Friday, April 29, 2016

አፋችሁን አትክፈቱ!

    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


                 

              ‹‹ኢከሰተ አፉሁ በሕማሙ›› እንዲል (ሐዋ. 832)::

  አርብ ሚያዚያ 21 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

          የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሁለተኛው ክፍል ‹‹የታሪክ ክፍል›› በመባል ይታወቃል፡፡ ይህም ከአገልጋዮቹ አንጻር ‹‹የሐዋርያት ሥራ››፤ ከሥራው ባለቤት አንጻር ደግሞ ‹‹የመንፈስ ቅዱስ ሥራ›› በመባል የሚታወቀው መጽሐፍ ነው፡፡ ‹‹ለድፍርስ መፍትሔው ምንጭ መውረድ ነው›› የማወቅ መመሪያዬ ነው፡፡ የክርስትናን መሠረተ ጅማሬ ለሥጋና ደም አሳብ ክፍተት በማይሰጥ መልኩ ቁልጭ ብሎ በምንመለከትበት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ፤ በሞተውና ከሙታንም በተነሣው በክርስቶስ ክርስቲያን የሆኑቱ በኅብረት የተቀበሉትን (ቤተ፡ ክርስቲያን) የመጀመሪያውን ታላቅ መከራና ስደት እናነባለን፤ ከእስጢፋኖስ መገደል በኋላ (ከሐዋርያት ሥራ ም. 7)፡፡


     ምእራፍ ስምንት ስደትና መከራውን (ክርስቶስ ስለ ጽድቅ የተቀበለውን መከራ መካፈል) ተከትሎ ወደ ይሁዳና ወደ ሰማርያ የሆነውን መበተን መርዶ በመንገር ይጀምራል፡፡ ይህንን ምእራፍ እንዲህ ከፍለን ልንረዳው እንችላለን፡ - 

                  1. በክርስትና የመጀመሪያው ታላቅ መከራ (ከቁ. 1-3)
                  2. የተበተኑት ምእመናን ወንጌልን መስበካቸውና ፊልጶስ በሰማርያ (4-8)
                  3. የሰማርያው ጠንቋይ ሲሞን እና በዚያ የሆነው (9-24)
                  4. ወንጌል በሳምራውያን ብዙ መንደሮች መሰበኩ (ቁ. 25)
                  5. ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ (26-40)

        በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ‹‹የእግዚአብሔር ቃል ግን ያድግና ይበዛ ነበር›› (ሐዋ. 12፡24) የሚለው፤ በክርስቲያኖች ላይ ከሆነው ታላቅ ስደትና መከራ በኋላ ከምናነባቸው ደስታን የሚሞሉ ቃላት መካከል አንዱ ነው፡፡ በዚህ መከራና ስደት ውስጥ ሳዉል የመሪነቱን ድርሻ እንደሚወስድ የምናውቅ ሲሆን (ሐዋ. 26፡10-11፤ 1 ቆሮ. 15፡9፤ ገላ. 1፡13)፤ ከተለወጠና ወደ ክርስትና ከመጣ በኋላ ግን ‹‹የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም›› (2 ጢሞ. 2፡9) በማለት ለእምነት ልጁ ጢሞቴዎስ ጽፎለታል፡፡

       የሕማም ሰው ደዌን የሚያውቅ (ኢሳ. 53፡3)፤ ከሙታንም በኩር (ቆላ. 1፡18) በሆነው የእግዚአብሔር ልጅ በማመን ለሆነው እውነተኛ ክርስትና የአሁኑ ዓለም ምላሽ ዛሬም እንዲህ ያለ ቢሆንም፤ ዳሩ ግን የእግዚአብሔር ቃል ማደግና መብዛቱ ፈጽሞ አይቆምም፤ ቃሉ አይታሰርምና፡፡ ‹‹የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ›› (ሐዋ. 8፡4)፤ ምን ሰበኩላቸው? ለሚለው ‹‹ክርስቶስን ሰበከላቸው›› ተብለናል፡፡ አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ፤ አንገላችም የነበረው ሐዋርያ ጳውሎስ (1 ጢሞ. 1፡13)፤ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን (ገላ. 1፡23) ‹‹እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን›› (1 ቆሮ. 1፡23) በማለት ይሰብካል፡፡

        ሐዋርያው ጴጥሮስና ዮሐንስም ‹‹በሳምራውያን በብዙ መንደሮች ወንጌልን ሰበኩ›› (ሐዋ. 8፡25) ተብለናል፡፡ ‹‹ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው›› (ሮሜ 1፡3)፡፡

         በዚህ ምእራፍ ከሥልጣን አንጻር ሐዋርያ ያይደለ ከሰባቱ አንዱ የሆነ ፊልጶስ ከጌታ መልአክ እንደ ተነገረው ከኢየሩሳሌም (ሊሰግድ) ወደ ኢትዮጵያ (ግዛትን በተመለከተ አሁን የምናውቀውን ብቻ አይደለም) ይመለስ የነበረውን ጃንደረባ እንደተገናኘ እናነባለን፡፡ የንግሥት ህንደኬ አዛዥና በገንዘብዋ ሁሉ የሠለጠነ ይህ ሰው በሠረገላው ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር፡፡ ያነበው የነበረ የመጽሐፉ ክፍል፤

       ‹‹እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል?›› የሚል ነበር፡፡

         ፊልጶስ ወደዚህ ሰው የቀረበው ‹‹በእውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?›› የሚል ትልቅ ጥያቄ ይዞ ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብና ማድመጥ ‹‹እምነት ከመስማት ነው›› (ሮሜ 10፡17) ለሚለው መመሪያ ትክክለኛው የመታዘዝ መንገድ ቢሆንም፤ ‹‹ማስተዋል›› ግን የመረዳት ቁልፍ ነው (2 ቆሮ. 4፡4)፡፡ መጽሐፍ ‹‹የማያስተውል ሕዝብ ነውና ስለዚህ ፈጣሪው አይራራለትም፤ ሠሪውም ምሕረት አያደርግለትም›› (ኢሳ. 27፡11) እንደሚል፤ ‹‹ጌታም በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጥህ›› (2 ጢሞ. 2፡7) የሚለው ቡራኬ በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡

        ጃንደረባው ያነበው ከነበረው የመጽሐፍ ጥቅልል ጌታችን በአይሁድ ምኩራብ ‹‹የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና . . ›› (ሉቃ. 4፡17-19) የሚለውን ክፍል አንብቦአል፡፡ ይህም ከጌታችን አፍ ከሚወጣው ከጸጋው ቃል ጋር ተያይዞ ተብራርቶአል፡፡ ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ የሚወድ እግዚአብሔር (1 ጢሞ. 2፡3-4)፤ ሰዎች ሁሉ የሚድኑበትን ጸጋ እንደገለጠ እንረዳለን (ቲቶ 2፡11፤ ዮሐ. 3፡16፤ 1፡14)፡፡ ታዲያ ከኢየሩሳሌም አምልኮ የሚመለሰው ሰው በኢሳይያስ 53 አስቀድሞ በትንቢት የተነገረውን በአዲሱ ኪዳን ቀራንዮ ላይ በተግባር የተፈጸመውን (ኢሳ. 53 ገና ወደ ፊት ሊሆን ያለን ክስተት የሚያመለክት ትምህርት እንዳለው ሆኖ) ቤዛነታችንን ያነብ ነበር፡፡

       እንግዲህ ለዚህ ጽሑፍ ርዕስ ያደረግነውን ያገኘነው ከዚሁ የንባብ ክፍል ነው፡፡ ‹‹ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ . . ግፍን አላደረገም ነበር፤ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም ነበር›› (ኢሳ. 53፡7)፤ መጽሐፍ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋል ባለበት ክፍል ‹‹ጉሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፤ በመላሳቸውም ሸንግለዋል፤ የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፤ አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል . . ›› (ሮሜ 3፡13) ይለናል፡፡ በዚህ ዓለም በዚህ መንገድ የሚከፈቱ አንደበቶችን ማሰብ እጅግ የሚረብሽ ነው፡፡ ከተከፈተ መቃብር እንደሚወጣው ደስ የማያሰኝ ጠረን የሕይወት አየር ብክለቶች ምንጫቸው እንዲህ ያለም ነው፡፡

      መድኃኒታችን ኢየሱስ በክፉዎች ከበባ መካከል በሆነበት የሕማሙ ጊዜ በዝምታው ውስጥ የነበረውን የጽድቅ ጩኸት፤ ለሚሰማ ጆሮ በእውነት ላይ መደላደልን የሚሰጥ ነው፡፡ እርሱ መከራን ባፀናችበት ዓመፀኛ ዓለም፤ በሥና በደም ፊት ዓመፅን አልተናገረም፤ ዓመፅንም አላደረገም፡፡ ‹‹ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ ዓመፅን ደግሞ ያደርጋል . . ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፤ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና፡፡ ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ›› (1 ዮሐ. 3፡4፤8) እንደተባለ፤ ስለ ኃጢአታች ‹‹በመከራው ታገሠ›› (ዕብ. 12፡2)፡፡

        ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች እንዲሉ፤ እርሱ ስለ እኛ ስለ በደላችን ተላልፎ የተሰጠ ነው (ሮሜ 4፡24፤ ዮሐ. 15፡13)፡፡ ሸላቾቹ ፊት ያለን በግ አስባችሁታል? የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጥቅልል ሁሉም በአንድነት አንድ ጥያቄ ያቀርባሉ፤ ‹‹የመሥዋዕቱ በግ ወዴት ነው?›› (ዘፍ. 22፡7) የሚል፤ እንዲሁ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጥቅልል መልስ ይሰጣሉ፤ ‹‹እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ›› (ዮሐ. 1፡29)፡፡ በዕብራውያን መልእክት ‹‹እነሆ በመጽሐፍት ጥቅልል ስለ እኔ እንደ ተጻፈ›› (ዕብ. 10፡7) ተብሎ እንደተነገረ፤ እያንዳንዱ የቅዱስ መጽሐፍ ጥቅልል ገጽ የሕያው እግዚአብሔርን ልጅ ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የሚገባን (ሐዋ. 4፡12) አድርገው ያቀርቡልናል፡፡

        እርሱ ጌታ የዓለም መድኃኒት ለግፍና ለተንኮል አፉን አልከፈተም፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰልን ልንኖር የምንወድ ከሆንን (2 ጢሞ. 3፡12) ክርስቶስ ስለ ጽድቅ የተቀበለውን መከራ እንካፈላለን፡፡ እንግዲያስ እርሱ አፉን ባልከፈተበት ስፍራ ላይ ዝምታን መልመድ ያስፈልገናል፡፡ በትክክለኛው ጊዜ፤ ትክክለኛ ቦታ ላይ፤ ትክክለኛ ነገር ማድረግ ‹‹ክርስቶስ ምን ያደርግ ነበር›› ብሎ መመላለስ ነው፡፡ ለለዓመፃ፤ ለስድብ፤ ለአድማ፤ ለማቁሰል፤ ለተንኮል . . ብዙ አፎች ይከፈታሉ፤ እናንተ ግን ከሚድኑት የሆናችሁ አፋችሁን አትክፈቱ (ስድብ አይደለም)፡፡

       የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ‹‹ፊልጶስም አፉን ከፈተ›› (ሐዋ. 8፡35) ይለናል፡፡ ጌታ ኢየሱስ እንደ በግ በሸላቾቹ ፊት ዝም ባይል ኖሮ፤ እስከ መስቀል ሞት ባይታዘዝ (ፊል. 2፡8) ፊልጶስ አፉን ምን ብሎ ይከፍት ነበር? ብለን ለማሰብ እንገደዳለን፡፡ በኢየሩሳሌም እንደ ዋና (አዕማድ) መስለው (ገላ. 2፡9) የሚታዩት ሐዋርያው ጴጥሮስና ዮሐንስ ‹‹እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም›› (ሐዋ. 4፡20) እንዳሉ፤ ፊልጶስም የተናቀ፤ ከሰውም የተጠላ፤ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ፤ ስለ መተላለፋችን የቆሰለ፤ ስለ በደላችንም የደቀቀ ስለ ሆነልን ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት፡፡ አፍን ለዚህ መክፈት ምን ያህል የተገባ እንደ ሆነ ውጤቱ ያስረዳናል፡፡ ጃንደረባው ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ›› አለ፤ ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፤ ‹‹አጠመቀውም›› (ቁ. 37-39)፡፡

        በ34 ዓ/ም ክርስትና አዲስ ኪዳን ወደ አገራችን እንደ ገባ የምንተርክበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት በዚህ ክፍል ላይ ያለው ታሪክ ነው፡፡ አገልጋዩ ፊልጶስ የተናገረውን፤ ተገልጋዩ ጃንደረባ የሰማውን ወንጌል ልብ ስንል ‹‹ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ›› ነው፡፡ ‹‹ማንም ቢሆን የተለየውን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን›› (ገላ. 1፡8-9)፡፡ በጃንደረባው ዘንድ የቃሉን ፍቺ የሚሻ ልብ መኖሩ፤ በዚህ ዓለም ነገር ባለ ሥልጣን ሆኖ ሳለ ለመስማትና በሙሉ ፈቃድ ለመቀበል የእሽታ መንፈስ ማሳየቱ ‹‹ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት›› (ሐዋ. 16፡14) እንደተባለላት ልድያ ካልሆነ በቀር በሥጋና በደም አሳብ ይህ አይሆንም፡፡

    እንኳን የሰዎችን መከራ ምቾታቸውን መሠረት ያደረግ ወደ አብ የሚያደርስ የምስራች ፈጽሞ የለም፡፡ ‹‹ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ›› (1 ጢሞ. 1፡15) እንደተባለ፤ ለሰዎች ሁሉ የምንናገረው የምስራች የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነው (ሮሜ 4፡24-25)፤ ከዚህ ውጪ አፋችሁ እንዳይከፈት አብልጣችሁ ልትጠነቀቁ ያስፈልጋችኋል፡፡ ጃንደረባው ‹‹ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበር›› (ቁ. 39)፤ በሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከማመን የሚበልጥ ምን የደስታ ርዕስ አለ? እንዲህ ያለው ደስታ ይሁንላችሁ!

     ቤተ ፍቅር፤ በቅርብም በሩቅም ላላችሁ ቤተ ሰዎቻችን መልካም በዓል እንላለን!    

                            ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment