Friday, April 29, 2016

መልእክት ፡ ኀበ ፡ ሰብአ ፡ ኤፌሶን፡፡ (1)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


የሐዋርያው ፡ የጳውሎስ ፡ መልእክት ፡ ወደ ፡ ኤፌሶን ፡ ሰዎች፡፡

አርብ ሚያዚያ 21 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

    ‹‹ወአርአየነ ምክረ ፈቃዱ በከመ ሥምረቱ›› (ኤፌ. 1፡9)!

·        የመልእክቱ ጸሐፊ፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ
መልእክቱ የተጻፈበት ጊዜ፡ ከ61-63 ዓ/ም ባሉት ዓመታት
·        መልእክቱ የተጻፈበት ቦታ፡ ሮም
በጊዜው የመልእክቱ ተቀባዮች፡ የኤፌሶን ቤተ፡ ክርስቲያን (ማኅበረ ምእመናን)
·        የመልእክቱ ጭብጥ፡ የክርስቶስ ባለ ጠግነት በቤተ፡ ክርስቲያን 
(The Orthodox study Bible) 

        ሐዋርያው በክርስቶስ እስር ሆኖ ከጻፋቸው መልእክታት የኤፌሶን መልእክት አንዱ ነው፡፡ ባለፈው ጥናታችን በሐዋርያው ለግለሰብ ከተጻፉት መልእክታት መካከል በእስር ቤት ሆኖ የጻፈውን የፊልሞናን መልእክት ማጥናታችንን እናስታውሳለን፡፡ እግዚአብሔር ቢፈቅድ፤ ቅዱስ መንፈሱም ቢረዳን ይህንን መልእክት ጨምሮ ሐዋርያው በእስር ቤት ሆኖ የጻፋቸውን ቀሪ መልእክታት እናጠናለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ባለፈው ጥናት ብዙ እንደ ተጠቀማችሁ፤ ወደ እግዚአብሔር ቃል ፊታችሁን ዘወር እንዳደረጋችሁ በአንድም በሌላ መንገድ ለገለጻችሁልኝ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡

        ተወዳጆች ሆይ፤ ‹‹ . . ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ›› /2 ጴጥ. 1፡19/ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ የእግዚአብሔርን ቃል መረዳትና መታዘዝ አካሄዳችንን ከእግዚአብሔር ጋር የምናደርግበት ትክክለኛ ሕይወት ነው፡፡ እግዚአብሔር እንደሚያይ እይታን የምናገኘው በቃሉ በኩል ነው፡፡ ሐዋርያው ‹‹የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና የሚሠራም . . ›› ካለ በኋላ በዚያው ንባብ ‹‹እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት . . ›› /ዕብ. 4፡12-13/ በማለት ቃሉን ከእግዚአብሔር እይታ ጋር ያስተሳስረዋል፡፡

        የእግዚአብሔር ቃል ሲኖረን እንኳን ሌላውን ራሳችንን የምናይበት ማየት ሚዛኑ ልክ ይሆናል፡፡ የሰውን ፊት አይቶ በሚያደላው ዓለም መካከል የቃሉን ቱንቢ መያዝ ከብዙ ኪሳራ ይታደጋል፡፡ ለእኛ በጨለማ ስፍራ አጥርተን የምናይበት፤ ያለን ብቸኛ ብርሃን ‹‹ቃሉ›› ነው፡፡ የአምላካችንን ቃል በመጠንቀቅ መኖር ለእኛ የለመለመ መስክ፤ የእረፍት ውኃ ነው፡፡ መልካምነታችን ይህንን መሰረት ከማድረግ የወጣም ሊሆን አይችልም፡፡ የሰዎችን ስሜትና ፍላጎት በመጠንቀቅ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ልናደርግ አይሆንም፡፡ የሰው መልካም ‹‹መርገም ጨርቅ›› (ኢሳ. 64፡6) ከሚል ያለፈ ማብራሪያ አልተሰጠውምና፡፡

         የጠላታችንን የውጊያ ሜዳ በተመለከተ ‹‹ . . የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ›› /2 ቆሮ. 4፡4/ ተብለናል፡፡ ደግሞ ሐዋርያው በሌላ ስፍራ ‹‹ . . የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ . . ታውቁ ዘንድ . . ›› (ኤፌ. 1፡18) ይለናል፡፡ ፈታኙ እንዳይበራልን (እንዳናውቅ) በብርቱ የሚሠራው ክርስቶስን ነው፡፡ ‹‹እነሆ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ . . ›› (ዕብ. 10፡7) እንደተባለ፤ እናስተውለውና እናምነው ዘንድ በቅዱሱ የመጽሐፍ ጥቅልል የአባቱን ፈቃድ በሙላት በምድር የከወነ ልጅ ‹‹እኔ›› ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ 

        አለማወቃቸው እንደ ጎዳቸው በግልጥ የሚናገሩ ሰዎችን እንሰማለን፡፡ ዳሩ ግን ‹‹ምን አለማወቅ?›› ብለን ብንጠይቅ፤ የሚቆጩባቸው ነገሮች የዘላለምን ቀርቶ የጊዜውን ለማሻገር በራሳቸው ብቁ አይደሉም፡፡ ሰው ‹‹ዘላለም መሞትን›› ተሸክሞ ፊቱን ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ማድረግ አለመቻሉ አስገራሚ ነው፡፡ የጊዜውን አለማወቅ ኪሳራው በጊዜው የሚሰላ ሲሆን የዘላለሙን አለመረዳት ደግሞ የሚያስከፍለው ዋጋ በዘላለም የሚሰላ ነው፡፡ ተወዳጆች፤ ቃሉን አጥኑ!

        በኤፌሶን መልእክት በደኅንነታችን ውስጥ የአብ፤ ወልድና መንፈስ ቅዱስን አንድ አምላክ ሥራ፤ በክርስቶስ ለቤተ፡ ክርስቲያን የተገለጠውን በረከት፤ የበረከታችን መሰረት ክርስቶስ፣ የበረከታችን ስፍራ ሰማይ፣ የበረከታችን ዓይነት መንፈሳዊ እንደ ሆነ፤ ለተገለጠው የእግዚአብሔር ጸጋ የእኛን ትክክለኛ ምላሽ፤ በመንፈሳዊ ውጊያዎቻችን ላይ የእግዚአብሔርን ኃይል፤ የምናይበት እጅግ የሚያበረታ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው፡፡   

        ራሳችሁን እንዲህ ጠይቁ፡ -

·        ቃሉን ለመስማት ምን ያህል የልብ ዝግጅት አለኝ?
·        የሰማሁትን ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ለማመሳከር ምን ያህል እተጋለሁ?
·        ያልተረዳሁትን ለመረዳት ምን ያህል ፍላጎት አሳያለሁ?

                                      ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment