Monday, May 30, 2016

መልእክት ፡ ኀበ ፡ ሰብአ ፡ ኤፌሶን፡፡ (2)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!



የሐዋርያው ፡ የጳውሎስ ፡ መልእክት ፡ ወደ ፡ ኤፌሶን ፡ ሰዎች፡፡

ሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

‹‹ወአርአየነ ምክረ ፈቃዱ በከመ ሥምረቱ›› (ኤፌ. 1፡9)!

v  የጥናቱ መግቢያ

·  የኤፌሶን ቤተ፡ ክርስቲያን የተመሰረተችው በሐዋርያው ጳውሎስ ሁለተኛ ሐዋርያዊ የአገልግሎት ጉዞ ነው፡፡

·  ሐዋርያው በቆሮንቶስ ከተማ ለ18 ወራት ከነበረው የአገልግሎት ቆይታ በኋላ (ሐዋ. 18፡11)፤ ከጵርስቅላና ከአቂላ ጋር በመሆን ኤፌሶንን ጎብኝቷል (ሐዋ. 18፡18)፡፡

·  ሐዋርያው በኤፌሶን የነበረው የመጀመሪያ ቆይታ ለአጭር ጊዜ የነበረ ሲሆን፤ ዳሩ ግን እንደሚመለስ ቃል ገብቶላቸው ነበር (ሐዋ. 18፡19-21)፡፡ ነገር አዋቂ፤ በመጻሕፍት እውቀት የበረታ፤ የጌታን መንገድ የተማረ፤ የዮሐንስን ጥምቀት የሚያውቅ፤ በመንፈስ የሚቃጠል፤ ስለ ኢየሱስ የሚናገርና በትክክል የሚያስተምር ለሆነው አጵሎስ ‹‹የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ በትክክል ገለጡለት›› የተባለላቸው ጵርስቅላና አቂላ በኤፌሶን ቆይተዋል (ሐዋ. 18፡24-26)፡፡

· ሐዋርያው በሦስተኛ ሐዋርያዊ ጉዞው ወደ ኤፌሶን የተመለሰ ሲሆን፤ በዚያም ለሦስት ዓመታት በአገልግሎት ቆይቶአል (ሐዋ. 19፡8-10፤ 20፡31)፡፡ አንደኛ እና ሁለተኛ የቆሮንቶስ መልእክታትን የጻፈው በእስያ ዋና ከተማ ከሆነችው ከኤፌሶን ነው (1 ቆሮ. 16፡8፤9)፡፡ በዚያ ብዙ ድንቅና ተአምራት በእርሱ በኩል ተከናውነዋል (ሐዋ. 19፡12)፡፡

· ሐዋርያው በእድሜው ማብቂያ ከኤፌሶን አስጠርቶአቸው ከመጡ ሽማግሌዎች (ባለ አደራ) ጋር በሚሊጢን እንደተገናኘ፤ ምክርና ማስጠንቀቂያ አዘል የስንብት መልእክት አስተላልፏል (ሐዋ. 20፡16-38)፡፡

·  የኤፌሶን ቤተ፡ ክርስቲያን (ማኅበረ ምእመናን) በአዲስ ኪዳን ከአንድ በላይ መልእክት የተጻፈላት ብቸኛ ጉባኤ እግዚአብሔር ናት፡፡ ከዚህ መልእክት ሌላ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ራእይ ቅዱስ ዮሐንስ ባየውና በጻፈውም መልእክት ውስጥ ተጠቅሳለች (ራእ. 2፡1-7)፡፡
ከሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናት በበለጠ፤ በሐዋርያው ጳውሎስ፣ በሐዋርያው ዮሐንስ፣ በአጵሎስና በጢሞቴዎስ ትምህርትና ስብከት የተገለገለች ቤተ፡ ክርስቲያን (ማኅበረ-ምእመናን) ናት፡፡

