Monday, March 14, 2016

መልእክት ኀበ ፊልሞና፡፡(6)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


 ሰኞ መጋቢት 5 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት


(መልእክት ወደ ፊልሞና)

‹‹እምጳውሎስ ሙቁሐ ለኢየሱስ ክርስቶስ፡ (ኤፌ. 3፡1)!››

‹‹ወእመሰ እኁየ አንተ ተወከፎ ከማየ፤ ለእኔስ ወንድሜ ከኾንህ እኔ እንደ ተቀበልሁት ተቀበለው፡፡ አንድም ለእኔ ወንድሜ ከኾነ እኔን እንደ ተቀበልህ ተቀበለው››፡፡

‹‹ . . እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው ›› /ቁ. 17/

        ሐዋርያው ጳውሎስ አናሲሞስን ‹‹እንደ እኔ›› ተቀበለው በማለት ይጠይቀዋል፡፡ ፊልሞና ጳውሎስን ተቀብሎ ለዘላለም እንደያዘው እናውቃለን፡፡ አሁንም በወንጌል እውነት በማመን ወደ ክርስትና የተቀላቀለውን አናሲሞስን ፊልሞና ጳውሎስን በተቀበለበት በዚያው መቀበል ሊቀበለው የተገባ ነው፡፡ ‹‹እንደ ባልንጀራ ብትቆጥረኝ›› ሲል በሁለቱ መካከል ያለውን የቀረበ ወዳጅነት ማስተዋል እንችላለን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹ባልንጀራህን እንደ ራስህ›› (ማቴ. 19፡19) የሚለውን ቅዱስ ትእዛዝ እንዴት ተግባራዊ እንዳደረገ በዚህ አጻጻፉ ልብ እንላለን፡፡

        አስቀድመን ባየናቸው ቁጥሮች ውስጥ ‹‹ስለ ልጄ›› ‹‹ልቤ እንደሚሆን›› በማለት ፊልሞና አናሲሞስን ይቀበለው ዘንድ ለምኖአል፡፡ እውነተኛ ልጅ ደግሞ አባቱን መምሰሉ እውነታ ነው፤ እንደ እኔ ተቀበለው ማለቱም የአናሲሞስን እውነተኛ መለወጥ፤ የጳውሎስንም እውነተኛ መውደድ እናይበታለን፡፡ እንዲህና እንደዚያ ነው ልንል በማንችልበት ሁኔታ በጳውሎስና በፊልሞና መካከል ልዩ የሆነ መቀራረብና ጥብቅ ወዳጅነት እንደ ነበር ከመልእክቱ መረዳት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ክርስትና መልክ ክርስቶስን ማሳየቱ ዛሬ ላለነው ወቀሳም ጭምር ነው፡፡

‹‹ይህን በእኔ ላይ ቁጠር››

       እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው ካለ፤ ቀጥሎ በእርሱ ላይ ያለውን ሁሉ በእኔ ላይ ቁጠር ማለቱ የአሳብ ትክክለኛ ፍሰት ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ አናሲሞስ በድሎ አልያም እዳ ኖሮበት ቢሆን ሁሉንም በእርሱ ላይ እንዲቆጥረው ይጠይቀዋል፡፡ ይህ አካሄድ ችግሮችን ለመፍታት እንዴት ያለ የተዋበ መመሪያ ነው? ፊልሞና በአናሲሞስ ድርጊት ውስጡ የቆሰለ ቢሆን እንኳ የጳውሎስ ንግግሮች ለዚያ ቁስል የዘይት ያህል ናቸው፡፡ ጌታ በተያዘበት ምሽት ‹‹እነዚህ ይሂዱ ተዉአቸው›› (ዮሐ. 18፡8) በማለት ራሱን የሰጠበትን ሁኔታ በዚህ ስፍራ ማስታወስ በእጅጉ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

       አናሲሞስ በነፍሱ ያለበት እዳ በክርስቶስ ቤዛነት ተከፍሎአል፡፡ አሁን ከእምነቱ የተነሣ ሙሉ ለሙሉ ከኃጢአትና ከሞት ተጠያቂነት (ሕጉ ከሚጠይቀው) ፍጹም ነጻ ነው፡፡ ፊልሞና ከሚያነሣው በደል አልያም እዳ ደግሞ እኔ እጠየቃለሁ የሚል ወንድም ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን እያደረገ ነው፤ ስለዚህ ከዚህም ነጻ ነው፡፡ ኦ! ምንኛ ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው፡፡ ሐዋርያው ‹‹በእጄ እጽፋለሁ›› ሲል ‹‹እኔ እመልሰዋለሁ›› ማለቱን እርግጥ ለማድረግ እንደ ሆነ እንገነዘባለን፤ ልክ እንደ ፊርማ እናስበው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ፊልሞናን እንዳገለገለው ስናስብ ‹‹የራስህ ደግሞ ብድር እንዳለብህ አልልህም›› የሚለውን ግልጽ እናደርጋለን፡፡  

‹‹በክርስቶስ ልቤን አሳርፍልኝ››     

       በአናሲሞስና በፊልሞና መካከል የተፈጠረው ክፍተት ቀለል ያለ እንደ ሆነ አናስብም፡፡ በሮም ሕግ መሠረት አንድ ከጌታው የኮበለለ ባሪያ የሞት ፍርድ ውሳኔ ይጠብቀዋል፡፡ ከዚህ መልእክት ጋር ወደ አሳዳሪው ፊልሞና የሚመለሰው አናሲሞስ ሞገስን ካገኘ ውጤቱ ከሞት የመትረፍን ያህል ነው፡፡ ሐዋርያው ልቤን አሳርፍልኝ ማለቱ በክርስቶስ መሆኑ የፊልሞናን ልብ ለፍቅር የሚፈትን ነው፡፡ በእርግጥም እንዲህ ያለውን ተማጽኖ ፊልሞና ረግጦ ወደ ዓለም ዳኝነት ፈቅ ሊል አይችልም፡፡

      ሐዋርያው ሃያ አምስት ቁጥሮች ባሉት በዚህ መልእክት ውስጥ ሁለት ጊዜ ‹‹ወንድሜ ሆይ›› በማለት በቀጥታ ተናግሮአል፡፡ በክርስትና ውስጥ በወንድማማችነት መቀባበል የሁሉም ምእመን ትክክለኛ ስፍራ ነው፡፡ ልዩ ልዩ በሆነው የእግዚአብሔር ጸጋ ስጦታ ልዩነት ቢኖርም መንፈስ ግን አንድ ስለሆነ፤ መንፈስ ከሆነው ከእግዚአብሔር የተወለድን እኛ ደግሞ ልጆች ወንድማማቾች ነን፡፡ ‹‹እኔ እንድጠቀምብህ ይሁን›› የሚለው፤ ለእኔ እንደ ዋልክልኝ ቁጠረው ማለት ይሆናል፤ ስለ አናሲሞስ ፈንታ ጳውሎስ ራሱን ምትክ አድርጎአል፡፡ ስለዚህ የአናሲሞስን መጉዳት መጉዳቱ፤ ለአናሲሞስ የሚሆነውን መጥቀም ደግሞ እንደ ጥቅሙ ተመልክቶታል፡፡          

         ባሪያ የሆነውን አናሲሞስን በተመለከተ እንደ ሮማውያን ሕግ የጳውሎስን ልብ የሚያሳርፍ አንዳችም ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ ጸጋንና እውነትን ተመልቶ በእኛ ካደረው (ዮሐ. 1፡14) ከክርስቶስ የተነሣ ግን ለአናሲሞስም ለጳውሎስም ለፊልሞናም እረፍት የሚሆን ነገር ሆኗል፡፡ ‹‹አሳርፋችኋለሁ›› (ማቴ. 11፡28) ያለ ጌታ ለክርስቲያን በማንኛውም ጉዳዩ ላይ እውነተኛ እረፍት ነው፡፡ የሚተራረቁም የሚያስተራርቁም ልቦች ትክክለኛ የእረፍት ስፍራ ክርስቶስ ነው!
               ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment