Wednesday, August 31, 2016

የተደረገልን /2/

              በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

 እሮብ ነሐሴ 25 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

           ተወዳጆች ሆይ፤ ጥበብ ለእናንተ ምንድነው? እውነተኛ ጥበብ መገኛው የት ነው? ጥበብን ስለ ማግኘት ልንከፍለው የምንችለው ዋጋ ስንት ነው? ባለፈው ክፍል ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ በቂ አሳቦችን አይተናል፡፡ ትክክለኛውን ጥበብ ጥበባችን አድርገን እንኖር ዘንድ ጸጋው ይርዳን፡፡

           ጽድቅ

           ‹‹ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ!›› (ኢሳ. 64፡1)፤ በቀደመው ኪዳን የነቢዩ የኢሳይያስ ብርቱ ጸሎትና መሻት ነበር፡፡ ይህንን ልመና ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርብ ምክንያት የሆነውን ነገር ስንመረምር ደግሞ ‹‹ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፤ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው . . ›› (ኢሳ. 64፡6) ተብሎ ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ከገባበት (ሮሜ 5፡12) ጊዜ አንስቶ የሥጋ ለባሽ ሁሉ ብርቱ የጋራ ጩኸት ‹‹የጽድቅ ያለህ›› የሚል ነው፡፡

       ‹‹ከርኩስ ነገር ንጹሕን ሊያወጣ ማን ይችላል? አንድ እንኳ የሚችል የለም›› (ኢዮ. 14፡4)፤ ‹‹ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ጻድቅስ ይሆን ዘንድ ከሴት የተወለደ ምንድር ነው?›› (ኢዮ. 15፡14) እንደተባለ፤ ደግሞ ነቢዩ ‹‹እግዚአብሔርን፡- አንተ ጌታዬ ነህ አልሁ፤ ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም፡፡›› (መዝ. 15፡2) እንዳለ፤ የሰው መፍትሔ የደኅንነት አምላክ ከሆነው ከእግዚአብሔር ብቻ እንደ ሆነ ሲጠበቅ ኖረ (መዝ. 67፡20)፡፡

       ወንጌላዊው ማርቆስ እንደጻፈው ‹‹ . . ሰማያት ሲቀደዱ መንፈስም እንደ ርግብ ሲወርድበት አየና፡- የምወድህ ልጄ አንተ ነህ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅ ከሰማያት መጣ›› (ማር. 1፡10)፡፡ እግዚአብሔር የነቢዩን ጸሎት የመለሰ ቢሆንም፤ ዳሩ ግን ልጁ ወደ ዓለም የመጣው በመለኮት የዘላለም አሳብና በተቀጠረ ዘመን ነው፡፡ መጽሐፍ ‹‹ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤›› (ገላ. 4፡4) እንደሚል፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ሆኗል፡፡

       ተወዳጆች ሆይ፤ ጽድቅ በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ፤ በጽድቅም ሕይወት፤ እንደዚሁም ሁሉ ጽድቅን ስላደረጉ (በክርስቶስ) ሕይወት ለሰው ሁሉ (ለሚያምኑ) ደረሰ (ሮሜ 5፡18-19)፡፡ ሐዋርያው ከጥበብ ቀጥሎ፤ በእግዚአብሔር እንመካ ዘንድ ክርስቶስ ጽድቅ እንደተደረገልን ይናገራል፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ ባለበት ክፍል ‹‹ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም›› (ማቴ. 5፡17-20) በማለት ተናግሯል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ ‹‹አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጧል፤ እርሱም ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው . . ›› (ሮሜ 3፡21) ይለናል፡፡

       ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ የሚበልጠው ጽድቅ በክርስቶስ የተገለጠው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፡፡ ይህም የእምነት አባት ከሆነው ከአብርሃም ጀምሮ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነው ‹‹በማመን የሚገኝ የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው›› (ሮሜ 4፡3፤ ገላ. 3፡6)፡፡ እንዲህ ይሆን ዘንድ ደግሞ ‹‹እርሱንም (ክርስቶስ) እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው . . ›› (ሮሜ 3፡25)፡፡

        በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት እናገኝ ዘንድ ክርስቶስ ጽድቃችን ሆኗአል፡፡ ‹‹የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም›› (ሮሜ 10፡3) እንደተባለ፤ ዛሬም በጻፎችና በፈሪሳውያን ጽድቅ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች ስለ መሆን የሚደክሙ ሁሉ ከክርስቶስ ተለይተው ከጸጋው የወደቁ ናቸው (ገላ. 5፡4)፡፡

       ኃጢአትና ሞት ወደ ዓለም የገባው በአንድ ሰው እንደ ሆነ፤ እንዲሁ ሰው በሆነው ዳሩ ግን ከዚህ ከኃጢአተኛ ዓለም ባልሆነው፤ ከተቀደደው ሰማይ ለእኛ ጽድቅና ሕይወት ሊሆን በመጣው በእግዚአብሔር ልጅ ደኅንነት ሆኗል (ኤፌ. 2፡5)፡፡ ሥጋ የሆነውን ቃል፤ አባቱ በአንተ ደስ ይለኛል ብሎታል (ዮሐ. 1፡14)፡፡ ሰማይ ተቀዶ እንዲህ ያለ ድምጽ የመጣለት ሥጋ ለባሽ ምድሪቱ ላይ አልነበረም ወደፊትም የለም፡፡ ሰው ከኃጢአት በታች የኖረበት ዘመን እግዚአብሔር ፍጹም ደስ የሚሰኝበት ጽድቅ በሰው ውስጥ እንዳልተገኘና እንደማይገኝም በቂ ማሳያ ነው፡፡

        ቤተ ሰዎቼ ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ጽድቅ ተገዝታችኋልን? ወይስ የራሳችሁን ጽድቅ ስለማቆም ሕያው እግዚአብሔር ላይ ታምጻላችሁ? ‹‹የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና››፡፡ እምነት ከመስማት ነው፤ ቃሉን እመኑ፡፡ ለምን እግዚአብሔር ጽድቅን በእምነት አደረገው የሚል ልብ ቢኖር፤ ‹‹ . . ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ›› መልስ ነው፡፡

ይቀጥላል -

                                   ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment