Tuesday, October 30, 2012

መልከኞቹ (ማጠቃለያ)



               ማክሰኞ ጥቅምት 20/2005 የምሕረት ዓመት

6. የማያመሰግኑ፡ - እግዚአብሔርን አለማማረር ብቻ ሳይሆን ማመስገን አለመቻልም ኃጢአት ነው፡፡ በደሙ ዋጋ የገዛንን ጌታ ተመስገን ማለት ዋጋው ብዙ ነው፡፡ ሌሎች የሰጡን ቁሳዊ እርሱ ግን የሰጠን መንፈሳዊ በረከት ነው፡፡ ሰዎች ስለ እኛ ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ አሳባቸውን ሰጥተው ይሆናል፡፡ እርሱ ግን ነፍሱን ስለ እኛ አኑሯል (ዮሐ. 15÷13)፡፡ በሰዎች ዘንድ ስለተደረገልን ነገር የምንሰጠው የምስጋና ምላሽ “ኪስ አይገባም” በሚል ማራከሻ ይጣጣል ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ግን ምስጋናችንን የመሥዋዕት ያህል በፊቱ ልክ እንደተወደደ መዓዛ ይቀበለዋል (ዕብ. 13÷15)፡፡  
         በአስተሳሰብ ብስለት ውስጥ ባሉ ሰዎች መካከል ምስጋና የመልካም ሰብእና አንዱ መለኪያ ነው፡፡ ተቀብሎ ያላመሰገነ እንደ ቀማኛ ይቆጠራል፡፡ ምስጋና ሰጭውን ለበለጠ ልግስና ሲጋብዝ አመስጋኙን ደግሞ ከቁራሽ ላይ የሚቆርስ አዛኝ ያደርገዋል፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወትም አመስጋኝነት ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያሳይ ልኬት ነው፡፡ እንደውም የምትቀበለው በአመሰገንከው ልክ ነው የሚባል አባባል አለ፡፡ በእርግጥም ምስጋና ሰብእናችንን የምናስውብበት ጥሩ መዋቢያ ነው፡፡
        ዙሪያችንን ስንቃኘው ሰዎች ከምስጋና ቃል ይልቅ በብዙ የምሬት ንግግር የተሞሉ ናቸው፡፡ በቤት በአደባባይ፣ በጉዞ በመንደር የምንሰማው ሁሉ ከመዓት ቀጥሎ ያለ ሌላ መዓት ነው፡፡ አንዳንዴ በአፋችን እንደተናገርነው እንደዚያው እየተደረገብን እንደሆነ አስባለሁ፡፡ በየዕለቱ ለእግዚአብሔር ከምናቀርበው ውዳሴ በላይ ወቀሳችን የበዛ ነው፡፡ ኢዮብ ሁሉን አጥቶ “ይባረክ” (ኢዮ. 1÷21) ያለውን እግዚአብሔር እኛ ባናመሰግነው ያ ሁኔታ ምን ያህል ይወቅሰናል?
         ተወዳጆች ሆይ ምስጋና ጥቂቱን ብዙ የሚያደርግ ኃይል ነው፡፡ በሆነው ብቻ ሳይሆን ባልሆነውም፣ በተቀበላችሁት ብቻ ሳይሆን ምላሽ በዘገየባችሁ ነገር፣ አለኝ በምትሉት ብቻ ሳይሆን ነበረኝ በሆነባችሁም ነገር ሁሉ ጌታን አመስግኑ፡፡
7. ዕርቅን የማይሰሙ፡ - እንደዚህ ዘመን ሰው ከራሱ ጋር የተጣላበት ጊዜ ያለ አይመስልም፡፡ ሁሉም ራሱን እያስታመመ፣ እያባበለ፣ ለማስተራረቅ እየሞከረ ነው፡፡ ነገር ግን ከራሳችን ፀብ ጋር ለመታረቅ እንኳ የእግዚአብሔር መሐል መግባት ያስፈልገናል፡፡ ሁሉ ቢጣላ ኖሮ ማን ያስታርቅ ነበር? ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ? የእግዚአብሔር ቃል “የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” (ማቴ. 5÷9) ይላል፡፡
         የእግዚአብሔር ልጅ በመሆን ውስጥ ካሉት ትልልቅ ደስታዎች አንዱ ማስታረቅ ነው፡፡ ዛሬ መለያየትን ወደ አንድነት ለማምጣት፣ ጠላትነትን ወደ ወዳጅነት ለመቀየር የሚጠይቀው ድካም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ለስንት ዓመታት የሚሸመገሉ ሰዎች አሉ፡፡ እንዲህ ያለው ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ የሃይማኖት ሰዎች የሚባሉትን ሳይቀር ይጠቀልላል፡፡ አንዳንዴ ምን አለ የጊዜውን ርዝማኔ እንኳ አክብረው ቢታረቁ ያሰኛል፡፡ እግዚአብሔር እንደ መፍትሔ አስቀምጦን እንደ ችግር ኖሮ ከማለፍ ይጠብቀን፡፡
          አንዳንዶች ለበቀል የእኔ የሚሉትን አንድ ቀን በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ ቀኑን በሙሉ በደፈጣ ያሳልፋሉ፡፡ ብዙ ሊታረቅልን የሚገባ ነገር ያለን ሰዎች ነን፡፡ እንግዲህ እርቅን አለመስማት በፀብ እንደጸኑ መቀጠል ነውና ጌታ ከሚያስተራርቁት ወገን ያድርገን፡፡
8. መልካሙን የማይወዱ፡ - መልካም አለማድረግ ምርጫ ነው፡፡ መልካሙን መቃወም ግን ከዚህ ይከፋል፡፡ በመልካምነት ላይ ውጊያ የተጀመረው ምድር ላይ አይደለም፡፡ ገና ከስነ ፍጥረት ጅማሬ አንሥቶ በሰማይ የፈነዳ አብዮት ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መልካምነትና መልካሞች ሲሰደዱ ኖረዋል እየኖሩም ነው፡፡ በዚህም ዓለም እየሆነ ያለው ይኼው ነው፡፡ መልካም የምንሆነው ጠላት ላለማፍራት አይደለም፡፡ ምርጫችን ስለ ሆነ ግን መልካም እንሆናለን፡፡ ሰው በምርጫው ደጉን ብቻ ሳይሆን ክፉውንም ያስተናግዳል፡፡ እናም ጽኑ!
         መልከኛው ክርስትና ከተገለጠባቸው ጠባያት ትልቁ ይህ ይመስለኛል፡፡ የመልካም ጥግ እግዚአብሔር ነው፡፡ ሰው የቱንም ያህል መልካም ቢሆን እግዚአብሔርን አልፎ መልካም አይሆንም፡፡ ታዲያ እንዲህ ያለውን ጌታ በመልካምነት ኃይል ሳይሆን በመልካምነት መልክ (በውስጠ ምስጢር ክፉ) ለማክበር መሞከር ምን ያህል ድፍረት ነው፡፡ ሰዎች አህዛብ ጋር ያገኙትን መልካምነት እኛ ጋር መጥተው ካጡት “ታዲያ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ” (ማቴ. 5÷46) የተባለው ለዚህም አይደል?
9. ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን መውደድ፡ - እግዚአብሔርን የምንወድበት መንገድ የሥጋ ወላጆቻችንን እንኳ ከምንወድበት ፍቅር  ይለያል፡፡ እነርሱን በሥጋ ልደት ይህንን ዓለም እንድንቀላቀል መንገድ ስለሆኑን እንወዳቸዋለን፡፡ እርሱን ደግሞ በመልኩ እንደ ምሳሌው ስለ ፈጠረን በሰውም መካከል ሰው ሆነን እንድንገኝ ስለ ፈቀደ እንወደዋለን፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ በውድ ልጁ ከዘላለም ሞት ስላዳነን እንወደዋለን፡፡ በዚህም ዓለም በሚኖረን የእግረ መንገድ ቆይታ በእያንዳንዱ የሕይወት ክፍላችን ውስጥ የምናገኛቸውን ሰዎች (ትዳርንም ጨምሮ) እንወዳቸዋለን፡፡ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርን የመወደድ ስፍራ ማንም ሊይዘው አይገባም፡፡  
        በዚህ ክፍል ላይ ሐዋርያው የሚወቅሳቸው ሰዎች እግዚአብሔርን በዚህ ዓለም ተድላ የለወጡ ናቸው፡፡ ዴማስ የአሁኑን ዓለም ተድላና ደስታ ወዶ ከእውነት እንዴት ፈቀቅ እንዳለ እናውቃለን (2ጢሞ. 4÷10)፡፡ በዘመናችንም ሰዎች ተድላንና እንደ ዓለም የሆነውን ደስታ ዋጋ ከፍለው እየወደዱ ነው፡፡ የእግዚአብሔርንም ነገር እንዲህ ባለው መንገድ ለመሸፈን እየተሞከረ ነው፡፡ ያንን የቀራንዮ ደስታ ግን የትኛውም የዚህ ዓለም ከንቱ ነገር ሊጋርደው አይችልም፡፡ ጌታን የጋረደብን ማንኛውም ተድላና ደስታ ቢኖር ግን በስሙ ሥልጣን እንዲወገድም መጸለይ ይኖርብናል፡፡   
         እግዚአብሔር ከየትኛውም ነገራችን በላይ እንድንወደው ይጠይቀናል (ዮሐ. 21÷15)፡፡ እርሱ በእኩል ፍቅር ከሌሎች ጋር የምንወደውና የምናመልከው አምላክ አይደለም፡፡ ነፍስን እስከ መስጠት ደግሞም እስከ መስቀል ሞት ታዝዞ የወደደንን ጌታ በሚበልጥ ፍቅር እንድንወደው ጸጋ ይብዛልን፡፡
መፍትሔ፡ - በአብዛኛው የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል ተብሎ ስለ ተነገረባቸው የአፍ አማኞች ጠባይ ለመዘርዘር ሞክረናል፡፡ አሁን ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ ለእውነተኛ ምዕመናን ያስቀመጠውን መፍትሔ እናያለን፡፡
ሀ. ቃሉ፡ - የእግዚአብሔር ቃል ጥሩ መንሽ ነው፡፡ እውነቱን ከሐሰት፣ ቅዱሱን ከርኩሰት፣ ጽድቁን ከኃጢአት አጥርተን እንድንለይ ይረዳናል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ መደናገርና ለስሕተት አሠራር መመቸት የሚመጣው ቃሉን በሙላት ባለመረዳት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መፍትሔው ቃሉን ዕለት ዕለት መመርመር ነው (ሐዋ. 17÷10)፡፡ ይህ ከሆነ ኃይለኛ እንጂ መልከኛ በሆነ አምልኮ ውስጥ አንወድቅም፡፡
ለ. እውነቱን መከተል፡ - ሰዎች እውነትን መረዳት ብቻ ሳይሆን የተረዱትንም እውነት መከተል ይቸግራቸዋል፡፡ ጌታ የሚወደኝ ቢኖር ይከተለኝ ሲል በእውነተኛነቴ የተስማማ ቢኖር ይከተለኝ ማለቱ ነው፡፡ ለተረዳነው የእግዚአብሔር ቃል ምላሽ የምንሰጠው እውነቱን በመከተልና በቃል ብቻ ሳይሆን በሥራ ላይም በማዋል ነው፡፡
ሐ. መራቅ፡ - መራቅን በትንሹ በሁለት መንገድ ልናየው እንችላለን፡፡ የልብና የአካል በሚል! ሁለቱም ችግሩ በሚጠይቀው መጠን አስፈላጊ ናቸው፡፡ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዓመፅ ይራቅ” (2ጢሞ. 2÷19) የሚለው ማኅተም ያለበት የተደላደለ የእግዚአብሔር መሠረት እስካለ ድረስ ክርስትናን በእውነተኛ ኑሮ መግለጥ ለሚፈልጉ ሁሉ ጠንካራ ትዕዛዝ ነው፡፡ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን የክርስትና ኑሮአችንን የሚያጠፋው ከሆነ ጊዜ መስጠት ለቀብር መሰናዳት ነው፡፡ ማስተዋል ይብዛላችሁ!
            

Tuesday, October 23, 2012

መልከኞቹ (ካለፈው የቀጠለ)

                                                    ማክሰኞ ጥቅምት 13/2005 የምሕረት ዓመት 

“እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፡፡ ዳሩ ግን የሚያስጸይፉና የማይታዘዙ ለበጎ ሥራም ሁሉ የማይበቁ ስለ ሆኑ በሥራቸው ይክዱታል” (ቲቶ. 1÷17)፡፡
          ባለፈው ንባብ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የእምነት ልጁ ለሚሆን ጢሞቴዎስ የአምልኮት መልክ ካላቸው ነገር ግን ኃይሉን ከካዱት ሰዎች እንዲርቅ የመከረበትን ክፍል መነሻ አድርገን መንፈስ ቅዱስ ለልባችን ያለውን የልቡን ምክር ለማየት ሞክረናል፡፡ እንደ ተናገሩ አለመኖርና ያመኑበትን በተግባር ምስክርነት አለማጽናት የክርስትናው ፈተና ብቻ አይደለም፡፡ አላመኑም ብለን በምንፈርጃቸው ከክርስትናው ጥሪ ተካፋይ ባልሆኑ ወገኖች ዘንድም ብርቱ ችግር ነው፡፡ ማኅበራዊ ኑሮአችን ላይም መራርነት የሚሞጅርበት እንዲህ ያለው ነገር ነው፡፡ በንግግራቸው ውስጥ መስማማት ያስተዋልንባቸው ሰዎች በተግባር ግን ሲጣሉ ተመልክተናል፡፡ ምክንያቱም በተግባር መገለጥ በቃል ከማብራራት በብዙ ከፍ ያለ ስለ ሆነ ነው፡፡
          ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ቀርቶ ሰው ከሰው በሚኖረው አብሮነት ውስጥ እንኳን መልከኛ እንጂ ኃይለኛ (የተግባር ሰው) አለመሆን ጉዳቱ የከፋ ነው፡፡ ብዙ ቤተሰባዊነት፣ ጓደኝነት፣ ወዳጅነት፣ ትዳርና ማኅበራዊነት በመልከኝነት በሽታ የተጠቁ ናቸው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ልክ በጢሞቴዎስ ዙሪያ እንደነበረው ሁሉ የሐሰተኞች ትምህርት መበራከት ነው፡፡ ሐዋርያው ይህንን መልእክት እንዲልክ ግድ ያለው በጊዜው የነበሩ የስህተት አስተማሪዎች ምእመናኑ ክርስትናን በኃይሉ (በትንሣኤው) ከመኖር ይልቅ በመልኩ (ማስመሰል) ወደ መኖር ዝቅታ እንዲመለሱ ተጽእኖ ያደርጉ ስለነበር ነው፡፡
          እንደ እውነተኛ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሐዋርያው ያሳይ የነበረው ትጋት በእጅጉ የተገባ ነበር፡፡ በእውነት ላይ ከፍ ከፍ የሚል የትኛውንም የስህተት ትምህርትና የሥጋ ትምክህት በእግዚአብሔር አሳብ መቃወም ቅዱስ ተጋድሎ ነው፡፡ በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህንን እወቅ የሚለው አሳብ የእግዚአብሔር ሰዎች እያንዳንዱን ዘመን መዋጀት እንዳለባቸው የሚያነቃቃ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የአምልኮት መልክ እንዳላቸው ነገር ግን ኃይሉን እንደካዱ የሚነግረን ሃይማኖተኞች ጠባይ በጥቂቱ ሲቃኝ፡ -  
1. ራስ ወዳድነት፡ - መወደድና መውደድ በሰው ታሪክ ውስጥ ቋሚ ተግባር ነው፡፡ የማኅበራዊነት ማጣፈጫው ቅመምም ይህ በፍቅር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ራስ ወዳድነት አሉታዊ ጎኑ ብቻ ሲጠቀስ እናስተውላለን፡፡ ነገር ግን ራስን መውደድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተነቀፈው ባልንጀራችንን በዚያው ልክ ካልወደድን ነው (ማር. 12÷31)፡፡ ከዚህም ባለፈ ሰው ራሱን ካልወደደ ከክፉ እንዴት መራቅ ይችላል?
             ክርስትና በክርስቶስ ወንድማማቾች የሆኑ ልዩ ልዩ ወገኖች ሕብረት ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ የተወሰደብን መብት አለ፡፡ ያውም እውነተኛ ክርስቲያን የሆነ አንድ ሰውን “ወንድሜ አይደለህም” ማለት አለመቻል ነው፡፡ በሥጋ ከአባችን የተወለደ ወንድማችንን ወንድሜ አይደለህም ማለት በሕግም በሕሊናም አግባብ እንደማይሆነው ማለት ነው፡፡ ራስ ወዳድነት እኛን በምንወድድበት ልክ ሌላውን መውደድ አለመቻል፣ እኛን የሚያስፈልገን ነገር ሌላውንም እንደሚያስፈልገው አለማሰብ ነው፡፡
2. ገንዘብን ወዳድነት፡ - በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የክፋት ሁሉ ስር የሚለውን ስፍራ የያዘው ገንዘብን መውደድ ነው (1 ጢሞ. 6÷10)፡፡ ጌታ በትምህርቱ አንድ ሰው ለሁለት ጌቶች መገዛት እንደማይችልና ወይ አንዱን መውደድና ሌላውን መጥላት አልያም አንዱን ንቆ ሌላውን መጠጋት እንዳለበት አስረድቶአል (ማቴ. 6÷24)፡፡ ስለዚህም ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም! በማለት ይደመድማል፡፡ ብዙዎቻችን ከእግዚአብሔር ሌላ የዚህ ዓለም ገዥ የሆነውን ዲያብሎስ ብቻ ነው የምናውቀው፡፡ ዳሩ ግን ቃሉ ገንዘብንም እንደ ሌላ ጌታ ያቀርብልናል፡፡ ጌታ የምንገዛለት አካል ነው፡፡ ገዢ ደግሞ በሙሉ ነገራችን ላይ አዛዥ ነው፡፡
            ለአንድ ክርስቲያን ገንዘብ በአግባቡ ጥቅም ላይ የሚያውለው ምድራዊ ነገር ነው፡፡ የሚያስተዳድረው እንጂ የሚተዳደርለት፣ የሚገዛው እንጂ የሚገዛለት ሊሆን ግን አይገባም፡፡ ገንዘባቸው የሚመራቸውን ሰዎች ማሰብ የምድሪቱን መከራ የማሰብ ያህል ነው፡፡ በምድራችን ላይ ከሚሠራው ከየትኛውም አመጽ ጀርባ ያለው ደጀን ገንዘብ ስለሆነ፡፡ (መልካሙን ለማድረግ የሚተጉ እንዳሉ ሆነው) ገንዘብን መውደድ የሚለው አሳብ ገንዘብን ወደ መጥላት መፍትሔ ባያደርሰንም የክፋት ስር የሚሆንበትን ሁኔታ በማስተዋል የሕይወታችንን ጌታ በገንዘባችንም ላይ ጌታ እንድናደርገው ያስገነዝበናል፡፡  
3. ትምክህትና ትዕቢት፡ - ባላቸው ነገር የሚመኩ ሰዎች እንደ አገልጋይ ያሳዝኑናል፡፡ ምክንያቱም ዓለምና ሞላዋ የእነርሱ ብትሆን እንኳ አንድ ቀን (በእግዚአብሔር የትግበራ ጊዜ) እንደ መጎናፀፊያ ልትጠቀለል የተፈረደባት በመሆኑ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንኳን ኃጢአት የሆነውን የዚህ ዓለም ነገር ቀርቶ ጽድቃችን የምንለውን የእኛን ትምክህት የዘጋው የመርገም ጨርቅ ብሎ ነው፡፡ ሰው ይመካ ዘንድ ለሰው የተተወ አንዳች ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ የለም፡፡ እግዚአብሔር የማንም ባለ ዕዳ ስላይደለ የሚመካ ቢኖር በእግዚአብሔር ይመካ!
            በየዘመናቱ የእግዚአብሔር ቅጣት ፍጥነትና ኃይል ከተገለጠባቸው ነገሮች አንዱ ትዕቢት ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ትምክህትና ትዕቢት ልክ እንደ ጨው ይዋዋሳሉ፡፡ የብዙ ጎበዞች ውድቀት መጀመሪያው ትዕቢት ነው፡፡ ትዕቢት ሌላውን አሳንሶ ራስን ኮፍሶ መኖር ነው፡፡ ታዲያ የእግዚአብሔር ክንድ በየጊዜው እንዲህ ያለውን ክምር ሲንድ ነው የኖረው፡፡ ትዕቢት ራስን ላለመግዛት ትልቅ አርነት ነው፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረውን አሳብ ልብ ካልነው “ትህትና” የሚል ነው (ፊል. 2÷5)፡፡ ትዕቢት የእግዚአብሔር ልጅ ራሱን ባዶ ባደረገበት በዚህ አሳብ ፊት እንዴት የሚብስ ቅጣት ይቀበል ዘንድ ይገባዋል?   
4. ሐሜትና ስድብ፡ - “ለቀብር የሄዱ ሰዎች አስከሬን ቀርቶባቸው “በሕይወትም እያለ አርፋጅ ነበር፡፡ ዛሬ እንኳ ምናለ በሰዓቱ ቢገኝ?” እየተባባሉ ያሙታል፡፡ ታዲያ ገና ሳይጨርሱ በለቀስኛ ታጅቦ ይደርሳል፡፡ እነዚያው ያሙት ሰዎች “ውይ እድሜው ረጅም ነው፡፡ ስናነሳው መጣ” ተባብለው በውሸት እንባ እውነተኞቹን ተቀላቀሉ፡፡” የሚል ታሪክ ባልንጀራዬ አጫውቶኛል፡፡ የሞተን ሰው እድሜው ረጅም ነው! ያሰኛቸው የሐሜት አመል ነው፡፡ ለብዙዎች ሐሜትና ስድብ ፈቃድ ያላቸው ኃጢአቶች እንደሆኑ ይሰማቸዋል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በዚህ ላይ ምንም አይነት ቅራኔ እንደሌለው ስለሚያስቡ ነው፡፡
            አሉ አሉ! የብዙ ሰዎችን ኑሮና ትዳር አናግቷል፡፡ ቡና አፍልተው ማማትም ማሳማትም የማለዳ ተግባራቸው የሆነ ሰዎችንም እናውቃለን፡፡ እድሜው ይጠር እያሉ ተብዬው ሲደርስ እድሜህ ረጅም ነው የሚሉ ሸንጋዮች ብዙ ናቸው፡፡ ስድብንም ስናይ ከሰዎች ክፉ ንግግር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሁለቱም በአፍ መበደል ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ስለ ስድብ ብርቱ ትምህርትን ይሰጠናል፡፡ “የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያቢሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲከራከር፡- ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም” (ይሁዳ 9) ተብሎ ተጽፏል፡፡ እውነተኛ አማኝ ለአፉ ጠባቂ አለው፡፡     
5. አለመታዘዝ፡ - መታዘዝ ከመሥዋዕት እግዚአብሐርን ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል (1 ሳሙ. 15÷22)፡፡  ቅዱስ ጳውሎስ መታዘዝን እዚህ ቦታ ላይ ያቀረበው ከወላጆች ጋር በማያያዝ ነው፡፡ ቃሉ እግዚአብሔር የሕፃንነታችን ወዳጅ እንደሆነ ቢናገርም ተግባራዊ በሆነ ሁኔታ እኛ ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት ከማድረጋችን በፊት ከወላጆቻችን ጋር ያለን ግንኙነት ይቀድማል፡፡ መንፈሳዊውን ልደት (ዳግም መወለድ) የሥጋ ልደት ይቀድመዋልና፡፡ ለወላጆች መታዘዝ አምላካዊ መመሪያ ያለው ትዕዛዝ ነው፡፡ የምናያቸውን የሥጋ ወላጆች መታዘዝን ካልተማርን የማናየውን የመንፈስ ወላጅ እግዚአብሔርን እንዴት እንታዘዘው ዘንድ ይቻለናል?
         ልጆች እውነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ወላጆቻቸውን መታዘዝ ይኖርባቸዋል፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል በሚቃወምና መመሪያውን በሚጥስ መልኩ ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲታዘዙ አግባብ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ስለ ስሜ ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል (ማቴ. 19÷29) የሚለው የጌታ ቃል የታመነ ነው፡፡ (በዚህ ብሎግ “እሺታ ያለ ቦታው” የሚለውን ርዕስ እንድታነቡት እንጋብዛለን)!
                                                                - ይቀጥላል - 

Wednesday, October 17, 2012

መልከኞቹ

                                        ማክሰኞ ጥቅምት 6/2005 የምሕረት ዓመት

       
“የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ፡፡ (2 ጢሞ. 3÷5)”
           
         በአንድ አጋጣሚ ከባልንጀራዬ ጋር የተገኘሁበት ቤት ውስጥ ያየኋቸው ስድስት ልጆች ትዝ ይሉኛል፡፡ ታዲያ የልጆቹ ውበት ልዩ ነው፡፡ አንዱን አይታችሁ ወደ ሌላዋ ስትዞሩ የባሰ እንጂ ያነሰ ቁንጅና አታዩም፡፡ እኛ በዚያ ቤት ውስጥ በተቀመጥንበት ትንሽ ሰዓት የመጡ ሁሉ ሰዎች ለአባትየው ስለ ልጆቻቸው ቁንጅና ሳይናገሩ አይወጡም፡፡ ስለ ትልቁ ልጃቸው ግርማ ሞገስ፣ ስለ ተከታይዋ ሸንቃጥነት፣ ስለ ትንሹ ልጃቸው ቅላት ብቻ አንዱ ከሌላው አፍ እየነጠቀ የልቡን አድናቆት ይገልጣል፡፡
            አባት ስለ ልጆቻቸው የተባለውን ሁሉ ከሰሙ በኋላ “ልክ ናችሁ ልጆቼ መልከኛ ናቸው፡፡ ነገር ግን ኃይለኛ አይደሉም” ብለው ከአንገታቸው አቀረቀሩ፡፡ ለረጅም ሰዓት ቤቱን ዝምታ ወረሰው፡፡ እኛም በዚህ ተሸኘን፡፡ እንደወጣን ለባልንጀራዬ “ለማለት የፈለጉት ገብቶሃል?” ስል ጠየኩት፡፡ እርሱም “ሁለተኛ ጢሞቴዎስ ሦስተኛው ምእራፍ ነው” አለኝ፡፡
         የሰዎች ልብ ከሚሸነፍበት ነገር አንዱ ውበት ነው፡፡ የሌላቸው ለማምጣት ያላቸው ደግሞ ለመጠበቅ ዋጋ የሚከፍሉበትም የኑሮ ክፍል ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከውስጥ ይልቅ ለውጪያዊ ውበትና መልክ ሰዎች ሲንበረከኩ፣ እራሳቸውንም በሚፈልጉት የውበት ደረጃ ላይ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ዓለም በዚህ መንገድ በትጋት ብዙ ምስጉን ሰዎች አሏት፡፡ የማያስነቅፍ ደምግባት፣ የማያስነቅፍ ቁመት፣ የማያስነቅፍ ቅርጽ በብዙዎች ላይ ይታያል፡፡ የዚህም ስስት የያዛቸው በዝተዋል፡፡ ትልቁ ጥያቄ ግን የማያስነቅፍ ኑሮ ምን ያህል ሰዎች ላይ ይስተዋላል? የሚለው ነው፡፡
            ከላይ ቤተሰባቸውን እንደ መግቢያ የተጠቀምንበት አባወራ የተናገሩት ከመልክ ጋር ከተያያዘው ነገር ይልቅ ከኃይል ጋር የተያያዘው እንደሚበልጥ ነው፡፡ በእርግጥም ኃይልን ስናስብ ብዙ ነገሮች ወደ አእምሮአችን ይመጣሉ፡፡ ኃይል የብዙ ክንውኖች መሰረት ነው፡፡ ኃይል ሕልውናም ጭምር ነው፡፡ አለ! የምንለው ሰው መኖር የሚጠይቀውን መሰረታዊ ኃይል ያሟላ ነው፡፡ ሰው ብዙ ነገሮችን የሚከውነው በመልኩ አይደለም፡፡ መልካችንን ተከትሎ የሚሳብ ይኖር ይሆናል፡፡ መልክ ውስጥ ግን ኃይል የለም፡፡
            ሕሊና እንጂ መልክ አያስብም፡፡ አንደበት እንጂ መልክ አይናገርም፡፡ መልካምነት እንጂ መልክ ከሰው አያኖርም፡፡ ስነ ምግባር እንጂ መልክ አያስከብርም፡፡ እምነትና ፍቅር እንጂ መልክ ሞትን አያሻግርም፡፡ መልክ የላይ ማንነትን እንጂ የውስጥ ሰብእናን አይገልጥም፡፡ ፊት ቀልቶ ውስጥ ሊጠቁር፣ ውጪ አጊጦ ልብ ሊቆሽሽ ይችላል፡፡ ምድራችን የመልከኞች ሆናለች፡፡ ማስመሰል ቀላሉ የኑሮ ዘይቤ ተደርጎ እየተቆጠረ ነው፡፡ ገጣሚው፡ -
አርሜ ኮትኩቼ የሎሚ ዘንጓን
መልከኛ ወሰዳት ወይ ገባር መሆን፡፡ እንዳለ . . .
            ድካሙና ኃይሉ ያለው አራሚ ኮትኳቹ ጋር ነው፡፡ ሴቲቱ የተሸነፈችው ግን ለመልከኛው ነው፡፡ በመፍጠርና በማዳን ዋጋ የከፈለብን እግዚአብሔር ነው፡፡ የተወደደው ልጁ እስከ መስቀል ሞት በመታዘዝ ለመዳናችን መከራን ተቀብሏል፡፡ ዛሬም በቃሉ በኩል የሚረባንን ወደ ሕይወታችን ለማድረስ በመንፈሱ በኩል ይተጋልናል፡፡ ብዙዎች ግን የመልከኛዋ ዓለም ሆነዋል፡፡ በፍቅር ኃይለኛ፣ በማዳን ኃይለኛ፣ በምሕረት ኃይለኛ፣ በፍርዱ ኃይለኛ የሆነው እግዚአብሔር ወደ ጎን ተትቶ ሰዎች በፊታቸው መልካም መስሎ የታያቸውን ሁሉ በትጋት እያደረጉ ነው፡፡
             ዓለም የሆኑ ሳይሆን እንደሆኑ መስለው የሚታዩ የሚፋንኑባት አደባባይ ናት፡፡ ከፍቅር ይልቅ ፍቅር ለሚመስል፣ ከሰላም ይልቅ ሰላም ለሚመስል፣ ከእውነት ይልቅ እውነት ለሚመስል፣ ከኃይል ይልቅ ኃይል ለሚመስል መልክ ምድሪቱ ተገዝታለች፡፡ ያለ ጭንብል መኖር የማንችለውም ለዚሁ ነው፡፡ መልክ እንጂ ኃይል፣ ቅብ እንጂ የጨከነ እውነት፣ የምድሩ እንጂ የሰማዩ አያስደስተንም፡፡ የክርስትና ውድቀት ትልቁ ልኬት ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡     
