Wednesday, November 30, 2011

የቱ ይሻላል?


      የሌሎችን ስህተት መዳኘቱ ቀላል ሲሆን የራሳችንን ድካም ማስተዋሉ ደግሞ ከባድ ነው፡፡ ቀላሉ ሳያገናዝቡ ማውራት ሲሆን ከባዱ ደግሞ ምላስን መግታት ነው፡፡ የሚወደንን ሰው መጉዳት ቀላል ሲሆን የሚከብደው ደግሞ ያንን ቁስል ማዳኑ ነው፡፡ ሌሎችን ይቅር ማለት ቀላል ሲሆን ይቅርታን መጠየቅ ግን ከባድ ነገር ነው፡፡ ሕጎችን ማውጣት ቀላል ሲሆን እነርሱን መከተሉ ደግሞ ከባድ ነገር ነው፡፡ ቀላሉ በእያንዳንዱ ምሽት ማለሙ ሲሆን ከባዱ ደግሞ ለስኬታማነቱ መዋጋት ነው፡፡
     ሙሉ ጨረቃን ማድነቁ ቀላል ሲሆን ሌላኛውን ጎን ማየቱ ግን ከባድ ነገር ነው፡፡ ቀላል የሆነው ለአንድ ሰው የሆነ ቃል ኪዳን መግባቱ ሲሆን የሚከብደው ደግሞ ያንን ቃል መፈጸሙ ላይ ነው፡፡ እወዳችኋለሁ ማለት ቀላል ሲሆን ከባዱ ደግሞ ያንን በሕይወት ማሳየቱ ነው፡፡ ሌሎችን መተቸት ቀላል ሲሆን ራስን ማሻሻል ደግሞ ከባድ ነው፡፡ ስህተትን መሥራት ቀላል ሲሆን ከዚያ መማሩ ደግሞ ብርታትን ይጠይቃል፡፡ ስላጣነው ፍቅር ማንባቱ ቀላል ሲሆን ላለማጣት መንከባከቡ ግን ይከብደናል፡፡ መቀበል እጅግ ቀላል ሲሆን መስጠት ደግሞ ልባዊ ርኅራኄን ይጠይቃል፡፡ ስለ መሻሻል ማሰብ ቀላል ሲሆን ከባዱ ግን ወደ ተግባር መቀየሩ ላይ ነው፡፡ ወዳጅነትን በቃላት መጠበቁ ቀላል ሲሆን ትርጉማቸውን መጠበቁ ግን ከባድ ነገር ነው፡፡
     ልጅ እያለን ከሰማናቸው ነገሮች መካከል አንዱ በአካባቢያችን ውሻ ሲያላዝን (የተለየ ድምጽ ሲያሰማ) "ሰው ሊሞት ነው' የሚለው አባባል ነው፡፡ እጅግ በሚገርም ሁኔታ ግን "እኔ ልሞት ነው' የሚል ያለመኖሩ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ አልጋ የያዙ ካሉ የሰዉ ሁሉ ትኩረት መጠቋቆሚያ የመሆናቸው ጉዳይ አጠያያቂ አይሆንም፡፡ ግን የቱ ይሻላል? ሰውን ማስተካከል ወይስ ራስን ማስተካከል፣ እነርሱ ልክ አይደሉም ማለት ወይስ እኔ ልክ አይደለሁም ማለት፣ የሌሎችን ስህተት መዳኘት ወይስ የራስን ድካም መታገል የቱ ይሻላል? ተወዳጆች ሆይ ለሚከብደውና ለሚበልጠው እንትጋ!

2 comments:

  1. የተሻለውን እንድናስተውል ጌታ ይርዳን፡፡

    ReplyDelete
  2. erasen enday selegabezkgn amesegnalew betam astemari,yemilewt blog new.geta yebarkh.

    ReplyDelete