·  ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስይስ መልእክቱ ‹‹ይህችም መልእክት በእናንተ ዘንድ ከተነበበች በኋላ በሎዶቅያ ሰዎች ማኅበር ደግሞ እንድትነበብ አድርጉ›› (ቆላ. 4፡16) ብሎ የጻፈው የኤፌሶንን መልእክት መጥቀሱ እንደ ሆነ በሚታመነው መሠረት፤ ይህ መልእክት በእስያ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት በዙር የተነበበ የእግዚአብሔርን ፈቃዱን ምስጢር መገለጥ የያዘ መልእክት ነው፡፡

      በሰው ልብ ውስጥ የሌላውን ልብ የማወቅ ፍላጎት ከፍተኛ ነው፡፡ ምን እያሰብን እንዳለን ከመጠንቀቅ ይልቅ፤ ሌሎች ምን እያሰቡ እንደ ሆነ ለመረዳት መሞከር የብዙዎችን አቅም የጨረሰ የዘወትር ጥረት ነው፡፡ ማወቅ ስለምትፈልጉት ነገር ብጠይቃችሁ፤ ምን ያህል ዝርዝር ፍላጎቶች ሊኖሯችሁ እንደሚችሉ አብረን ካልገመትን በቀር ልኩ እናንተ ጋር የለም፡፡ ማንነቶቻችን በብዙ መሻቶች የተሞሉ ናቸው፡፡ ፍለጋውም እጅግ አድካሚ ነው፡፡ ቃሉ ግን ይለናል፤ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው (መዝ. 104፡3)፡፡

       ተወዳጆች ሆይ፤ ስለ እግዚአብሔር ያለን መረዳት ራሱ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል በገለጠልን እውነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የኤፌሶን መልእክት ደግሞ ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ልብ ውስጥ ያለው ቅዱስ ምክር ለእኛ ግልጥ የሆነበት መጽሐፍ ነው፡፡ ዓለም ሳይፈጠር፤ ከዘላለም ዘመናት በፊት የመለኮት እቅድ ምን መሆኑን ማወቅ ለሚወድ ልብ ሁሉ የእግዚአብሔር ልብ (አሳብ) በዚህ መልእክት የታወቀ ነው (በገለጠልን መጠን)፡፡

       ሰው የልቡን የሚገልጠው ለሚወደው ነው፡፡ እርሱ እግዚአብሔር ወዶናል (ዮሐ. 3፡16፤ የዮሐንስ ወንጌል ቁልፍ ጥቅስ)፡፡ የእርሱ የሆነውን እንድናውቅም አድርጎናል፡፡ እግዚአብሔር ጅማሬን ብቻ ሳይሆን በፍጻሜው ምን ሊያደርግ እንዳለውም የተናገረ ነው፡፡ ብዙ እቅዶች ለሌሎች ሽሽግ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሰው ይሠጋል፤ ባልያዘው ነገም ይፈራል፡፡ ሰውን ያይደለው እግዚአብሔር (አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ) የልቡን አውጥቶ ሊነግረን የሰው ፊት አላየም፡፡ ያስከተለን መድረሻችንን ገልጦ ነው፡፡

      በእርግጥ! የልቡን አሳብና ምክር ለገለጠው ሕያው እግዚአብሔር ሰው የእምነትና ፍቅር ምላሽ ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ የአፋቸውን ሳይሆን የልባቸውን እንድናውቅ ለፈቀዱልን፤ ስውሩንም ነገራቸውን ለገለጡልን ለፍቅራቸው መሸነፋችን የሚጠበቅ ነው፡፡ ለተገለጠው የእግዚአብሔር የልብ አሳብ መታዘዝ አለመቻል የማይጠበቅ እንደ ሆነ አስተዋላችሁን? አዎ! በሙላት የእሽታ መንፈስ ሊኖረን የተገባ ነው፡፡

    ሐዋርያው ጳውሎስ የኤፌሶንን መልእክት ለሚጽፍላቸው ማኅበረ ምእመናን፤ የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ፤ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣቸው (ኤፌ. 1፡17)፤ በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፊት ይንበረከካል (ኤፌ. 3፡14፤15)፡፡ በመልእክቱ የመጀመሪያ ምእራፍ ‹‹የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ›› (1፡18፤19) ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ የሰማይ ነገርን ሰው በራሱ የሚያስተውልበትና የሚሸከምበት አቅም የለውም፡፡ ሰዎች በተለምዶ ‹‹የበራለት›› እና ‹‹ያልበራለት›› የሚለውን መደልደያ የሚጠቀሙት ለዚህ ይሆናል፡፡
  
     እግዚአብሔር ሰጪ ብቻ ሳይሆን የሰጠንን የምንሸከምበት አቅምም የሚሰጠን ነው፡፡ እኛ ምቹ የሆነውን ነገር እንኳ የእኛ በሆነው ማንነት በአግባብ ማስተናገድ የማንችል ደካሞች ነን፡፡ ሐዋርያው በሌላው መልእክቱ ‹‹ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ›› (ፊል. 4፡12) ያለው፤ አስቀድሞ ‹‹መዋረድንም አውቃለሁ፤ መብዛትንም አውቃለሁ . . . ›› ካለን በኋላ ነው፡፡ ምቾቶቻችንን እንኳ የምንሸከምበት ጉልበትና ኃይል ክርስቶስ ነው፡፡ በዚህ መጠላለፍ የሆነባቸው ብዙ ናቸውና፡፡

    ‹‹በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ የፈቃዱን ምስጢር አስታውቆናልና . . ›› (ኤፌ. 1፡9) የሚለን ሐዋርያ እግዚአብሔር ያስታወቀንን እንድንረዳው ተንበርክኮ ይጸልያል፡፡ ወደዚህ ጥናት ስንመጣ ልናደርገው የተገባውን ትልቅ ነገር ከዚሁ የመልእክት ክፍል እንረዳለን፡፡ ቤተ ሰዎቼ፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ገፆች አብዛኛውን እንዳነበባችሁ፤ ብዙ ጉባኤያት ላይ እንደተሳተፋችሁ፤ ለመረዳትና ለመግለጥ የበረታችሁ እንደ ሆነ ቢሰማች፤ እውነቱ ግን የእግዚአብሔርን የዘላለም ምክርና አሳብ ልናውቅና ልንኖር የምንችለው በእርሱ ጸጋ ነው፡፡
              
      የኤፌሶን ማኅበረ ምእመናን በክርስቶስ በማመን ክርስቲያን የሆኑና መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸውና በዘንዳቸው የሚሠራ ናቸው፡፡ ዳሩ ግን ‹‹የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ›› ሐዋርያው ይለምንላቸዋል፡፡ ቤተ ሰዎች እኛስ ይህ አያስፈልገንምን? እንደ ሐዋርያው በአባት ፊት ለመንበርከክ የሚሆን የልብ መነካት ይሁንላችሁ፡፡

ምእራፍ አንድ
                   ርዕስ፡- የመለኮት ዘላለማዊ አሳብና የልብ ምክር፡፡

አከፋፈል፡-

1.    የመልእክቱ መግቢያ (ቁ. 1-2)
2.   የተወደደ ምስጋና (ቁ.3)
3.   የሕያው አብ ሥራ (ቁ. 4-6)
4.   የሕያው ወልድ ሥራ (ቁ. 7-12)
5.   የሕያው መንፈስ ቅዱስ ሥራ (ቁ. 13-14)
6.  ለክብር አባት የቀረበ ምስጋናና ጸሎት (ቁ. 15-23)

ቤተ ሰዎቼ፤ ራሳችሁን እንዲህ ጠይቁ፡-


ü ስለ ኤፌሶን ከተማ ምን ታውቃላችሁ?
ü ሐዋርያው በከተማይቱ ሲያገለግል የገጠመው ፈተና ከምን ጋር የተያያዘ ነበር?
ü ዛሬ ወንጌልን በመስበክ አገልግሎት ቤተ ክርስቲያን ያለባት ተግዳሮት ያንጊዜ ከሆነው ጋር ያለው መመሳሰልና መለያየት ምን ይመስላል?

E-mail: bfb.tube@gmail.com ወይም facbook: Bete Fikir Fam ላይ ልትመልሱ ትችላላችሁ፡፡

‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment