Thursday, February 19, 2015

የጽድቅ መንገድ

                                             

                         በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
                                 ሐሙስ የካቲት 12 ቀን 2007 ምሕረት ዓመት
         ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ከመምጣቱ አስቀድሞ እውነተኛ የጽድቅ መንገድ አልታወቀም ነበር። ነገር ግን ዛሬ ሰማያዊ አባታችን እግዚአብሔር እውነተኛውን የጽድቅ መንገድ አሳየን። ይኸውም የጽድቅ መንገድ የተባለ አንድ ልጁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከሱ በቀር ሌላ ወደ ሰማያዊ አባታችን ወደ እግዚአብሔር የሚወስድ የለም። እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ የእውነትና የሕይወት መንገድ ነኝ በኔ በኩል ካልሆነ በቀር አንድም ወደ አብ የሚመጣ የለም ብሎ ተናግሮዋል። (ዮሐ. 146)፡፡

         ስለዚህ እኛ ሁላችን የማያሳስት እውነተኛውን የጽድቅ መንገድ ክርስቶስን ብቻ ይዘን ከሄድን ዘወትር እየናፈቅን አባታችን ሆይ፤ እያልን ከምንጠራው ከሰማያዊ አባታችን ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ሰማያዊት አገራችን ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደርሳለን፤ ዳግም በሥራችን እንጸድቃለን፤ መንግሥተ ሰማያት እንገባለን ብለን አንመካም፤ የምንጸድቅበት ሃይማኖታችን ክርስቶስ ብቻ ነው። ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እናንት ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ወደኔ እኔም አሳርፋችኋለሁ ቀምበሬን በላያችሁ ተሸከሙ›› ብሏል (ማቴ. 1128)፡፡ እንዲህም ማለቱ በኔ ጽኑ ሲል ነው።
         ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ ጽድቅ በሃይማኖት ብቻ እንዲገኝ ሥራ በመሥራት እንዳይገኝ በጻፋቸው መልእክቶች ሁሉ ያስተምረናል፡፡ ‹‹ሰው ሥራ ሳይሠራ በሃይማኖት ብቻ እንዲጸድቅ እናውቃለን›› ብሏል። (ሮሜ.328)፡፡ ከዚህም ቀጥሎ 4ኛው ምዕራፍ 4ኛና 5ኛው ቁጥር የሚሠራ ሰው ዋጋው አይቆጠርለትም፤ እንዲያው እንደሚገባው ሥራ ይባላል እንጂ። የማይሠራ ግን ኃጢአተኛውን በሚያጸድቅ በእግዚአብሔር ቢያምን ማመኑ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል ብሏል። ደግሞ ይልቁንም በጣም የመሚያስረዳ በኤፌሶን መልእክቱ ‹‹አምነን በጸጋው ድነናልና፤ እናንተም የዳናችሁ በእግዚአብሔር ቸርነት ነው እንጂ በሥራችሁ አይደለም፤ እኛም የዳን በሥራችን አይደለም፤ ማንም የሚመካ እንዳይኖር›› ብሏል። (ኤፌ.28-9) ዳግም ወደ ገላትያ ሰዎች በጻፈው 2ኛው ምዕራፍ 21ኛው ቁጥር ‹‹የእግዚአብሔርን ጸጋ አልክድም የኦሪትን ሥራ በመሥራት የሚጸድቁ ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ ለከንቱ የሞተ ነዋ›› ብሎ ተናግሮአል። ይህም ሰው ሁሉ በሥራው እንዳይጸድቅ በእግዚአብሔር ጸጋና በክርስቶስ ሞት እንዲጸድቅ ያስረዳል። ክርስቶስ መሞቱ ሰው በሥራው መጽደቅ የማይችል ስለ ሆነ ነው።
           /የቤተክርስቲያን ጸሎት፤ ለ3ኛ ጊዜ የታተመ፤ ንባቡና ሥርዓቱ ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር የተስማማ፤ ትንሣኤ ማተሚያ ድርጅት፤ አዲስ አበባ፤ ገጽ 93፤ 1997 ዓ.ም/


No comments:

Post a Comment