እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት
‹‹ታላላቆችም ብላቴኖቻቸውን ወደ ውኃ ሰደዱ፤ ወደ ጕድጓድ መጡ፤ ውኃም
አላገኙም፥ ዕቃቸውንም ባዶውን ይዘው ተመለሱ፡፡ አፈሩም ተዋረዱም
ራሳቸውንም ተከናነቡ።›› (ኤር. 14÷3)፡፡
አቤት ምድረ በዳ፤ አቤት ቃጠሎ፤ አቤት የውኃ ጥም፤ አቤት አቅም
ማጣት፤ አቤት ሥጋት፤ አቤት መጨካከን፤ አቤት መጣደፍ፤ አቤት መተራመስ፤ አቤት አዙሪት፤ አቤት መዛል፤ አቤት እፍረት፤ አቤት መዋረድ፤
አቤት መደበቅ፤ አቤት አለመፈናፈን፤ አቤት ማለክለክ፤ አቤት የዕንባ ጅረት፤ አቤት የዓይን መጠውለግ፤ አቤት የማይቆጠር በድን፤
አቤት የተማሱ ጉድጓዶች፤ አቤት አፉን የከፈተ መቃብር፤ አቤት የሕፃናት ጩኸት፤ የአዛውንቶች ሲቃ፤ አቤት ሰይፍ፤ አቤት ቸነፈር፤
አቤት መበተን፤ አቤት ክሳት፤ አቤት መከራና ሰቆቃ!
የተነሣንበት
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ወደ ኤርምያስ ስለ ድርቅ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ አፈሩ . . . ተዋረዱ . . . ራሳቸውንም
ተከናነቡ፤ የሚሉትን ቃላት ስናነብ፤ ልክ በዚያ ዘመን እንደ ነበረ ትኩስ ሀዘንተኛ የከበዱብን ነገሮች ወደ ፊታችን ይመጣሉ፡፡ ማንም
ሰው በሕይወቱ እንዲህ ያሉ ውርደቶች ባይሆኑ ጽኑ መሻቱ ነው፡፡ ይሁዳ ያለቀሰችበት፤ ደጆችዋም ባዶ የሆኑበት፤ ብርሃኗን የተነጠቀችበት፤
ጩኸቷን አብዝታ ያሰማችበት የጭንቅ ጊዜ፤ የኑሮ በረሃዎቻችንን ግልጥልጥ አድርጎ ያሳየናል፡፡
እግዚአብሔር የከለከለንን ማንም እንደማይሰጠን፤ የዘላለም አምላክ
ያላሰበንን ማንም እንደማያስበን፤ የአማልክት አምላክ ያልራራልንን ማንም እንደማይራራልን፤ የጌቶች ጌታ ያልሰበሰበንን ማንም እንደማይሰበስበን፤
የነገሥታት ንጉሥ ያልሞላውን ጉድለት ማንም እንደማይሞላው፤ እርሱ ከጨከነብን የማንም ፊት እንደማይበራልን የምንረዳበት ክፍል ነው፡፡
አብዛኛውን ጊዜ የእግዚአብሔርን ቁጣ በአንድ መንገድ ብቻ እንደምናየው ይሰማኛል፡፡ ከቅጣትና ከጥፋት መልእክቱ አንፃር! ዳሩ ግን
እንደዚያ ብቻ መልእክት እንዳለው እንዳናስብ የሚረዱን የእግዚአብሔር ትምህርቶች በቃሉ ውስጥ አሉልን፡፡ በዚሁ በነቢዩ በኤርምያስ
የተግሣጽ ክፍል ውስጥ ውሸተኛ ነቢያት በእግዚአብሔር ስም ያልተላኩትን፤ ያላዘዛቸውን፤ ያልተናገራቸውን ግን የልባቸውን ሽንገላ ለሕዝቡ
ሲናገሩ እናያለን፡፡ ሰላምን ለሕዝቡ ቢናገሩም፤ በረከትን ለሕዝቡ ቢተነብዩም እንደዚያ ግን አልሆነም፡፡