Saturday, May 10, 2014

አታላምዱን

                                           
                                   Please Read in PDF: Atalamdun

                ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት

       በአንድ አጋጣሚ በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ከሌላ ሁለት ወንድሞች ጋር እየተነጋገርን አሳብ እንለዋወጣለን፡፡ ታዲያ አንደኛው ወንድም አውደ ንባቡ ሊያስተላልፍ ከፈለገው ጠንካራ አሳብና ተግሣጽ ሸሽቶ ያነሠ ነገር ለማንጸባረቅ ሞከረ፡፡ ታዲያ በጊዜው ችላ ብዬ ያለፍኩት ዘግይቶ ግን ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር፤ ሰው እግዚአብሔር ካልረዳው በቀር የማይላመደው ነገር አለመኖሩን ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ ክፍል ክፉ ልምዶችን የሚቃወም ሆኖ ሳለ፤ በጊዜው ግን ወጣቱ እየተላለፈ ያለውን የመለኮት ቃል ቢያውቅም እንኳ ከእግዚአብሔር አሳብ ጋር ለመቆም ፍላጎት አላሳየም፡፡

       እኛ ያልታዘዝነውን ሌሎች እንዳይታዘዙት፤ እኛ ያልደረስንበትን ሌሎች እንዳይደርሱበት፤ እኛ የፈዘዝንበትን ሌሎች እንዳይነቁበት ዝቅታውን ማላመድ ከበደልም በደል ነው፡፡ በየዘመናቱ የእግዚአብሔር ቃል በብዙ ወጀብና አውሎ ውስጥ አልፏል፡፡ ነገር ግን ጎልቶ የማይታይና ቶሎ የማይታወቅ ቢሆንም እንኳ ቃሉን በሚመሰክሩ አገልጋዮች በኩል የሚዘረጋው የጠላት ወጥመድ፤ በተለይ በዘመናችን ለእውነት ተግዳሮት ነው፡፡ ለብዙ ነውሮችና ሃይማኖት ለበስ አመፆች የእግዚአብሔር ቃል እንደ ድጋፍና ሽፋን ሲጠቀስ ማስተዋል እየቀለለ መጥቷል፡፡

       በተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ሌሎች የከበረ እውነት የያዙ ክፍሎችን መተው፤ ቃሉን ጠምዝዞ የራስ ስውር አሳብ ሎሌ ማድረግ (ይህ ‹‹መረዳት አላቸው›› ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች ጭምር ‹‹ሰነፍ ስልት›› ነው)፤ በጠንካራ የቃሉ ተግሣጽ ላይ ለዘብተኝነት ማሳየት፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተፃፈው የእግዚአብሔር አሳብ ይልቅ ከፀሐይ በታች ያሉ የሰው ታሪኮችንና ልምምዶችን እንደ ዋና አሳብ ማግዘፍ፤ ተረትና ፌዝን የአገልግሎት ቅመም አድርጎ ማቅረብ፤ ሰዎችን በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በራስ ላይ መትከል (መንፈሳዊ ካድሬዎችን መፍጠር)፤ ለጌታ የሚመጣውን ክብርና ምስጋና ሳይሆን ራስን ስለ ማበልጸግና በመንፈስ ተሸሽጎ ለሥጋ መሰብሰብ ጥቂት መገለጫዎች ናቸው፡፡

       ወደ መረዳት ባለ ጠግነት ላልመጡና ከፍ ወዳለ መንፈሳዊ ልምምድ ላልደረሱ ክርስቲያኖች፤ ብርሃን እያወሩ ጨለማን ማላመድ፤ ጽድቅ እየተናገሩ ወደ ኩነኔ መስደድ፤ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ በሚል አገልግሎት ውስጥ የሟርትና የዛር መንፈስን መናፍስታዊ ጥማት ማርካት፤ በጎ እየሠሩ ጥልቅ የሆነውን የሰው መንፈስ በረቀቁ አመፆች መሙላት፤ ጌታን እየገለጡ ክርስቶስን መጋረድ፤ ጋኔን ስቦ፣ ለሰይጣን አጫጭሶ ለእግዚአብሔር መለፈፍ (በእግዚአብሔር አታሎ ለዲያቢሎስ ማስቆጠር) ምን ማለት እንደ ሆነ ለመረዳት ይቸገሩ ይሆናል፡፡ መንፈስን ሁሉ እንዳናምን፤ ግን እንድንመረምረው (1 ዮሐ. 4÷1) መታዘዛችን ለዚህም አይደል?

        ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ሕብረት እንኳን እንድንመረምረው ቃሉ ያዘናል (በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ እንዲል)፡፡ ክርስቲያን ወደ ውስጡ መመልከትና ሕይወቱን ማጥራት አለበት፡፡ መፋዘዝ እምነት ሆኖ አያውቅም፡፡ በመታወቅ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት የማይፈልገው ጠላት ዲያብሎስ እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፡፡ ወንዶች ፀጉራቸውን አያሳድጉ ሲባል መንፈሳዊ አመለካከታቸውን ማቀንጨሪያ (እውቀት አይደግ) ማለት አይደለም፡፡ ሴቶች እራሳቸውን ይሸፈኑ ማለትም በሰው አሳብ ተከናንበው ‹‹ሲጠሩት አቤት፤ ሲልኩት ወዴት›› አይነት ይሁኑ ማለት አይደለም፡፡ ሰዎች በክርስትናው ውስጥ በሰው የተላመዷቸው ጌታን የማያከብሩ የሥጋ ነገሮች እየጨመሩ መጥተዋልና ንቁ!

      በዚህ ርዕስ እንድጽፍ መነሻ የሆነኝ ክ/ሀገር ለአገልግሎት ሄጄ ያገኙኝ አዛውንት ናቸው፡፡ ወደ እኔ ቀርበው ልጃቸው በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት /ግብረ ሰዶም/ እንደሚሰቃይና መውጣት ቢፈልግም ልማድ አይሎ ባሪያ እንዳደረገው ነገሩኝ፡፡ በተጨማሪም እንዲህ ያለው ተግባር በበጎ አድራጎት ሽፋን፤ ስር እንደ ሰደደና እራሱን የቻለ ብልሃታዊ አካሄድ፤ የተጠና ስልት እንዳለው ገለጹልኝ፡፡ በጊዜው ለአዛውንቱ በቂ የሆነ ምላሽ እንደሰጠኋቸው ባይሰማኝም ዳሩ ግን ለእኔ የቤት ሥራ ሰጥተውኝ ተለያየን፡፡

      አሁን ያለንበት ጊዜ እያላመደን ካለው ነገር ውስጥ ይህ ‹‹የተመሳሳይ ፆታ ሩካቤ›› አንዱ ይመስለኛል፡፡ የዚህ ዓለም አንዱ ጠባይ ማላመድ ነው፡፡ ባለፉት ዘመናት ጆሮዎቻችንን ጭው የሚያደርጉ ብዙ ነገሮችን ሰምተናል፡፡ ዛሬ ተላምደነው የማንደነግጥበት፤ ዘወር በል ብለን የማንጋፈጠው፤ ቀሎን ተስማምቶን የምናላምጠው፤ ለመፍትሔ ሠርተን የማናስወግደው ብቻ ጆሮአችን ሲሰማው፣ ዓይናችን ሲመለከተው፣ እግራችን ሲደርስበት ፈግገን የምናልፈው ግን ክፉ እየበዛ ነው፡፡ 

     ቤተ እምነቶች፤ የአገር ሽማግሌዎች፤ የስነ ምግባር አስተማሪዎች፤ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች፤ በሕዝቡ ላይ ባለ አደራ መሪዎች፤ ደራሲና አርቲስቶች ሁሉም የጋራ ሸክም እንዳለባቸው ይሰማኛል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ዙሪያ ጠንከር ያለ ተግሣጽና በቂ ትምህርት አለው፡፡ በቀጣይ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ መንፈሳዊና ስነ ልቦናዊ አሳቦችን ማዕከል አድርገን እንደምንነጋገር ቃል እየገባን፤ ለአሁን ግን ከዚህ በታች የጠቀስነውን ‹‹የኢትዮጽያዊነት ድምጽ›› ከሚባለው ድረ-ገጽ ላይ ያገኘነውን ‹‹የአደጋው-ደውል-ድምጽ-በትምህርት-ቤቶች›› በሚል የተፃፈውን መረጃ እንድታነቡት እየጋበዝን፤ ያላችሁን አስተያየትና እውነተኛ መረጃ ብትልኩልን በቀጣይ ለሚኖረን የጽሑፍ ዝግጅት እንደሚጠቅመን በትህትና እንገልፃለን፡፡
           ድረ-ገጹ፡
                     http://ethiopiawinote.wordpress.com
       

1 comment: