Saturday, April 9, 2016

መልእክት ኀበ ፊልሞና፡፡ (8)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! 


ቅዳሜ ሚያዚያ 1 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

(መልእክት ወደ ፊልሞና)

‹‹እምጳውሎስ ሙቁሐ ለኢየሱስ ክርስቶስ፡ (ኤፌ. 3፡1)!››

No. 14-17, ‹‹While the master-slave relationship continues, it is transcended by brotherhood in Christ.›› /The Orthodox Study Bible; New Testament and Psalms New King James Version/.

‹‹አምኀከ ኤጳፍራስ ዘተጼወወ ምስሌየ በኢየሱስ ክርስቶስ፡፡››
‹‹በክርስቶስ ኢየሱስ ከእኔ ጋር የታሰረ ኤጳፍራ . . ››፡-

          ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ መልእክት የስንብት ክፍል የጠቀሰው ሌላው የተወደደ አገልጋይ ኤጳፍራ ነው፡፡ ሐዋርያው ይህንን መልእክት የጻፈው በእስር ቤት ሆኖ እንደ መሆኑ፤ አብሮት ስለ ክርስቶስ የታሠረ ሌላውን አገልጋይ ይጠቅሳል፡፡ ባለፈው ጥናታችን ሐዋርያው ከእስር ተፈትቶ በፊልሞና ቤት ያለችውን ቤተ ክርስቲያን እንደሚጎበኛት ያለውን ተስፋ ለተወደደውና አብሮት ለሚሠራ ለፊልሞና ሲገልጽለት አይተናል፡፡

        በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ስለ ኤጳፍራ የምናገኘውን ምስክርነት በመመልከት የእግዚአብሔር መንፈስ የሚያስተምረንን እንወስዳለን፡፡ በቆላስይስ መልእክት ‹‹ከተወደደ ከእኛም ጋር አብሮ ባሪያ ከሆነው ከኤጳፍራ እንዲህ ተማራችሁ፤ እርሱም ስለ እናንተ ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ ነው፡፡ ደግሞም በመንፈስ ስለሚሆን ስለ ፍቅራችሁ አስታወቀን፡፡›› (ቆላ. 1፡7-8) የሚል ምስክርነት በሐዋርያው ተጽፎ እናነባለን፡፡   

        ኤጳፍራ በቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን ምስረታ የወንጌልን እውነት ቃል የሰበከ እና በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ተረድተውና ፍጹማን ሆነው እንዲቆሙ ሁልጊዜ በጸሎቱ ስለ እነርሱ የሚጋደል የክርስቶስ ባሪያ ነው (ቆላ. 4፡12)፡፡ በሎዶቅያና በኢያራ ከተማም ስላሉቱ እጅግ ይቀና ነበር፡፡ ወደ ሮም ሄዶ ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር በተገናኘ ጊዜ በመንፈስ ስለሆነው ስለ ቆላስይስ ምእመናን ፍቅር አስታውቋል፡፡ በዚህ መልእክት መጀመሪያ አሳብ እንደምንረዳው የቆላስይስ ምእመናን ከኤጳፍራ ‹‹በሰማይ ከተዘጋጀላችሁ ተስፋ የተነሣ፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ስለ እምነታችሁ፤ ለቅዱሳንም ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ሰምተን . .›› እንደ ተባለ፤ እምነት፤ ተስፋና ፍቅር (1 ቆሮ. 13፡13) ተምረዋል፡፡

        እነዚህ በአንድ ክርስቲያን ውስጥ መንፈስ ቅዱስ የሚያስገኛቸው የተባረኩ ነገሮች ናቸው፡፡ እምነት ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት የሚመሰረትበት ትክክለኛ ስፍራ ሲሆን፤ ተስፋ ደግሞ የእምነታችንን ፍጹም በረከት የምንገናኝበት መድረሻ ነው፤ ፍቅር ጅማሬንም ፍጻሜንም የሚያስቀጥል የነገሮች ሁሉ ማሠሪያ ነው፡፡ በክርስቶስ ያለን እምነት የሚገለጠው ለምእመናን ሁሉ በሚኖረን ፍቅር ነው፡፡ እምነት፤ ተስፋ፤ ፍቅር መሰረታቸው የወንጌል እውነት ቃል ነው፡፡

        ኤጳፍራ ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ በክርስቶስ ኢየሱስ ከእርሱ ጋር የታሰረ ነበር፡፡ ስለ ቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን ለሐዋርያውና ለሌሎች አገልጋይ ወንድሞች የነገራቸውም በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ ‹‹ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ›› እንደ ሆነ የተመሰከረለት እርሱ ስለ ቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን በሚያገለግሉ በሌሎቹ ዘንድ ያስታወቀው እውነቱን ነው፡፡ ኤጳፍራ የስሕተት ትምህርት ፈተና ውስጥ ለነበረችው ለቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል የተሰጠ አገልጋይ እንደ ነበር ልብ እንላለን፡፡ የጌታ ጸጋ የምናገለግል ብቻ ሳንሆን ላገለገልናቸው በጸሎት የምንጋደል ያድርገን!

        በመቀጠል የምናየው ሐዋርያው ‹‹አብረውኝ የሚሠሩ›› በማለት የጠቀሳቸውን አገልጋዮች ነው፡፡ ስለ ማርቆስ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የምናውቀውን በጥቂቱ እንመልከት፡፡ በአንጾኪያ በርናባስን እና ሐዋርያው ጳውሎስን እስኪለያዩ ድረስ ወደ መከፋፋት ያደረሳቸው ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ ጉዳይ እንደ ነበረ እናነባለን (ሐዋ. 15፡36-41)፡፡ በውጤቱም በርናባስ ማርቆስን፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ ሲላስን መርጠው ለአገልግሎት ተሰማሩ፡፡ ሐዋርያው ከእነርሱ ጋር ማርቆስን ሊወስድ ያልፈቀደበትን ምክንያት ‹‹ከጵንፍልያ ተለይቶ ነበርና፤ ወደ ሥራም ከእነርሱ ጋር አልመጣም ነበርና›› ተብለናል፡፡

          በኋላ ግን ለጢሞቴዎስ ሁለተኛ ጊዜ በተላከለት መልእክት ‹‹ማርቆስ ለአገልግሎት ብዙ ይጠቅመኛልና ይዘኸው ከአንተ ጋር አምጣው›› (2 ጢሞ. 4፡11) የሚል እናነባለን፡፡ ‹‹ይጠቅመኛል›› የሚለው ቃል አናሲሞስ (ጠቃሚ) ከሚለው ጋር ያለውን የትርጉም ተዛምዶ አስተውሉ፡፡ ሐዋርያው አስቀድሞ ብዙም እንደማይጠቅም ያሰበው አልያም ብዙ የማይጠቅም የነበረው ማርቆስ በኋላ በብዙ የሚጠቅም እንደ ሆነ ተመስክሮለት እንመለከታለን፡፡

          ተወዳጆች ሆይ፤ እንደማትጠቅሙ በልባችሁና በሌሎች ልብ የታሰባችሁበት ጊዜ ዛሬም ድረስ ሕመማችሁ ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን የእግዚአብሔር ጸጋ ይህንን ይለውጣል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ያድግና ይበዛ እንደ ነበር በተጠቀሰበት ክፍል በርናባስና ሳውል አገልግሎታቸውን ፈጽመው ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ በተመለሱ ጊዜ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስን ከእነርሱ ጋር ይዘውት መጥተው ነበር (ሐዋ. 12፡25)፡፡

        በዚያን ጊዜ በመካከላቸው የነበረው ሁሉ በፍቅር ነበር፡፡ በኋላ ግን ማርቆስ ለበርናባስና ጳውሎስ መከፋፋት በመካከላቸው እስከሚሆን ድረስ የልዩነት ርእስ ሆነ፡፡ ደግሞ በሌላ ጊዜ ‹‹ለአገልግሎት ብዙ ይጠቅመኛል›› ተባለ፡፡ አሁንም ለፊልሞና በተጻፈው መልእክት ውስጥ ማርቆስ ‹‹አብሮ ሠራተኛ›› ነው፡፡ ሐዋርያው ለተሠራው ሥራና ለተገኘው ውጤት ሁሉ ራሱን በብቸኝነት አላቀረበም፤ በብቸኝነት የምንገልጠው ጌታን ብቻ ነውና፡፡ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል የእግዚአብሔር ጸጋ የተገለጠው በእኔ ብቻ ሳይሆን በእነርሱም ነው እንደ ማለት ያለ ሐዋርያው የተወደዱትን አገልጋዮች ከራሱ ጋር አብሮ ይጠቅሳል፡፡

        ቀጣይ የምናገኘው የመቄዶንያ ሰው የሆነ የተሰሎንቄውን አርስጥሮኮስን ነው (ሐዋ. 27፡2)፡፡ ሁለት ሰዓት ሙሉ የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት እየተባለ በተጮኸባት የኤፌሶን ከተማ በነበረው አገልግሎት አርስጥሮኮስ በዚያ እንደ ነበር፤ በከተማው ከሆነው ድብልቅልቅ የተነሣም ነጥቀው ወደ ጨዋታ ስፍራ እንደወሰዱት እናነባለን (ሐዋ. 19፡29)፡፡ በዚያ በኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ምስረታ ከሐዋርያው ጋር የነበረውን የአገልግሎት ኅብረትና የከፈለውን ዋጋ መረዳት እንችላለን፡፡ እንዲሁ ሐዋርያው ታስሮ ሳለ ‹‹አብሮ ከእኔ ጋር የታሰረ›› በማለት እንደሚነግረን የቆላስይስ መልእክት ሲጻፍ ከሐዋርያው ጋር በእስር እንደ ነበር እናውቃለን (ቆላ. 4፡10)፡፡
        
        ዴማስና ሉቃስ፤ በቆላስይስ መልእክት እንደ ተጠቀሰው ‹‹የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል›› (ቆላ. 4፡14) ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ስለ ዴማስ በዚህ ክፍል ከተጠቀሰው በተጨማሪ የምናገኘው ‹‹ዴማስ የአሁኑን ዓለም ወዶ ትቶኛልና›› (2 ጢሞ. 4፡10) የሚል ነው፡፡ ይህ አገላለጽ አዎንታዊ ባይሆንም ዴማስ የተወው ሐዋርያው ጳውሎስን እንደ ሆነ ልብ ማለት አግባብ ካልሆነ ፍርድ ይጠብቀናል፡፡ ዳሩ ግን ሐዋርያው ጳውሎስን ስለ መተዉ ሳይሆን የአሁኑን ዓለም ስለ መውደዱ ሐዋርያው ዮሐንስ የሚለው አለው፡- ‹‹ . . ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም›› (1 ዮሐ. 2፡15-16)፡፡ ያለ አባት ፍቅር መኖር ውጤቱ ደግሞ ግልጽ ነው፡፡

       ከአሕዛብ ወገን የሆነው ሉቃስን በተመለከተ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል (የሉቃስ ወንጌል) እና የመንፈስ ቅዱስ ሥራ (የሐዋርያት ሥራ) ሁለት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን እንደ ጻፈ እናውቃለን፡፡ ሐዋርያው ስለ እርሱ ሲናገር ‹‹የተወደደ ባለ መድኃኒት›› ይለዋል፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ሐኪምና መድኃኒት አዋቂ ቢሆንም እንኳ ‹‹ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና›› (ሉቃ. 2፡11) ለማለት አልተፈተነም፡፡

       የትኛውም ጥበብ ‹‹ጥበብሰ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ›› የሆነውን ከመናገር ሊከለክለን አይገባም፡፡ በአሁኑ ዓለም ያለው በሚመጣው ዓለም የሚገለጠውን ክብር ሊጋርድብን አንፍቀድለት፡፡ ቅዱሱ ቃል የዚህችን ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነው ይለናል (1 ቆሮ. 3፡18)፡፡ እናንተስ ፊት? ስልጣኔ እንደ ጨመረ፤ ቴክኖሎጂ እንደረቀቀ፤ የሰዎች ማስተዋል እንደ ሰፋ ስትሰሙ በእርግጥም ዓለም ሞኝነቷ አስክሯታል ማለት ነው፤ ማንም ራሱን አያታልል፡፡

      ‹‹ሰላምታ ያቀርቡልሃል›› የሚለው፤ የተወደደና አብሮ ሠራተኛ ለሆነው ለፊልሞና በሌሎቹ አገልጋዮች ዘንድ ያለውን ተቀባይነትና ኅብረት የበለጠ የሚያጠናክር ነው፡፡ እንዲህ ባለው ቅዱስ የሰላምታ ልውውጥ ውስጥ ፍቅርን መመልከት ከባድ አይሆንም፡፡ ሐዋርያው በሌሎቹ መልእክቶቹ እንዳደረገው ከእርሱ የተላከ መልእክት እንደ ሆነ በሚያረጋግጥ ሁኔታ ለፊልሞና የጻፈለትን ይፈጽማል፤ እኔም ፈጸምኩ፡፡
 
‹‹ወጸጋሁ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ምስለ መንፈስክሙ፡፡››

‹‹የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን፡፡››!

‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment