Wednesday, August 17, 2016

ሁለቴ የኔ ነሽ፡፡ (2)

/ካለፈው የቀጠለ/      
   

እሮብ ነሐሴ 11 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

       ኤሎሂም የእርሱ ሥራ በሆነው ፍጥረት በኩል የጥበቡ ኃይል ብርታት ይገለጣል፡፡ ስለ ፍጥረት በተጻፈበት ክፍል ‹‹አቤቱ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፤ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፤ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች፡፡›› (መዝ. 103፡24) ተብሏል፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ እጁ ሠርታናለችና (ዘፍ. 2፡7) ስለ እኛ ሕያው እግዚአብሔር እጅግ የተመሰገነ ይሁን፡፡

       ዓለም ከተፈጠረበት ይልቅ፤ የበደለው ዓለም የዳነበት የእግዚአብሔር ጥበብ እንደሚበልጥ ሲነገር ሰምታችሁ እንደ ሆነ አስባለሁ፡፡ የእግዚአብሔር የኃይሉ ታላቅነትና የብርታቱ ጉልበት የሚታይበትን ሁለተኛውን ታላቅ ጥበብ ስናነብ ‹‹እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን፡፡›› (ኤፌ. 2፡10) ተብሎ እናነባለን፡፡ ልብ በሉ! በዚህ ክፍል ላይ ያለው መፈጠር አስቀድሞ ካየነው የተለየና አዲስ ነው፡፡ መፍጠር የሚለውን ቃል በተመለከተ ግን በግሪኩ ተመሳሳይ ግስ የምናገኘው በሮሜው ባየነውና በዚህ በኤፌሶኑ ክፍል ብቻ ይሆናል፡፡
      
        ብዙ ብልሽቶች እድል ከተሰጣቸው መሻሻል እንደሚያሳዩ፤ ደግሞም ለውጥ እንደሚያመጡ ሊታሰብ ይችላል፡፡ ዳሩ ግን የሞተ ሰው ወዴት ይሻሻላል? በስንት የትምህርት ክፍለ ጊዜስ ይለወጥ ይሆን? (ሮሜ 6፡23) ኃጢአት ሞትን ያመጣበት ሰው፤ እግዚአብሔርን ‹‹ከመፍጠር›› ያነሰ ነገር አልጠየቀውም፡፡ ስለዚህም መጽሐፍ ‹‹ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው›› (2 ቆሮ. 5፡17) ይለናል፡፡ አስተውለን ከሆነ በጠና ታመው፤ ወደ ሞትም አፋፍ ደርሰው የተመለሱ፤ የእግዚአብሔር ምሕረት እድል የሰጣቸው ሰዎች እንደ አዲስ ተፈጥረው እየኖሩ እንዳለ ሲሰማቸውና ሲያወሩ እንሰማለን፡፡ በእርግጥም በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት የሆነ ሰው በእምነቱ ውስጥ ሊሰማው የሚችለው ነገር እንደዚሁ ነው፡፡

       ደኅንነት አዲስ ፍጥረት የሆንበትን ስፍራ በእምነት መያዝ ነው (ገላ. 3፡26)፡፡ ይህም የክብር አባት እግዚአብሔር በልጁ በክርስቶስ ያደረገው ነው (ኤፌ. 1፡6፤21)፡፡ እግዚአብሔር ለመዳናችን በሠራው ሥራ ብቻውን ክብር ይወስዳል፡፡ ዛሬ ስለ ኃጢአታችን በሞተውና ከሙታን ተለይቶ በተነሣው፤ በማያልፍ የሕይወት ኃይል በሚኖረውና ወደፊት ጠላቶቹ የእግሩ መረገጫ በሚደረጉት በኢየሱስ የመለኮት ኃይልና መቻል ግልጥ ነው፡፡ ‹‹መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው›› (ዮሐ. 1፡18) ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ ‹‹ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነው›› (ሮሜ 1፡16)፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ፍጥረታትን በመፍጠር ከተገለጠው የእግዚአብሔር  ጥበብና ክንድ በላይ ለማዳን የሆነው ኃይሉ ተገልጧል (1 ጢሞ. 1፡15)፡፡

       ሁሉ በእርሱና ለእርሱ የተፈጠረ (ቆላ. 1፡16)፤ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል የደገፈ (ዕብ. 1፡3)፤ መጽሐፉን ይወስድ ዘንድ፤ ኅተሞቹንም ይፈታ ዘንድ የተገባው (ራዕ. 5፡9) ጌታ በመፍጠርም በማዳንም በእኛ ላይ ብቸኛው ባለ ሥልጣን እርሱ ነው፡፡ እንኳን አድኖን (አዲስ ፍጥረት)፤ ፈጥሮንም (አሮጌ ፍጥረት) ጉልበት ሁሉ ለእርሱ ይንበረከካል (መዝ. 144፡15)፡፡ ‹‹ጌታችንና አምላካችን ሆይ፤ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና፤ ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል›› (ራዕ. 4፡11) እንደ ተባለ፤ እንዲሁ ደግሞ ‹‹የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል›› (ራዕ. 5፡12) ተብሎ ተጽፏል፡፡ መፍጠርም ማዳንም ከአንዱ ከእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

       ባለ ጥበቡ ጌታ ሆይ፤ ሁለቴ ያንተ ነን፡፡ ለምርጫችን ያልተውከን፤ ከላይ ወደ ታች መጥተህ የፈለከን፤ ለወዳጅ ከሚከፈለው በላይ ለጠላቶችህ የከፈልክልን፤ አዎ! በደላችን መተዉ ብቻው እንኳ በቂ ነበር፤ እንደ ጠላት አልቆጥራችሁም ብትለንም ይህ ከበቂ በላይ ነበር (ሮሜ 5፡10) ፤ ደግሞ ኩነኔውን አንስቻለሁ ብትለን ለእኛ እጅግ ከበቂ በላይ ነበር፡፡ አንተ ግን አልፈህ አደረክልን፤ የሚበቃውን ሳይሆን ግምታችን እንኳ የማይነካውን ወደ እኛ አቀረብከው ‹‹ልጆች ናችሁ›› አልከን፡፡ ኦ! ይህ ምንኛ ድንቅ ነገር ነው፡፡ ብዙ አሳዝነንህ ሳለ ጸጋህ ግን ‹‹ከመጠን ይልቅ በለጠ›› (ሮሜ 5፡20-21)፡፡ አባት ሆይ፤ ይህ ድምጽ ብቻ ያንበረክካል፤ ዓይን በዕንባ ሞልቶ በእግርህ ስር ያኖራል፤ ከዚህ ዓለም ልብህ ከሌለበት ነገር ሁሉ ይቀድሳል፤ አፍን በእልልታ ሞልቶ ከንፈሮችን በምስጋና ፍሬ ያደምቃል፡፡ እጅግ ተመስገን!

       የተወደዳችሁ ሆይ፤ እግዚአብሔር የእጁ ሥራ ለሆነው ለፈጠረው፤ በኃጢአት ምክንያት ደግሞ ለሞተው ሰው ዳግም የራሱ ስለ ማድረግ ኃይሉንና ጥበቡን ተጠቅሞ እድል ሰጥቶናል፡፡ ሁሉን የሚችል አምላክ ምን ያህል ምክንያት እንዳሳጣን፤ እጃችንንም በአፋችን ላይ የምንጭንበትን እንዳደረ ታስተውላላችሁን? ‹‹ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ . . ›› (ሮሜ 1፡21)፤ እንዲሁም ‹‹እኔ መጥቼ ባልነገርኋቸውስ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኃጢአታቸው ምክንያት የላቸውም፡፡›› (ዮሐ. 15፡22) አልተባለምን? እግዚአብሔር ለታላቅነቱ ፍጻሜ የለውም፤ እጅግም የተመሰገነ ነው (መዝ. 144፡3)፡፡

       እንግዲህ ከሰው ሁሉ ምክንያትን ትቆርጡ ዘንድ በዚህ ነገር እግዚአብሔርን ለመምሰል ራሳችሁን አስለምዱ፡፡ እግዚአብሔር ለፈጠረው እድል ከሰጠ፤ ዋጋ ከፍሎ ከሞት ካስመለጠ፤ በምሕረት እጁን ከዘረጋ፤ ኃይሉን ለማዳን ከተጠቀመ፤ እንዲሁ እኛም ላልፈጠርነው ግን እግዚአብሔር ለፈጠረው፤ ሲያልፍም ላዳነውና ሕይወት ለሰጠው ሰው ‹‹ሁለተኛ የእኛ›› ለማድረግ ጌታ ክርስቶስን እያየን ልንታዘዝ ያስፈልገናል፡፡ በቃሉ ያለው እውነትና መንፈሱ በቆሰላችሁበት በዚያ ቦታ ላይ እንደ ዘይት ይፍሰስ፡፡ በአንዱ ሕይወት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፤ አሜን፡፡
                                     ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment