Thursday, August 11, 2016

ሁለቴ የኔ ነሽ፡፡

                         
            
             በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ሐሙስ ነሐሴ 5 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

         ‹‹አንድ ትንሽ ልጅ በእጁ የሠራት ጀልባ ከዕለታት በአንዱ ቀን ተሰረቀችበት፡፡ እንዲህ ከሆነ ከብዙ ቀናት በኋላ፤ ዕቃ እያስያዘ ገንዘብ በሚያበድር ሰው ሱቅ በኩል ሲያልፍ ጀልባውን አያት፡፡ በደስታ ወደ ሰውየው ሮጦ ‹‹ያቺ የእኔ ትንሽ ጀልባ ናት›› አለው፡፡ ዕቃ አስይዞ አበዳሪውም ‹‹የለም፤ እኔ ስለገዛኋት የእኔ ናት›› ብሎ መለሰለት፡፡ ‹‹አዎ፤›› አለ ትንሹ ልጅ፤ ‹‹ግን የእጄ ሥራ ስለሆነች የእኔ ናት›› በማለት አስረዳው፡፡ ‹‹እንግዲያውስ›› አለ ዕቃ አስይዞ አበዳሪው፤ ‹‹ሁለት ዲናር ከሰጠኸኝ ልትወስዳት ትችላለህ›› አለው፤ ጀልባውን ዳግም የራሱ ለማድረግ በብርቱ የፈለገው ልጅ የተጠየቀውን ለመክፈል የጉልበት ሥራዎችን በመሥራት ገንዘቡን አገኘ፡፡

          ከዚያም ወደ ሱቁ በመሔድ ገንዘቡን ከፍሎ ጀልባውን አስመለሰ፡፡ በመጨረሻም ጀልባውን በእጆቹ አቅፎ እየሳመ ‹‹አንቺ ውድ ትንሽ ጀልባ፤ እወድሻለሁ፡፡ አንቺ ሁለቴ የእኔ ነሽ፡፡ በፊት ሠራሁሽ፤ አሁን ደግሞ ገዛሁሽ›› አለ፡፡ /William Moses Tidwell, Pointed Illustrations (Kansas City, Mo.; Beacon Hill Press, 1951) P. 97/.

        ከላይ ያነበብነው ታሪክ የወጣ ሲመለስ፤ የጠፋ ሲገኝ፤ የወደቀ ሲነሣ . . ያለውን ደስታና እርካታ ቆም ብለን እንድናስብ ይጋብዘናል፡፡ ሁሉም ነገር ላይ ‹‹የማይዘልቅ›› የሚል በተለጠፈባት የአሁኗ ዓለም የኑሮ ሥርዓት ውስጥ ባትጠፉ እንኳ የጠፋ ፈልጋችሁ እንደምታውቁ ግልጥ ነው፡፡ የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ (ቆላ. 414) በጻፈው የወንጌል ክፍል፤ ከዘኬዎስ መጎብኘት ጋር በተያያዘ ‹‹ኢየሱስም፡- . . የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና›› /ሉቃ. 199/ ተብሎ ተጽፎ እናነባለን፡፡ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ፈላጊም አዳኝም›› ነው፡፡

         መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር የኃይሉ ብርታት የተገለጠባቸውን እና ለእርሱ ብቻ ምስጋና የሚመጣባቸውን በዋናነት ሁለት ታላቅ ጥበቦች ይነግረናል፡፡ በሮሜ 120-21 ስናነብ ‹‹የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና›› የሚል ተጽፎ እናገኛለን፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሳችን የመጀመሪያ ክፍል እግዚአብሔርን በሉዓላዊነቱና ሁሉን በመቻሉ በኩል የሚያቀርብ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ ፍቅሩን ልብ እንላለን፡፡ ‹‹በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ፡፡›› /ዘፍ. 11/፡፡ የኤሎሂም የመፍጠር ኃይልና ብርታት በቃል የተገለጠበት ስፍራ ነው፡፡ ‹‹ራሱን ያለ ምስክር አልተወም›› /ሐዋ. 1417/ እንደተባለ፤ ሥነ ፍጥረትና መግቦቱ የእግዚአብሔርን ኃይልና ጥበብ ይመሰክራሉ፡፡

        አምላካችን በፍጥረቱና በመግቦቱ ይታወቃል፤ የምንልበት መሠረት ቅዱሱ መጽሐፍ ነው፡፡ ቀና ብለን የምንመለከተው ሰማይ፤ ከዚያም በላይ ያሉ ሰማያት፤ በውስጣቸው የያዙአቸው ፍጥረታት እግዚአብሔር የፍጥረት አስገኝና ባለቤት ስለ መሆኑ ይመሰክራሉ፡፡ ነቢዩ ‹‹ሰማያት ይነግራ ስብሐተ እግዚአብሔር፤ ወግብረ እደዊሁ ያየድዓ ሰማያት›› /መዝ. 181/ ‹‹ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል›› ይለናል፡፡ ደግሞ ምድርን በተመለከተ ‹‹ለእግዚአብሔር ምድር በምልኣ፤ ወዓለምኒ ወኩሎሙ እለ ይነብሩ ውስቴታ›› ‹‹ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት፤ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉ›› /መዝ. 231/ ይላል፡፡

        እግዚአብሔር ብቻውን ፈጣሪ ነው፡፡ ፍጥረት የእጁን ሥራ ያወራል፡፡ ይህም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያል፡፡ በላይ በሰማይ ፀሐይ፤ ጨረቃ፤ ከዋክብርት እግዚአብሔር የብርሃናት አባት እንደ ሆነ ምስክር ናቸው (ያዕ. 117)፡፡ እርሱ ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው፤ እንደ ድንኳንም ለመኖሪያ የሚደኩናቸው፤ ልካቸውን በስንዝር የለካ፤ ዝናምን መስኮቶች ከፍቶ የሚያዘንም፤ ነፋሳትንም የሚያዝ ነው፡፡ በታች በምድር ሜዳ ተራራው፤ ሳርና ዛፎቹ፤ በመስፈሪያው ተሰብስቦ የተያዘው አፈር፤ በሚዛኑ የመዘናቸው ኮረብቶች ስለ እርሱ ይናገራሉ (ኢሳ. 4012)፡፡ የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት ዓለምን ከምንም ወደ ሕልውና በማምጣቱ የታወቀ ነው፡፡

       እግዚአብሔር የኢዮብን ጥያቄ በጥያቄ ሲመልስ ‹‹ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት ነህ? . . በላይዋስ የመለኪያ ገመድ የዘረጋ ማን ነው? . . የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማን ነው? . . ባሕርን በመዝጊያዎች የዘጋ ማን ነው? . . በውኑ ከተወለድህ ጀምሮ ማለዳን አዝዘሃልን? ለወገግታም ስፍራውን አስታውቀኸዋልን? . . ›› (ኢዮ. 38) ይለዋል፡፡ ያሕዌ የኃይሉ ታላቅነትና ግርማ የማይወዳደር ነው፡፡ ከእያንዳንዱ ፍጥረት ጀርባ ብርቱ የሆነው የአምላካችን ክንድ አለ፡፡ የተደረሰበት የታወቀው፤ ያልተደረሰበት የተሰወረው ሁሉ የአምላካችንን አምላክነት በግልጥ ይመሰክራሉ፡፡

      እግዚአብሔርን አመስግኑት፡፡ ያልነበረውን የሚያመጣ፤ የነበረውንም የሚያሳልፍ ነውና ስለ መቻሉ አመስግኑት፡፡ ለሁሉ ውበት የሰጠ፤ ዳርቻና ወሰን ያበጀ፤ ሊያኖር ሊገድል ብቸኛ እርሱ ነውና አመስግኑት፡፡ ከፈጠረው ሁሉ አልቆ ሰውን በመልኩ በምሳሌው የፈጠረ እርሱ ነውና ስለ መውደዱ አመስግኑት፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ነቢዩ ‹‹ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች›› (መዝ. 13814) እንዳለ፤ ይህ እውቀት ያላችሁ ፈጣሪያችሁን አመስግኑት፡፡

     እግዚአብሔር ለኢዮብ መልስ ሲሰጥ ‹‹ያለ እውቀት በሚነገር ቃል፤ ምክርን የሚያጨልም ይህ ማነው?›› (ኢዮ. 382) በሚል ብርቱ ጥያቄ ነበር፡፡ እግዚአብሔር መልስ የሆነ ጥያቄ እንዳለው ማወቅ ምንኛ ማስተዋል ነው፡፡ ብዙዎች መልስ የሚፈልጉላቸውን ጥያቄዎች በቅጡ አለማስተዋላቸው፤ በጥያቄዎቹ ውስጥ ያለውን መልስ ልብ እንዳይሉ ተጋርደዋል፡፡ እግዚአብሔር በፍጥረቱ ይታወቃል፡፡ ዛሬም ያለ ቅዱስ እውቀት በሚነገር ቃል ምክር እየጨለመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፡- ‹‹እንግዲህ እንደ ሰው ወገብህን ታጠቅ እጠይቅሃለሁ፤ አንተም ተናገረኝ››፡፡

     ጥበበኛ የጥበብ ጥግ ያሕዌ ያለህና የምትኖር ሆይ፤ ከማወቃችን እጅግ ስለሚበልጠው ማወቅህ፤ ከምክራችን እጅግ ስለሚጠልቀው መካርነህት፤ ከብልሃታችን ስለሚጠበበው አደራረግህ ብዙ ክብር ላንተ ይገባሃል፡፡ መጻሕፍት ባይገለጡ፤ ጥቅሶች ባይጠቀሱ፤ ሰባኪ ባይቆም፤ ቃል ባይተረጎም አንተ ግን ፍጥረት ይጮህልሃል፡፡ ተራራው ከሜዳ፤ ሰማዩም ከትቢያ እየተቀባበለ ‹‹ሁሉን የሚችል ሠርቶናል›› ይሉሃል፡፡
                                                                                          - ይቀጥላል፡፡

       ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment