Saturday, November 19, 2011

ልክ በዚህ ሰዓት

ለብቻ አቅዶ ግብ ላይ መድረስ እንደ ጀብዱ፣ በራስ ምክር ብቻ መንቀሳቀስ አዋቂነት፣ የሰውን እርዳታ አለመሻት ቆራጥነት፣ ከራስ ጋር ብቻ ተጐራብቶ መኖር እንደ ስኬት በሚታይበት የዘመን ጭላጭ የከሰርነውን ንብረት ሳይሆን ያጣነውን ወዳጅነት ልንቆጭበት ይገባል፡፡ ወዳጅነት ስሙ እንጂ ተግባሩ፣ ዓጽሙ እንጂ አካሉ፣ ቃሉ እንጂ ሕይወቱ እንደሌለ ሰዎች መተማመን ላይ እየደረሱ ስለሆነም ልንጸልይ ያስፈልገናል፡፡አንድ በዕድሜ የገፉ እናት ምሬት በቃኘው ድምፃቸው:-ዛሬማ ጉርብትና በሽታ (ጠረን) ሆኗልያሉትን አስታውሳለሁ፡፡ እኛስ ጋር በምን ይሆን?
 ያለንበትን ዘመን ስንዋጀው የወዳጅነት ኑሮው ቀርቶ ጠረኑ እንኳን የተናፈቀበት፣ ያንጀት ሳይሆን የአንገት ባልንጀርነት የበረከተበት፣ የለበጣ ፍቅር የሰዎችን ልብ የገዛበት ነው፡፡ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅነት የለምየሚል የቢዝነስ መርኅ ትዝ ይለኛል፡፡ ይህ ለብዙዎችም የሕይወት መርኅ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ እኔ ግን እላችኋለሁ፡- በዘላቂ ወዳጅነት ውስጥ ሕያውና የማያቋርጥ ጥቅም አለ፡፡ በሙላታችሁ ብቻ ሳይሆን በጉድለታችሁ ውስጥም ለሌሎች የሚተርፍ በረከት አለ፡፡
በዕንባችሁ ውስጥ እንኳን እናንተ ሌሎች የሚያስተውሉት ደስታ አለ፡፡ ሕመማችሁ ውስጥ ሌሎችን የሚያቆም መድኃኒት አለ፡፡ ርሀባችሁ ውስጥ ለሌሎች ጥጋብ የሚሆን ነገር አለ፡፡ ዘላቂ ጥቅም ውስጥ ግን አንድ ድምፅ ብቻ አለ፡፡ ይህም ከንቱ የከንቱ ከንቱ ሁሉ ከንቱ የሚል ጥበብ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ዕረፍት የለም፡፡ ያለው ትጋት የሚመስል መቅበዝበዝ ነው፡፡ ግንኙነቱ በልብ ላይ ሳይሆን በጥቅም ላይ የተተከለ ነው፡፡ ቃል ኪዳኑም እስከ መሻሻጥ የሚደርስ ነው፡፡ እንኳን ስታነቡት እኔ እንኳን ስጽፈው በድን በድን እንደሚሸት ይሰማኛል፡፡
 አገሮች ዘላቂ ጥቅም አላግባባቸውም፡፡ ሕዝቦቻቸውንም ከሽምቅ ኑሮ አልታደገላቸውም፡፡ ዘላቂ ጥቅም እንኳን የቅርቡን የሩቁንም እየተጠራጠርን እንድንኖር፣ በስንት ያወጣል ግምት እንድንቀራረብ፣ ሁሉንም ከምን አገኛለሁ እንጂ ከፍቅር አንፃር እንዳናስተውል አድርጐናል፡፡ ተወዳጆች ሆይ ዘላቂ ጥቅም ዘላቂ ወዳጅነት የማምጣት አቅም የለውም፡፡ ዘላቂ ወዳጅነት ግን ዘላቂ ጥቅምን ይፈጥረዋል፡፡ ለዚህም ብርቱ ነው!
        ለዘላቂ ጥቅም ያደርነውን ያህል ለዘላቂ ፍቅር አልኖርንምና፡፡ ለዘላቂ ክብር የተሟገትነውን ያህል ለሚዘልቅ ወዳጅነት አልተቆረቆርንምና፡፡ ዕቃ ተቀማሁ ብለን የተበሳጨነውን ያህል ወዳጄን አጣሁ ብለን አልጮኽንምና ሁሉን የሚያውቅ ጌታ ይቅር ይበለን!
      ልብ በል! ልክ በዚህ ሰዓት የሆነ ሰው በአእምሮው እያሰበህ፣ በልቡም ለኑሮህ እየተጨነቀ፣ ሰብእናህንና ስኬትህን እያከበረው፣ ከእውነት እየወደደህ፣ መልካምነትህን እየዘከረ፣ ስለ አንተም እግዚአብሔርን እያመሠገነ ነው፡፡
        የሆነ ሰው ከአንተ ጋር መሆን ይፈልጋል፣ ሊያናግርህ ይጓጓል፣ አብሮነትህንም ይናፍቃል፣ እንድትፈልገው ይፈልጋል፣ ሥጦታ እንደሆንክ ያምናል፣ ላለህ ነገርና ለማንነትህ የከበረ ዋጋ ይሰጣል፡፡ እንደሚጠነቀቅልህ ታውቅ ዘንድ ይወዳል፡፡ ዓላማውንም ከአንተ ጋር ሊጋራ በብርቱ ይመኛል፡፡
        ልክ በዚህ ሰዓት የሆነ ሰው ደስተኛ እንድትሆንለት ይጥራል፡፡ በመከራም ውስጥ እንኳን ሰላም እንደሆንክ ተስፋ ያደርጋል፡፡ አትኩሮቱን ቢሰጠኝ ብሎ ይጠብቅሃል፡፡ ይበልጥ ትወዳጀውም ዘንድ ይማጸናል፡፡ በውስጡም ያስቀረኸውን ፍቅር፣ ጥንካሬና እውነተኛነት ያሰላስለዋል፡፡ ለሥጋህ ጤና፣ ለመንፈስህ ንጽሕና ለነፍስህም አርነትን ከልቡ ይመኝልሃል፡፡ ልክ በዚህ ሰዓት . . . . !

4 comments:

  1. The grace of Almighty God be with you!

    ReplyDelete
  2. የሆነ ሰው ከአንተ ጋር መሆን ይፈልጋል፣ ሊያናግርህ ይጓጓል፣ አብሮነትህንም ይናፍቃል፣ እንድትፈልገው ይፈልጋል፣ ሥጦታ እንደሆንክ ያምናል፣ ላለህ ነገርና ለማንነትህ የከበረ ዋጋ ይሰጣል፡፡ እንደሚጠነቀቅልህ ታውቅ ዘንድ ይወዳል፡፡ ዓላማውንም ከአንተ ጋር ሊጋራ በብርቱ ይመኛል፡፡

    ReplyDelete
  3. ልብ ይነካል! በርታልን፡፡

    ReplyDelete
  4. ቤተ ፍቅር በርታ!

    ReplyDelete