዘና ለሕመም የዳረገው፤ ሲያልፍም ያረከሰው የእህቱ ትዕማር ውበት ፍቅር ነው (2 ሳሙ. 13፡2)፤ የጲጥፋራ ሚስት በዮሴፍ ውበት ክፉ አስባለች (ዘፍ. 39፡6-10)፤ ውበትን የታከከ ፍቅር ለውድቀት የሆነባቸው ታሪኮች ብዙ ናቸው፡፡ ምድራችን ላይ ውበት ለእግዚአብሔር ክብር ከዋለበት ይልቅ ለአመጽ መሣሪያነት በእጅጉ አገልግሏል፡፡

         ያለፉ ድርጊቶችን ከታሪክ መለስ ብለን ስናገላብጥ በውበታቸው ክፉ ምክርን ያስፈጸሙ፤ መንግሥት ያናወጠ ሴራ ጫፍ ያደረሱ፤ አቅል አስተው ለስሜት የተነጠፈውን ለሞት ሽኝት ያደረጉ ሰዎችን እንደርስባቸዋለን፡፡ ቆነጃጅት እንደ ፍልጥ ሰዎች ለለኮሱት ግጭት ተማግደዋል፤ የባለ ጠጎች ማጫወቻም መጫወቻም ሆነዋል፡፡ ቆንጆ የተፈጥሮ አበባ ገበያ ላይ እንደሚውል፤ ሕሊናቸውን በሸጡና ለዚህም በሚተባበሩ ቆነጃጅት አየር ባየር የሰው ንግዶች ዓለም ላይ ደርተዋል፡፡ ስለ ውበት ብዙ ልንል እንደምንችል እንዳለ ሆኖ ወደ ተነሣንበት ርዕስ እንመለስ፡፡ 

           አቤሴሎም የስሙ ትርጉም ‹‹አባቴ ሰላም ነው›› የሚል ሲሆን፤ ለነቢዩ ዳዊት እጅግ የሚወደው ልጁም ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሌላ ስፍራ ደግመን በማናነበው መልኩ የአቤሴሎምን ውበት ‹‹ከእግሩ እስከ ራሱ ድረስ ነውር ያልነበረበት›› በማለት ይገልጸዋል፡፡ ስለ ጸጉሩ ውበት እንኳ ‹‹ጠጉሩም ይከብደው ነበርና በዓመት አንድ ጊዜ ይቆረጠው ነበር፤ ሲቆረጥም የራሱ ጠጉር በንጉሥ ሚዛን ሁለት መቶ ሰቅል ያህል ይመዘን ነበር›› (2 ሳሙ. 14፡26) ይለናል (አንድ ሰቅል አስራ ሁለት ግራም ያህል ይመዝናል)፡፡ በዚህ ሁሉ አገላለጽ አቤሴሎም ምን ያህል ውብ እንደ ነበር ልንረዳ ይቻለናል፡፡

         አቤሴሎም የንጉሥ ልጅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ውበቱ፤ የአባቱን መንግሥት ለመገልበጥና ዙፋን ላይ ለመቀመጥ የእስራኤልን ልብ ለመስረቅ ጠቅሞታል (2 ሳሙ. 15፡6)፡፡ በዚህም ሴራ ለአቤሴሎም ቁስ ሳይሆን ልቡን የሰጠው የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሁለት መቶ ነበር፤ እነርሱም የሚሆነውን ነገር ከቶ ሳያውቁ በየዋህነት የተዋበውን አቤሴሎም ተከተሉት (2 ሳሙ. 15፡11)፡፡ አቤሴሎም ሕቡዕ በሆነ ሴራው ከአባቱ ከንጉሥ ዳዊት የሚሸሸውን እና ወደ እርሱ የሚተባበረውን ሕዝብ እያበዛ ሄደ፡፡ አባቱ በዙፋን እያለም በኬብሮን ቀንደ መለከት አስነፍቶ ንጉሥ መሆኑን አወጀ፡፡

        የአቤሴሎም ክፋት አዛኝ ነው፡፡ አካሄዱም ማስተዋል ለሌለው ሰው በቀላሉ ግልጥ አልነበረም፡፡ አቤሴሎም ለእህቱ ለትዕማር የሚቆሮቆር፤ እግዚአብሔር የሾመው ዳዊትን ግን የሚያሳድድ ነበር፡፡ ከአመጸኛነቱ የተነሣ ሰው መጥራ ሲፈልግ እንኳ ‹‹እርሻውን አቃጥሉት›› የሚል ነበር፡፡ አቤሴሎም ወንድሙ አምኖንን ለማስገደል ሁለት ዓመት ከራሱ ልብ ጋር ሴራውን የመከረ፤ ይህንንም ለመፈጸም እንደ ንጉሥ ያለ ግብዣ ያዘጋጀ፤ ለሟች ወንድሙ የሚሰክርበትን ያስጠመቀ ነው፡፡ አባቱን የዙፋን ስደተኛ አድርጎ መካሮቹ በሰገነት ላይ በደኮኑለት ድንኳን ውስጥ ያባቱን ቁባቶች ያስነወረም ነበር፡፡

        የዳዊት መንግሥት ባለበት የእስራኤል ግዛት ውስጥ በወንድሙ ላይ የሞት ፍርድን ያስተላለፈ፤ ወንድሙን ለሞቱ በስካር ያጠገበ ነው (2 ሳሙ. 13፡28)፤ አባቱን ዳዊትን ደግሞ ተከናንቦ ያለ ጫማ እያለቀሰ ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት ያሳደደ ነው (2 ሳሙ. 15፡30)፡፡ አቤሴሎም የአባቱን ዙፋን ፍርድ በሕዝቡ ዘንድ ያክፋፋ፤ እጁን ዘርግቶ ያስም የነበረ ‹‹በአገር ላይ ፈራጅ አድርጎ ማን በሾመኝ?›› የሚል ምኞት ያሰከረው ምስኪን ነበር፡፡ አቤሴሎም የዳዊት መካር የሆነውን አኪጦፌልን በማሳመን በንጉሡ በአባቱ በዳዊት ላይ ሴራው ጽኑ ሆነለት (2 ሳሙ. 15፡12)፤ ዳዊትም ከልጁ ከአቤሴሎም ሸሸ (15፡14)፡፡

        ተወዳጆች ሆይ፤ በዳዊት ሕይወት የምንመለከታቸው ውድቀቶች እራሳቸውን የቻሉ የምልከታ ምእራፎች መሆናቸው እንዳለ ሆኖ እያየነው ያለነው የአባትነትን ሥፍራ ያላከበረውን የአቤሴሎምን ሕይወት ነው፡፡ ነቢዩ ሳሙኤልን ልኮ ዳዊትን የቀባው እግዚአብሔር ነው (1 ሳሙ. 16፡12-13)፤ የሳሙኤልን ዓይኖች በተመለከተ እግዚአብሔር ሲናገር ‹‹ሰው ፊትን ያያል እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል›› አለው (1 ሳሙ. 16፡7)፡፡ አቤሴሎም ከራሱ እስከ እግሩ ነውር እንደ ሌለበት ተነግሮናል፤ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ልብና ኩላሊትን ይመረምራል (መዝ. 7፡9)፡፡ አቤሴሎም የእስራኤልን ልብ መስረቅ የቻለ ቢሆንም የእግዚአብሔርን ልብ ግን አላገኘውም፡፡

       እግዚአብሔር ለእርሱ የተዋበ የሆነውን ‹‹እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ›› አለ (ሐዋ. 13፡22)፡፡ ምን ጊዜም እግዚአብሔር ልቡ ያለው እንደ ልቡ ምክር በሆነው ነገር ነው፤ ፈቃዱም የሚከናወነው እንደ ዘላለም አሳቡ ነው፡፡ የሰው ሩጫ የማይቀድመው፤ የሰው ጥበብ የማይጠበበው እግዚአብሔር ታላቅ ነው፡፡ የአቤሴሎም ውበት እግዚአብሔር የቀባውን ለመሸፈን፤ ሲያልፍም ስፍራውን ለመያዝ የቀናው ቢመስልም የነገሮች መጨረሻ ግን ‹‹እግዚአብሔር አትራፊ ነው›› ይላል፡፡ ለአቤሴሎም ደግሞ እጅግ ኪሳራ!

       በነቢዩ በዳዊት መዝሙር ‹‹ውበትህ ከሰው ልጆች ይልቅ ያምራል ሞገስ በከንፈሮችህ ፈሰሰ ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘላለም ባረከህ።›› (መዝ. 44፡2) የተባለለትን ውብ እናያለል፡፡ መዝሙሩ የቆሬ ልጆች ትምህርት ነውና ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም የጻፈው ቅኔ እንደ ሆነ ልናስብ አንችልም፡፡ ይልቁንም ከትምህርቱ ትንቢታዊ ይዘት የምንረዳው በቀጥታ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት እንድናመራ የሚጋብዘን መሆኑን ነው፡፡

       ‹‹የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል? በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል፤ መልክና ውበት የለውም፤ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም፡፡ የተናቀ ከሰውም የተጠላ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፤ እኛም አላከበርነውም›› (ኢሳ. 53፡1-3)፤ በዚህ የትንቢት ክፍል ከአቤሴሎም የሚበልጠውን፤ ውበቱ ከሰው ልጆች ሁሉ ይልቅ የሚያምረውን እናስተውላለን፤ ክርስቶስ ኢየሱስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ!

      ተወዳጆች ሆይ፤ ‹‹ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው›› (ዕብ. 4፡15) የተባለለት ክርስቶስ ነው፡፡ አቤሴሎም ውጫዊ መልኩ የሚማርክ እንደ ሆነ ብናውቅም፤ እንወደው ዘንድ ደም ግባት የለውም የተባለለት ጌታ፤ አብ ደስ የተሰኘበት ውበት ነው (ማቴ. 3፡17)፡፡ በአቤሴሎም ራስ ላይ በአመት አንድ ጊዜ የሚቆረጥ ብዙ ጠጉር የነበረ ሲሆን፤ ክርስቶስ ግን በራሱ ላይ የሾህ አክሊልን የደፋ ነው፡፡ በአቤሴሎም ራስ ላይ ያለው ጠጉር ከሚመዝነው ሰቅል በላይ ኢየሱስ ስለ ሁላችንም ኃጢአት በራሱ ላይ የተጫነው የእሾህ አክሊል እጅግ ይከብዳል፡፡ ክርስቶስ ኃጢአት የሌለበት ንጹሕ ነውና፡፡

      ጌታችን ኢየሱስ ‹‹ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና›› (ዮሐ. 6፡38) እንዳለ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመ ነው፡፡ እኔና አብ አንድ ነን (ዮሐ 10፡30) በማለት በምድር ላይ የአባቱን ውበት ያሳየ የመለኮት ሙላት ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ እርሱ የባሪያን መልክ የያዘ ቢሆንም፤ በሰው ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ ያደረገ ቢሆንም፤ በምስሉ እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን ያዋረደ ቢሆንም፤ ለመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ቢሆንም (ፊል. 2፡7) ከራሱ እስከ እግሩ ነውር የሌለበት ቤዛችን ክርስቶስ እርሱ ብቻ ነው፡፡

       ዓለም እንደ አቤሴሎም ባለ ውበት ብትሽቆጠቆጥ ለክብር የሚጋፉ፤ ለታይታ የሚተራመሱ፤ በሴራ ጉሽ የሰከሩ አደባባይ ናት፡፡ ለእኛ እውነተኛው አቤሴሎም ነውር የሌለበት ከሰማይ የወረደ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ነው፡፡ ስለ አቤሴሎም ‹‹በላያችን እንዲሆን የቀባነው›› (2 ሳሙ. 19፡10) በማለት ሕዝቡ በሰልፍ ለሞተው አቤሴሎም ቁጭታቸውን ሲገልጹ እናነባለን፡፡ ክርስቶስን በተመለከተ፤ ደቀ መዛሙርቱን ‹‹ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?›› ባላቸው ጊዜ ጴጥሮስ ‹‹ከእግዚአብሔር የተቀባህ ነህ›› አለ (ሉቃ. 9፡20)፡፡ ከእግዚአብሔር የተቀባውን ክብርና ስፍራ ማንም ሥጋን የለበሰ ሁሉ ሊወስድ አይቻለውም፡፡

       አቤሴሎምን ለዚህ ክፋት ምክንያቱ የነበረውንና የሕይወቱን ፍጻሜ እንመልከት፡፡ ‹‹አቤሴሎምም ሕያው ሳለ፡- ለስሜ መታሰቢያ የሚሆን ልጅ የለኝም ብሎ ሐውልት ወስዶ በንጉሥ ሸለቆ ውስጥ ለራሱ አቁሞ ነበር፤ ሐውልቱንም በስሙ ጠርቶት ነበር›› (2 ሳሙ. 18፡18) የሚል ተጽፎ እናነባለን፤ እንዲሁም ሞቱን ‹‹አቤሴሎም ከዳዊት ባሪያዎች ጋር በድንገት ተገናኘ፤ አቤሴሎምም በበቅሎ ተቀምጦ ነበር በበቅሎውም ብዙ ቅርንጫፍ ባለው በታላቅ ዛፍ በታች ገባ ራሱም በዛፉ ተያዘ በሰማይና በምድር መካከል ተንጠለጠለ፤ ተቀምጦበትም የነበረው በቅሎ አለፈ›› (2 ሳሙ. 18፡18) ተብሎ ተጽፎ እናነባለን፡፡

       የአቤሴሎም ፍጻሜ በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡ አቤሴሎም ከስሙ ጋር የተያያዘ ፍላጎት እንደ ነበረው አስተውለናል፡፡ በርግጥ አቤሴሎም በዚህ ስፍራ እንዳነበብነው ልጅ ያልነበረው አልነበረም (2 ሳሙ. 14፡27)፡፡ ነገር ግን ዙፋኑ የዳዊት ስለ ነበር አቤሴሎምን የራሱ ልጆች እንኳ ከንግሥና ጋር በተያያዘ ሊያስቡት አይችሉም፡፡ ስለዚህ በንጉሥ ሸለቆ ለራሱ ሐውልት አቆመ፡፡ እግዚአብሔር የእርሱ በሆነው እኛ እንዳንቆም ይርዳን፡፡ አቤሴሎም እንዳሰበው ሊሆን አልቻለም፡፡ እንደዚያ ያለ ሴረኛ በኤፍሬም ዱር ውስጥ ያለ አንድ የዛፍ ቅርንጫፍ አንጠለጠለው፤ አቤሴሎም ውበቱ ጥፋቱ ሆነበት፡፡

        ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ክብሩ ሳይሆን ስለ ክብራችን ራሱን አዋረደ፤ ከምድር ከፍ ከሰማይ ዝቅ ብሎ መስቀል ላይ ሞተ፡፡ አቤሴሎም ስለ ስሙ በምድርና በሰማይ መካከል በአንዲት ቅርንጫፍ ተንጠልጥሎ በጋሻ ጃግሬዎች ተመትቶ ሞተ፡፡ እርሱም በዱር ባለ በታላቅ ጉድጓድ ውስጥ ተጥሎ እጅግ ታላቅ የሆነ የድንጋይ ክምር ሸፈነው (2 ሳሙ. 18፡17)፤ የአቤሴሎም መታሰቢያው እንዲህ ሆነ፡፡ የተወደዳችሁ ሆይ፤ ክርስቶስ ስለ ሁላችንም መከራን ተቀብሎ፤ ሞቶ ከሞት ተነሥቶአል፡፡ ሁሉን በእርሱ ስም እናደርገው ዘንድ እርሱ ዛሬም ሕያው ነው፡፡

       በራሳችን ስም ለራሳችን የሚቆም ሐውልት የለም፡፡ ‹‹. . እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት›› (ቆላ. 3፡17) እንደ ተባለ፤ ለዚህ ሕያውና የሚሠራ ቃል መታዘዝ ያስፈልገናል፡፡ በብሉይ ኪዳን የተተረከልን አቤሴሎም ዛሬ የለ ይሆናል፤ ዳሩ ግን መንፈሱ ባመኑና በሚያገለግሉ ላይ ይሠራል፡፡ እንዲህ ባለው ርኩሰት ራስን አለማሳደፍ እግዚአብሔር ‹‹እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ፤ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ፡፡›› (መዝ. 2፡6) ያለለትን ልጁን ክርስቶስን በተግባር ማክበር ነው፡፡ ከሰማይ ወደ እኛ የወረደ ውበት፤ በአብ ዘንድ መታያ ውበት፤ በዘመናችን ሁሉ ዝርግፍ ጌጥ፤ በመለኮት ዙፋን ፊት የምንታይበት የውበት ልክ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ሮሜ 8፡29)!  
                                    ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment