Monday, February 9, 2015

ያዘጋጃል

                             በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

  ሰኞ የካቲት 2 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

        ‹‹እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፦ በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? በቀንድህ ዘይቱን ሞልተህ ሂድ በልጆቹ መካከል ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተልሔም እልክሃለሁ አለው።›› /1 ሳሙ 16÷1/!

        ‹‹. . . ሁሉን ያዘጋጀ ግን እግዚአብሔር ነው›› /ዕብ. 3÷4/፤ በብዙዎቻችን ልብ ውስጥ ዕረፍት እንዲሰማን ከሚያደርጉ የእግዚአብሔር አሳቦች መሀል አንዱ ነው፡፡ ብዙ ወገኖች ለድግሳቸው ማጀቢያ ጥቅሱን ይጠቀሙታል፡፡ ዳሩ ግን በሰው ዝግጅት ውስጥ የምናወጣቸው ብዙ እንከኖች ይኖራሉ፡፡ ሰው የቻለውን ያህል ተዘጋጅቶ ገና አሁንም የዝግጅት እጥረት እንዳለበት ልናወራ እንችላለን፡፡

        ሙሉ ያልነው ጎድሎ፤ ረጅም ያልነው አጥሮ፤ መልካም ያልነው ከፍቶ፤ ጉልህ ያልነው ደብዝዞ፤ ይበቃል ያልነው አንሶ እንቸገራለን፡፡ የሁሉም ዓይን ተስፋ በሚያደርገው /መዝ. 144፤15/ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ፈጽሞ እንዲህ የለም፡፡ እርሱ እግዚአብሔር የሚያስፈልገንን ሳንጠይቀው ቀድሞ ያውቃል፤ ከመሻታችንም አልፎ ሁሉን ያዘጋጃል /ማቴ. 6፡32/፡፡


        ዝግጅት ከዕለታዊ ኑሮአችን ጋር በእጅጉ የተያያዘ ነው፡፡ ሰዎች በመናገርና በመሥራት ውስጥ ይህንን በየደረጃው ይተገብራሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ያለ በቂ ዝግጅት በሚሆኑ ነገሮች ውስጥ ማፈር ተከትሎ ይመጣል፡፡ ከምድሪቱ መልክ መካከል እንዲህ ያለው ተጠቃሽ ነው፡፡ ሰዎች ለራሳቸው በደገሱት የሚያፍሩባት መልክዓ ምድር ውስጥ፤ ሥጋና ደም ከጋገረው አለመጥገቡ፤ ከጠመቀው አለመርካቱ፤ ከሸመነው አለማጌጡ፤ ከቀለሰው አለማረፉ ከፀሐይ በታች ያለው ሥርዓት ደማቅ ንባብ ነው፡፡

        ተወዳጆች ሆይ፤ እግዚአብሔር በግድ ያስፈልገናል፡፡ የተራቡ የሚያነቡትን ዕንባ፤ የጠገቡ ወገባቸውን ታጥቀው ያነቡታል፡፡ ፈተናና መከራ መንገዳቸው ላይ እንደ ጠጠር የተነጠፈባቸው ወገኖች የሚጨነቁትን ጭንቀት፤ ትርፍ ወሬ፣ ትርፍ ልብስ፣ ትርፍ ሀብት ያካበቱ ወገኖችም ይጨነቁታል፡፡ መከራ እንደ መዓት በሚታይበት የሰው ስርዓት መካከል ምቾት ቅጣት የሆነባቸው ብዙ ወገኖችን እናያለን፡፡

       እውነት እላችኋለሁ፤ አትጨነቁ ያለን /ማቴ. 6፡32/ ጌታ ያስፈልገናል፡፡ በጎ ስጦታ፤ ፍጹም በረከት /ያዕ. 1፤17/ ያለው አምላክ ያስፈልገናል፡፡ እርሱ ስለ ኑሮአችን ይገደዋል፡፡ መውጣትና መግባታችን ያሳስበዋል፡፡ ጉዳት ስቃያችን ይሰማዋል፡፡ የልጆቻቸውን ጥቃት ከማይፈልጉ የሥጋ ወላጆች ሁሉ በላይ መልካሙ እረኛ እግዚአብሔር ስለ ልጆቹ ይቆማል፡፡   

      ሰዎች ለሚያልቀው ደስታም፤ ለጊዜው ሀዘንም አደግድገው በሚደግሱበትና በሚዘጋጁበት ሁኔታ ውስጥ ወደ ዘላለም የጠራን እግዚአብሔር ትልቅ ነው፡፡ የተወደዳችሁ ሆይ፤ እያለቀሳችሁለት ያለው ነገር ምንድነው? ምናልባትም እግዚአብሔር የናቀው እንዳይሆን? የሰማያትና የምድር ጌታ የቆረጠበትን ልትቀጥሉ፤ የቀበረውን ልትምሱ፤ የወሰደውን ልታስመልሱ እንዳይሆን?

      በእምነት እየተመላለስን እንደሆነ እየተሰማን ዕረፍት የማይሰማን ፈቃዱን ባለማስተዋል ነው፡፡ የሳቅንለትን እግዚአብሔርና ሰማያት እንደሚስቁለት፤ ያለቀስንበትን ደግሞ መለኮት እንደሚኮሳተርበት ማሰባችን፤ ያለቀስንለትን ሁሉ ጌታ እንደሚራራለት፤ ደግሞ ያፌዝንበትን እርሱ ቸል እንደሚለው መስማማታችን እምነታችንን ምሪት አልባ አድርጎታል፡፡

      መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ /ማቴ. 22፡29/ እንደተባለ፤ ሰው እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ይጠፋል፡፡ ‹‹የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው?›› እግዚአብሔር ለነቢዩ ሳሙኤል ያቀረበው ጥያቄ ነበር፡፡ ምክንያታችን የቱንም ያህል ሊሆን ቢችል የእግዚአብሔርን ጽድቅ አያህልም፡፡ እርሱ በጨከነበት ላይ ጨክኑና ዘወር በሉ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ወደ ፊት!

      ሳሙኤል በዙፋን ላይ ላለው ሲያለቅስ፤ እግዚአብሔር ምድረበዳ ላይ ነበረ፡፡ ሳሙኤል በብዙ ተጎናባሾች መካከል ላለው ንጉሥ ሲንበረከክ፤ እግዚአብሔር ግን በወንድሞቹ ንቀት የጠገበውን በግ ጠባቂ ብላቴና ያዘጋጅ ነበር፡፡ አቤቱ ሆይ፤ አሳብህን የሚያህል ማሰብ፤ ሥራህንም የሚተካከል ተግባር የለምና ተመስገን፡፡

      እውነት ያለው እንጂ ዕንባ ያለው ሁሉ የሰማይን ደጅ አያስከፍትም፡፡ ከጽድቅ ጋር የቆሙ እንጂ በሥጋና በደም የተመሸጉ የመጣውን ቁጣ አይመልሱም፡፡ ፍም እስክትመስሉ የምታለቅሱለትን፤ ታጥቃችሁ የምትሟገቱለትን፤ አትንኩን ዜማ ሠርታችሁለት የተሰለፋችሁለትን በእምነት መርምሩ፡፡ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ከናቀው ጋር ቆማችሁ ምናልባት እንዳትገኙ፡፡

      በክርስቶስ የምወዳችሁ፤ ያዘናችሁለት ሁሉ እንደሚያሳዝን፤ የራራችሁለትም ሁሉ እንደሚያራራ አታስቡ፡፡ አካሄድን ከእግዚአብሔር ጋር ማድረግ ማለት እርሱ ያከበረውን አክብሮ የናቀውንም ንቆ ነው፡፡ በኑሮአችሁ ውስጥ ለሀዘን ርዕስ የሆኗችሁ ብዙ ሁኔታዎችን አስተናግዳችሁና እያስተናገዳችሁ ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን እግዚአብሔርን በቃሉና በጸሎት በኩል አድምጡት፡፡

      ማለፍ የማይችሉ ሰዎች እግዚአብሔር ጋር መድረስ አይችሉም፡፡ ነገር ግን ሁሉን እናልፋለን፤ ክርስቶስ ጋር ብቻ ስንደርስ እናርፋለን፡፡ ‹‹እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ›› /ማቴ. 11፡28/ ያለን መድኃኒት ክርስቶስ ኢየሱስ በእርግጥም ያሳርፋል፡፡

      ሀዘን ያጎሳቆላችሁ፤ ብቸኝነት ያሳነሳችሁ፤ ፈተና የበረታባችሁ፤ የወዳጅ ፍላፃው ለወጋችሁ እግዚአብሔር ‹‹አዘጋጅቻለሁ›› ይላችኋል፡፡ ለሳኦል ዕንባን የምታፈሱ፤ ከእግዚአብሔር የሆነውን ልብ በሉ፡፡ ያመነው አምላክ ስለ እያንዳንዱ የሕይወታችን ክፍል ያስብልናል፡፡ አዳም ከመፈጠሩ አስቀድሞ ለአዳም የሚያስፈልገው ሁሉ በእግዚአብሔር አስቀድሞ እንደተዘጋጀ ልብ በሉ፡፡

      ኤልያስ ሞቱን እየተመኘ፤ እግዚአብሔር ግን በሕይወት ሊወስደው የእሳት ሠረገላ አዘጋጅቶ ነበር /1 ነገ. 19፡4፤ 2 ነገ. 2፡11/፡፡ አብርሃም ልጁን ሊሠዋ ይዞት ሲሄድ እግዚአብሔር ግን መሥዋዕትን አዘጋጅቶ ነበር፤ ‹‹አብርሃምም፦ ልጄ ሆይ፥ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል አለው ሁለቱም አብረው ሄዱ›› /ዘፍ 22÷8/፡፡ ለችግሩ በሚመጥን ጉልበት እግዚአብሔር መፍትሔን ያዘጋጃል፡፡

      እያለቀስን የሚመጡ የእግዚአብሔር የደስታ ድምፆች፤ በሞቱብን ነገሮች ላይ የሚላኩ የትንሣኤው ቃላት ለደረቁብን ብዙ ነገሮች ልምላሜ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ከተንበረከክንበት አባብሎ ብቻ ሳይሆን ገስፆም ያስነሣል፡፡ ዕንባችንን በእሽታ ብቻ ሳይሆን በእንቢታም ያደርቃል፡፡

      እርሱ ያየላችሁን በእምነት እዩ፡፡ ሰው ያለ እግዚአብሔር እንጂ ያለ ሰው ይኖራል፡፡ የተናቀውን ሳኦል አክብሮ ከመኖር የናቀውን እግዚአብሔርን አክብሮ መኖር ለእውነት መታዘዝ ነው፡፡ ነቢዩ ሳሙኤል ዕንባውን ጠረገ፤ ያልገባውን ዘግይቶም ቢሆን አስተዋለ፤ ያፈሰሰው ዕንባ አልቆጨውም፤ የእርሱ ቁጭት እግዚአብሔር ያዘጋጀውን አለማስተዋሉ ነው፡፡


     ተወዳጆች ሆይ፤ እንግዲህ የሰውን ሳይሆን የእግዚአብሔርን፤ የጊዜውን ሳይሆን ዘላለማዊውን ልብ በሉ፡፡ ዕንባችሁን ጥረጉ፤ ያጠፋችሁትን ጉልበት ዘርጉ፤ በእውነትና በመንፈስ ካልሆነ በቀር እግዚአብሔር በዚህ መንገድ አይከብርም፡፡ እግዚአብሔር በጨከነበት ላይ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ጨክኑ፡፡ ጸጋና እውነት ያግዛችሁ!   
                                                        ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/! 

No comments:

Post a Comment