            ክርስትና በመልኩ ሳይሆን የተብራራው በኃይሉ (በተግባሩ) ነው፡፡ ያውም የትንሣኤው ኃይል! (ፊል. 3÷10)፡፡ “ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው” ተብሎ እንደተፃፈ አውርተን እንኳን ያልዘለቅነውን ዓለም የምናሸንፍበት፣ ከክፋትና ከርኩሰቱ የምናመልጥበት ኃይል ያለው እምነታችን ውስጥ ነው፡፡ ይህም እምነት በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ መልከኛ ክርስትና ግን የሚመስል እንጂ የሆነ ነገር አይታይበትም፡፡ ውጫዊ ገጽታው ያመነ ውስጡ ግን የካደ ነው፡፡ በቃል ብዙ ጥበብ በኑሮ ብዙ ስንፍናን ይገልጣል፡፡ መሳይ ክርስቲያኖች!
           ምላስ ረዝሞ እጅ ከተሰበሰበ፣ የምናወራው እግዚአብሔር እንጂ የምንኖረው እግዚአብሔር ከሌለ፣ የምናቅደው እንጂ የምንተገብረው መልካም ካነሰ መልከኞች እኛ ነን፡፡ በእውነትና በመንፈስ ስለማምለክ ተረድተን እንደ ፈቃዳችን ካመለክን፣ በመንፈስ ጀምረን በሥጋ ከጨረስን፣ ከእግዚአብሔር የልቡ ምክር አፈንግጠን ለዚህ ዓለም ከንቱ መለፍለፍና በብልሃት ለተፈጠረ ተረት ከተገዛን በእርግጥም መልከኞቹ እኛ ነን፡፡ ተራቁተን እንደለበስን፣ ደህይተን እንደበለፀግን፣ ታውረን እንደተኳልን፣ አንሶን እንደተረፈን ከተሰማን ተወዳጆች ሆይ መልከኞች እንጂ ኃይለኞች አይደለንም፡፡ “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ እራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ” (ያዕ. 1÷23) ተብሎ እንደተፃፈ ተግባራዊ የሆነ መንፈሳዊ ኑሮ ሊታይብን አግባብ ነው፡፡
           አንድ ሰው በሠራው ቤት ውስጥ የሚሰቅለው የእራሱን ፎቶ ነው፡፡ መታየት ያለበትም ባለ ቤቱ (የቤቱ ጌታ) ነው፡፡ እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደሶች (1 ቆሮ. 3÷16) እንደመሆናችን በቤቱ ውስጥ መታየት እንዲሁም በሙላት ማዘዝ ያለበት የቤቱ ሠሪና ጌታ የሆነው እግዚአብሔር ነው፡፡ በእምነት ጉዞም ሆነ በአገልግሎት እንደ እግዚአብሔር ቃል መሆን ያለበት ከዚህ የተለየ አይሆንም፡፡ ነገር ግን ጌታ እንደሆነ እየተናገርን በቤቱ ላይ ግን እኛ ካዘዝን፣ አፍአዊ በሆነ መንገድ ስለ እርሱ አብዝተን እየመሰከርን በተግባር ግን እራሳችንን የምንገልጥ ከሆነ መልከኝነት እንደተጠናወተን ኃይሉ ግን እንደራቀን ማሳያ ነው፡፡ ምሕረቱን ያብዛልን!
           አምልኮ አምላክነት ላለው አካል የሚደረግ መረዛት ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር ያለ ሕያው አምላክ ስለሌለ ሁለንተናዊ መገዛት ለእርሱ እናሳይ ዘንድ የተወደደ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምልኮ የግል ገንዘቡ ስለሆነ ለማንም አያጋራውም (ዘፀ. 20÷1)፡፡ በዚህ መንገድ የሚተካከለው፣ ጎን ለጎን አልያም ተክቶት ይህንን ክብር የሚወስድ ሌላ ማንም ሊኖር አይችልም (ኢሳ. 42÷8)፡፡ ለዘመናችን ትልቁ ፈተና ግን ለእግዚአብሔር ብቻ አለመገዛት ነው፡፡ ስለዚህም ጎን ለጎን የምንገዛላቸው ከውስጥም ይሁን ከውጪ ምንጫቸውን ያደረጉ ብዙ ደባሎች አሉ፡፡ ይህ የእግዚአብሔርን ኃይል ተግባራዊ በሆነ መንገድ መካድ ነው፡፡
           እግዚአብሔር ሰዎች እንዴት እንደሚከተሉትና እንደሚያመልኩት በቃሉ ውስጥ ግልጽ መመሪያ አለው፡፡ መልከኝነት ከዚህ አሳብ ማነስ አልያም በዚህ ላይ መጨመር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኃይል አልባ ሞቅታ ነው፡፡ በእምነት ስንኖር እራሳችንን እንድንመረምር ቃሉ ስለሚያዝ ኑሮ መፈተሸ አለበት፡፡ ዛሬ ዓለም በክርስትናው ተጽእኖ ስር መሆንዋ ቀርቶ ክርስቲያኖች በዓለም ተጽእኖ ስር ወድቀዋል፡፡ እንደ ጨው ማጣፈጫ መሆን ቀርቶ አጣፍጡኝ አይነት አልጫ ሆኗል፡፡
           በብዙ ጨለማዎች ፊት ብርሃን መሆን አልተቻለም፡፡ አልቅሰው መጥተው አልቅሰው የሚመለሱ፣ በጉድለት መጥተው በጉድለት የሚሸኙ፣ ከእነርሱ መንፈሳዊነት የእኔ ዓለማዊነት ይሻላል የሚሉ በዝተዋል፡፡ ክርስትናው መፍትሔ መሆኑ ቀርቶ ችግር፣ መልስ መሆኑ ቀርቶ ጥያቄ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለዚህ ብቸኛው ምክንያት ደግሞ መልከኛ እንጂ ኃይል ያለው ክርስትና መዳከሙ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የእምነት ልጁ ጢሞቴዎስን በብርቱ ይመክረዋል፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ የመልከኛ ክርስትና ዋና ዋና ጠባያትንና መፍትሔውን እንመለከታለን፡፡ ጌታ እግዚአብሔር መልከኛ ፍቅር፣ እምነት፣ ይቅርታ፣ ቅድስና፣ ጽድቅ . . . በበዛበት በዚህ ዘመን እንደ እርሱ መንግሥት ልጆች በኃይሉ እንድንገለጥ ጸጋውን ያብዛልን!!
                                                         
                                                         - ይቀጥላል -

Tuesday, October 9, 2012

እግዚአብሔር ሲገልጥ



         “ከዚህም ወራት በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰችና፡፡ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ያስወግድልኝ ዘንድ ጌታ በተመለከተበት ወራት እንዲህ አድርጎልኛል ስትል ራስዋን አምስት ወር ሰወረች” (ሉቃ. 1÷24-25)፡፡        
           እግዚአብሔር የመገለጥ አምላክ ስለሆነ ሰው በራሱ መንገድ ሊያስተውለው ደግሞም ፈልጎ ሊደርስበት አይችልም፡፡ እርሱን የሥጋ ለባሽ ጥረትም ሆነ ግምት አያገኘውም፡፡ ነገር ግን “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው (ዮሐ. 1÷18)” ተብሎ እንደተፃፈ እግዚአብሔር አንድያ ልጁ እንደተረከልን እንዲሁ ነው፡፡ አምላክነቱን እንደፈቃዱ ካላብራራልን “በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው?” ልንለው አንችልም፡፡ እርሱ ፍቅሩን ለልባችን ካልገለጠ አፋችን ስለ ፍቅር ማውራቱ የእግዚአብሔርን ፍቅር ወደ ማስተዋል አያደርሰንም፡፡
            እግዚአብሔር ጽድቁን ካላሳየን ለራሳችን ጽድቅ መሸነፋችን አይቀርም፡፡ እግዚአብሔር የእውነትን ፍቺ በልባችን ላይ ካላበራ በሚያባብል ቃል እየተሸነገልን መኖራችን በግልጥ የሚታይ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ጽድቅና መንግስት የእኛ አቅም የመሻትን ያህል ነው (ማቴ. 6÷33)፡፡ እግዚአብሔር እንደ እግዚአብሔርነቱ እንረዳውና እናምንበት ዘንድ በቃሉ በኩል ራሱን አሳይቶናል፡፡ ከሚያስፈልገን የተሸሸገ፣ ከሚረባን የቀረ ምንም የለም፡፡ ስለዚህም ጌታ ስሙ ብሩክ ይሁን!
            ለዚህ ርእስ መነሻ የሆነን የኤልሳቤጥ ታሪክ ነው፡፡ ባሏ ዘካርያስ የእግዚአብሔር ቤት አገልጋይ  ነበር፡፡ ደግሞም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ እግዚአብሔርን በኑሮአቸው ያከብሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ለብዙ ዘመናት ልጅ አልነበረውም፡፡ እግዚአብሔር እንድናገለግለው ሲጠራን እንደማንቸገርና እንደማይጎድለን ተስፋ አልሰጠንም፡፡ ሁሉን ለእርሱ ክብር እንድናደርገውና በጊዜውም ያለ ጊዜውም እንድንጸና ግን አዝዞናል፡፡ በመከራም ጭምር!
            በብዙ ክርስቲያኖች ዘንድ የእውነተኛ አገልጋይን ኑሮ የመረዳት ችግር ይስተዋላል፡፡ ለዚህም ይመስላል ብዙዎች አገልጋይ የሚያጽናና እንጂ የሚጽናና፣ የሚያስተምር እንጂ የሚማር፣ የሚያሳርፍ እንጂ የሚራብ የማይመስላቸው፡፡ ነገር ግን ሐዋርያው እንዳለ “አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል” (ፊል. 4÷19) የሚለው የተስፋ ቃል በየትኛውም ሁኔታና ዘመን በእውነትና በመንፈስ ለሚያገለግሉት ሁሉ የታመነ ነው፡፡ ለአገልግሎቱ ታማኝ አድርጎ የቆጠራቸው ሁሉ በዚህ ደስ ይላቸዋል፡፡
            ካህኑ ዘካርያስ እያገለገለ ጥያቄ ነበረው፡፡ በመቅደሱ እየተመላለሰ ያጣው ነገር ነበረ፡፡ እግዚአብሔርን የሚያገለግሉት ጥያቄያቸው ሁሉ የተመለሰላቸው፣ ጉድለታቸው ሁሉ የሞላላቸው፣ ሩጫቸው ሁሉ የተሳካላቸው አይደሉም፡፡ አገልግሎት ማጣት እያለ የበጎ ስጦታና የፍጹም በረከት ባለቤት የሆነውን፣ አለመመቸት ከብቦን አእምሮን የሚያልፍ ሰላም ባለቤት የሆነውን፣ ሀዘን ኑሮአችን ላይ አጥልቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የተባለለትን፣ ጠላት ተሰልፎብን የምወደው ልጄ ይህ ነው የተባለውን ጌታ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ በመታዘዝ ታማኝነት የመጽናት ትጋት ነው፡፡ ዘካርያስ የእድሜው መግፋት፣ የሚስቱ ምክነት በአገልግሎት ጌታ ፊት እንዳይቆም አላደረገውም፡፡ እኛ ከዚህ ላነሱ ምክንያቶች ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት ብናበላሽ ይህ የጥላ አገልግሎት ብቻውን ይወቅሰናል፡፡
            በብሉይ ኪዳን ለአንዲት ሴት መውለድ አለመቻል የሚያስነቅፍና የሚያገልል ጉዳይ ነበር፡፡ ከሌሎች የሚመጣውን ንቀት፣ ከውስጥ የሚሰማን የበታችነት ስሜት መጋፈጥን የሚጠይቅ ተግዳሮትም ነበር፡፡ የሕልቃና ሚስት ሐና ማኅፀንዋ ዝግ በነበረበት ዓመት ሁሉ ነቀፌታዋን ተሸክማ ጣውንቷ እያሽሟጠጠቻት ካህኑ ዔሊ እንደ ሰካራም እስኪቆጥራት ድረስ በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ታነባ እንደነበር ቃሉ ይነግረናል (1ሳሙ. 1÷7)፡፡ በዚያ ዘመን መውለድ አለመቻል የኃጢአትን ያህል ተቆጥሮ ነቀፌታ መሸከምን ያስከትል ነበር፡፡ ኤልሳቤጥም መውለድ አለመቻል የሚያስከፍለውን ዋጋ ስትከፍል ኖራለች፡፡ እግዚአብሔር እንዲያስባትም በመቅደሱ በፀሎትና በምልጃ ትተጋ ነበር፡፡
            እግዚአብሔር አብርሃም ልጅ ሳይኖረው የዘጠና ዘጠኝ ዓመት አዛውንት ሳለ እኔ ኤልሻዳይ ነኝ በፊቴ ተመላለስ (ዘፍ. 17÷1) አለው፡፡ ከእግዚአብሔር ስሞች መካከል አንዱ ኤልሻዳይ የሚለው ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱን ኤልሻዳይ ብሎ ያቀረበው ከአብርሃም ሁኔታ አንፃር ነው፡፡ አብርሃም ከዚህ በኋላ መውለድ አልችልም ብሎ ተስፋው የተሟጠጠበት፣ ልቡ የዛለበት ጊዜ ስለነበር እግዚአብሔር እኔ ሁሉን እችላለሁ! በሚል አለመቻሉን በተስፋ ሞላው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ስሞቹን የተጠቀመው ከሁኔታው አንፃር ነው፡፡
           እግዚአብሔር ሁሉን እንደሚችል ስናምንበት በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነን ያለ መጨነቅ በፊቱ መመላለስ ይሆንልናል፡፡ በኃይልም በፍቅርም ብርቱ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ይህም ብርታት ሌላ ተቀራራቢ ብርታት የለውም፡፡ ለመታሰብ በሚከብዱ ነገሮች ላይ እንኳ እግዚአብሔር ተግባራዊ ነው፡፡ እንዳልቻልነው በተሰማን ሥራ አንድ ሰው አይዞህ እኔ እወጣዋለሁ ቢለን ምን ያህል ያሳርፋል? ሰው እንዲህ ካስመካ እግዚአብሔር ምን ያህል ልባችንን እንጥልበት ዘንድ የተገባ ነው፡፡
          እግዚአብሔር የምክነትን ወራት አሳልፎ በልጅ በረከት የተነቀፉትን አፍ በእልልታ ይሞላል፡፡ በሕይወት ውስጥ ላሉ ልዩ ልዩ ምክነቶት (ፍቅር እየቀዘቀዘ ነው፣ መተማመን አላፊ እየሆነ ነው፣  ሥነ ምግባር እንደ ኋላቀርነት እየተቆጠረ ነው) መፍትሔው ኤልሻዳዩ ጌታ ነው፡፡ ዛሬም ብዙ ሙከራ፣ ብዙ መጠበብ ምድሪቱን አላስተካከላትም፡፡ አሁን እንኳን በዚህ ሰዓት ብዙ ነገሮች እየተሞከሩ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ባልቻልነውና ባቃተን ነገር ላይ ሁሉ ኤልሻዳይ ነው፡፡ የዕብራይስጥ ትርጉም አዋቂዎች የዚህን ስም ትርጉም ከእናት ጡት ማጥባት ጋር አያይዘው ያብራሩታል፡፡ እንደውም እግዚአብሔር ራሱን እንደ እናት ያቀረበበት መንገድ እንደሆነም ይጠቀሳል፡፡ ለአንድ ልጅ የጡት ወተት እናቱ ውስጥ የተሸሸገ በረከቱ ነው፡፡ ነገር ግን ምድራዊ እናቶቻችን ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ጡት ማጥባት ያቆማሉ፡፡ ልጁም ወደ ማደግ ከፍታ ሲመጣ ይተወዋል፡፡ የእግዚአብሔር መጋቢነት ግን ለዘላለም ነው፡፡ የትኛውም የእድገት ደረጃ ተመጋቢነታችንን አያቋርጠውም፡፡
          አብርሃምን በይስሐቅ፣ መካኒቱን ሐና በሰባት ልጅ ደስ ያሰኘ ጌታ ኤልቤጥንም አሰባት፡፡ የመታሰብ ወራት መጣ፡፡ እንባን ከአይኗ፣ ነቀፌታን ከልቧ ላይ አበሰ፡፡ እግዚአብሔር አስታዋሽ አምላክ ነው፡፡ ስለራሳችን ጉዳይ በረሳንበት ወራት እርሱ ግን ያለፈ ልመናችንን ቸል አላለም፡፡ የካህን ሚስት ለነበረችው ኤልሳቤጥ መውለድ አለመቻል ቀላል ነገር አልነበረም፡፡ ነቀፌታን ያሸክማል! ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ አይደሉምን?
         ኤልሳቤጥ ታሪኳ ሲለወጥ፣ ነቀፌታዋ ሲንከባለል፣ በሁሉን ቻዩ ስትታሰብ ይህንን ባደረገላት ጌታ ፊት አምስት ወር ራስዋል ሰወረች፡፡ እግዚአብሔር ስላደረገላት ነገር ለመደነቅ ይህም ትንሽ ነው፡፡ የሞተውን ህይወት ዘርቶበት፣ የደረቀውን አለምልሞት፣ የተተወውን ወደ ሕልውና አምጥቶት እርሱ ያልተደነቀ ማን ይደነቃል? እግዚአብሔር ግን ከምንልለት ከዚህም ያልፋል፡፡
         ኤልሳቤት የሚያሳፍር ሳይሆን የሚያስመካ፣ የሚሸሸግ ሳይሆን የሚገለጥ ነገር በሆዷ ተሸክማ ለሰው በማይታይ ለእግዚአብሔር ግልጥ በሆነ መንገድ በምስጋና እየተጋች ራስዋን ሰውራ ነበር፡፡ ዘመናችንን ስናየው በዓለምም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ሁሉም ለመታየት የሚጥርበት፣ ማማው ላይ ለመቀመጥ የሚጋደልበት ነው፡፡ ሰዎች ከዓላማቸው ይልቅ ስለ ራሳቸው በማውራት፣ በተግባር ከመታየት ይልቅ በሰው ለመታየት ጥረት በማድረግ ተጠምደዋል፡፡ እንኳ ለሌሎች የሚተርፈውን ለራሳቸው የማይበቃውንም ጨማምረው ለታይታ ያቀርቡታል፡፡
         ስለ ጌታ ብዙ ጊዜ እንዳይገልጡት አዘዛቸው (ማቴ. 12÷15፣ ማር. 3÷12) ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ኢየሱስን ያህል ንፁሕ ጌታ (ለሁሉ ሊሞት የመጣ አንድ መፍትሔ) ወደ እርሱ የመጡትን ሁሉ ፈውሶ ዳሩ ግን አትግለጡኝ ይል ነበር፡፡ ከሥራቸው ስንጠቀም ኖረን ከሞቱ በኋላ አልያም ግድ ሲሆን የተገለጡ መልካም ሰዎች አሉ፡፡ ሳይታወቁ ብዙ ጠቅመው ሰው ገልጦአቸው አድንቀን ሳንጨርስ የሞቱም አሉ፡፡ በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ውድቀት የሚጀምርበትን ነጥብ አስተውለነው ከሆነ መሰማራት ሲገባን የተሰበሰብንበት፣ መገለጥ ሲገባን ያንቀላፋንበት ደግሞ መደበቅ ሲገብን የተገላለጥንበት፣ መጸለይ ሲገባን አደባባይ የፎከርንበት ያ ሰዓት ነው፡፡ ብዙዎች በዚህ ኪሳራ ውስጥ ሲያልፉ አይተናል፡፡ ያለነው ካለፉት ካልተማርን የረገጡትን መርገጥ፣ ያጨዱትን ማጨድ አይቀርም፡፡
        “ጌታ ሆይ እኔ ልሰወር አንተ ብቻ ታይ” የሚል የአገልጋይ ጸሎት አውቃለሁ፡፡ እንደ ጸሎቱ ቢሆን ኖሮ አጨብጭቦ የሚያወጣ አጨብጭቦ የሚያወርድ፣ እልል ብሎ የሚያከብር እልል ብሎ ሰቅሎ የሚያዋርድ፣ ወደድኩ ብሎ የሚስም እዚያው ቦታ ላይ ጠላሁ ብሎ የሚነክስ፣ ነፋስን የሚከተል ሕዝብ ባላተረፍን ነበር፡፡ ሰው ሰውን አይቶ ወደ ሌላ ሰው ይገላበጥ ይሆናል፡፡ ሰው ጌታን አይቶ ግን ወዴት ይገላበጣል? የሚያምረው እርሱን ስናሳይ ነው!
         ክርስትና እግዚአብሔርን ማሳየት ነው፡፡ እኛን እግዚአብሔር ከገለጠን መታዘዝ እውነት ነው፡፡ ኤልሳቤጥ እራሷን ሰውራ አምስት ወር ቆየች፡፡ በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል ድንግል ማርያምን ሊያበስራት ሲመጣ “ዘመድሽ ኤልሳቤጥ” ብሎ ገለጣት፡፡ ነቢዩ ዳዊት እንደ እግዚአብሔር ልብ የሆንኩ ብሎ ሲናገር አናነብም፡፡ እግዚአብሔር ግን እንደልቤ የሆነ ዳዊት ብሎ ሲናገር እናያለን (የሐዋ. 13÷22)፡፡ ኢዮብ በምድር ላይ እንደ እኔ ፍጹምና ቅን እግዚአብሔርንም የሚፈራ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም ብሎ ሲናገር አናነብም፡፡ እግዚአብሔር ኢዮብን ሲገልጠው በሰይጣንም ፊት ሲመሰክርለት ግን እናነባለን (ኢዮ. 2÷3)፡፡ ታዲያ ተወዳጆች ሆይ ማን ይግለጠን?
         ሰው ተሰውሮ ክፉ አያድርግ እንጂ መልካምን መሥራት መዝገብን በላይ በሰማይ መሰብሰብ ነው፡፡ ብዙ ሰው በእጁ ያደረገውን አውርቶ በመርካት ዋጋውን ይቀበላል፡፡ የማቴዎስ ስድስት አሳብ እንዲህ ያለውን መገላለጥ አጥብቆ ይኮንነዋል፡፡ እኛ ስለ ራሳችን የምንገልጠው መልካም ልኩ የመርገም ጨርቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከገለጠን ግን በእርሱ ሚዛን ተለክቶአልና እርሱ ጽድቃችን ነው፡፡
         ራሳቸውን ሰውረው ደግሞም ላመኑበት እውነት እስከ ሞት ድረስ ዋጋ ከፍለው ጌታን በቃልና በኑሮ እንዳከበሩት (እንደገለጡት)፣ በሰው መፍትሔ መካከል የእግዚአብሔርን መፍትሔ እንዳሳዩት እውነተኞች እንድንኖር በጥበብና በማስተዋል ጸጋውን ያብዛልን፡፡