ሰኞ የካቲት
16 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት
1.
መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ አጥና፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን ሳያስታጉሉ ማጥናት ትልቅ በረከት ነው።
ሀ/
እንጀራ የሥጋ ምግብ እንደሆነ የእግዚአብሔር ቃልም የመንፈስ ምግብ ነውና። «ሰው በእንጀራ ብቻ ሊኖር አይቻልም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ።›› (ማቴዎስ፡4፡4)፤ ‹‹ለሚጠፋ መብል አትድከሙ፤ ለዘለዓለም ለሚኖረው ምግብ (መብል) እንጂ›› (ዮሐ.6፡27)፡፡
ለ/
ማጥናትን አንድ ቀን የተውህ እንደሆነ ፈጽሞ ለመተው ልምድ ምናልባት ይሆንብሃልና።
ሐ/
ምግብ ለሰውነት አስፈላጊ እንደሆነ እንዲሁም ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ለመንፈሳዊ ሕይወት አስፈላጊ ነው። ሙዋቹ የእንግሊዝ ንጉሥ ጆርጅ 5ኛ ማናቸውም ሥራ ቢኖርባቸው መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ያነቡ ነበር ይባላል። ጆን ክሪዞስቶም በሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት በየቀኑ ከሚያጠኑት በላይ የሮሜን መልእክት በሳምንት ሁለት ጊዜ ያነቡት ነበር። በየቀኑ 20 ምዕራፍ የሚያነብ አንድ ወዳጅ አለኝ፡፡ በየቀኑ ብዙ ምዕራፍ ማጥናት አስፈላጊ አይደለም። ነገር ግን ጥዋት አንድ ምዕራፍ ወይም የምዕራፍ አንድ ክፍል ቢቻልም ማታ ሌላ ምዕራፍ ማጥናት አስፈላጊ ነው።
2.
ለማጥናት የተወሰነ ጊዜ ይኑርህ፡፡
አንድ ሰዓት ወይም የበለጠ ሊሆን ይቻላል፤ ነገር ግን ይህ የማይቻል እንደሆነ 30 ወይም 15 ደቂቃ ይሁን። አንዳንድ ሰዎች ይህን ትርፍ ጊዜ አናገኝም እያሉ ያስቡ ይሆናል። ነገር ግን ተሳስተዋል። አንድ ትልቅ ሠራተኛ ማለዳ ማለዳ የመጀመሪያዎችን ሁለት ሰዓቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና በጸሎት ያሳልፋቸው እንደነበረ ከመሞቱ በፊት መስክሮ ተናገረ ይባላል። የሥራውም መከናወን ምክንያት ይህ መሆኑን መሰከረ።
ሥራህ ለመጽሐፍ ቅዱሰ ማጥናት የተወሰነውን ጊዜ በማናቸውም ምክንያት እንዳያሰናክልብህ ተጠንቀቅ። ይህ ጊዜ ከመብል በተለይም ከከባድ መብል በኋላ ባይሆን የተሻለ ነው። ለሁሉ የተሻለ ጊዜ ማለዳ በጥዋት ነው።
ሀ/
አእምሮ ክፍት የሚሆንበትና ሰውነት የሚነቃበት ጊዜ ስለሆነ ነው። በመኝታ ሰዓት ብዙ ጊዜ አእምሮ ይደክማል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የበለጠ ግልጥ የሆነ አእምሮ የሚፈልግ ሌላ ማጥናት ይኖር ይሆን?
ለ/
ጥዋት ከቀኑ የበለጠ የተከበረ ጊዜ ስለሆነ ነው።
ካለህ ሁሉ የበለጠውን ለእግዚአብሔር መስጠት ይገባሃል። «ዕውርን ለመሥዋዕት ብታቀርበው ክፉ አይደለምን? አንካሳና በሽተኛ ብታቀርብስ ክፉ አይደለምን? እስቲ ያነን ለሹምህ አቅርበውና ባንተ ደስ ይለው እንደሆነ ወይም አንተን ይቀበልህ እንደሆነ ይላል የሠራዊት አምላክ። ለአምላክ ርኩስ ነገር የሚያቀርብ አታላይ የተረገመ ይሁን ትልቅ ንጉሥ ነኝና ስሜም በአሕዛብ ዘንድ የሚያስፈራ ነው ይላል እግዚአብሔር የሠራዊት አምላክ። (ሚልክያስ 1፡8ና 14)፡፡
ሐ/
በዚህ ዓለምና በሚመጣው ዓለም ደስታ የምናገኝበት የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የበለጠ በዓለማዊ ሥራችን የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም እሹ፡፡ የቀረውም ሁሉ ይጨመርላችኋል። (ማቴ. 6፡33)፡፡
መ/
አድካሚ ከሆነው ከዓለም ሥራ አስቀድሞና ከማናቸውም ሰው ጋር ከመገናኘት በፊት ጥዋት ማልዶ ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት ከሁሉ የበለጠ የተመቸ ጊዜ ነው።
ሠ/
ቀኑን ሳትጀምር የእግዚአብሔርን መሪነትና እርዳታ ለማግኘት በጣም ስለሚያስፈልግህ ነው።
‹‹ቃልህ ለእግሬ መብራት ነው፡፡ ለእርምጃዬም ብርሃን።›› (መዝሙር 119፡105)፡፡
ከቅዱሳን አንዱ እንዲህ አለ፤ ‹‹የክርስቲያን የሳምንት ሕይወቱ እሁድን ባሳለፈበት ሁኔታ ይመሠረታል። እግዚአብሔር ሙሴን አለው ‹‹በጠዋት ተሰናድተህ ማለዳ ወደ ደብረ ሲና ውጣ በተራራውም ጫፍ በፊቴ ቁም።›› (ኦሪት ዘፀአት 34፡2)።
አንድ አስተማሪ ተማሪዎችን እንዲህ አላቸው። ‹‹ቀኑን የምትጀምሩበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ምዕራፍ ደህና አድርጎ ማጥናትና በተማራችሁት ትእዛዝ መሠረት ለመኖር መጠንቀቅ ነው።››
ረ/
በብዙ ፈተና የተከበብህ ስለሆንህና ራስህ ልትቃወመው ስለማትችል ነው።
ወታደር ያለ መሣሪያ ወደ ጦርነት መሄድ እንደማይችል እንዲሁ አንተ ወደ ዓለም ከመግባትህ በፊት የእግዚአብሔርን መሣርያ ልበስ። ‹‹ኃጢአት በደጃፍ ናት በአንተም ታደባለች።›› (ኦሪት ዘፍጥረት 4፡7)።
ጳውሎስ የመንፈስ ቅዱስ ሠይፍ «ብሎ በጠራው በእግዚአብሔር ቃል ክርስቶስ ፈተናን ካሸነፈ›› በክፉ ቀን ማሸነፍ እንድትችል የእግዚአብሔርን ቃል ለመያዝ ለእኛ ለደካሞች ይልቅ ብዙ አስፈላጊ ነው።
3.
በዕረፍት ጊዜህ መጽሐፍ ቅዱስን አጥና፡፡
ማንም ሰው ምግብ እስቲሰናዳ ወዳጅና ሐኪም ሲጠባበቅ ትርፍ ጊዜ አለው። ብዙ ሰዎች ጊዜን በከንቱ ማሳለፍ ሕይወትን በከንቱ ማሳለፍ እንደሆነ ባለማወቅ ይህን ትርፍ ጊዜ በሚገባ ለማዋል ስለማያውቁ በከንቱ ያሳልፉታል። የኪስ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳለህ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ወይም በቃል ያጠናኸውን ቁጥር በሕሊና በማሰብ በዚህ ትርፍ ጊዜ ለመጠቀም ሞክር። አንድ ነጋዴ በዕረፍቱ ጊዜ በሱቁ ሆኖ ያጠናው ስለ ነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ደህና አድርጎ ዓወቀ ይባላል።
አንድ ዓዋቂ ሰው እንዲህ አለ ‹‹ከሁሉ የበለጠ ቁጠባ የጊዜ ቁጠባ ነው፤ ከሁሉ የበለጠ የጊዜ ቁጠባም መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ጊዜን ማሳለፍ ነው።››
4.
ፈቃደኛ በሆነ መንፈስ አጥናው፡፡
ሳይርበው ከሚበላ ይልቅ ርቦት የሚበላ ከምግቡ የበለጠ ጥቅም እንደሚያገኝ አይጠረጠርም። ‹‹ቃልህን ባገኘሁ ጊዜ ተመገብሁት። ቃልህም የልቤ ደስታና ሐሴት ሆነልኝ።›› (ኤርምያስ 15፡16)፡፡
አንዲት ሴት አንድ መጽሐፍ አነበበችና ደስ የሚያሰኝና የማይጠቅም መሰላት። ከጥቂት ወራት በኋላ ከጸሐፊው ጋር ተገናኘችና አገባችው። ከዚህ በኋላ መጽሐፉን እንደገና አነበበችና በጣም ደስ የሚያሰኝ ሆኖ አገኘችው። የአሳቧ መለወጥ ምክንያቱ እርሷ ራስዋ እንጂ መጽሐፉ አይደለም። ጸሐፊውን ዓወቀችው ወደደችውና መጽሐፉን በፈቃደኛ መንፈስ አነበበችው። እግዚአብሔርን ካወቅኸው በኋላ በዚህ መንፈስ መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ የምታገኘው ይህ ነው።
/ሐፍዝ ዳውድ፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደሚጠና፤
1939 ዓ.ም፤ ገጽ 19-24፤ አዲስ አበባ/
‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!
No comments:
Post a Comment