Wednesday, November 30, 2011

የሚዛናዊነት ያለህ


ሰፋፊ ነጻ መንገዶችና የተንጣለሉ ውብ ሕንጻዎች ነገር ግን የጠበቡ አመለካከቶች አሉን፡፡ የምናወጣው ብዙ ሲሆን ያለን ግን ጥቂት ነው፡፡ የምንገዛው ያየለ የምናገኘው ደስታ ግን እዚህ ግባ የማይባል ነው፡፡ የበዙ ማዕረጎች ሲኖሩን ግን ጥቂት እርካታ ብቻ አለን፡፡ ብዙ እውቀት ግን ደግሞ ያነሰ ፍርድ፡፡ በቁጥር የበዙ ባለሙያዎች ነገር ግን የትየለሌ ችግሮች፣ በየዕለቱ አዳዲስ መድኃኒት ዳሩ ግን በጣም ያነሰ ጤንነት አለን፡፡ ብዙ እናወራለን ጥቂት እናደርጋለን፡፡ ለምንሰበስባቸው ነገሮች ከፍተኛ አመለካከት ሲኖረን የራሳችንን ዋጋ ግን እናሳንሰዋለን፡፡
በሕይወት ላይ ዕድሜን ስንጨምር፣ በዕድሜያችን ላይ ግን ሕይወትን መጨመር ተስኖናል፡፡ እስከ ጨረቃ ያለውን የደርሶ መልስ ጉዞ ስንፈጽም ያለፈውን ወዳጅነት ለማደስ አልያም አዲስ ወዳጅ ለማፍራት ግን መንገዱን ማቋረጡ ጭንቅ ሆኖብናል፡፡ ውጫዊውን ቦታ ስንይዝ ውስጣዊውን ስፍራ ግን መቆጣጠር ተስኖናል፡፡ ብዙ እንጽፋለን ጥቂት እንማራለን፡፡ ብዙ እናቅዳለን ጥቂት እንተገብራለን፡፡ በጣም መፍጠንን ስናውቅ መጠበቅን ግን አንረዳውም፡፡
የትልልቅ ሰዎችና የትንንሽ ጠባይ፣ የጠነከረ ትርፍ ግን ደግሞ ሥር ያልሰደደ ባልንጀርነት የሚታይበት፣ በአንድ ምሽት ብዙ ነገር የሚያልፍበት ዓይነተ ብዙ፤ ግብረ ለየቅል ዘመን የምንኖርባት ዓለም ቋሚ ጠባይ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ ብዙዎች በሕይወት እየሆነ ባለው ነገር ግራ ይጋባሉ፣ ከመኖርም ሞትን ይመርጣሉ፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ልከኛ ኑሮና ደስተኛ ሕይወትን ለመምራት፣ ለምድሪቱም ደዌ ፈውስን ለማምጣት ለተፈጥሮና በዚህም ውስጥ እየሆነ ላለው ሁሉ ሚዛናዊና ያልተዛባ መረዳት እንዲሁም አመለካከት ሊኖረው ግድ ነው፡፡ ምክንያቱም እርካታ አልባ ለሆነ ኑሮ፣ ለማያቋርጥ የሕይወት ስቃይ ዋናው ምነጭ ይህ ነውና፡፡
ደስታን በቅጡ መከራንም በአግባቡ ለማሳለፍ የሚቸገሩ፣ ለትንሽ ቀናት ሐዘን ለወራት ማቅ ለብሰው የሚያዝኑ፣ አንድ ሰው ጎዳኝ ብለው ሁሉን እያሳደዱ የሚኖሩ፣ ለሰዓታት የሕይወት ደመና፣ ለደቂቃዎች  የፈተና ጉም፣ ለዓመታት በራቸውንና ልባቸውን የሚዘጉ ወገኖች የኑሮን ፈረቃ ያልተረዱ፣ በሕይወት እየሆነ ላለውም ሚዛናዊ የሆነ እይታ የሌላቸው ናቸው፡፡
አንድን ሰው በቅድሙ ፈገግታው የሁልጊዜ ሕልውናውን፣ በአሁኑ መከፋት የወደፊት ነባራዊ ሁኔታውን መናገር ሚዛን አልባነት እንደሆነ ሁሉ፤ ለራሳችንም የሚኖረን አስተያየት ጤናማ ካልሆነ ከደስታ ሳይሆን ከሐዘን፣ ከቅድስና ሳይሆን ከርኩሰት እንደተጎራበትን ከምሬትና ሮሮ እንደተጣባን እንጨርሳለን፡፡
ሰማይ ተገምሶ ቢወድቅባቸው፣ ምድር ተንዳ ብትከዳቸው እንኳን የሚቆሙ የመሰሉን በዓለም መርዶ ሲንከባለሉ፣ ከደስታ እንደተሰሩ ያሰብናቸውን መከራ ሲንዳቸው፣ ስንቱን ተናግረው ያሳመኑ፣ መክረው ያቀኑ፣ ገስፀው የመለሱ መጽናናት ሲያቅታቸው ልባችን አስተውሏል፡፡ ከዚህም የምንረዳው የሰው ቋሚ የሥጋ ለባሽ ብርቱ እንደሌለው ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን የጸና ግንብ ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ በዚህ ደስታና ሐዘን፣ ፍቅርና ጥላቻ በሚፈራረቁበት ዓለም ሚዛናዊነት የሕይወት ጨው ነውና በኖርንበት ጊዜ፣ ባለንበት ቦታ፣ በከወንነው ነገር ሁሉ ሚዛናዊ እንሁን፡፡                  (ይቀጥላል)

1 comment:

  1. ኧረ የሚዛናዊነት ያለህ፡፡ ለቤተ ክህነቱም ለቤተ መንግስቱም እግዚአብሔር ይህንን ያድርግ፡፡

    ReplyDelete