Friday, February 21, 2014

ምክር፡

                               
                           አርብ የካቲት 14 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት

          ልጄ ሆይ፤ ዋዘኛና ቀልደኛ አትሁን፡፡ በመከራ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የምታዝንና የምትራራ ሁን፤ በድኃ ላይ አትጨክን፤ ርስቱንና ቤቱንም በምክንያት አትውሰድበት፤ ለመጨረስም የማትችለውን ነገር አትጀምር፡፡ እሳትና የሞላ ውኃ አትድፈር፡፡ በማናቸውም ነገር ከሚበልጥህ ሰው ጋር ባልንጀርነት አትያዝ፡፡ ከዳኛ ጋር ወዳጅ ሁን፡፡ በፊቱ በቆምህ ጊዜ እውነቱን እንዲፈርድልህ፡፡ ከሀኪምም ጋር ወዳጅ ሁን፡፡ በታመምህ ጊዜ ፈጥኖ እንዲመጣልህ፡፡

          ልጄ ሆይ፤ በልተህ ስትጠግብ ረኃብን፤ ስትበለጥግ ድኅነትን፤ ስትሾም ሽረትን፤ ሌላውንም ይህን የመሰለውን ሁሉ አትርሳ፡፡

         ልጄ ሆይ፤ ለሞተው ወዳጅህ ከማልቀስ ይልቅ በሕይወቱ ሳለ የክፋት ሥራ ለሚሠራ ወዳጅህ አልቅስለት፡፡

         ልጄ ሆይ፤ ባለ ጠጋ ሲወድቅ ሰው ሁሉ ይደግፈዋል፤ ድኃ ሲወድቅ ግን ሰው ሁሉ ወዲያው ይገፋዋል፡፡ ባለ ጠጋ ሲከሰስ በሸንጎ የተቀመጠው ሁሉ ይሟገትለታል፤ ድሀ ሲከሰስ ግን በሸንጎ የተቀመጠው ሁሉ ይፈርድበታል፡፡ መልካም ዳኛ በመካከላቸው የተቀመጠ እንደ ሆነ ግን ፍርዱ እንደ ፀሐይ ያበራለታል፡፡ ስለዚህ በምትኖርበት ሀገር መልካም ዳኛ አያጥፋብህ፡፡


         ልጄ ሆይ፤ በማናቸውም ነገር ቢሆን ሞት አይቀርም፡፡ ነገር ግን በሰው እጅ ከመውደቅ በእግዚአብሔር እጅ መውደቅ ይሻላል፡፡ ለአፍህ መሐላ አታልምደው፤ እግዚአብሔር ስሙን ከንቱ ያደረገውን ሳይቀስፈው አይቀርምና ስሙን በከንቱ አትጥራ፡፡

         ልጄ ሆይ፤ በዚህ ዓለም ኃይለኞች ገንዘብና እውቀት ሁለቱ ብቻ ናቸው፡፡ ገንዘብና እውቀት ያለው ሰው እስከ ጊዜው ደስ ብሎት ይኖራል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ገንዘባቸውን በማይረባ ጉዳይና ሰውን በማጥፋትና ራሳቸውን ብቻ ለመጥቀም አድርገው ኃይላቸው ይደክማል፡፡ ገንዘባቸውን ለንግድና ለድሀ፤ እውቀታቸውንም ለሥራና ለሰው ጥቅም የሚያደርጉ ሰዎች ግን በኃይል ላይ ኃይል እየጨመሩ ይኖራሉ፡፡ እነሆ ለዚህ አንድ ምሳሌ እነግርሃለሁ፤ ነጭ ስንዴ በባለ ሙያ እጅ ሲሆን እጅግ ያማረና የጣፈጠ እንጀራ ይሆናል፡፡ በባለ ሙያ እጅ ያልሆነ እንደ ሆነ ግን እንደ ዘንጋዳ እንጀራ ይሆናል፡፡ ገንዘብና እውቀትም በደግ ሰው እጅ ሲገቡ ለመልካም ነገር ይሆናሉ፡፡ በክፉ ሰው እጅ ሲገቡ ግን ለጥፋት ነገር ብቻ ይሆናሉ፡፡

         ልጄ ሆይ፤ የምትሠራውን ሥራ ሁሉ ሰው ቢያየው ቢሰማውም አይጎዳኝም ብለህ እንደ ሆነ ነው እንጂ አይታይብኝም፤ አይሰማብኝም ብለህ አትሥራው፡፡ አንተ ምንም ተሰውረህ ብትሠራው ከተሠራ በኋላ መታየቱና መሰማቱ አይቀርም፡፡

        ልጄ ሆይ፤ አንተ አስቀድመህ በሰው ላይ አትነሣ፤ ሰው በአንተ ላይ ቢነሣብህ ግን እንዳትሸነፍ ጠንክረህ መክት፡፡ እምነትህንም በእግዚአብሔር ላይ አድርግ፡፡

         ልጄ ሆይ፤ ሚስትህ ሰነፍ የሆነች እንደ ሆነ የቤትህን ስርዓት አንተው ጠብቀህ ኑር እንጂ ለእርሷ ፈቃል አትስጣት፡፡ ልባም የሆነች እንደ ሆነ ግን፤ የቤትህን ሥራ ሁሉ ለእርሷ ልቀቅና አንተ በውጪ ሥራህን አሳምር፤ አንተ የውጪውን እርሷ የውስጡን ሥራ ብትሠሩ ትበለጥጋላችሁ፡፡

        ልጄ ሆይ፤ ሰው ሳይኖር ብቻህን ከሴት ጋር አትነጋገር፡፡ ባሏ አለመኖሩን በደጅ ጠይቀህ ከደጅ ተመለስ እንጂ ወደ ቤት አትግባ፡፡ ሰው ሳይኖር ብቻህን ከሴት ጋር የተነጋገርህ እንደ ሆነ ግን፤ ምንም ሌላ ምስጢር ባይኖራችሁ በመነጋገራችሁ ብቻ መጠርጠር አይቀርም፡፡

         ልጄ ሆይ፤ ለልጆችህ የምታወርሳቸው ብዙ ገንዘብ በሳጥን ውስጥ ከማስቀመጥ፤ አንተ በሕይወተ ሥጋ ሳለህ ወደ ትምህርት ቤት እየሄዱ እውቀትና እንዲማሩ ገንዘብህን ብትሰጣቸው ይሻላል፡፡ ባሏ ለሞተባት ሴት አባታቸውም ለሞተባቸው ልጆች እጅህ አጭር አይሁን፡፡

        ልጄ ሆይ፤ በጌታህም ቤት ቢሆን በሌላም ስፍራ ቢሆን ገንዘብ ወይም ሌላ እቃ ወድቆ ብታገኝ አታንሣ፡፡ ብታነሣውም መልሰህ ለጌታህ ወይም ለዳኛ ስጥ እንጂ ሰውረህ አታስቀር፡፡

        ልጄ ሆይ፤ በፍፁም ልብህ ለማትወደው ሰው ቤትህንና የቤትህን ዕቃ አታሳይ፡፡

        ልጄ ሆይ፤ ንፁሕ አለመሆንህን እግዚአብሔር ያውቃልና በእርሱ ፊት ንፁሕ ነኝ አትበል፡፡ በንጉሥ ፊትም ብልህ ነኝ አትበል፤ የብልሃት ሥራ ሠርተህ አሳየኝ ያለህ እንደ ሆነ ታፍራለህና፡፡

       ልጄ ሆይ፤ ጠላት በዛብኝ፤ ምቀኛ አሴረብኝ ብለህ እጅግ አትጨነቅ፡፡ በዓለም የሚኖር ፍጥረት ሁሉ ጠላትና ምቀኛ አለበት እንጂ ባንተ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚሁም በጥቂቱ እጽፍልሃለሁ፡፡

       በፍየል ነብር፤ በበግ ተኩላ፤ በአህያ ጅብ፤ በላም አንበሳ፤ በአይጥ ድመት፤ በዶሮ ጭልፊት አለባቸው፡፡ ይህንንም የመሰለ ብዙ አለ፡፡ ሰውም እርስ በርሱ እንዲሁ ነው፡፡ ስለዚህ የሚመጣብህን ነገር ሁሉ በትእግሥት ሆነህ ተቀበለው፡፡ በመጨረሻው ግን ሁሉ አላፊ ነውና ጠላቶችህ ሁሉ ያልፋሉ፡፡ ወይም አንተ አስቀድመህ ታልፍና ከዚህ ዓለም መከራና ጭንቀት ታርፋለህ፡፡

       ልጄ ሆይ፤ እስቲ ያለፉትን ሰዎች ሁሉ አስባቸው፡፡ እነዚያ ሁሉ ጀግኖች ሁሉም መሬት ሆነዋል፡፡ እነዚያ ሁሉ ዓለመኞች፤ እነዚያ ሁሉ ቀልደኞችና ፌዘኞች፤ እነዚያ ሁሉ ግፈኞች፤ እነዚያ ሁሉ በድኃ ላይ የሚስቁና የሚሳለቁ ሁሉም መሬት ሆነዋል፡፡ እነዚያ ሁሉ ድሆች ሲበደሉ፣ ሲያዝኑ፣ ሲያለቅሱ ካንዱ ሀገር ወደ ሌላው ሀገር ሲሰደዱ፣ ሲራቡ፣ ሲጠሙ፣ ሲታረዙ የነበሩ መሬት ሆነዋል፡፡

      ስንት ሰዎች የነበሩ ይመስልሃል?  

      የድኃ እንባ ሲፈስ የወንዝ ውኃ የሚፈስ የሚመስላቸው ስንት ሰዎች ነበሩ፡፡ ድኃ ሲጮህ ውሻ የሚመስላቸው ስንት ሰዎች ነበሩ፡፡ ድኃ ታስሮ ወይም በሌላ ጭንቅ ነገር ተይዞ ሲሞት የወፍ ግልገል የሚሞት የሚመስላቸው ስንት ሰዎች ነበሩ፡፡ ጉልበት ካለን ብለው በደካሞች ላይ ያሰቡትን ሁሉ የሚሠሩ ስንት ሰዎች ነበሩ፡፡ ሰውን ለማጥፋት እጅግ የሚጥሩ ሰውን ካላጠፉ እንቅልፍ የማይወስዳቸው ስንት ሰዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቀድሞ የነበሩት ሁሉም መሬት ሆነዋል፡፡ ከመሬት የተገኘ ሁሉ መሬት ስለ ሆነ ወደ መሬትም የማይመለስ ስለሌለ እኛም ነገ እንደዚያው እንሆናለን፡፡

      ስለዚህ በማናቸውም ምክንያት ቢሆን፤ የሰው ደስታውና አዘኑ እጅግ አጭር መሆኑን በጣም እወቅው፡፡

      ልጄ ሆይ፤ ቀን በሥራህ ላይ፤ ሌሊት በአልጋህ ላይ፤ የሚጠብቅህ እግዚአብሔር ነውና ማታ ስትተኛ፤ ጧት ስትነሣ እግዚአብሔርን አምላክህን መለመንና ማመስገን አትተው፡፡

        /ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፤ ለልጃቸው ለፈቃደ ሥላሴ የፃፉት ምክር፤

          ወዳጄ ልቤና ሌሎችም፤ ገጽ 76-100፤ አ.አ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ፤ 2002 ዓ.ም/

No comments:

Post a Comment