በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
እሮብ ነሐሴ 25 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት
ተወዳጆች ሆይ፤ ጥበብ ለእናንተ
ምንድነው? እውነተኛ ጥበብ መገኛው የት ነው? ጥበብን ስለ ማግኘት ልንከፍለው የምንችለው ዋጋ ስንት ነው? ባለፈው ክፍል ለእነዚህ
ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ በቂ አሳቦችን አይተናል፡፡ ትክክለኛውን ጥበብ ጥበባችን አድርገን እንኖር ዘንድ ጸጋው ይርዳን፡፡
ጽድቅ
‹‹ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ!›› (ኢሳ. 64፡1)፤ በቀደመው ኪዳን የነቢዩ የኢሳይያስ ብርቱ ጸሎትና መሻት
ነበር፡፡ ይህንን ልመና ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርብ ምክንያት የሆነውን ነገር ስንመረምር ደግሞ ‹‹ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፤
ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው . . ›› (ኢሳ. 64፡6) ተብሎ ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም
ከገባበት (ሮሜ 5፡12) ጊዜ አንስቶ የሥጋ ለባሽ ሁሉ ብርቱ የጋራ ጩኸት ‹‹የጽድቅ ያለህ›› የሚል ነው፡፡