እሮብ ሐምሌ 24/2005 የምሕረት
ዓመት
“ቃየንም ወንድሙን አቤልን፡- ና ወደ ሜዳ እንሂድ አለው። በሜዳም ሳሉ
ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፥ ገደለውም” (ዘፍ. 4÷8)፡፡
ግንኙነትን አስመልክቶ የሚያሻክሩ ምክንያቶችን ከአንድ እስከ አምስት ነጥቦች ባለፈው ንባባችን ለማየት የሞከርን ሲሆን
በዚህ ክፍል ደግሞ ቀሪ ምክንያቶችን የምንዘረዝርና ርእሳችንን በደንብ የምናብራራ ይሆናል፡፡
6. ሁሉም
ጥሩ ወይም ሁሉም መጥፎ፡- እንደዚህ ያሉ ሰዎች ማንኛውንም ነገር ነጭ ነው አልያም ጥቁር ነው፣ መልካም ነው አልያም መጥፎ
ነው ከማለት ውጪ ነገሮችን በሚዛናዊነት ለመዳኘትና ከተለያየ አቅጣጫ ለማየት ጥረት አያደርጉም፡፡ ሁሉም ነገር ለእነርሱ ከሁለት
አንዱ ነው፡፡ እንዲህ ያለው አመለካከት ግንኙነትን ሚዛን ያሳጣል፡፡ ሁሉም መጥፎ እንደ ሆነ በምናስብበት ሁኔታ ውስጥ ስንሆን ደጉን
ነገር ለመመልከት ጭፍኖች እንሆናለን፡፡ ሁሉም ጥሩ እንደ ሆነ በምናስብበት ሁኔታ ደግሞ ኑሮአችን ጥንቃቄ የጎደለው “በሬ ከአራጁ
ጋር ይውላል” አይነት ይሆንብናል፡፡ ተወዳጆች ሆይ ሚዛናዊ ሁኑ!
7. ለፍርድ
መቸኮል፡- በሰው የመፍረድ ዝንባሌ ግንኙነትን ጉዳት ላይ ይጥለዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በዚህ መንገድ የመተያየት ልማዳዊ አለማስተዋል
ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን በዚህ መንገድ ሰዎችን ማስተካከል አይቻልም፡፡ ደግሞ አብዝተን በምንፈርድባቸው ነገሮች ዘግይቶም ቢሆን
ራሳችንን እናገኘዋለን፡፡ ታዲያ እውነተኛነት እኛ በደከምን ጊዜ ለድካማችን የምናሳየውን ርኅራኄ ለሌሎችም ውድቀት እንዲሁ ማሳየት
ማለት ነው፡፡ ለመፍረድ አለመቸኮል ያበላሸ እንዲያስተካክል እድል መስጠት ነው፡፡ አለመፍረድ የወደቀ እንዲቆም መደገፍ ነው፡፡ እስቲ
በዛላችሁባቸው ወራቶች በቁስላችሁ ላይ እንጨት የሰደዱባችሁን አስቡ፡፡ ምን ያህል ከባድ ነበር? እናንተ ግን ፈጽማችሁ እንዲህ አታድርጉ፡፡
ፍርድን ለጌታ ስጡ!
8. አሳብ
ማንበብ፡- ብዙ ሰዎች የሌሎችን አሳብ ማንበብ እንደሚችሉ ይሰማቸዋል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለው ሁኔታ በእለት ከእለት ግንኙነቶቻችን
ላይ ተጽእኖው ከፍተኛ ነው፡፡ ልትል የፈለከው ገብቶኛል . . . ገና ሳትናገር ሁኔታህ ይነግረኛል . . . ብዙ አትድከም አሳብህን
መቼ አጣሁት . . . የሚሉት ቃላቶች ባይሰሙንም ግንኙነቶቻችንን እንደ ብል በልተው ለጉዳት የሚዳርጉ ልማዶች ናቸው፡፡ ማንም ሰው
የሌላውን አእምሮ (አሳብ) የማንበብ አቅም የለውም፡፡ ባልተገለጠ አሳብ ውስጥ ያለው መብት የአሳቢው ብቻ ነው፡፡ በቃል አልያም
በአካል እንቅስቃሴ (በተግባር) መገለጥ ያልቻለ አመለካከት ምስጢር ነው፡፡ አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል እንዲሉ የሰዎች አሳብ
ሲገለጥ ብቻ የምናየው ነገር ይኖራል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ያውም አቅማችን ባልሆነ ነገር ግንኙነቶቻችንን መጉዳት አይኖርብንም፡፡