Tuesday, May 3, 2016

ምስኪን ማነው?

             በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
             

ማክሰኞ ሚያዝያ 25 ቀን 2005 የምሕረት ዓመት


         በክርስትና መሠረተ ትምህርት ውስጥ የ‹‹ትንሣኤ ሙታን›› አሳብ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡  ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የመጀመሪያይቱን የቆሮንቶስ መልእክት ሲጽፍ በጊዜው መፍትሔ ከተሰጠባቸው ችግሮች አንዱ ‹‹ትንሣኤ ሙታን የለም›› የሚለው የአንዳንድ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መረዳት ነው፡፡ የቆሮንቶስ መልእክት በምሕረቱ ባለ ጠጋ (ኤፌ. 2፡4) የሆነውን የእግዚአብሔርን ጸጋ የምናስተውልበት መጽሐፍ ነው፡፡ በመልእክቱ መግቢያ ‹‹በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ፡ ክርስቲያን፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት›› (1፡2) የሚለው አገላለጽ እግዚአብሔር በክርስቶስ ያሉትን ምእመናን ድካም የሚመለከትበትን የጸጋ ዓይን እንድናይ ያደርገናል፡፡

ምእራፍ 15፡ 
ርዕስ፡ - ትንሣኤ እርግጥ ነው!

                       .  የክርስቶስ ትንሣኤ ወንጌል (1-11)
                       .  ክርስቶስ ባይነሣ ስፍራችን (12-19)
                       .  ክርስቶስ እንደ በኩራት (20-28)
                       .  ስለ ሙታን ትንሣኤ የቀረበ ተግባራዊ ማስረጃ (29-34)
                       .  ስለ አካል መነሣት የተሰጠ ትምህርት (35-49)
                       .  የጌታ መምጣትና በእርሱ በኩል ያለን ድል መንሣት (50-58)፡፡ 

         ሐዋርያው በዚህ ምእራፍ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በተመለከተ ሁለት ማስረጃዎችን ያቀርባል፡፡ አንደኛ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሲሆን፤ ሁለተኛ ደግሞ የዓይን ምስክሮችን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ‹‹እንዲሁ እንሰብካለን፤ እንዲሁም አመናችሁ›› (1 ቆሮ. 15፡11) በማለት ወደ ክርስትና የመጡበትን እውነት ያሳስባቸዋል፡፡ ሐዋርያው በአቴና ‹‹የኢየሱስንና የትንሣኤውን ወንጌል›› እንደ ሰበከ እናውቃለን (ሐዋ. 17፡18)፡፡ እርሱ ወደ ክርስትና፤ ሐዋርያም ሆኖ ወደ መሾም የመጣው ከሙታን በኩር ሆኖ የተነሣውን ጌታ ደማስቆ ላይ ከተገናኘ በኋላ ነው (ሐዋ. 9፡1-8፤ 1 ጢሞ. 1፡12)፡፡ በእርሱ በኩል ካልሆነ በቀር እንዲህ አይሆንም፡፡

         ከትንሣኤ ጋር በተያያዘ በቆሮንቶስ ያለው ችግር ክብደት እንዲህ ተቀምጧል፤ ‹‹ትንሣኤ ሙታን ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣም፤ ክርስቶስ ካልተነሣ ስብከታችን ከንቱ ነው፤ ስብከታችን ከንቱ ከሆነ እምነታችንም ከንቱ ነው፤ እምነታችን ከንቱ ከሆነ አገልጋዮቹ ሐሰተኞች ነን፤ እንዲህ ከሆነ ደግሞ እስካሁን ድረስ በኃጢአታችን አለን፤ በክርስቶስ አምነው ያንቀላፉትም ጠፍተዋል›› (ቁ. 12-18)፡፡ የክርስትናችን መሠረት የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነው (ሮሜ 4፡24-25)፡፡

          ‹‹ይህም ወንጌል . . ›› (ሮሜ 1፡3) ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ ወንጌል በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ለእኛ የመጣውን ትርፍ መረዳት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተነሣ፤ እንዲሁ እኛም እንነሣለን (1 ተሰ. 4፡14)፡፡ ሐዋርያው ክርስቶስ ስለ በደላችን አልፎ በመሰጠቱ፤ እኛንም ስለ ማጽደቅ ከሙታን በመነሣቱ ‹‹አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት›› (ዘፍ. 15፡6) የሚለው ስለ እርሱ ብቻ ሳይሆን ስለ እኛም እንደ ሆነ ‹‹ለምናም ለእኛ ይቆጠርልን ዘንድ አለው›› (ሮሜ 4፡25) ይለናል፡፡

