Tuesday, May 13, 2014

ቀላል ነው!

                                   Please Read in PDF: Kelal New                                                   
                            ማክሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት  

    ‹‹እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፡- ነፋስ አታዩም፤ ዝናብም አታዩም፡፡ ይህ ሸለቆ ግን ውኃ ይሞላል፤ እናንተም ከብቶቻችሁም እንስሶቻችሁም ትጠጣላችሁ፡፡ ይህም በእግዚአብሔር ዓይን ቀላል ነገር ነው››  (2 ነገ. 3÷17)፡፡

        እግዚአብሔር ከልምምዶቻችን በላይ ነው፡፡ እኛን የሚያጽናናው ራሱን እያጣቀሰ ነው፡፡ እርሱ ብቻ ‹‹እኔ›› ሊል ይቻለዋል፡፡ እኔነት ከእኛ አንፃር ችግር ሲሆን፤ ከእግዚአብሔር አንፃር ግን መፍትሔ ነው፡፡ እኔነት ከእኛ አንፃር ኃጢአት ሲሆን ከእርሱ አንፃር ግን ጽድቅ ነው፡፡ እኔነት ከሥጋ ለባሽ አንፃር ሞት ሲሆን ከጌታ አንፃር ግን ሕይወት ነው፡፡ እኛ ማብራሪያችን ድካምና ብርታት፤ አቀበትና ቁልቁለት ሲሆን እግዚአብሔር ግን ያውና ሕያው ነው፡፡ ያለ፤ የነበረ፤ የሚኖር እንደ እግዚአብሔር ማን ነው? በዓለም ስሌት፤ በሰዎች የአስተሳሰብ ደረጃ፤ በስልጣኔ ክንድ የማይተገበሩ ነገሮችን የእኛ አምላክ ግን ሊያደርግና ሊሠራ ይችላል፡፡ የችግሮቻችን ልዕልና በእኛ ዓይኖች ፊት ብቻ ነው፡፡ በትልቁ እግዚአብሔር ዘንድ የማይቻል የለም፡፡ እግዚአብሔር ‹‹ቀላል ነው›› የሚላችሁ ገምቶ አይደለም፡፡ እርሱ የነገሮችን ጅማሬና ፍፃሜ ጠንቅቆ የሚያውቅ አዋቂ ነውና፡፡ /የሰውን ድካሙን አንተ ታውቃለህ እንዲል ቅዳሴው/

       እኛ ካልገባን፤ ገና ካልተረዳነው ማንነታችን ጋር የምንኖር ምስኪኖች ነን፡፡ ትንሽ ተጉዘን የረጅም የምንፈነጭ፤ ጥቂት ጨብጠን የብዙ የምንፎክር፤ እየተንገዳገድን የቆምን ይመስል፤ እየሸሸን የቅርብ ያህል የሚሰማን፤ እንኳን ከመንፈሳችን ከስሜታችን ጋር የተሸዋወድን፤ ‹‹ያፋልጉኝ›› የተለጠፈበት ሰሌዳ ቢኖር የእኛ እኔነት ነው፡፡ የእግዚአብሔር እጆች እንዲህ ያለውን ሕመምተኛ ማገላበጥ፣ ማጉረስና ቀና ማድረግ፤ ማውጣትና ማግባት ሰልችተው አያውቁም፡፡ ሰው በእግዚአብሔር ቋሚ እንክብካቤ ስር ነው፡፡ የነገሮች ክብደት በእኛ እንደምንኖር ለእኛ የመለፈፋችን ውጤቶች ናቸው፡፡

       ክርስቲያን ችግሩን የሚያነጋግርበት ቋሚ ቋንቋ ጌታ እግዚአብሔር ነው፡፡ ጉድለት ስለ ጉድለት በማውራት፤ ስቃይ ስለ ሰቆቃ በመናገር፤ መከራ ስለ ፈተና በመለፈፍ አይቀረፍም፡፡ እግዚአብሔር በጉድለታችን ፊት ጽኑ ሙላት ነው፡፡ እርሱ በስቃያችን ፊት የእረፍት ጥግ ነው፡፡ ጌታ በፈተናዎቻችን ፊት የማይቀለበስ ድል ነው፡፡ በዘመናት ሁሉ የተሻገርነው ሳይሆን ያሻገረን፤ ያመለጥነው ሳይሆን ያስመለጠን ሕያው ነው፡፡ ሰንሰለታችንን ለዘላለም አናየውም፡፡ ከእሥራት የፈታን ግን የዘላለም አምላክ ነው፡፡ ዕንባ ዕንባ እንደ ሆነ አይዘልቅም፡፡ አባሹ ጌታ ግን የዘወትር ትዝታችን ነው፡፡

        ጌታ የሁልጊዜ እልልታችን ነው፡፡ ኖኅ ከጥፋት ውኃ ያመለጠው በመርከብ ተንሳፎ ነው፡፡ ዳሩ ግን ውኃው ከደረቀ በኋላ መሥዋዕት ያቀረበው ለእግዚአብሔር እንጂ ለመርከቡ አልነበረም፡፡ ክብርን ሁሉ ሊወስድ የሚገባው እርሱ እግዚአብሔር ነውና፡፡ ኖኅ ከጥፋት ውኃ መድረቅ በኋላ ከመርከቧ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደ ነበረው አልተፃፈም፡፡ ታሪክና ቅርስ ብሎም አላስቀመጠም፡፡ እንደዚያ የመሆን አቅም በመርከቧ፤ እንደዚያ የማድረግ ፍላጎት በኖኅ ውስጥ አልነበረም፡፡ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ እግዚአብሔር ጋር መድረስ ምንኛ በረከት ነው? አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የመርከቧን ጥላነት ጠቅሶ አካሉ የክርስቶስ እንደ ሆነ ይነግረናል፡፡ ‹‹ሞገድ የማይሰብረው መርከባችን›› ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ!

        በኑሮአችን እግዚአብሔር በተለያየ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ወደ ሕይወታችን የሚያመጣቸው ሰዎችና ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ ዳሩ ግን ዓይን ሁሉ የተሰቀለውን ጌታ ይመለከት (ዕብ. 3÷1) ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ጽድቅ ይህ ነው፡፡ ጥላው ወደ አካሉ፤ ምሳሌው ወደ እውኑ፤ ንባቡ ወደ ትርጉሙ ካላደረሰን ከሚምረው ጋር በምሕረቱ፣ ከሚያከብረው ጋር በክብረቱ፣ ከሚራራው ጋር በበረከቱ እየተሸወድን፤ እርሱን ሳይሆን የእርሱን እያሳደድን እንኖራለን፡፡ ነገር ግን ሰዎች ቢሆኑ፤ ገንዘብ ቢሆን፤ ቁሳ ቁስ ቢሆን ሁሉም ለእግዚአብሔር ሊመጣ የሚገባውን ክብር ሊያስቀሩ ጉልበት የላቸውም፡፡ ሥርዓት ለውጦ የሚያነግሥ፤ አዋጅ በአዋጅ ሽሮ የሚያከብር፤ የጠላትን ክንድ አድቅቆ የሚያቆም፤ ወጥመድ ሰብሮ የሚያስመልጥ፤ የእሳትን ኃይል የሚያጠፋ፤ የአንበሶችን አፍ የሚዘጋ እግዚአብሔር ክብርና ምስጋና የእርሱ ብቻ ነው፡፡ ‹‹ይህች ትውልድ እርሱን የምትፈልግ ናት፤ የያዕቆብን አምላክ ፊት የምትፈልግ፡፡›› (መዝ. 23÷6) ተብሎ እንደተፃፈ፤ ፍለጋ ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ይጠጋል፡፡

