Tuesday, October 9, 2012

እግዚአብሔር ሲገልጥ



         “ከዚህም ወራት በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰችና፡፡ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ያስወግድልኝ ዘንድ ጌታ በተመለከተበት ወራት እንዲህ አድርጎልኛል ስትል ራስዋን አምስት ወር ሰወረች” (ሉቃ. 1÷24-25)፡፡        
           እግዚአብሔር የመገለጥ አምላክ ስለሆነ ሰው በራሱ መንገድ ሊያስተውለው ደግሞም ፈልጎ ሊደርስበት አይችልም፡፡ እርሱን የሥጋ ለባሽ ጥረትም ሆነ ግምት አያገኘውም፡፡ ነገር ግን “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው (ዮሐ. 1÷18)” ተብሎ እንደተፃፈ እግዚአብሔር አንድያ ልጁ እንደተረከልን እንዲሁ ነው፡፡ አምላክነቱን እንደፈቃዱ ካላብራራልን “በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው?” ልንለው አንችልም፡፡ እርሱ ፍቅሩን ለልባችን ካልገለጠ አፋችን ስለ ፍቅር ማውራቱ የእግዚአብሔርን ፍቅር ወደ ማስተዋል አያደርሰንም፡፡
            እግዚአብሔር ጽድቁን ካላሳየን ለራሳችን ጽድቅ መሸነፋችን አይቀርም፡፡ እግዚአብሔር የእውነትን ፍቺ በልባችን ላይ ካላበራ በሚያባብል ቃል እየተሸነገልን መኖራችን በግልጥ የሚታይ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ጽድቅና መንግስት የእኛ አቅም የመሻትን ያህል ነው (ማቴ. 6÷33)፡፡ እግዚአብሔር እንደ እግዚአብሔርነቱ እንረዳውና እናምንበት ዘንድ በቃሉ በኩል ራሱን አሳይቶናል፡፡ ከሚያስፈልገን የተሸሸገ፣ ከሚረባን የቀረ ምንም የለም፡፡ ስለዚህም ጌታ ስሙ ብሩክ ይሁን!
            ለዚህ ርእስ መነሻ የሆነን የኤልሳቤጥ ታሪክ ነው፡፡ ባሏ ዘካርያስ የእግዚአብሔር ቤት አገልጋይ  ነበር፡፡ ደግሞም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ እግዚአብሔርን በኑሮአቸው ያከብሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ለብዙ ዘመናት ልጅ አልነበረውም፡፡ እግዚአብሔር እንድናገለግለው ሲጠራን እንደማንቸገርና እንደማይጎድለን ተስፋ አልሰጠንም፡፡ ሁሉን ለእርሱ ክብር እንድናደርገውና በጊዜውም ያለ ጊዜውም እንድንጸና ግን አዝዞናል፡፡ በመከራም ጭምር!
            በብዙ ክርስቲያኖች ዘንድ የእውነተኛ አገልጋይን ኑሮ የመረዳት ችግር ይስተዋላል፡፡ ለዚህም ይመስላል ብዙዎች አገልጋይ የሚያጽናና እንጂ የሚጽናና፣ የሚያስተምር እንጂ የሚማር፣ የሚያሳርፍ እንጂ የሚራብ የማይመስላቸው፡፡ ነገር ግን ሐዋርያው እንዳለ “አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል” (ፊል. 4÷19) የሚለው የተስፋ ቃል በየትኛውም ሁኔታና ዘመን በእውነትና በመንፈስ ለሚያገለግሉት ሁሉ የታመነ ነው፡፡ ለአገልግሎቱ ታማኝ አድርጎ የቆጠራቸው ሁሉ በዚህ ደስ ይላቸዋል፡፡
            ካህኑ ዘካርያስ እያገለገለ ጥያቄ ነበረው፡፡ በመቅደሱ እየተመላለሰ ያጣው ነገር ነበረ፡፡ እግዚአብሔርን የሚያገለግሉት ጥያቄያቸው ሁሉ የተመለሰላቸው፣ ጉድለታቸው ሁሉ የሞላላቸው፣ ሩጫቸው ሁሉ የተሳካላቸው አይደሉም፡፡ አገልግሎት ማጣት እያለ የበጎ ስጦታና የፍጹም በረከት ባለቤት የሆነውን፣ አለመመቸት ከብቦን አእምሮን የሚያልፍ ሰላም ባለቤት የሆነውን፣ ሀዘን ኑሮአችን ላይ አጥልቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የተባለለትን፣ ጠላት ተሰልፎብን የምወደው ልጄ ይህ ነው የተባለውን ጌታ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ በመታዘዝ ታማኝነት የመጽናት ትጋት ነው፡፡ ዘካርያስ የእድሜው መግፋት፣ የሚስቱ ምክነት በአገልግሎት ጌታ ፊት እንዳይቆም አላደረገውም፡፡ እኛ ከዚህ ላነሱ ምክንያቶች ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት ብናበላሽ ይህ የጥላ አገልግሎት ብቻውን ይወቅሰናል፡፡
            በብሉይ ኪዳን ለአንዲት ሴት መውለድ አለመቻል የሚያስነቅፍና የሚያገልል ጉዳይ ነበር፡፡ ከሌሎች የሚመጣውን ንቀት፣ ከውስጥ የሚሰማን የበታችነት ስሜት መጋፈጥን የሚጠይቅ ተግዳሮትም ነበር፡፡ የሕልቃና ሚስት ሐና ማኅፀንዋ ዝግ በነበረበት ዓመት ሁሉ ነቀፌታዋን ተሸክማ ጣውንቷ እያሽሟጠጠቻት ካህኑ ዔሊ እንደ ሰካራም እስኪቆጥራት ድረስ በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ታነባ እንደነበር ቃሉ ይነግረናል (1ሳሙ. 1÷7)፡፡ በዚያ ዘመን መውለድ አለመቻል የኃጢአትን ያህል ተቆጥሮ ነቀፌታ መሸከምን ያስከትል ነበር፡፡ ኤልሳቤጥም መውለድ አለመቻል የሚያስከፍለውን ዋጋ ስትከፍል ኖራለች፡፡ እግዚአብሔር እንዲያስባትም በመቅደሱ በፀሎትና በምልጃ ትተጋ ነበር፡፡
            እግዚአብሔር አብርሃም ልጅ ሳይኖረው የዘጠና ዘጠኝ ዓመት አዛውንት ሳለ እኔ ኤልሻዳይ ነኝ በፊቴ ተመላለስ (ዘፍ. 17÷1) አለው፡፡ ከእግዚአብሔር ስሞች መካከል አንዱ ኤልሻዳይ የሚለው ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱን ኤልሻዳይ ብሎ ያቀረበው ከአብርሃም ሁኔታ አንፃር ነው፡፡ አብርሃም ከዚህ በኋላ መውለድ አልችልም ብሎ ተስፋው የተሟጠጠበት፣ ልቡ የዛለበት ጊዜ ስለነበር እግዚአብሔር እኔ ሁሉን እችላለሁ! በሚል አለመቻሉን በተስፋ ሞላው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ስሞቹን የተጠቀመው ከሁኔታው አንፃር ነው፡፡
           እግዚአብሔር ሁሉን እንደሚችል ስናምንበት በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነን ያለ መጨነቅ በፊቱ መመላለስ ይሆንልናል፡፡ በኃይልም በፍቅርም ብርቱ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ይህም ብርታት ሌላ ተቀራራቢ ብርታት የለውም፡፡ ለመታሰብ በሚከብዱ ነገሮች ላይ እንኳ እግዚአብሔር ተግባራዊ ነው፡፡ እንዳልቻልነው በተሰማን ሥራ አንድ ሰው አይዞህ እኔ እወጣዋለሁ ቢለን ምን ያህል ያሳርፋል? ሰው እንዲህ ካስመካ እግዚአብሔር ምን ያህል ልባችንን እንጥልበት ዘንድ የተገባ ነው፡፡
          እግዚአብሔር የምክነትን ወራት አሳልፎ በልጅ በረከት የተነቀፉትን አፍ በእልልታ ይሞላል፡፡ በሕይወት ውስጥ ላሉ ልዩ ልዩ ምክነቶት (ፍቅር እየቀዘቀዘ ነው፣ መተማመን አላፊ እየሆነ ነው፣  ሥነ ምግባር እንደ ኋላቀርነት እየተቆጠረ ነው) መፍትሔው ኤልሻዳዩ ጌታ ነው፡፡ ዛሬም ብዙ ሙከራ፣ ብዙ መጠበብ ምድሪቱን አላስተካከላትም፡፡ አሁን እንኳን በዚህ ሰዓት ብዙ ነገሮች እየተሞከሩ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ባልቻልነውና ባቃተን ነገር ላይ ሁሉ ኤልሻዳይ ነው፡፡ የዕብራይስጥ ትርጉም አዋቂዎች የዚህን ስም ትርጉም ከእናት ጡት ማጥባት ጋር አያይዘው ያብራሩታል፡፡ እንደውም እግዚአብሔር ራሱን እንደ እናት ያቀረበበት መንገድ እንደሆነም ይጠቀሳል፡፡ ለአንድ ልጅ የጡት ወተት እናቱ ውስጥ የተሸሸገ በረከቱ ነው፡፡ ነገር ግን ምድራዊ እናቶቻችን ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ጡት ማጥባት ያቆማሉ፡፡ ልጁም ወደ ማደግ ከፍታ ሲመጣ ይተወዋል፡፡ የእግዚአብሔር መጋቢነት ግን ለዘላለም ነው፡፡ የትኛውም የእድገት ደረጃ ተመጋቢነታችንን አያቋርጠውም፡፡
          አብርሃምን በይስሐቅ፣ መካኒቱን ሐና በሰባት ልጅ ደስ ያሰኘ ጌታ ኤልቤጥንም አሰባት፡፡ የመታሰብ ወራት መጣ፡፡ እንባን ከአይኗ፣ ነቀፌታን ከልቧ ላይ አበሰ፡፡ እግዚአብሔር አስታዋሽ አምላክ ነው፡፡ ስለራሳችን ጉዳይ በረሳንበት ወራት እርሱ ግን ያለፈ ልመናችንን ቸል አላለም፡፡ የካህን ሚስት ለነበረችው ኤልሳቤጥ መውለድ አለመቻል ቀላል ነገር አልነበረም፡፡ ነቀፌታን ያሸክማል! ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ አይደሉምን?
         ኤልሳቤጥ ታሪኳ ሲለወጥ፣ ነቀፌታዋ ሲንከባለል፣ በሁሉን ቻዩ ስትታሰብ ይህንን ባደረገላት ጌታ ፊት አምስት ወር ራስዋል ሰወረች፡፡ እግዚአብሔር ስላደረገላት ነገር ለመደነቅ ይህም ትንሽ ነው፡፡ የሞተውን ህይወት ዘርቶበት፣ የደረቀውን አለምልሞት፣ የተተወውን ወደ ሕልውና አምጥቶት እርሱ ያልተደነቀ ማን ይደነቃል? እግዚአብሔር ግን ከምንልለት ከዚህም ያልፋል፡፡
         ኤልሳቤት የሚያሳፍር ሳይሆን የሚያስመካ፣ የሚሸሸግ ሳይሆን የሚገለጥ ነገር በሆዷ ተሸክማ ለሰው በማይታይ ለእግዚአብሔር ግልጥ በሆነ መንገድ በምስጋና እየተጋች ራስዋን ሰውራ ነበር፡፡ ዘመናችንን ስናየው በዓለምም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ሁሉም ለመታየት የሚጥርበት፣ ማማው ላይ ለመቀመጥ የሚጋደልበት ነው፡፡ ሰዎች ከዓላማቸው ይልቅ ስለ ራሳቸው በማውራት፣ በተግባር ከመታየት ይልቅ በሰው ለመታየት ጥረት በማድረግ ተጠምደዋል፡፡ እንኳ ለሌሎች የሚተርፈውን ለራሳቸው የማይበቃውንም ጨማምረው ለታይታ ያቀርቡታል፡፡
         ስለ ጌታ ብዙ ጊዜ እንዳይገልጡት አዘዛቸው (ማቴ. 12÷15፣ ማር. 3÷12) ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ኢየሱስን ያህል ንፁሕ ጌታ (ለሁሉ ሊሞት የመጣ አንድ መፍትሔ) ወደ እርሱ የመጡትን ሁሉ ፈውሶ ዳሩ ግን አትግለጡኝ ይል ነበር፡፡ ከሥራቸው ስንጠቀም ኖረን ከሞቱ በኋላ አልያም ግድ ሲሆን የተገለጡ መልካም ሰዎች አሉ፡፡ ሳይታወቁ ብዙ ጠቅመው ሰው ገልጦአቸው አድንቀን ሳንጨርስ የሞቱም አሉ፡፡ በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ውድቀት የሚጀምርበትን ነጥብ አስተውለነው ከሆነ መሰማራት ሲገባን የተሰበሰብንበት፣ መገለጥ ሲገባን ያንቀላፋንበት ደግሞ መደበቅ ሲገብን የተገላለጥንበት፣ መጸለይ ሲገባን አደባባይ የፎከርንበት ያ ሰዓት ነው፡፡ ብዙዎች በዚህ ኪሳራ ውስጥ ሲያልፉ አይተናል፡፡ ያለነው ካለፉት ካልተማርን የረገጡትን መርገጥ፣ ያጨዱትን ማጨድ አይቀርም፡፡
        “ጌታ ሆይ እኔ ልሰወር አንተ ብቻ ታይ” የሚል የአገልጋይ ጸሎት አውቃለሁ፡፡ እንደ ጸሎቱ ቢሆን ኖሮ አጨብጭቦ የሚያወጣ አጨብጭቦ የሚያወርድ፣ እልል ብሎ የሚያከብር እልል ብሎ ሰቅሎ የሚያዋርድ፣ ወደድኩ ብሎ የሚስም እዚያው ቦታ ላይ ጠላሁ ብሎ የሚነክስ፣ ነፋስን የሚከተል ሕዝብ ባላተረፍን ነበር፡፡ ሰው ሰውን አይቶ ወደ ሌላ ሰው ይገላበጥ ይሆናል፡፡ ሰው ጌታን አይቶ ግን ወዴት ይገላበጣል? የሚያምረው እርሱን ስናሳይ ነው!
         ክርስትና እግዚአብሔርን ማሳየት ነው፡፡ እኛን እግዚአብሔር ከገለጠን መታዘዝ እውነት ነው፡፡ ኤልሳቤጥ እራሷን ሰውራ አምስት ወር ቆየች፡፡ በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል ድንግል ማርያምን ሊያበስራት ሲመጣ “ዘመድሽ ኤልሳቤጥ” ብሎ ገለጣት፡፡ ነቢዩ ዳዊት እንደ እግዚአብሔር ልብ የሆንኩ ብሎ ሲናገር አናነብም፡፡ እግዚአብሔር ግን እንደልቤ የሆነ ዳዊት ብሎ ሲናገር እናያለን (የሐዋ. 13÷22)፡፡ ኢዮብ በምድር ላይ እንደ እኔ ፍጹምና ቅን እግዚአብሔርንም የሚፈራ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም ብሎ ሲናገር አናነብም፡፡ እግዚአብሔር ኢዮብን ሲገልጠው በሰይጣንም ፊት ሲመሰክርለት ግን እናነባለን (ኢዮ. 2÷3)፡፡ ታዲያ ተወዳጆች ሆይ ማን ይግለጠን?
         ሰው ተሰውሮ ክፉ አያድርግ እንጂ መልካምን መሥራት መዝገብን በላይ በሰማይ መሰብሰብ ነው፡፡ ብዙ ሰው በእጁ ያደረገውን አውርቶ በመርካት ዋጋውን ይቀበላል፡፡ የማቴዎስ ስድስት አሳብ እንዲህ ያለውን መገላለጥ አጥብቆ ይኮንነዋል፡፡ እኛ ስለ ራሳችን የምንገልጠው መልካም ልኩ የመርገም ጨርቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከገለጠን ግን በእርሱ ሚዛን ተለክቶአልና እርሱ ጽድቃችን ነው፡፡
         ራሳቸውን ሰውረው ደግሞም ላመኑበት እውነት እስከ ሞት ድረስ ዋጋ ከፍለው ጌታን በቃልና በኑሮ እንዳከበሩት (እንደገለጡት)፣ በሰው መፍትሔ መካከል የእግዚአብሔርን መፍትሔ እንዳሳዩት እውነተኞች እንድንኖር በጥበብና በማስተዋል ጸጋውን ያብዛልን፡፡  

2 comments:

  1. My God bless you as you continue to encourage us with the truth. I love your blog. Ke argetoch teret kemesela tera wera hiwot yemiset kalun hulgizem megeben. Be'ewent berehaneh bertolegal.
    D.yeneneh

    ReplyDelete