Wednesday, October 17, 2012

መልከኞቹ

                                        ማክሰኞ ጥቅምት 6/2005 የምሕረት ዓመት

       
“የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ፡፡ (2 ጢሞ. 3÷5)”
           
         በአንድ አጋጣሚ ከባልንጀራዬ ጋር የተገኘሁበት ቤት ውስጥ ያየኋቸው ስድስት ልጆች ትዝ ይሉኛል፡፡ ታዲያ የልጆቹ ውበት ልዩ ነው፡፡ አንዱን አይታችሁ ወደ ሌላዋ ስትዞሩ የባሰ እንጂ ያነሰ ቁንጅና አታዩም፡፡ እኛ በዚያ ቤት ውስጥ በተቀመጥንበት ትንሽ ሰዓት የመጡ ሁሉ ሰዎች ለአባትየው ስለ ልጆቻቸው ቁንጅና ሳይናገሩ አይወጡም፡፡ ስለ ትልቁ ልጃቸው ግርማ ሞገስ፣ ስለ ተከታይዋ ሸንቃጥነት፣ ስለ ትንሹ ልጃቸው ቅላት ብቻ አንዱ ከሌላው አፍ እየነጠቀ የልቡን አድናቆት ይገልጣል፡፡
            አባት ስለ ልጆቻቸው የተባለውን ሁሉ ከሰሙ በኋላ “ልክ ናችሁ ልጆቼ መልከኛ ናቸው፡፡ ነገር ግን ኃይለኛ አይደሉም” ብለው ከአንገታቸው አቀረቀሩ፡፡ ለረጅም ሰዓት ቤቱን ዝምታ ወረሰው፡፡ እኛም በዚህ ተሸኘን፡፡ እንደወጣን ለባልንጀራዬ “ለማለት የፈለጉት ገብቶሃል?” ስል ጠየኩት፡፡ እርሱም “ሁለተኛ ጢሞቴዎስ ሦስተኛው ምእራፍ ነው” አለኝ፡፡
         የሰዎች ልብ ከሚሸነፍበት ነገር አንዱ ውበት ነው፡፡ የሌላቸው ለማምጣት ያላቸው ደግሞ ለመጠበቅ ዋጋ የሚከፍሉበትም የኑሮ ክፍል ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከውስጥ ይልቅ ለውጪያዊ ውበትና መልክ ሰዎች ሲንበረከኩ፣ እራሳቸውንም በሚፈልጉት የውበት ደረጃ ላይ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ዓለም በዚህ መንገድ በትጋት ብዙ ምስጉን ሰዎች አሏት፡፡ የማያስነቅፍ ደምግባት፣ የማያስነቅፍ ቁመት፣ የማያስነቅፍ ቅርጽ በብዙዎች ላይ ይታያል፡፡ የዚህም ስስት የያዛቸው በዝተዋል፡፡ ትልቁ ጥያቄ ግን የማያስነቅፍ ኑሮ ምን ያህል ሰዎች ላይ ይስተዋላል? የሚለው ነው፡፡
            ከላይ ቤተሰባቸውን እንደ መግቢያ የተጠቀምንበት አባወራ የተናገሩት ከመልክ ጋር ከተያያዘው ነገር ይልቅ ከኃይል ጋር የተያያዘው እንደሚበልጥ ነው፡፡ በእርግጥም ኃይልን ስናስብ ብዙ ነገሮች ወደ አእምሮአችን ይመጣሉ፡፡ ኃይል የብዙ ክንውኖች መሰረት ነው፡፡ ኃይል ሕልውናም ጭምር ነው፡፡ አለ! የምንለው ሰው መኖር የሚጠይቀውን መሰረታዊ ኃይል ያሟላ ነው፡፡ ሰው ብዙ ነገሮችን የሚከውነው በመልኩ አይደለም፡፡ መልካችንን ተከትሎ የሚሳብ ይኖር ይሆናል፡፡ መልክ ውስጥ ግን ኃይል የለም፡፡
            ሕሊና እንጂ መልክ አያስብም፡፡ አንደበት እንጂ መልክ አይናገርም፡፡ መልካምነት እንጂ መልክ ከሰው አያኖርም፡፡ ስነ ምግባር እንጂ መልክ አያስከብርም፡፡ እምነትና ፍቅር እንጂ መልክ ሞትን አያሻግርም፡፡ መልክ የላይ ማንነትን እንጂ የውስጥ ሰብእናን አይገልጥም፡፡ ፊት ቀልቶ ውስጥ ሊጠቁር፣ ውጪ አጊጦ ልብ ሊቆሽሽ ይችላል፡፡ ምድራችን የመልከኞች ሆናለች፡፡ ማስመሰል ቀላሉ የኑሮ ዘይቤ ተደርጎ እየተቆጠረ ነው፡፡ ገጣሚው፡ -
አርሜ ኮትኩቼ የሎሚ ዘንጓን
መልከኛ ወሰዳት ወይ ገባር መሆን፡፡ እንዳለ . . .
            ድካሙና ኃይሉ ያለው አራሚ ኮትኳቹ ጋር ነው፡፡ ሴቲቱ የተሸነፈችው ግን ለመልከኛው ነው፡፡ በመፍጠርና በማዳን ዋጋ የከፈለብን እግዚአብሔር ነው፡፡ የተወደደው ልጁ እስከ መስቀል ሞት በመታዘዝ ለመዳናችን መከራን ተቀብሏል፡፡ ዛሬም በቃሉ በኩል የሚረባንን ወደ ሕይወታችን ለማድረስ በመንፈሱ በኩል ይተጋልናል፡፡ ብዙዎች ግን የመልከኛዋ ዓለም ሆነዋል፡፡ በፍቅር ኃይለኛ፣ በማዳን ኃይለኛ፣ በምሕረት ኃይለኛ፣ በፍርዱ ኃይለኛ የሆነው እግዚአብሔር ወደ ጎን ተትቶ ሰዎች በፊታቸው መልካም መስሎ የታያቸውን ሁሉ በትጋት እያደረጉ ነው፡፡
             ዓለም የሆኑ ሳይሆን እንደሆኑ መስለው የሚታዩ የሚፋንኑባት አደባባይ ናት፡፡ ከፍቅር ይልቅ ፍቅር ለሚመስል፣ ከሰላም ይልቅ ሰላም ለሚመስል፣ ከእውነት ይልቅ እውነት ለሚመስል፣ ከኃይል ይልቅ ኃይል ለሚመስል መልክ ምድሪቱ ተገዝታለች፡፡ ያለ ጭንብል መኖር የማንችለውም ለዚሁ ነው፡፡ መልክ እንጂ ኃይል፣ ቅብ እንጂ የጨከነ እውነት፣ የምድሩ እንጂ የሰማዩ አያስደስተንም፡፡ የክርስትና ውድቀት ትልቁ ልኬት ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡     
            ክርስትና በመልኩ ሳይሆን የተብራራው በኃይሉ (በተግባሩ) ነው፡፡ ያውም የትንሣኤው ኃይል! (ፊል. 3÷10)፡፡ “ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው” ተብሎ እንደተፃፈ አውርተን እንኳን ያልዘለቅነውን ዓለም የምናሸንፍበት፣ ከክፋትና ከርኩሰቱ የምናመልጥበት ኃይል ያለው እምነታችን ውስጥ ነው፡፡ ይህም እምነት በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ መልከኛ ክርስትና ግን የሚመስል እንጂ የሆነ ነገር አይታይበትም፡፡ ውጫዊ ገጽታው ያመነ ውስጡ ግን የካደ ነው፡፡ በቃል ብዙ ጥበብ በኑሮ ብዙ ስንፍናን ይገልጣል፡፡ መሳይ ክርስቲያኖች!
           ምላስ ረዝሞ እጅ ከተሰበሰበ፣ የምናወራው እግዚአብሔር እንጂ የምንኖረው እግዚአብሔር ከሌለ፣ የምናቅደው እንጂ የምንተገብረው መልካም ካነሰ መልከኞች እኛ ነን፡፡ በእውነትና በመንፈስ ስለማምለክ ተረድተን እንደ ፈቃዳችን ካመለክን፣ በመንፈስ ጀምረን በሥጋ ከጨረስን፣ ከእግዚአብሔር የልቡ ምክር አፈንግጠን ለዚህ ዓለም ከንቱ መለፍለፍና በብልሃት ለተፈጠረ ተረት ከተገዛን በእርግጥም መልከኞቹ እኛ ነን፡፡ ተራቁተን እንደለበስን፣ ደህይተን እንደበለፀግን፣ ታውረን እንደተኳልን፣ አንሶን እንደተረፈን ከተሰማን ተወዳጆች ሆይ መልከኞች እንጂ ኃይለኞች አይደለንም፡፡ “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ እራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ” (ያዕ. 1÷23) ተብሎ እንደተፃፈ ተግባራዊ የሆነ መንፈሳዊ ኑሮ ሊታይብን አግባብ ነው፡፡
           አንድ ሰው በሠራው ቤት ውስጥ የሚሰቅለው የእራሱን ፎቶ ነው፡፡ መታየት ያለበትም ባለ ቤቱ (የቤቱ ጌታ) ነው፡፡ እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደሶች (1 ቆሮ. 3÷16) እንደመሆናችን በቤቱ ውስጥ መታየት እንዲሁም በሙላት ማዘዝ ያለበት የቤቱ ሠሪና ጌታ የሆነው እግዚአብሔር ነው፡፡ በእምነት ጉዞም ሆነ በአገልግሎት እንደ እግዚአብሔር ቃል መሆን ያለበት ከዚህ የተለየ አይሆንም፡፡ ነገር ግን ጌታ እንደሆነ እየተናገርን በቤቱ ላይ ግን እኛ ካዘዝን፣ አፍአዊ በሆነ መንገድ ስለ እርሱ አብዝተን እየመሰከርን በተግባር ግን እራሳችንን የምንገልጥ ከሆነ መልከኝነት እንደተጠናወተን ኃይሉ ግን እንደራቀን ማሳያ ነው፡፡ ምሕረቱን ያብዛልን!
           አምልኮ አምላክነት ላለው አካል የሚደረግ መረዛት ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር ያለ ሕያው አምላክ ስለሌለ ሁለንተናዊ መገዛት ለእርሱ እናሳይ ዘንድ የተወደደ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምልኮ የግል ገንዘቡ ስለሆነ ለማንም አያጋራውም (ዘፀ. 20÷1)፡፡ በዚህ መንገድ የሚተካከለው፣ ጎን ለጎን አልያም ተክቶት ይህንን ክብር የሚወስድ ሌላ ማንም ሊኖር አይችልም (ኢሳ. 42÷8)፡፡ ለዘመናችን ትልቁ ፈተና ግን ለእግዚአብሔር ብቻ አለመገዛት ነው፡፡ ስለዚህም ጎን ለጎን የምንገዛላቸው ከውስጥም ይሁን ከውጪ ምንጫቸውን ያደረጉ ብዙ ደባሎች አሉ፡፡ ይህ የእግዚአብሔርን ኃይል ተግባራዊ በሆነ መንገድ መካድ ነው፡፡
           እግዚአብሔር ሰዎች እንዴት እንደሚከተሉትና እንደሚያመልኩት በቃሉ ውስጥ ግልጽ መመሪያ አለው፡፡ መልከኝነት ከዚህ አሳብ ማነስ አልያም በዚህ ላይ መጨመር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኃይል አልባ ሞቅታ ነው፡፡ በእምነት ስንኖር እራሳችንን እንድንመረምር ቃሉ ስለሚያዝ ኑሮ መፈተሸ አለበት፡፡ ዛሬ ዓለም በክርስትናው ተጽእኖ ስር መሆንዋ ቀርቶ ክርስቲያኖች በዓለም ተጽእኖ ስር ወድቀዋል፡፡ እንደ ጨው ማጣፈጫ መሆን ቀርቶ አጣፍጡኝ አይነት አልጫ ሆኗል፡፡
           በብዙ ጨለማዎች ፊት ብርሃን መሆን አልተቻለም፡፡ አልቅሰው መጥተው አልቅሰው የሚመለሱ፣ በጉድለት መጥተው በጉድለት የሚሸኙ፣ ከእነርሱ መንፈሳዊነት የእኔ ዓለማዊነት ይሻላል የሚሉ በዝተዋል፡፡ ክርስትናው መፍትሔ መሆኑ ቀርቶ ችግር፣ መልስ መሆኑ ቀርቶ ጥያቄ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለዚህ ብቸኛው ምክንያት ደግሞ መልከኛ እንጂ ኃይል ያለው ክርስትና መዳከሙ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የእምነት ልጁ ጢሞቴዎስን በብርቱ ይመክረዋል፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ የመልከኛ ክርስትና ዋና ዋና ጠባያትንና መፍትሔውን እንመለከታለን፡፡ ጌታ እግዚአብሔር መልከኛ ፍቅር፣ እምነት፣ ይቅርታ፣ ቅድስና፣ ጽድቅ . . . በበዛበት በዚህ ዘመን እንደ እርሱ መንግሥት ልጆች በኃይሉ እንድንገለጥ ጸጋውን ያብዛልን!!
                                                         
                                                         - ይቀጥላል -

1 comment: