Friday, April 8, 2016

መልእክት ኀበ ፊልሞና፡፡(7)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


አርብ መጋቢት 30 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

(መልእክት ወደ ፊልሞና)

‹‹እምጳውሎስ ሙቁሐ ለኢየሱስ ክርስቶስ፡ (ኤፌ. 3፡1)!››

‹‹አእሚርየ ከመ ትወስክ እንዘ አዘዝኩከ፤ ካዘዝሁህም አብልጠህ እንድትሠራ ዐውቄ ጻፍኩልህ፡፡›› /ቁ. 21/

         ፍቅርን ለሚመለከቱ ቅን ልቦች የፊልሞና መልእክት መዋደድን ሊሞላን የሚችል ቅዱስ አሳብ የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ ግንኙነቶቻችንን የምንጠብቅበት ሰማያዊ መመሪያና መለኮታዊ አካሄድን በጥልቀት እንረዳበታለን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልሞና እና በአናሲሞስ መካከል የተፈጠረውን መለያየት አስመልክቶ ‹‹ልቡን  የሚያሳርፍ›› መፍትሔ እንዲመጣ በፍቅር ዝቅ ማለቱን እንመለከታለን፡፡ በአገራችን የሰዎችን አለመግባባት ለመፍታት የሚያስተራርቁ ሰዎች ድንጋይ ጭምር ተሸክመው በመካከል እንደሚቆሙ እናውቃለን፡፡

        በዚህ አጭር መልእክት ውስጥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሥር ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ ኢዮብ ‹‹ይኸው ስትሰድቡኝ አሥር ጊዜ ነው፤ ስታሻክሩኝም አላፈራችሁም›› (ኢዮ. 19፡3) እንዳለ፤ እንዲሁም በልማድ ‹‹አሥር ጊዜ አትነዝንዘኝ›› እንደሚባል (ይህንን ለመጀመሪያ ጊዜ ያለው የመጽሐፉ ኢዮብ ይመስለኛል)፤ ሐዋርያው ለቆሮንቆስ ምእመናን ‹‹ነገር ግን ወንድሞች ሆይ፤ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ›› (1 ቆሮ. 1፡10) ያለውን እዚህም ተግባራዊ እንዳደረገ ልናስብ እንችላለን፡፡     

       የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም የኃጢአታችንን ስርየት የተቀበልንበት ስም እንደ ሆነ ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል (ሐዋ. 10፡43)፡፡ ስሙ ሸክም ሳይሆን ሸክማችን የወረደበት ነው፡፡ የዋህ በልቡም ትሑት፤ ቀንበሩ ልዝብ፤ ሸክሙም ቀሊል (ማቴ. 11፡29) በሆነው ጌታ ስም የሚያስተራርቁ ብጹአን ናቸው (ማቴ. 5፡9)፤ መጠሪያቸውም የእግዚአብሔር ልጆች ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ፊልሞናን እየለመነው ያለው ከስም ሁሉ በላይ ያለውን ስም በወረሰው፤ በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በእርሱ ስም ይንበረከኩለት ዘንድ ባለው በጌታችን በኢየሱስ ስም ነው (ፊል. 2፡9-11፤ ዕብ. 1፡4)፡፡
      
       ሐዋርያው ስለ ፊልሞና የሚሰጠውን ምስክርነት ልብ በሉ፤ ‹‹ከምልህ ይልቅ አብልጠህ እንድታደርግ አውቄ፤ እንድትታዘዝም ታምኜ›› ይለዋል፡፡ እንዲህ ላለው የጌታ ሠራተኛ መልእክት መጻፍ በእጅጉ ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡ ለአመጸኞች ስለ ተጻፉ ደብዳቤዎች የምንኖርበት የአሁኑ ዓለም መልክ ምስክር ነው፡፡ አሁን እናንተ ይህንን ጽሑፍ እያነበባችሁ ባላችሁበት ቅጽበት ሰዎች ስለሚለዋወጡት መልእክት ጥቂት አስቡ፡፡ ምን ያህሉ የፍቅር ይዘት ያላቸው ይመስልሃል? ምን ያህሉስ የእውነት መሠረት ያላቸው ይመስልሻል?

        በሚታዘዙ ልቦች መካከል የሚኖረው የመልእክት ልውውጥ በመለኮታዊ እረፍት የተሞላ ነው፡፡ እንዲህ ባሉ አንድነቶች ዘንድ ድብቅነት ቦታ የለውም (ሐዋርያው ‹‹አውቄ›› እንዲል)፤ የይፈጸም ይሆን? ሥጋትም አናስተውልም (ሐዋርያው ‹‹ታምኜ›› እንዲል)፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ፊልሞና ከልኩ አብልጦ መልካም የሆነውን የሚያደርግ ክርስቲያን ነበር፡፡ በእናንተ ዘንድ የሰዎች ልካቸው ተሰፍሮ ቢሆን፤ ከዚያ ከፍ ብላችሁ ጽድቅ የሆነውን አድርጉ፡፡ ‹‹ . . እንደ ተባለ ሰምታችኋል፡፡ . . ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል፡፡ . . . ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ?›› (ማቴ. 5፡38-48)፡፡      
                 
       ሐዋርያው ጳውሎስ የሚጽፈው መልእክት ከንቱ እንዳላይደለ፤ ‹‹አውቄ›› እና ‹‹ታምኜ›› የሚሉት ቃላት እርግጠኝነትን ይገልጹልናል፡፡ በሌሎቹ መልእክታት ፊልሞናን በተመለከተ አንዳች ክፉን አለማግኘታችን እንደ ተጻፈው እንደዚያው በአናሲሞስና በፊልሞና መካከል ላለው ችግር የተጻፈው መልእክት መፍትሔ እንደ ሆነ እንረዳለን፡፡ ከእግዚአብሔር የሆነው ሁሉ የማይፈታው ቋጠሮ የለም፡፡ ባለ እንቆቅልሾች ፈቺውን እንኩ፤ ክርስቶስ ኢየሱስ!  

‹‹የማስተናገጃ ቤት አዘጋጅልኝ››

        ‹‹እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና›› (ዕብ. 6፡10)፤ ያለን ሐዋርያ፤ ‹‹በጸሎታችሁ ለእናንተ እንድሰጥ ተስፋ አደርጋለሁና የማስተናገጃ ቤት አዘጋጅልኝ›› በማለት ፊልሞናን ይጠይቀዋል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው ለፊልሞና ቢሆንም በመልእክቱ መግቢያ ላይ ‹‹ለእኅታችንም ለአፍብያ ከእኛም ጋር አብሮ ወታደር ለሆነ ለአርክጳ በቤትህም ላለች ቤተ፡ ክርስቲያን›› እንዳለ አሳስባችኋለሁ፡፡

       ሐዋርያው ለሮሜ ክርስቲያኖች ‹‹ትጸኑ ዘንድ መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እናፍቃለሁና›› (ሮሜ 1፡11) እንዳለ፤ በፊልሞና ቤት የምእመናን ኅብረት እንደ መኖሩ በሐዋርያው በኩል የእግዚአብሔርን ጸጋ እንዲካፈሉ (1 ቆሮ. 15፡10)፤ በጸሎት የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደ ለመኑ እንረዳለን፡፡ ‹‹ጳውሎስም በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፤ ወደ እርሱም የሚመጡትን ሁሉ ይቀበል ነበር . . የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር›› (ሐዋ. 28፡30) ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ እንዲሁ በፊልሞናም ቤት ያገለግል ዘንድ ‹‹አዘጋጅልኝ›› ይለዋል፡፡

       በችግሮች መካከል ስፍራችን መፍትሔ መሆን እንደሚገባው ይህ መልእክት ያሳስበናል፡፡ የሰዎችን ዘላለማዊ ችግር በወንጌል መፍታት ትልቅ ተግባር መሆኑ እንዳለ ሆኖ፤ በዚህም ዓለም የጊዜው ኑሮ ውስጥ ሰዎች የሚገጥማቸውን የግንኙነት ፈተና ለመፍታት ከእምነት የሆነ ትጋት ማሳየትም አስፈላጊ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለአናሲሞስ ወንጌል መስበኩ በራሱ በቂ እንደ ሆነ ማስብ ብንችልም፤ እርሱ ግን ከዚህ አልፎ ባሪያ የሆነውን አናሲሞስ አሳዳሪው ከሆነው ከፊልሞና ጋር ለማስታረቅ እንደ ክርስቶስ አገልጋይ በጽድቅ ሁሉን አድርጓል፡፡                                                                    ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!







No comments:

Post a Comment