Wednesday, July 24, 2013

ካፈርኩ አይመልሰኝ!


                                  እሮብ ሐምሌ 17/2005 የምሕረት ዓመት

“ቃየንም ወንድሙን አቤልን፦ ና ወደ ሜዳ እንሂድ አለው። በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፥ ገደለውም” (ዘፍ. 4÷8)፡፡

       በሰው ልጆች የእለት ከእለት ኑሮ ውስጥ ትልቁም ከባዱም ነገር ግንኙነት ነው፡፡ ብዙ ወገኖች በዚህ መንገድ ይፈተናሉ፡፡ በአንድ የጦር ሜዳ ውስጥ ከጠላት ትልልቅ ዒላማዎች መካከል የግንኙነት መስመሩን ማቋረጥ ቀዳሚ አጀንዳው ነው፡፡ እግዚአብሔር እንኳ ምድርም ሁሉ በአንድ ቋንቋና በአንድ ንግግር ነበረች (ዘፍ. 11) በተባለበት ዘመን በሰናዖር ሜዳ በእግዚአብሔር አሳብ ላይ በጠላትነት በተነሡት ሕዝቦች ፊት የሰማይና የምድር ጌታ የወሰደው እርምጃ ቋንቋቸውን መደባለቅ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር የግንኙነት መስመራቸውን አቋረጠው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ና የተባለው እየሄደ፣ ሂድ የተባለው እየመጣ፣ ውጣ የተባለው እየገባ፣ ቁም የተባለው እየተቀመጠ ጤናማ ግንኙነት ጠፋ፡፡ እናም መጨረሻቸው ጥፋት ነበረ፡፡

       የነገሮች ሁሉ መፍረስ ጅማሬን አስተውላችሁ እንደ ሆነ “ግንኙነት” ተጠቃሽ ነው፡፡ ውጣ ውረድ በበዛበት፣ መውጣትና መግባታችን በብዙ እንቅፋቶች በተሞላበት ዓለም ሰው በሰላም ለመገናኘቱ ዋጋ ቢሰጥ ሲያንስ ነው፡፡ ምክንያቱም መገናኘት ቀላል አይደለምና፡፡ እኛ ስንተያይ ሌሎች ጋር መለያየት፣ እኛ ሰላምታ ስንለዋወጥ ሌሎች ጋር መነካከስ፣ እኛ ጤና ይስጥልኝ ስንባባል ሌሎች ቀብር ላይ መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ አዘውትሬ ከእንቅልፍ ስነሣ መንጋቱን እንደተመለከትኩ በአእምሮዬ የሚመላለስ ነገር ቢኖር “መንጋት ቀላል አይደለም” የሚለው ቃል ነው፡፡ በእርግጥም እውነቱ ይህ ነው፡፡ ሌሊት ስንት አንቡላንስ ጮኋል፣ ሌሊት ስንቶች በጥይት እሩምታ ያለ በደላቸው ሞተዋል፣ ሌሊት ስንቶች ከጨለማና ከሰው ጅብ ጋር ሲታገሉ አድረዋል፣ ሌሊት ለስንቶች ሲለቀስ ታድሯል፣ ሌሊት ስንት ሰው መርዶ ሰምቷል፣ ሌሊት . . . . አዎ መንጋት ቀላል አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ሌሊት ልክ እንደ እናት ምጥ ነው፡፡ ቀኑን የምንቀበለውም ልክ እንደ አዲስ በመወለድ ነው፡፡ ሰው በቀን ላይ የመቅጠር አቅም የለውም፡፡ እግዚአብሔር ግን በቀጠረው ቀን ሁሉን ያደርግ ዘንድ ቻይ ነው፡፡ አሁን አብራችሁ ያላችሁ እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ ይህም ስለኖራችሁ ነው፡፡


       ሰው ከራሱ ጋር መኖር በተቸገረበት ዘመን ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር መቻል ስኬት ነው፡፡ በተለይ በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ የሥጋና የዲያቢሎስ ተጽእኖ ስለሚያይል በዚህ የሚንገላቱ ብዙ ናቸው፡፡ አልፎም ተርፎ የአቤል እጣ ፈንታ በቃየል ወንድማቸው የደረሰባቸው በዙሪያችን እንደ ደመና ናቸው፡፡ ዛሬ በክርስትና ውስጥ የግንኙነት ብስለት ጎዶሎነት መንፈሳዊውን ማኅበረሰብ ሆድና ጀርባ አድርጎታል፡፡ እንዲህ ያለው ቅሌት በአገልጋዮች መካከል መታየቱ ደግሞ ይበልጥ ልብ ይነካል፡፡ በየደረጃ ማለትም በቤተሰብና በትዳር፣ በጓደኝነትና በማኅበራዊ ኑሮ ግንኙነቶቻችን መጎዳታቸው ጠቅላላ የኑሮ ስርዓታችንን የሚያናጋው ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ ጥናቶች ለግንኙነት እንደ እንቅፋት ከሚያስቀምጧቸው ምክንያቶች መካከል ጥቂቶቹን ብናነሣ አግባብ ይመስለኛል፡፡

1. መረጃ አልባ ፍረጃ፡- በብዙ ግንኙነቶች መካከል በበጥባጭነቱ በዋናነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ያለ በቂ ምክንያት በሰዎች/ ግንኙነት ላይ ተገቢነት የሌለውን ውሳኔ ማሳለፍ፡፡ አብዛኞቹ ዝንባሌዎቻችን ለፍረጃ የቀረቡ መሆናቸው በግንኙነት ውስጥ ያለውን ጣዕም እንዳናስተውል ግርዶሽ ይሆኑብናል፡፡ መልካም ሰው ክፉውን እንዴት በጎ አደርገዋለሁ ብሎ ይጨነቃል እንጂ ክፉን ክፉ በማለት ጊዜ አያባክንም፡፡ ቻይናዎቹ ጨለማን ጨለማ ብትለው ውለህ ስትለው ብታድር ለውጥ አይመጣም፡፡ ቁራጭ ሻማ ብትለኩስ ግን ልዩነቱን ታጣጥማለህ ይላሉ፡፡ በእርግጥም ሊሆን የሚገባው እንደዚህ ነው፡፡

      ውሳኔ ላይ ለመድረስ አትቸኩሉ፡፡ “ጎጆ መሥራት ነው ከባዱ፤ ጊዜ አይወስድም ለመናዱ” የሚለውን የአንድ ወንድም አባባል ብናስታውሰው የምንማርበት ይመስለኛል፡፡ መጠላላት ቀላል ነው፡፡ መለያየት ዋጋ አያስከፍልም፡፡ እግዚአብሔር አዳምና ሄዋንን ከዔደን ገነት ሲያስወጣቸው ሰዓታታ አልወሰደም፡፡ እኛን ወደ እቅፉ ለመመለስ ግን አንድ ልጁን ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ለዚህም የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ የተገለጠ፣ እንደ ሰው በጥቂቱ ያደገ፣ ሠላሳ ዘመን በሰው መካከል የኖረ፣ ለቀናት የተንገላታ፣ ለሰዓታት የተሰቀለ፣ ለቀናት በመቃብር የተቀበረ መሆን አስፈልጎታል፡፡ በእኛ ላይ የዘላለም ሞት ፍርድ እንዲ መጣ ባለ መታዘዝ አንዲትን ፍሬ መብላት በቂ ነበር፡፡ እኛ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ግን የመፍትሔዎች (እውነተኛው የወይን ግንድ) ሁሉ ቁንጮ አስፈልጎ ነበር፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ!

      ግንኙነት ቆም ማለትን፣ ማውጣት ማውረድን፣ ማድመጥ ማመዛዘንን ይጠይቃል፡፡ ውሳኔው የትም አይሄድባችሁምና አትቸኩሉ፡፡ የሄደን ወዳጅ ግን መመለስ ከባድ ነው፡፡ በአፍ የሸኛችሁትን በቃል አትወዳጁትም፡፡ ልባችሁንም ትኩረታችሁንም ነፍጋችሁ ችላ ያላችሁትን በእየዬ አትመልሱትም፡፡ ለችግሮች በቂ መረጃ ይኑራችሁ፡፡ የበደላችሁ ሰው ሰው አስቶት ነው? በራሱ ስቶ ነው? ወይስ በዓላማ ነው? ያረጋችሁ ካረገላችሁ፣ ያደረሰባችሁ ከደረሰላችሁ፣ የቀማችሁ ከዋለላችሁ ይበልጣልን? በእርሱና በእናንተ መካከል ያሉት ወሬዎችና ሰዎች ለመስማማታችሁ የሚተጉ ናቸው ወይንስ ለልዩነት የሚሠሩ? በበቂ መረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ አልፎ አይቆጭም፡፡

2. ከክምር ላይ ሳር መምዘዝ፡- ግንኙነትን ከሚያፈርሱ ነገሮች መካከል ሌላው ተጠቃሽ ከብዙ መልካም መካከል አንዷን መጥፎ ለይቶ በመምዘዝ ከዚያ አንፃር ሰውን መዳኘት ነው፡፡ እንደ ክምሩ ብዙ መልካም ነገር ሰዎች እያላቸው ልክ እንደ ሳሩ አንዷንና ትንሿን መዝዞ  ሌላውን በጎና አስፈላጊ ነገር ዋጋ ማሳጣት ተገቢ አይደለም፡፡ አስተውለን እንደ ሆነ ከአንድ ሰዓት ንግግር ውስጥ ሰዎች አዳራሹን ለቀው ሲወጡ የሚያወሩት ተናጋሪው ያስነጠሰበትን ክፍል ነው፡፡ ከሚያስተክዙን ነገሮች አንዱ ያለንን ብዙ ትተን ያጣነውን አንድ መምዘዛችን ነው፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች ለደስታ እሩቅ ናቸው፡፡ ቢከተላቸውም ይሸሹታል፡፡ ቢመለከታቸውም ይሰወሩታል፡፡ ለማመስገን ምክንያታቸው ብዙ ሆኖ ሳለ ለማማረር የታጠቁ ናቸው፡፡ የቤት ሠራተኞቻቸውን ቁጭ ብድግ የሚያደርጉ ሰዎች ምክንያታቸው ውኃ ቀጠነ ነው፡፡

       ልብ አድርጉ! እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን ግፍ የቤት ሠራተኛ አድርጎ አይመልስ ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን በምቾት ባርነት እንባ ከልባችሁ ይታለባል፡፡ ከሰዎች ድካም አትጀምሩ፡፡ ለብርታታቸው ቅድሚያ ትኩረት ስጡ፡፡ መደናነቅ ልምምዳችን ሊሆንም ይገባል፡፡ በሽንገላ አይሁን እንጂ ሰዎች ለሠሩት ተግባር እውቅና/ አድናቆት መስጠት ስህተት የለውም፡፡ ይህ ልኩን ልክ ነው የማለት ያህል ነው፡፡

3. ልኩን ያለፈ ድምዳሜ፡- እኛ ጋር ባለው አለመግባባት መንደሩ ሁሉ አይግባባም ማለት ነውር ነው፡፡ እኛን በተሰማን የሌሎችን ስሜት መተርጎም የማይገናኝ ማገናኘት ነው፡፡ ከልክ ባለፈ ሁኔታ ነገሮችን ከአንድ ከተወሰነ አቅጣጫ ተነሥቶ ማጠቃለያ ላይ መድረስ አግባብ አይደለም፡፡ አንድ መጽሐፍ ጸሐፊ መግቢያውን ጽፎ ማጠቃለያ ሊጽፍ እንዴት ይቻለዋል? ምክንያቱም በመካከል ሊኖሩ የሚገባቸውን ምእራፎች ሁሉ በአግባቡ መፃፍና መፈተሽ ስለሚገባው ነው፡፡ የማይገናኙ ነገሮችን በማገናኘት ማጠቃለያ ላይ የመድረስ ሂደት የግንኙነት (ልክ ያለፈ ድምዳሜ) እንቅፋት ነው፡፡ በተቻለ መጠን የሚገናኙ ነገሮችን ከማይገናኙት የመለየት ችሎታችንን ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

      የተለያዩ ጉዳዮችን እንደ አንድ የመጠረዝ አካሄድ በግንኙነት መካከል የሚስተዋል ነው፡፡ ነገር ግን ልዩ ልዩ ነገሮች በራሳቸው አይነትና ተርታ መዳኘት አለባቸው፡፡ ይህ ባልሆነበት ሂደት ሁሉ በሰዎች መካከል ቅራኔ እንዲሁም አልፎ ተርፎ መለያየትን ሊያስከትል ይችላል፡፡

4. ግነትና ማኮሰስ፡- እንደነዚህ አይነቶቹ ለእነርሱ ስሜት ትርጉም ያለውን ነገር በማጋነን በተቃራኒው ደግሞ ለስሜታቸው ትርጉም አልባ የሚሆንባቸውን ነገር በማጥላላት የሚታወቁ ናቸው፡፡ የሰዎች ስሜት መለዋወጥ እውነታን የተከተለ አይደለም፡፡ ሰው እንደ መሆናችን ትንንሽ በሚባሉ ምክንያቶች ልንበሳጭ አልያም ቶሎ ደስ ሊለን ይችላል፡፡ አየር ሲለወጥ፣ አካባቢ ስንቀይር፣ አዳዲስ ወዳጅነቶች ስንመሰርት፣ ውስጣዊ የሰውነታችን ክፍል ሁኔታ ብቻ በእኛ ስሜት ላይ ለሚስተዋለው ተጽእኖ የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸው እንዳለ ሆኖ እውነታውን መቀበል አለመቻል ግን አደጋ ነው፡፡ እንደነዚህ አይነት ሰዎች በልከኝነት ይቸገራሉ፡፡ ለእነርሱ ልክ እውነታው ሳይሆን እውነታውን የሚዳኙበት ስሜት ነው፡፡ ስለዚህ ደስ ያላቸውን በብዙ አድናቆትና ይሁንታ ሲያጅቡት ያልመሰላቸውን ደግሞ ያጣጥሉታል፡፡ ነገር ግን በግንኙነት መካከል በተቻለ መጠን ሚዛናዊ ለመሆን መሞከር መፍትሔ ነው፡፡

5. ግላዊ ማዛመድ፡- የግንኙነቶቻችንን ጤና ከሚያውኩ ምክንያቶች መካከል ግላዊ ማዛመድ (ነገሮችን ከራስ ጋር ማያያዝ) እንዲሁ ጎጂ ልምምድ ነው፡፡ ሰዎች የሚናገሩትን፣ የሚጽፉትን፣ የሚተገብሩትን ሁሉ እኔን ለመንካት ነው ብለው የሚያስቡ አይነት ወገኖች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ባል ቤት ውስጥ ስለ ሴቶች ሲያወራ ሚስት እኔን ለመንካት ነው ብላ ካሰበች፤ ሚስት ለባሏ ስለ ቀድሞ ጓደኛዋ ስታወራ እኔን ለማስቀናት አልያም ለማጥላላት አስባ ነው ብሎ ካሰበ ነገሮችን ግላዊ ማድረግ ይሆናል፡፡ ይህም መልካሙን ግንኙነት ያቆሽሻል፡፡ በዚህም እኔነት በከፍተኛ ሁኔታ ይስተዋላል፡፡    

       ነገሮችን ከሚነገሩበት ዓላማና ከራሳቸው ይዘት አንፃር ማጤንና መዳኘት ግንኙነቶቻችንን ጤናማ ያደርጋቸዋል፡፡ ሁሉን ለእኛ የመተርጎም ችግር የብዙ ወጣቶች ችግር ነው፡፡ እንዲህ ያለው ልምምድ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ እኛ ውስጥ ትርጉም እንዲኖራቸው ሲያደርግ፤ እኛን ደግሞ ሁሉም ቦታ ርእስ ያደርገናል፡፡ ዳሩ ግን ሁለቱም ከእውነት የራቁ ስለሆኑ ለማነጽም ለመታነጽም አይጠቅሙም፡፡  

                                                            - ይቀጥላል -

1 comment:

  1. lela minim alilim IGZIABIHER AMLAK yibarkih tebarkeh kir yih stuf kalewubet neger iyawetagn new

    ReplyDelete