በስመ አብ
ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
አርብ የካቲት 6 ቀን 2007 የምሕረት
ዓመት
ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አንድ አጋጣሚ በዚህ ሰሞን ትዝ ይለኛል፡፡
ስልክ ተደውሎ መልእክት እንዳለኝ ተነገረኝ፡፡ መልእክቱ ከማን እንደመጣ፤ ምን እንደ ሆነ ለመጠየቅ ያደረኩት ሙከራ፤ እኔን ለማስደነቅ
ሊደረግ ባለ አሳብ ምክንያት ዘገየ፡፡ ይህንንም ‹‹ይቆይህ›› ብለው አሳሰቡኝ፡፡ እኔም ለጊዜው ካላወኩት ሰው የመጣውን መልእክት
ለመቀበል አመነታሁ፡፡ ዳሩ ግን የተላኩት ሰዎች ዋጋ ተቀብለውበታልና ጠንከር ባለ ቃል ጭምር የት እንዳለሁ ደጋግመው ጠየቁኝ፡፡
ሽጉጥም
ቢሆን አደባባይ ላይ ይሻላል ብዬ ፒያሳ ከምን ይልክ ሐውልት ዝቅ ብሎ ባለው አካባቢ ፀሐይ እየሞኩ፤ መጽሐፍ ገልጬ ቀጠርኳቸው፡፡
ቀጥሎ ምን እንደ ሆነ ለመናገር ትንፋሽ እንድሰበስብ ፍቀዱልኝ . . . መልእክተኞቹ አካባቢው ላይ ደርሰው በስልክ ልብስና መልኬን
ጠየቁኝ፡፡ እግዚአብሔር አያድርስባችሁ፤ ሁለት ቁመታቸው ዘለግ፤ ደረታቸው ሰፋ፤ ጡንቻቸው ፈርጠም ያሉ ወጣቶች በፍጥነት ወደ እኔ
እየተራመዱ መጡ፡፡
ለእኔ
ሕይወት ክርስቶስ ሞትም ጥቅም ነውና /ፊል. 1፡21/ የሚለው እምነቴ፤ በዙሪያዬ ያለው የሚተራመስ ሕዝብ ኮቴ ሁለቱም ከውስጥና
ከውጪ እየጮሁብኝ ፊት ለፊቴ ሁለት ሰው ቆመ፡፡ ስሜንና ስልኬን አረጋግጠው ለጊዜው ባልገባኝ ፉጨት ሦስተኛ ሰው ትልቅ የጎፈረ ቀይ
አበባ /ጽጌረዳ/ ይዞ መጣ፡፡ ያልዘረጋሁት እጄ ላይ አስቀምጦ፤ የላከልኝ ሰው ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እንደሚደውልልኝ አንሾካሽኮብኝ
ከሌሎቹ ጋር በፍጥነት ሄደ፡፡
በአንድ በኩል
አገሬ ላይ እንደዚህ ዓይነት ሰርፕራይዝ መኖሩን አለማወቄ ከመረጃ እርቄ ይሆን እያልኩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሚያስደስተኝን ሳያውቅ
በጠራራ ፀሐይ አደባባይ ላይ፤ በብዙ ተመልካች መካከል ሊያስደስተኝ የሞከረውን ሰነፍ ሰው ለማወቅ ልቤ እየተቻኮለ፤ የፊቴን ላብ
በሦስት ብር ሶፍት እየጠረኩ፤ በጉልበተኛ ከፍዬ የማላሸክመውን አበባ ተሸክሜ ሶምሶማ ተራመድኩ፡፡
ከዘብራቃ ስሜቴ የስልኬ ድምጽ አነቃኝ፡፡ ከአገር ውጪ የተደወለ፤ የማላውቀው
ስልክ ነበር፡፡ አንስቼ ወደ ጆሮዬ ሳስጠጋው ለማመን እየተቸገርኩ የማውቀውን ድምጽ ሰማሁ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተማርኳት፤ ሁሉን
ለሚችል አምላክ በእምነት አሳልፌ የሰጠኋት ልጅ እንደ ውለታ ቆጥራው እኔን ለማስደሰት የላከችው እቅፍ አበባ ነበር፡፡ ስሜቴን ገስጬ
በመንፈስ ተናገርኳት፡፡
አለመተዋወቃችን፤
ለከበረው ወንጌል የሰጠችው ቦታ፤ እውነት የሌለው ተራ ሰው የሚሆነው አይነት ድፍረቷ መደነቅ ሞላብኝ፡፡ እርሷ እኔን ያስደስታል፤
ወዳጅነታችንን ያጠናክራል፤ ቀጥሎ ላለው አሳቧ ልቤ ላይ መንገድ ይጠርጋል ያለችው ለመቆራረጥ /ለልዩነት/ ሆነ፡፡ በመንፈስ ከሆነውና
ሞትን ከሚሻገረው ኅብረት ይልቅ ከዚህ ያነሰው ተልቆባት በምርጫዋ ተቆራረጥን፡፡
ተወዳጆች ሆይ፤ ‹‹እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ
የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ
ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ
ነው።›› /ኤፌ. 2፡14-16/ ተብሎ እንደተጻፈ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም የእውነተኛ ኅብረት መሠረት ነው፡፡
ለክርስቲያን የግል ሕይወት፤ የቤተሰብ ኑሮ፤ ማኅበራዊ ግንኙነት ትልቁ
የአንድነት ዋስትና ክርስቶስ ነው፡፡ ከፀሐይ በታች ባለው የሰው ኑሮ ስርዓት መካከል ግንኙነት ሊቆምባቸው እንደሚያስችሉ የሚታሰቡ
ብዙ የሰው መንገድና ልማዶች ይኖራል፡፡ እኔ ግን የሚበልጠውንና መሠረታዊውን ነገር በጌታ ታምኜ እነግራችኋለሁ፡፡ ግንኙነት የሚቆመው
የጥልን ግድግዳ በሥጋው ባፈረሰው፤ ስለ ኃጢአታችንም ዋጋ ራሱን ለእግዚአብሔር
የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ አሳልፎ በሰጠው በጌታችን በኢየሱስ ነው /ኤፌ. 5፡2/፡፡
ያቺ እህት ያስደስተዋል ያለችው ለሀዘኗ ሆነ፤ ሁሉን የሚያስደስት ስጦታ
ክርስቶስ ነው /ዮሐ. 3፡16/፡፡ ለዚህ ዓለም ገጽታና ጠባይ ባይመችም በክርስቶስ የሆነው ነገር ግን እውነት ነው፡፡ ደስታዎቻችን
እግዚአብሔርን ቢያጣቅሱ፤ እውነትን መሠረት ቢያደርጉ፤ ከማያልፈው ጋር ቢተሳሰሩ ኖሮ ፈረቃውና ጊዜ መጠበቁ ባላስፈለገ ነበር፡፡
የክርስትናው ፍቅር እግዚአብሔር ነው /1 ዮሐ. 4፡8/፡፡ በዚህም ተነሡና ሀሴትን አድርጉ፡፡ መሠረቱ ይህ የሆነለትንም ፍቅር ተሰጣጡ፡፡
‹‹ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር
ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል።›› /ሮሜ 5፡8/፤ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ሦስት ‹‹ሳለን›› ታስተውላላችሁ፡፡ ደካሞች ሳለን፤
ኃጢአተኞች ሳለን፤ ጠላቶች ሳለን፤ ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቷል፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳናል፡፡ በጌታ
የተወደዳችሁ ቤተሰቦቼ፤ እግዚአብሔር እንደሚወዳችሁ ማሳያው ምንድነው? እናንተስ ይህንን እንዴት ታውቃላችሁ?
ሰዎች
እንደ ሰው ባለው ኑሮ ስኬታቸውን ተከትሎ እግዚአብሔር እንደሚወዳቸው ያስባሉ፤ ደግሞም ይታሰባሉ፡፡ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ለእኛ
ያለውን ፍቅር የምናውቅበት ዋናው መንገድ ምንድነው? ሰዎች እግዚአብሔር እንደሚወዳቸው በብዙ መንገድ ሊያብራሩልን ይችላሉ፡፡ ቃሉ
ግን እግዚአብሔር እርሱ ራሱ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያስረዳን ገና ደካሞች፤ ኃጢአተኞችና ጠላቶች ሳለን ‹‹ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቷልና››
እንደ ሆነ ያሳስበናል፡፡
ከዚህ ሌላ
የእግዚአብሔርን ፍቅር የሚያስረዳ ነገር የለም፡፡ ፍቅር እንደሌለ፤ ግብዝነት እንደበዛ በሚለፈፍበት፤ በአንድነት ሽፋን ልዩነት፤
ተቃቅፎ ግፊያ በበዛበት የዚህ ዓለም ስርዓት ውስጥ ትልቁ ፍቅር የተብራራው ቀራንዮ ላይ ነው፡፡ ጠላት ዲያብሎስ እግዚአብሔር በክርስቶስ
የገለጠውን ፍቅር ማረሳሻና ማራከሸ ቀይ አስለብሶ፤ ቀይ አበባ አስታቅፎ፤ ኃጢአት የሚያራጨውን ወገኔን በዚህ ሰሞን አስበዋለሁ፡፡
ሸክሜ ሸክማችሁ የሆነ በብርቱ ጸልዩ፡፡ አጀንዳ የሚቀርፀውን፤ ርዕስ የሚሰጠውን ሰይጣን በኢየሱስ ስምና ሥልጣን በእውነትና በመንፈስ
ሆናችሁ ተዋጉ፡፡
ተወዳጆች ሆይ፤ መንፈሳዊ ሰው ከሚታየው አልፎ ሊያይ ያስፈልገዋል፡፡ ደፍረን
በዚህ ጉዳይ ቁርጥ ነው! ልንልና ልንቆርጥም ይገባል፡፡ የካህናት አለቆችና የመቅደስ አዛዦች እንዲሁም ሰዱቃውያን ጴጥሮስና ዮሐንስን
በኢየሱስ ስም ፈጽመው እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ ባዘዟቸው ጊዜ ‹‹ቁረጡ›› ብለው መለሱላቸው /ሐዋ. 4፡19/፡፡ ክርስቲያን
ሄደት መጣ፤ ወጣ ገባ የሚል ሳይሆን በክርስቶስና በክርስትናው እውነት የቆረጠ ነው፡፡ መቀደሳችን ከዓለም ልማድና ወግም ጭምር ነው፡፡
በጥቂቱ የማትጨክኑ ከሆነ በሚበልጠውማ እንዴት?? ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!
Ewnet new ye Fikir tigu ...demo tigunim yalefew Geta yebarek.....more bless!!!
ReplyDeleteተባረክ፤ በክርስቶስና በክርስትናው እውነት መቁረጥ ግድ ነዉ። የሰከነ ጽሁፍ ነዉ፤ ጌታ በልጅነት ሲጠራህ አቤት! በማለትህ ለትዉልድ የሚበቃ ጥበብ ሰጠህ፤ አደራህን ይህንን ፀጋ ተንከባከበዉ።እኔም እጸልያለሁ።
ReplyDelete