Wednesday, November 30, 2011

ሁለት ባልዲዎች


       ጀምበር አዘቅዝቃ ወደ መኝታዋ ስታዘግም የተሰማ የባልዲ ቁም ነገር ነው፡፡ ሁለት ባልዲዎች(የውሃ መቅጃ) በሁለቱ ጫፍ በገመድ የተወጠሩለት አንድ አነስተኛ መዘውር ነበር፡፡ አንደኛው ባዶ ሆኖ ወደ ጉድጓድ ሲወርድ በሌላኛው ጫፍ የተንጠለጠለው ባልዲ ደግሞ በውሃ ተሞልቶ ወደ ላይ ይወጣል፡፡ አንደኛው መቅጃ ዓለም የምታቀርበው በጣም ጥቂት ነገር ብቻ ነው እያለ የማይቋረጥ ማማረሩን ቀጥሏልወደ ጉድጓዱ አፍ ሙሉ ሆኜ ወጥቼ ወደ ታች ስመለስ ግን ሁል ጊዜም ባዶ ነኝእያለ ይጨነቃል፡፡
      ሌላኛው ባልዲ በበኩሉ በደስታ ተሞልቶ እንዲህ ሲል ይመልሳልምንም ያህል ባዶ ሆኜ ወደታች ብወርድም እንኳን ሁልጊዜም ሙሉ ሆኜ ከፍ እላለሁ፡፡ብዙው ነገር የሚወሰነው እኛ በውስጣችን እንዳስቀመጥነው ነው፡፡ ንፋስ በረሃማ ቦታ ላይ ሲነፍስ የሚያፍን የአቧራ ክምር ይፈጥራል፡፡ ዳሩ ግን ያው ነፋስ በአትክልት ቦታ ውስጥ ቢያልፍ የማራኪ አበቦችን ጣፋጭ መዓዛ ይረጫል፡፡
     አንድ ሕፃን ለመራመድ ሲፍጨረጨር ብናስተውል ማብቂያ የሌላቸውን ውድቀቶች እናያለን፡፡ ስኬቶቹ ግን በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ነገር ግን በተደጋጋሚ ውድቀቶቹ እንዳሉ ሆነው የማይቻል የሚመስለውን ነገር ማድረግ የቻለው ሕጻን በኃይለኛ ደስታ ውስጥ ይዋጣል፡፡ በጊዜው አቋሙን ስለ መጠበቁ እንጂ ስለ ወደቀባቸው ጊዜያት ያን ያህል ሳይጨነቅ ከደስታ ወደ ደስታ ይሸጋገራል፡፡
     አንተም አታማር፣ ጊዜም አታጥፋ፡፡ ተስፋ በማድረግና ጠንክረህ በመሥራት ሕይወትህን በደስታ ሞልተሃት ኑር፡፡ እርግጥ ነው ብዙ ነገሮች አስቸጋሪ ይሆኑብናል፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜም ቢሆን ሕይወትህን ስኬታማ የምታደርግበት፣ ራስህን በውብ ወጣትነት የምትቀርጽበትና በውስጣዊ ሕይወትህ ያለህን ብልጽግና የምትጨምርበት እልፍ መንገድ አለ፡፡
     ስለዚህ ሙሉ ዓለም ቢታሰስ ለአንተ የተሻለ ቦታና ሁኔታ ሊኖር እንደማይችል ማሰብህን አቁም፡፡ ስኬት የምታመራው ፈጽሞ ተስፋ ወደማይቆርጡና አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ለማተኮር ወደወሰኑ ሰዎች ነው፡፡ ምንም እንኳን ያልተሳኩ ነገሮቻችን፣ የውደቀት መጠናችንና የስህተታችን ብዛት ቢያይልም ከዚህም የተነሣ ምንም ያህል ባዶ ሆነን ወደታች ብንወርድም እንኳን ሁልጊዜም ሙሉ ሆነን ከፍ እንላለን፡፡ የትንሣኤ ምስጢር ያለውም እዚህ ውስጥ ነው። እንደ ምድረ በዳ ያሉ የሕይወት ውጣውረዶች እንደ ተራራ ወደአለ ከፍታ፣ እንደ መቃብር ያሉ የኑሮ ዝቅታዎች እንደ ትንሣኤ ወደአለ ልዕልና የሚያሻግሩን ናቸው።
     አሁን አንተን አንድ ጥያቄ እጠይቅህ ዘንድ እወዳለሁ። ከመዘውሩ በአንደኛው ጫፍ ላይ እንዳለህ አስብና አንተ ብትሆን ልትል የምትችለውን አእምሮህ ሰሌዳ ላይ ጻፍ። እርሱንም ከእውነታውና መሆን ካለበት ከትክክለኛው ነገር ጋር አነጻጽር። ልክ እንዳልሆንክ አንዳች የተሳሳተ ነገር እያደረክ እንደሆነ ከተሰማህ ችግሩ የሚጠይቀውን መፍትሔ ከማድረግ ወደኋላ አትበል። ያለ ዕለት ከዕለት ግጥሚያዎቻችን እና ፈተናዎቻችን ሕይወት ባዶና አንድ ዓይነት ትሆናለች፡፡ ችግሮች አብዛኛውን ጊዜ ልንማራቸው ግድ የሚሉን እውቀቶች ናቸው፡፡
    ስለዚህ ሁሉንም የሕይወት ተሞክሮዎች ደስተኝነት ከሰፈነበት አቀባበልና ከእምነት ጋር ተግባባቸው፡፡ በሚያጋጥምህ በእያንዳንዱ ችግር ውስጥ የተደበቁትን ስጦታዎች በማስተዋል ሆነህ መርምር፡፡ ሰው መሆን እንደ እንግዳ ቤት ነው፡፡ እያንዳንዱ ማለዳ አዲስ አዳራሽ ነው፡፡ ደስታ፣ ሐዘን፣ ሕመም እና ጊዜያዊ ግንዛቤዎች እንደአልተጠበቀ ጎብኚ ሆነው ይመጣሉ፡፡ ሁሉንም በጸጋ ተቀበላቸውና ተደሰትባቸው ለሕይወትህም ፍስሐ ይሆኑ ዘንድ ፍቀድላቸው፡፡

4 comments:

  1. ሙሉ ዓለም ቢታሰስ ለአንተ የተሻለ ቦታና ሁኔታ ሊኖር እንደማይችል ማሰብህን አቁም፡፡

    ReplyDelete
  2. ሰው መሆን እንደ እንግዳ ቤት ነው፡፡ እያንዳንዱ ማለዳ አዲስ አዳራሽ ነው፡፡ በርቱልን!

    ReplyDelete
  3. betam des yemil yemiyatsnana heyewotenem kebzu angle endenmeleketat ymiyastemr blog new.geta yeagelgelotzemenhen yeberk.

    ReplyDelete
  4. yih blog erasen endayew new yeredagn. chgren endet mayet malef endalebgn astemroghal.

    ReplyDelete