          ተወዳጆች ሆይ፤ በሕያው እግዚአብሔር ተቀባይነትን ያገኘነው በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነው፡፡ ‹‹ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ›› ተብሎ የተጻፈውም ቃል (1 ቆሮ. 15፡54) ፍጻሜን የሚያገኘው በዚህ መሠረት ነው፡፡ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ፤ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ ዜማችን ‹‹ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ ድል መንሣትህ የት አለ?›› የሚል ይሆናል (1 ቆሮ. 15፡53-57)፡፡ ሁል ጊዜ ከጌታ ጋር ወደ መሆን (1 ተሰ. 4፡17) ክብር የምንመጣበት ብቸኛው መንገድ ‹‹ከእርሱ ጋር አስነሣን›› (ኤፌ. 2፡6) እንደ ተባለ፤ በማመን ትንሣኤ ሕይወት መሆናችን ነው፡፡ ይህም በሚመጡ ዘመናት በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠው የጸጋው ባለ ጠግነት ይታያል፡፡

         በቆሮንቶስ ቤተ፡ ክርስቲያን ክርስቶስ እንደ ተነሣ ይሰበካል፤ ዳሩ ግን ‹‹ትንሣኤ ሙታን የለም›› የሚሉ ነበሩ፡፡ በእርግጥ ይህ ትልቅ አለማመን ነው፡፡ እንዲህ አስቡት፤ ‹የምስራች! ክርስቶስ ተነሥቶአል› ተብሎ ይሰበካል፤ ሰሚው ግን ‹በሞትና በመበስበስ ለሚደመደም ሕይወት› እያለ ይቆዝማል፡፡ የክርስቶስ መነሣት እንኳን መንፈሳዊውን፤ የሰዎችን ስነ ልቦናዊ ጥያቄም መልሷል፡፡ ሰዎች ከሞት በኋላ ያላቸውን የፍጹም ዕረፍት ሕይወት በማሰብ በተስፋና በደስታ እንደሚሞሉ፤ የአካላቸውን ትንሣኤ በማወቅ ደግሞ ለራሳቸው ያላቸው ምልከታና ጥንቃቄ ከፍተኛ እንደሚሆን የባህርይ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

         ከማንኛውም ጥቅም በላይ የክርስቶስ ትንሣኤ በበለጠ ሁኔታ በሕይወት የመኖራችንን ቀጣይነት አረጋግጦልናል (ዮሐ. 11፡25)፡፡ በብሉይ ኪዳን ኢዮብ ‹‹አሁን በምድር ውስጥ እተኛለሁ፤ ማለዳ ትፈልገኛለህ፤ አታገኘኝም›› (ኢዮ. 7፡21) እንዳለ እናነባለን፤ ዳሩ ግን የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ወርዶ በሞቱ አግኝቶናል (ኤፌ. 4፡9)፡፡ የትኛውም መከራና ፈተና የማያስቀረው፤ ሞትን ድል ያደረገ የተባረከ ተስፋ አለን (ቲቶ 2፡112)፡፡ ጌታ ስሙ ይቀደስ!

         ተወዳጆች ሆይ፤ ክርስቶስን ተስፋ ያደረጋችሁት ለምንድነው? ሐዋርያው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ያስጠነቅቃል፤ ‹‹በዚህች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን›› (1 ቆሮ. 15፡19)፡፡ ከንፈር የምንመጥላቸውን፤ ፍርፋሪ የምንጥልላቸውን ምስኪን እንደ ሆኑ ቆጥረናቸው ኖረናል፡፡ አሁን ግን ከጊዜው ማጣት ባለፈ በዘላለም አምላክ ፊት ያለውን ምስኪንነት ልብ ማለት ያስፈልገናል፡፡ በክርስቶስ አምኖም ምስኪንነት እንዳለ ማስተዋል በእጅጉ ተገቢ ነው፡፡

       ክርስትና በዚህ ዓለም ከሚኖረው መደላደል ያለፈ አጀንዳ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሞሰብ ሙሉ እንጀራ እንዲሆንላቸው የሚፈልጉ ውስጣቸው እርሱን ያልጠገበ ናቸው፡፡ ልምጣ የማይል ያምጣ ክርስትና በዚህች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረገ ነው፡፡ የእኛን ተስፋ በተመለከተ ‹‹እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው›› (1 ዮሐ. 2፡24) ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ክርስቶስ ተነሥቶአልና ሕያው ተስፋ አለን፡፡ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ እድፈትም ለሌለበት ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ›› (1 ጴጥ. 1፡3)፡፡

       ክርስቶስን በአሁኑ ዓለም ሕይወት ብቻ ሳይሆን ሊመጣ ባለውም ዓለም ሕይወት ተስፋ እናደርገው ዘንድ ተነሥቶአል፡፡ በቆሮንቶስ ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ አንዳንዶች እንደ ነበሩ ስናነብ፤ ዛሬ ግን ትንሣኤ ሙታን የለምን በተግባር የሚኖሩ ብዙ ሰዎችን ማየት እንችላለን፡፡ ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን፤ በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን የምንል ዳሩ ግን በትንሣኤው ኃይል የማንመላለስ ከሆነ ከቆሮንቶስ አንዳንዶች የእኛ ብልጫው ምንድነው? ደስታችንም ሀዘናችንም ውስጥ ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ ሊገለጥ ያስፈልገናል፡፡ መጥገብንም መራብንም፤ ችግርንም ምቾትንም የምንችልበት ኃይል ክርስቶስ (ፊል. 4፡12-13) ማስተዋልን ያብዛልን!

                             ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment