Wednesday, July 17, 2013

የንጉሥ እልልታ (ካለፈው የቀጠለ)


               
                                እሮብ ሐምሌ 10/2005 የምሕረት ዓመት

“በያዕቆብ ላይ ክፋትን አልተመለከተም፡፡ በእስራኤልም ጠማምነትን አላየም፡፡ አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነው፡፡ የንጉሥም እልልታ በመካከላቸው አለ (ዘኁ. 23÷21)”

       ከዚህ በፊት በተነጋገርንበት ክፍል ድብልቅ ሕዝብ እግዚአብሔር “የእኔ” ብሎ በለየው ሕዝብ መንፈሳዊ ሁኔታ ላይ የነበረውን ተጽእኖ በዚህ ዘመን ካለው የክርስቲያናዊ ኑሮ ፈተናዎች ጋር በማዛመድ ለማየት ሞክረናል፡፡ በዚህ ክፍል በቀጥታ ከርእሳችን ጋር ወደሚዛመደው አሳብ እንገባለን፡፡ ነህምያ ባነበበው የሕጉ ክፍል ላይ ድብልቁ ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ እንዳይገባ ትዕዛዝ የተሰጠበት አንዱ ምክንያት “ይረግማቸው ዘንድ በለዓምን ስለ ገዙባቸው ነው” የሚለው ይጠቀሳል (ከሞዓብ አንፃር)፡፡ ይህ አገላለጽ ደግሞ በቀጥታ ወደ ኦሪት ዘኁልቍ መጽሐፍ ምእራፍ 23 እና 24 አሳብ ይወስደናል፡፡ የሴፎር ልጅ ባላቅ የሞዓብ ንጉሥ በነበረበት ዘመን በለዓም የእስራኤልን ሕዝብ እንዲረግምለት የተስማማበት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው፡፡

       ስለ ሞዓብ ጥቂት ለማስታወስ ብንሞክር ሞዓብ ሎጥ ከታላቅ ሴት ልጁ የወለደው የሞዓባውያን አባትና የሰዶም ፍሬ ሲሆን (ዘፍ. 19÷37)፡፡ ሞዓባውያን ለእስራኤል በመንገዳቸው ሁሉ ብርቱ ፈተናና እንቅፋት የሆኑ ሕዝቦች ነበሩ (መሳ. 11÷17)፡፡ ከተግባሮቻቸውም መካከል በለዓም ሕዝቡን እንዲረግም በጀት በጅተው የተንቀሳቀሱበት ታሪክ በብዙ የአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ውስጥ ይታወሳል፡፡ በእግዚአብሔር አሳብ ላይ የሰይጣን ብልሃትና የሥጋ ጠላትነት በግልጥ የሚስተዋል ብርቱ ተግዳሮት ነው፡፡ እንደ ሞዓብ ያለ የአሮጌው ሰው ጠባይና እንደ በለዓም ያለ የመናፍስት ሟርታዊና ሰይጣናዊ አሠራር የተቀደሰውን ማንነት ያለማቋረጥ የሚታገሉ ፈተናዎች ናቸው፡፡

       በለዓምና ባላቅ እስራኤልን ለመርገም የተጓዙበት መንገድ በፊታችን አስደናቂ ትምህርትን ያስቀምጥልናል፡፡ “በለዓምም ባላቅን፦ ሰባት መሠዊያ በዚህ ሥራልኝ፥ ሰባትም ወይፈን ሰባትም አውራ በግ በዚህ አዘጋጅልኝ አለው” (ዘኁ. 23)፡፡ ጠላት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለመርገም በእግዚአብሔር ፊት መሠዊያንና መሥዋዕትን መጠቀሙ በእጅጉ አስገራሚ ነው፡፡ ብዙ ማደናገሪያዎችና አመፃዎች በሃይማኖት ሽፋንና በእግዚአብሔር ስም መደረጋቸውን ስናስብ እናዝናለን፡፡ ዛሬም እንኳ በሚያፋቅረው ክርስትና መጠላላታችን፣ በረከትን እንወርስ ዘንድ ክርስቶስ በሞተለት ክርስትና ጥላ ስር ሆነን መረጋገማችን፣ እግዚአብሔርን እየጠራን ጉድጓድ መማማሳችን የምንወቀስበት ነው፡፡

       “ባላቅም በለዓም እንደ ተናገረ አደረገ ባላቅና በለዓምም በየመሠዊያው ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረጉ።” ከስጦታው ባለፈ የሰጪውን ልብ የሚመረምር እግዚአብሔር ፃድቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር በስጦታዎቻችን የሚደለል ሕፃን አይደለም፡፡ እርሱ ለእውነቱ የጨከነ ነው፡፡ ባለ ጠጋ፣ ባለ ሥልጣን፣ ባለ እውቀት፣ ባለ ጥበብ፣ ባለ ዝና፣ ባለ ኃይል . . . እነዚህ ሁሉ የእግዚአብሔርን ተግባር ቀርቶ አሳብ የማስለወጥ አቅም የላቸውም፡፡ እርሱ ለሚሠራው ነገር አማካሪ፣ ለሠራው ነገርም አስተያየት ሰጪ አያሻውም፡፡ በለዓምና ባላቅ ግን ሁሉን በሚችል አምላክ ፊት እቃቃ የመጫወትን ያህል እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ አልቆጠሩትም፡፡ እነርሱ በዘረጉት መሠዊያና ባቀረቡት መሥዋዕት ተደልሎ ሕዝቡን ለእርግማን የሚሰጥ፣ የልባቸውን እሺ የሚል አምላክ እንዲሆን አስበዋል፡፡ እርሱ ከመረጃም ከግምታችንም ልዩ ነው፡፡ እርሱ ስለ ራሱ የተናገረው ብቻ ምን ጊዜም ልክ ነው፡፡


       “በለዓምም ባላቅን፦ በመሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ፥ እኔም እሄዳለሁ ምናልባት እግዚአብሔር ሊገናኘኝ ይመጣል እርሱም የሚገልጥልኝን እነግርሃለሁ አለው። ወደ ጉብታም ሄደ።” በእርግጥ እግዚአብሔር ይህ የሚነጋገሩትን አይሰማምን? ዓይኖቹስ እንዲህ ያለውን ክፋት አያስተውሉምን? ሰው ግን ይኼው ነው፡፡ በራሳችን ጉብታ ላይ በምንሆንበት ሁኔታ ውስጥ የእግዚአብሔርን ከፍታ ለማስተዋል እንቸገራለን፡፡ የሞዓብ ንጉሥ በመሥዋዕቱ ዘንድ ቆይቶ በለዓም ከእግዚአብሔር ይዞ የሚመጣው ምን ይሆን? ከእነርሱ አንፃር እግዚአብሔር ይመለክበት ዘንድ መርኅ በሆነው መንገድ መሥዋዕታቸውን በፊቱ አሳርገዋል፡፡ እናም የለመኑትን እንደማይነሣቸው፣ ባላቅ በሕዝቡ መረገም፣ በለዓም ከንጉሡ ጋር በተዋዋለው ገንዘብ ለልባቸው እልልታ፣ ለአፋቸው ሳቅ ይሆናል ብለው ያስቡ ይሆን? ለቅዠቶቻችን ማብቂያ የለውም፡፡

       “እግዚአብሔርም ከበለዓም ጋር ተገናኘ እርሱም፦ ሰባት መሠዊያዎች አዘጋጀሁ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረግሁ አለው።” በለዓም በአንዳች ስካር ውስጥ እንዳለ ቃላቶቹ ይመሰክራሉ፡፡ ክፉ ካሰከራቸው ጉሽ ወይን ጠጅ ያሰከራቸው ይሻላሉ፡፡ እነዚህ የልባቸውን አውርተው፣ ራሳቸውን ከቀኝ ወደ ግራ ከግራ ወደ ቀኝ አንከራተው፣ ካሻቸው ተሳድበው ይገባሉ፡፡ እነዚያ ግን የልባቸውን ሠርተው፣ ሰው አንከራተው፣ ካሻቸው አቁስለውና ገድለው አይረኩም፡፡ በለዓም ለተገለጠለት እግዚአብሔር የተናገረው ማባበያ ይገርመኛል፡፡ ሲጀመር ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎች የእርሱን መገለጥ እንዴት ባለ እምነትና ትጋት እንደተጠባበቁ አስተውለን በለዓምን ማሳብ የእግዚአብሔርን ያህል ባይሆን እንኳ በአቅማችን የሚያስቆጣ ነው፡፡ የተገለጠው እግዚአብሔር ቃል ሳይናገር፤ መገለጡን ይጠባበቅ የነበረው በለዓም ተሽቀዳድሞ መሠዊያዎችን እንዳዘጋጀ፣ መሥዋዕት እንዳሳረገ ለእግዚአብሔር ነገረው፡፡ እግዚአብሔር የምትወደውን አድርጌአለሁና የምወደውን አድርግልኝ የምንለው ባለ ውለታ አይደለም፡፡ የሚወደውን እያደረግን የሚወደው የሚደረግልን ልጆቹ ነን፡፡ ይህ እውነት ባልጣመን ጊዜ ሁሉ ስፍራችን በለዓም ነው፡፡

       መሥዋዕት አቅራቢዎቹን በለዓምንና ባላቅን፣ መሥዋዕት ሆነው የቀረቡትን ወይፈንና አውራ በግ የፈጠረው እግዚአብሔር አይደለምን? አዘጋጀሁ . . . አሳረግሁ . . . የሚሉት ቃላት እግዚአብሔርን ተረጅ በለዓምን አስረጅ (መረዳትና ማስረዳት) ያደርገዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጸሎታችን እግዚአብሔርን የማስረዳት የሚሆንበት አጋጣሚ አለ፡፡ የምንጸልየው እግዚአብሔርን ለማስረዳት አይደለም፡፡ በእኛ ሕይወት እየሆነ ያለውን ነገር በአግባቡ የማያውቅ አምላክ ካለን እርሱ በእኛ ለደረሰብው ችግር መፍትሔ መሆን አይችልም፡፡ እውነተኛው እግዚአብሔር ግን ገና ሳንጠይቀው የሚያስፈልገንንና የምንፈልገውን የሚያውቅልን፣ እንደ ልቡ አሳብና ምክር ሁሉን መዝኖ እንደ ፈቃዱ የሚያደርግ ነው፡፡ በለዓም ከባላቅ ጋር ሕዝቡን ለመርገም እንደተማከሩ፣ ለዚህም ከንጉሡ በጀት ተመድቦለት እየተንቀሳቀሰ እንደ ሆነ፣ አንተም ለዚህ እንድትተባበረን መሠዊያና መሥዋዕት አቅርበናል አለን? በፍፁም አላለም፡፡ እውነቱ ግን ይህ አልነበረምን? ልክ ወላጆች ቤት ሲደርሱ ልጆች እያጠፉ ቆይተው በር ሲንኳኳ ተሯሩጠው አባታቸው ወይም እናታቸው ላይ ተጠምጥመው “ዛሬ የቤት ሥራዬን ሠርቼ . . . ንጽሕናዬን ጠብቄ . . . ያዘዛችሁኝን ሠርቼ . . . ” በማለት ጥፋታቸውን ለመሸፋፈን እንደሚሞክሩት አይነት በለዓምም ተሽቀዳድሞ እግዚአብሔርን እንዲህና እንዲያ አለው፡፡

       እግዚአብሔር ትዕግስቱ ምንኛ መልካም ነው፡፡ እንኳን ክፉዉ ሥራችን መልካሙ ተግባራችን እንኳ እድል ያገኘው በእርሱ ትእግስት ነው፡፡ እርሱ ባይታገስ ደግ ያልነው ከፍቶ እውነታው፣ ክፉ ያልነው መልካም ሆኖ ጽድቁ ባልታወቀ ነበር፡፡ እንዲህ ያለውን አመጽ የታገሠ እግዚአብሔር የእኛንም አመጽ የታገሠ ነው፡፡ እርሱ ፊት እንደ በለዓም ባለ ሞኝነትና የሥጋ ብልሃት ምን ያህል ጊዜ ቆመናል? የተገለጠውን ልንሰማው፣ ከእርሱ ልንማር፣ ከመንገዳችን ልንስተካከል ሲገባ ከእኔነታችን የወጣውን ነገር ያስረዳንበት፣ ከአሳባችን ጋር ዝቅ ብሎ እንዲስማማ እግዚአብሔርን የጠየቅንበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለዚህም ትእግስት ማሳየቱ ምንኛ ድንቅ ነው? ተመስገን!

       “እግዚአብሔርም ቃልን በበለዓም አፍ አድርጎ። ወደ ባላቅ ተመለስ፥ እንዲህም በል አለው።” ኦ እግዚአብሔር ግሩምና ድንቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር በለዓምን ሊያወጣጣው አልያም እንደዋሸው ሊሞግተው አልሞከረም፡፡ እንዲያማ ቢሆን ሰውን መሆኑ አይደለምን? እኛ ብንሆን እንኳን ባወቅነው ነገር ይቅርና በጠረጠርነው ነገር እንኳ ሰው ስናስጨንቅ ውለን ስናስጨንቅ እናድራለን፡፡ ሌሎች ጋር ያለው ነገር ካልተፍረጠረጠ እኛ ጋር ሰላም አለመሆኑ ሁሌም የምደነቅበት ነገር ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ሲያርም ደስ ይላል፡፡ በለዓምን ያረመበት መንገድ በዚህ ዘመን ላለነው ክርስቲያኖች እንዴት መተራረም እንዳለብን የሚያስተምረን እንደሚሆን አስባለሁ፡፡

       እኛ የመተራረሚያ መንገዶቻችን የሚያንፁ አይደሉም፡፡ አንዳንዴ ልናርመው ከሚገባን ችግር በላይ ማረሚያ መንገዱ የበለጠ ችግር የሚሆንበት ጊዜ ብዙ ይመስለኛል፡፡ በአዲስ ኪዳን ጌታ በምንዝር አገኘናት ብለው ፈሪሳውያን ወደ እርሱ አንዲት ሴትን ሲያመጡ መሳሳታቸውን የገለጠበት መንገድ ይደንቀኛል (ዮሐ. 8)፡፡ የእያንዳንዳቸውን የግል ድካም እርሱ ያውቅ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ስለሠሩት ኃጢአትና ነውር በማውራት እነርሱን ለማስተማር ሲሞክር አናይም፡፡ ይልቁንም እንደዚያ ያለውን ትልቅ ስህተት በአንድ አረፍተ ነገር አረመው “ኃጢአት የሌለበት ቢኖር በድንጋይ ይውገራት” እንግዲህ ይህች ቃል ናት ሕሊናቸው እንዲወቅሳቸው፣ ስህተታቸው እንዲሰማቸው ያደረገቻቸው፡፡ ጌታ ለጻፎችና ለፈሪሳውያን ስህተት ከቃል ያለፈ ነገር አልተጠቀመም፡፡ ያውም አጠርና መጠን ያለ ቃል፡፡ ቃልህ ብርቱ ነው!  

       እግዚአብሔርም በለዓም ለሠራው ስህተት ማረሚያ “ቃል” ብቻ ሲጠቀም እናስተውላለን፡፡ በእርግጥም ጌታ ቃል ብቻ ይናገር፡፡ ሸክም፣ ውጥረትና ምጥ ለሆኑብን ነገሮች ሁሉ እርሱ ቃል ብቻ ይናገር፡፡ ቃሉ ውስጥ መፍትሔ አለ፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ኃይል አለ፡፡ ቃሉ ራሱን ያስፈጽማል፡፡ የእግዚአብሔር መፍትሔ የእኛም መፍትሔ ሊሆን የተገባ ነው፡፡ ሰዎች በእኛ ፊት ለሚያሳዩት ችግር፣ ወደ ኑሮአችን ለሚመጣው መከራ ቃሉን እንደ መፍትሔና የጦር ዕቃ ማቅረብ አግባብ ነው፡፡ ለእርግማን ባሰፈሰፈው የበለዓም አንደበት ላይ እግዚአብሔር ቃሉን አስቀመጠበት፡፡ እርሱን ማን እንዲህ አድርግ ወይም አታድርግ ሊለው ይችላል? ምንም እንኳ የበለዓምን አንደበት ባላቅ ሂሳብ ቢከፍልበትም እግዚአብሔር እንዳይሠራበት ግን ከልካይ ኃይል አልነበረም፡፡ ተወዳጆች ሆይ ጌታ ሳያውቅ በእናንተ ላይ የሚሆን አንዳች ነገር የለም፡፡ ቁም ነገሩ ወደ እናንተ አሳብና ኑሮ ላይ የሚወረወረው ቀስትና ፍላፃ አይደለም፡፡ የእኛ ቁም ነገራችን በጠላት ፊት ጽኑ ጋሻ የሆነው እግዚአብሔር ነው፡፡ ዋስትናችን የትኛውንም ኃይል ያደቅቃል፡፡ እግዚአብሔር በለዓምን ወደ ባላቅ እንዲመለስና እንዲናገር ሲያዝዘው ምን እንደሚናገር ግን በአፉ ላይ ቃል ከማስቀመጥ ውጪ በጆሮው ምንም አልተናገረም፡፡ በለዓምም ወደ ባላቅ ተመልሶ ምን እንደሚል እግዚአብሔርን አልጠየቀውም፡፡

        እግዚአብሔር በቅንዓት ሲነሣ ጥያቄ የመጠየቅ አቅምና ፋታ እንኳን የለም፡፡ በለዓም እሽታውን ራሱን በመነቅነቅ ሊገልጥ እንደሚችል አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ቃልን በአንደበቱ ሞልቷልና “ለእሺ” ስፍራ የለም፡፡ ብቻ መሄድ . . እግዚአብሔር በኃይል ብሏልና ወደ ፊት . . ምንኛ ግሩም ነው፡፡ በለዓም ወደ ባላቅ ተመልሶ ለእስራኤል ሕዝብ ዋስትና፣ ለባላቅ መርዶ የሆነ ቃል በምሳሌ ተናገረ “እግዚአብሔር ያልረገመውን እንዴት እረግማለሁ? . . በአሕዛብም መካከል አይቈጠርም . . የያዕቆብን ትቢያ ማን ይቈጥራል? የእስራኤልንስ እርቦ ማን ይቈጥራል? የጻድቃንን ሞት እኔ ልሙት፥ ፍጻሜዬም እንደ እርሱ (ዘኁ. 24÷17) ፍጻሜ ትሁን” እንዲህ ያለው ንግግር ለሰሚው ለባላቅ ቀርቶ ለተናጋሪው ለበለዓም እንኳ አዲስና አስደንጋጭ ነው፡፡ ግን እግዚአብሔር ብሏልና ይህንን ሊለውጥ ሰው አቅም የለውም፡፡ ለካስ በመቆጠር መጽሐፍ ውስጥ የማይቆጠር ትቢያና እርቦ አለ፡፡ ማን ይሆን?

         እንዲህ ካለው የእግዚአብሔር ምላሽ በኋላ በለዓምና ባላቅ ሌላ ሙከራ ሲሞክሩ እንመለከታለን፡፡ “ባላቅም በለዓምን፦ ያደረግህብኝ ምንድር ነው? ጠላቶቼን ትረግምልኝ ዘንድ ጠራሁህ እነሆም፥ ፈጽመህ ባረክሃቸው አለው፡፡ እርሱም መልሶ (በለዓም)፦ በውኑ እግዚአብሔር በአፌ ያደረገውን እናገር ዘንድ አልጠነቀቅምን? አለው።” ባላቅ በሕዝቡ ላይ ሊያሟርትና አንዳች ርግማንን ሊያደርግ እየደከመ ባለበት ሁኔታ በእርሱ ላይ የሆነ ነገር እንደተደረገበት ማሰቡ ግሩም ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች በኑሮአቸው መሻሻል አለመምጣቱ፣ በሕይወት ስኬትን አለመጎናፀፋቸውን ሰዎች የሆነ ነገር አድርገውብኝ ይሆናል ከሚል የስንፍና ቃል ጋር ያያይዙታል፡፡ እግዚአብሔር አያደርግምን? እንደ እርሱ የሚሠራ፣ የጠላትን ምሽግ ለማፍረስ የበረታ የለም፡፡

       በለዓም ለባላቅ የሰጠውን ምላሽ ልብ ብለነው ከሆነ የሚረባንን ትምህርት እናገኝበታለን፡፡ በውኑ እግዚአብሔር በአፌ ያደረገውን እናገር ዘንድ አልጠነቀቅምን? የሚለው አነጋገር በመናገር መጠንቀቅ እንዳለ ያስረዳናል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ጥንቃቄ ከመቆጠብ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከመሰብሰብ፣ ካለመናገር፣ ካለመፈፀም ጋር የተሳሰረ አሳብ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ውስጥ መጠንቀቅ ማለት ምን ማለት ነው? በመናገር መጠንቀቅ፣ በመመስከር መጠንቀቅ፣ በመግለጥ መጠንቀቅ ነው፡፡ ለቅድስና የምንጠነቀቀው ቅድስናን በመኖር ነው፡፡ ለእውነት የምንጠነቀቀው እውነትን ያለማቋረጥ በመግለጥ ነው፡፡ ለጽድቅ መጠንቀቅ ማለት በጽድቅ መኖር ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ በክርስትና ውስጥ ጠንቃቆች ለተገለጠው እውነት በቃልና በኑሮ የታዘዙ ናቸው፡፡ መጠንቀቅ በርን ዘግቶ መቀመጥ፣ ከሰው ተሰውሮ በአንድ ስፍራ ማሳለፍ አይደለም፡፡ መጠንቀቅ ብርሃናችንን በሰው ሁሉ ፊት ማብራት ነው፡፡ ኦ እንዲህ ያለውን እውነት ወደ ልባችን ያመጣ ጌታ ብሩክ ነው፡፡

       ከዚህ በኋላ በለዓምና ባላቅ ስፍራ ቀይረው ቀድሞ እንዳደረጉት በእግዚአብሔር ፊት አደረጉ፡፡ በለዓምም ባላቅ በመሠዊያው ዘንድ እንዲቆይ አዝዞት እግዚአብሔር የሚለውን ለመስማት ሄደ፡፡ የሚያድን እግዚአብሔር ከሞኝነታችን ያድነን! ምንአልባት እግዚአብሔር ከአሳባችን ጋር ያልተስማማው መሠዊያዎቹ አንሰውት ሊሆን ይችላል፡፡ አልያም ለመሥዋዕት ያቀረብናቸው አውራ በጎችና ወይፈኖች አንሰውት ይሆናል በማለት የቁጥርና የይዘት ለውጥ እንዳደረጉ አናነብም፡፡ ሰባት ቁጥር ፍፁምነትን የሚያሳይ እንደ መሆኑ ከዚህ አልፈው ምንም ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ እግዚአብሔር ፊት ሕብረት ለማድረግ ከዚህ በተለየ ሁኔታ ወደ እርሱ መቅረብ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ቦታ ለወጡ፡፡ እግዚአብሔር ግን ከቀድሞው የተለየ ምንም አላደረገም፡፡ በለዓምን ወደ መጣበት እንዲመለስ አፉ ላይ ቃል አኑሮ ላከው፡፡ አሁን የመጣው ቃል ከፊት ይልቅ የበረታ ቁርጥ ነበር፡፡

       “ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም። እርሱ ያለውን አያደርገውምን? የተናገረውንስ አይፈጽመውምን? እነሆ፥ ለመባረክ ትእዛዝን ተቀብያለሁ እርሱ ባርኮአል፥ እመልሰውም ዘንድ አልችልም። በያዕቆብ ላይ ክፋትን አልተመለከተም፥ በእስራኤልም ጠማምነትን አላየም፤ አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነው፥ የንጉሥም እልልታ በመካከላቸው አለ” በለዓም በምሳሌ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት ምንኛ ያሳርፋሉ፡፡ እግዚአብሔር ቅድም ያለውን አሁን እንዲሽር መጠበቅ ምን ማለት ሊሆን ይችላል? እርሱ ይጸጸት ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በያዕቆብ ላይ ክፋትን እንዳልተመለከተ፣ በእስራኤል ላይ ጠማምነትን እንዳላየ መናገሩ ይገርማል፡፡ እርሱ ለምርጦቹ በሚቀናበት ጊዜ የሚሆነው ይኼው ነው፡፡ ሰይጣን ኢዮብን ለመክሰስ እግዚአብሔር ፊት ሲቆም እግዚአብሔር ስለ ኢዮብ ቅድስናና ጽድቅ ለዲያቢሎስ ያወራል፡፡ ከኢዮብ ጋር ሲገናኝ ደግሞ ስለ ባሪያው ኢዮብ ድካም ይነጋገራል፡፡ በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር ፃድቅ ነው፡፡    

      በሚታይ ሁኔታ ንጉሥ ለሌለው ሕዝብ እግዚአብሔር ንጉሡ ነኝ አለ፡፡ በሕዝቡም መካከል እግዚአብሔር ራሱን በእልልታ ገለጠ፡፡ የንጉሡ የእግዚአብሔርን እልልታ እስራኤል መካከል ያደረገው፣ ሕዝቡ ካላስተዋለው ጠላት ጋር በስውር ሙግት እንዲገጥም ያደረገው፣ በኃይልና በቅንዓት እንዲገለጥ እግዚአብሔርን ያስገደደው ምን ነበር? “ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር በለዓምን ይሰማ ዘንድ አልወደደም አምላክህም እግዚአብሔር ወድዶሃልና እርግማኑን በረከት አደረገልህ (ዘዳ. 23÷5)፡፡ እርግማኑን ከእኛ የሚያርቀው እኛ ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር ሳይሆን እግዚአብሔር ለእኛ ያለው መውደድ ነው፡፡ እንዲሁ በሌላ ስፍራ ላይ “አምላክሽ እግዚአብሔር በመካከልሽ ታዳጊ ኃያል ነው በደስታ በአንቺ ደስ ይለዋል፥ በፍቅሩም ያርፋል፥ በእልልታም በአንቺ ደስ ይለዋል ይባላል” (ት. ሶፎ 3÷17) ይላል፡፡

      የአብን ደስታ በእስራኤል መካከል ያደረገው በሥጋ ከእነርሱ ይወለድ ዘንድ ያለው የማይጠፋ ዘር ኢየሱስ ነው (ሮሜ. 9÷5)፡፡ በአዲስ ኪዳን አብ ስለ ክርስቶስ ሲናገር “እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ” (ማቴ. 3÷17)። አብ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ካለ እኛም በእርሱ ደስ የሚለው የሚወደው ልጁ እርሱ ነው ልንል እውነት ነው፡፡ የአብን ደስታ በመካከላችን የሚያደርገው ይህ ነው፡፡ “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና” (ማቴ. 18÷20) ተብሎ እንደተፃፈ የአብ ደስታ በመካከላችን የሚሆነው ደስታው በሆነው በልጁ ስም መሰብሰባችን ነው፡፡ የማናችንም መገኘት እውነተኛ ደስታን አይፈጥርም፡፡ በ1ኛ ሳሙ. 4÷5 ክብር ከእስራኤል በለቀቀ ጊዜ የእስራኤል እልልታ ከጠላት አላስመለጠም፡፡ የሕዝቡን እልልታ ምድሪቱ ማስተጋባቷን ተከትሎ የመጣው ሽንፈትና እንባ ነው፡፡ ሰው በሥጋ ትምክህት እግዚአብሔር ፊት ለመቆም በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ሁሌም ያለው ሽንፈት ነው፡፡ የእግዚአብሔር እልልታ ግን ከማንኛውም የጠላት ወጥመድ መጠጊያ ነው፡፡ የሰዎች ደስታ ለራሳቸውም አይበቃም፡፡ የጌታ ደስታ ግን የሁል ጊዜ ደስታችን ነው፡፡ ጠላት የእስራኤልን ማኅበር በሀዘንና በለቅሶ ሊሞላው ለእርግማን አቅዶ መጣ፡፡ እግዚአብሔር ግን ለበረከት አደረገው፡፡ ከክርስቶስ የተነሣ እርግማናችን ለበረከት ተቀይሮልናል፡፡


         “ጠላቴ እልል አይልብኝምና ስለዚህ እንደ ወደድኸኝ አወቅሁ፡፡ . . . . . ከዘላለም እስከ ዘላለም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፡፡ (መዝ. 40÷13) አሜን አሜን አሜን!

3 comments:

  1. “ጠላቴ እልል አይልብኝምና ስለዚህ እንደ ወደድኸኝ አወቅሁ፡፡ . . . . . ከዘላለም እስከ ዘላለም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፡፡ (መዝ. 40÷13) አሜን አሜን አሜን!

    ReplyDelete
  2. “እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ” (ማቴ. 3÷17)። አብ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ካለ እኛም በእርሱ ደስ የሚለው የሚወደው ልጁ እርሱ ነው ልንል እውነት ነው፡፡ የአብን ደስታ በመካከላችን የሚያደርገው ይህ ነው፡፡........He is the truth, the way and the life!

    ReplyDelete
  3. TEBAREK WONDMACHIN TSEGAW YBZALH KBR LEGETA YHUN AMEN

    ReplyDelete