በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወንጌል ያስተማርኳትን አንዲት ሴት በቢሮዬ መንገድ ላይ አግኝቻት፤
በፀጉሯ መንጣት፤ በሰውነቷ መግዘፍ፤ በፊቷ መሸብሸብ ስገረም፤ ‹‹የነገርከኝ ቃል ግን አላረጀም›› አለችኝ፡፡ ታዲያ ስለ ባለቤቷና
ልጆቿ እየጠየኳት፤ በመሐል ‹‹ምን ሆነህ ነው? ፊትህ ደህና አይደለም›› እያለች ምራቋን እጇ ላይ እንትፍ ብላ ለእኔ የማይታየኝን
እሷ የምታየውን ከፊቴ ላይ ታብሳለች፡፡
በእርግጥ በጊዜው ያዘንኩበት ነገር ቢኖርም፤ ያ ከአሳቤ በስተ ውስጥ የነበረ ነው፡፡ ሴቲቱ ፊቴ ላይ ምን ታይቷት እየደጋገመች ምራቅ
እንዳጠገበችው ባላውቅም፤ በጊዜው ግን ቅንነቷን እንዳደነቅሁ አስታውሳለሁ፡፡ ምንም እንኳን ለጭርት ወጪ ብታስወጣኝም ማለት ነው፡፡
ሴቲቱ እንደ ከፋኝ እያወራች በምራቅ ጉንጬን አራሰችው፡፡ በጊዜው እኔ ያዘንኩበት ነገር እድሜው አጭር፤ ክብደቱ ቀሊል፤
መፍትሔው ግልጽ ነበር፡፡ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን።›› የሚለው የታመነ ቃል ልቤን ሞልቶት ነበር፡፡ የከፋኝን ለማስወገድ
/በእርሷ ግንዛቤ/ ከከፋኝ የከፋ ነገር አደረገች፡፡ እንግዲህ ይህ ከሁለት አመታት በፊት የሆነ አጋጣሚ፤ በዚህ ርዕስ ዙሪያ ልጽፍ
ሳስብ ትዝ አለኝ፡፡ ለመነሻም እንዲሆን አሰብኩ፡፡