        ተወዳጆች ሆይ፤ ነቢዩ እንዳለ እግዚአብሔር እንዲሁ ነው፡ ‹‹አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፡፡ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፥ ጕልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል።›› (ኢሳ. 40÷28-29)! እግዚአብሔር የሚያዘው በቃሉ ነው፡፡ ስለ እርሱ የተፃፈው፤ ለእኛ የተሰጠው ተስፋ፤ የገባው ኪዳን ሁሉ አንድ በአንድ ይፈጸማል፡፡ እርሱ ካለው የሚቀር፤ ከፈቀደው የሚተርፍ የለም፡፡ ልባችን ሙሉነትን የሚያገኘው በእግዚአብሔር እውነተኛ ቃላት ላይ ራሳችንን ካሳረፍን ነው፡፡

1. የዘላለም አምላክ፡ ለብዙዎች ዘላለም ማለት የነገሮች አለመቋረጥና ረጅም ጊዜ በሕልውና መቀጠል ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ ዳሩ ግን ይህ ብቻ ዘላለምን አያብራራውም፡፡ ዘላለም ያልተፈጠረ ማለትም ጭምር ነው፡፡ ብቻውን በጽናት የሚኖር (ዘፀ. 3÷14)! የአማልክትን አምላክ የዘላለም አምላክ እንለዋለን፡፡ ሁሉ በእርሱ ዘላለም ውስጥ ተቆጥሮለት፤ ተሰልቶለት፤ ድንበር ተሰምሮለት ይኖራል፡፡ ሊያኖር ሊያሳልፍ፤ ሊሠራ ደግሞ ሊያፈርስ እርሱ አምላክ ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ‹‹አምላክ አለኝ›› ማለት መደገፍ ነው፡፡ የምንደገፈው ደግሞ የማይጥል ነው፡፡ ከእርሱ ጋር ብቻ የዘላለምን ጫፍ እንነካለን፤ በሕልውና እንዘልቃለን፡፡ ቀናት አልጨበጥ ላሉን፤ ዘላለምን ያስጨበጠን ጌታ ስሙ ብሩክ ይሁን፡፡

2. የምድር ዳርቻ ፈጣሪ፡ እግዚአብሔር ሁሉን የፈጠረ፤ ገዥና አሳላፊ ነው፡፡ ፍጥረት የእጁ አሻራ፤ የክብሩ ነጸብራቅ፤ የውለታው ወዝ አርፎበታል፡፡ ከሆነው ሁሉ ያለ እርሱ የሆነ አንድ ስንኳ የለም፡፡ ሁሉም በውስንነቱ ውስጥ ሆኖ የዳርቻዎች ጌታ የሆነውን እግዚአብሔር ያከብረዋል፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ እጃችሁ ያጠረበት፤ መከናወን ያጣችሁበት፤ የጠበበባችሁና አላፈናፍን ያላችሁ ያ ነገር ምንድ ነው? እርሱ ጌታ ዳርቻዎችን ያሰፋል፤ መሰማሪያን ይሰጣል፡፡ እርሱን ክንድ አድርጋችሁ ‹‹ቀላል ነው››፤ ትምክህት አድርጋችሁት ‹‹ቀና›› ነው፡፡

       በረሃውን በጠል ሊያረሰርሰው፤ ደረቁን ሊያለመልመው፤ ሸለቆውን ያለ ዝናብና ያለ ነፋስ እይታ በውኃ ሊሞላው ቻይ ነው፡፡ ዳርቻዎችን ሁሉ የሚያጠጣ፤ ለስፍራው ሁሉ የሚበቃ በረከት እርሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ ለፈጠረው ሁሉ ታምኖ ቀለብ ሰፋሪ፤ ጎጆ ሆኖ አሳዳሪ፤ ከፊት ሆኖ በለምለሙ አሰማሪ፤ ሁሉ ሲተው ቀሪ ኗሪ የሠራዊት አምላክ፤ የጭፍሮች አለቃ እግዚአብሔር ነው፡፡

3. አይደክምም፤ አይታክትም፡ ልባችሁን ዝቅ፤ ዕንባችሁን ዱብ ስላደረገው ነገር ብዙ ልትናገሩ ብትችሉም፤ መዛል፤ መረታት፤ መውደቅ መነሣት የሌለበት ጌታ ግን ጉንጫችሁን የሚሞላ የምስጋና ቃል ነው፡፡ ድካም ቶሎ የሚከበን፤ በትንሹ ታካቾች፤ ቶሎ የምንከፋ፤ ተስፋ ለመቁረጥ ፈጣኖች ነን፡፡ የማይደክመው ብርታታችን፤ የማይታክተው ጽናታችን እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱን በመጠጋት ኪሳራ፤ ጉልበት አድርገነው መከራ ከንቱ ነው፡፡ ለሚደርስብን የሚደርስልን፤ ጭንቃችንን ትግሉ አድርጎ የሚታገልልን፤ እንደ ወፍ ከአዳኝ ወጥመድ የሚያስመልጠን፤ ወጥመድ ሰብሮ በድል ዜማ የሚሞላን፤ ‹‹እነርሱን ተዉአቸው፤ እኔን እንኩ›› የሚል እረኛ እግዚአብሔር፤ እርሱ ብቻ ጌታ ነው፡፡ ዛሬም ሕይወታችሁ በማይደክመውና በማይታክተው በእርሱ ቅጥር ውስጥ ነው፡፡   

4. የማይመረመር ማስተዋል፡ ‹‹የአዋቂዎችን ማወቅ ከንቱ የሚያደርግ አዋቂ ነው›› /ቅዳሴ/ እግዚአብሔር ምርምራችን፤ መጠበባችን አያውቀውም፡፡ ራሱን የሚገልጥ፤ እንደ ፈቃዱ የሚያብራራልን፤ ወደ ሙላቱ የሚያደርሰን እርሱ ነው፡፡ ቃሉን መርምረን፤ ከእውቀት ከፍለን ብናውቅም፤ እግዚአብሔር ሙሉ እውቀት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሙሉ ጥበብ ነው፡፡ እርሱ ሙሉ ማስተዋል ነው፡፡ ሰው ከእውነት ከፍሎ ያውቃል፤ ከጥበብ ከፍሎ ይጠበባል፤ ከብርታት ከፍሎ ይበረታል፤ ከማስተዋል ከፍሎ ያስተውላል፤ እርሱ ጌታ ግን ሙላታችን ነው፡፡ ሙሉነት በእርሱ በኩል በመታየት ነው፡፡ ፈላስፎች፤ ሊቃውንትና ነገሥታት መርምረውና አስመርምረው ሊደርሱበት አልቻሉም፡፡ እርሱ የረዳው ብቻ እርሱን ይረዳዋል፡፡ ጌታ ያገዘው ብቻ ጌታን ይገዛዋል፡፡     

5. ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፡ ቃሉ ‹‹ዳዊት ግን በአምላኩ በእግዚአብሔር ልቡን አበረታ›› (1 ሳሙ. 30÷6) እንደሚል፤ እግዚአብሔር ልባችሁ የሚበረታበትን የመጽናናት ድምጽ ወደ እናንተ ሊያመጣ፤ የምትቆሙበትን ኃይል ሊያጎናጽፋችሁ የታመነ ነው፡፡ ኃይል ለነገሮቻችን ክንዋኔ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ የኃይል እጥረት እንዳለባቸው በምንሰማበት አጋጣሚ ብዙ ኪሳራና ምሬትን አስተውለናል፡፡ አቅም ማጣት ምንኛ ያማል? ሰው የሚሞተው እንኳ የመኖር ኃይሉ ተዳክሞ እጅ ሲሰጥ ነው፡፡ በቃ! ልብ እንደ ልብ ለመሥራት፤ አእምሮ እንደ እንደ ሕሊና ለመምራት፤ ጨጓራ እንደዚያው በአግባቡ ለመፍጨት ኃይል ሲከዳው፤ መተግበር ሲሳነው ሰው ያኔ በድን ነው፡፡ ጉዞውም መቃብር ነው፡፡

       ድካማችንን እንደ እግዚአብሔር የሚረዳ ማነው? ሰዎች ባወቁት ትንሽ ድካም እድሜ ዘመናቸውን በፍርድ ያቆስሉናል፡፡ በግብዝ ቃል ያደሙናል፡፡ ድካማችን እንደ መጽሐፍ የተገለጠለት፤ ውስጣችን እንደ ምድረ በዳ የተራቆተለት ጌታ ግን ኃይልን ያስታጥቀናል፡፡ ለወደቅንለት ሳይሆን ለቆመልን ለእርሱ ያበረታናል፡፡ እግሮቻችን እንደ ብሆር እግሮች፤ አጥንቶቻችን እንደ ይሳኮር ነገዶች ይጸናል፡፡ ልበ ቆራጥ፤ አጥንተ ብርቱ፤ ኃያል ጽኑ የሚያሰኝ እግዚአብሔር ስሙ ይቀደስ፡፡ ‹‹ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ›› (ፊል. 4÷13)፡፡ አዎ እችላለሁ!

6. ብርታትን ይጨምራል፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ደመወዝ ጭማሬ እንዴት ነው? ዘገየ፣ ታለፋችሁ፣ አነሠ፤ እና ተከፋችሁ? እንዲህ ያለውን ተራ የሚመስል ነገር እንኳ የምንሸከምበት፤ ልባችን ሰፍቶ የምናልፍበት ብርታት ከእግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱ ብርታትን ዕለት ዕለት ይጨምራል፡፡ ትላንት በበላነው ዛሬ እንደማንቆም፤ ትላንት በበረታንበት ዛሬም ብርቱ አንሆንም፡፡ እግዚአብሔር ሁኔታዎቻችን ምን ያህል ብርታት እንደሚጠይቁ በልክ ያውቃል፡፡

      በዚያ በኩል ምን ያህል ፈተና ጨመረ? በዚህ በኩልስ ምን ያህል ሠልፍ ከበበን? ጌታ ስንቅ ይጨምራል፤ ጦር ይጨምራል፤ ጭፍሮችን ያበዛል፤ ምሽጎችን ይገለብጣል፤ እንደ እልፍ ይዋጋል፤ ምርኮን አስጨንቆ ይበዘብዛል፤ ድል ለእኛ ተቆጥሮ ምስጋናን እርሱ ይወስዳል፡፡ ጨምሮ አያንሰውም፤ ቀንሶ አይጎድለውም፤ የኔ ጌታ!   
                                  - ይቀጥላል -

4 comments:

  1. ጌታ ስንቅ ይጨምራል፤ ጦር ይጨምራል፤ ጭፍሮችን ያበዛል፤ ምሽጎችን ይገለብጣል፤ እንደ እልፍ ይዋጋል፤ ምርኮን አስጨንቆ ይበዘብዛል፤ ድል ለእኛ ተቆጥሮ ምስጋናን እርሱ ይወስዳል፡፡ ጨምሮ አያንሰውም፤ ቀንሶ አይጎድለውም፤ የኔ ጌታ! Hallelujah!

    ReplyDelete
  2. ‹‹ዳዊት ግን በአምላኩ በእግዚአብሔር ልቡን አበረታ››

    ReplyDelete
  3. ድካማችንን እንደ እግዚአብሔር የሚረዳ ማነው? ሰዎች ባወቁት ትንሽ ድካም እድሜ ዘመናቸውን በፍርድ ያቆስሉናል፡፡ በግብዝ ቃል ያደሙናል፡፡ ድካማችን እንደ መጽሐፍ የተገለጠለት፤ ውስጣችን እንደ ምድረ በዳ የተራቆተለት ጌታ ግን ኃይልን ያስታጥቀናል፡፡ ለወደቅንለት ሳይሆን ለቆመልን ለእርሱ ያበረታናል፡፡ Amen!

    ReplyDelete
  4. ‹እነርሱን ተዉአቸው፤ እኔን እንኩ››

    ReplyDelete