Wednesday, August 24, 2016

የተደረገልን

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

እሮብ ነሐሴ 18 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

       ማንኛውም እውነተኛ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ትክክለኛ ኅብረት ከእርሱ ዘንድ የተደረገለትን በማወቅና በማመን ይጀምራል፡፡ እንዲህ የማይጀመር መንፈሳዊ ኑሮ እግዚአብሔርን ተቀባይ ራሱን ደግሞ ሰጪ አድርጎ ይሰይማል፡፡ እግዚአብሔር በፊቱ ከምናሳያቸው ትጋቶች ሁሉ በላይ ከእርሱ ለእኛ ያደረገውን ማወቃችን በእጅጉ ደስ ያሰኘዋል፤ ክብርና ምስጋናንም ያመጣለታል፡፡ ‹‹ነገር ግን፡- የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ፤ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው፡፡›› (1 ቆሮ. 130) ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ እግዚአብሔር ያደረገው ሁሉ በእርሱ እንመካበት ዘንድ የተደረገ ነው፡፡

        የቆሮንቶስ መልእክት መጀመሪያይቱ በቤተ፡ ክርስቲያኒቱ (ማኅበረ ምእመናን) የነበረውን መንፈሳዊ ችግር ለመፍታት እንደ መጻፉ፤ በመልእክቱ መጀመሪያ ምእራፍ መንፈስ ቅዱስ ይህንን አሳብ ማጻፉ የቀጣይ መፍትሔ አሳቦች ትልቅ መሠረት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ላይ የማይደገፍ ሰው፤ ቢያንስ አንድ ሌላ የሚደገፍበት አለው፡፡ ሰው ከምንም ነገር ነጻ ቢሆን እንኳ፤ ከራሱ ግን ነጻ አይደለም፡፡ ሕያው የሆነ አምላካችን እግዚአብሔር ደግሞ በሌላው ቀርቶ በራሳችንም እንድንመካ አይፈቅድልንም፡፡ ‹‹ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም›› (ኤፌ. 28) ተብሎ ተጽፎአልና፡፡

         ምእራፍ አንድ፡ - በአሁኑ ዓለም የቤተ፡ ክርስቲያን መለየትና ምስክርነት፡፡

አከፋፈል፡ -

1. በጸጋው የተደረገልን፤ እንዲሁም የተሰጠን ዋስትና (11-9)
2. ክርክርና መለያየት (110-16)
3. የክርስቶስ መስቀልና የእግዚአብሔር ኃይል (117-31)

           ሐዋርያው ጳውሎስ በድካም ውስጥ ያሉትን የቆሮንቶስ ማኅበረ ምእመናን ‹‹ወንድሞች ሆይ፤ መጠራታችሁን ተመልከቱ›› (1 ቆሮ. 126) በማለት ያሳስባቸዋል፡፡ ክርስትና ጥሪ ነው፡፡ በክርስቶስ ጸጋ (ገላ. 16) ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት (1 ቆሮ. 19) በቅዱስ አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነው (2 ጢሞ. 19)፡፡ እርሱ ደግሞ የታመነ ነው (2 ቆሮ. 1፡18)፡፡

           የቆሮንቶስ ቤተ፡ ክርስቲያን የተመሠረተችውም በዚሁ የእውነት ዓምድና መሠረት ነው (1 ጢሞ. 315)፡፡ እኛ ከሰማያዊው ጥሪ (ዕብ. 31) ተካፋዮች እንድንሆን፤ እግዚአብሔር የምንድንበትን ሙሉ ነገር ማድረግ አስፈልጎታል (ቲቶ 2፡11)፡፡ ‹‹ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው . . ›› (ሮሜ 832) እንደ ተባለ፤ ስለ ሁላችን ተላልፎ በተሰጠው በክርስቶስ (ሮሜ 424-25) ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብ፤ ጽድቅ፤ ቅድስና እንዲሁም ቤዛነታችንን አግኝተናል (ኤፌ. 17)፡፡  

        እግዚአብሔር እውነተኛ አምላክ ነውና ያለው እንዲሆን ይጠይቀናል፡፡ ስለዚህም ‹‹ . . ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ›› መታዘዝ ያስፈልገናል፡፡ ብዙ ሰውየምኖረው የተጻፈልኝን ነውይላል፤ ዳሩ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ልንኖረው የተጻፈልንን ውድ አሳብ በፊታችን ያቀርባል፡፡ ከዚህ የዘላለም አሳብና ምክር ውጪ የተጻፈልን ምን ሊሆን ይችላል? እናንተን በተመለከተ ከፈጠራችሁ አምላክ በቀር የእናንተ ሙሉ ነገር እውቀት ያለው ማንም እንደሌለ ካመናችሁ በእርግጥም የእርሱ እስትንፋስ የሆነውን ቅዱስ ቃል የሕይወት መመሪያችሁ ለማድረግ አትቸገሩም፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ የመከረውንና የገለጠውን ማስተዋል መቻል ያልተጻፈልንን ከመኖር ይጠብቀናል፡፡   

        ሰው በራሱ አልያም ከሰው በተደረገለት ፍጹም ሊረካ አይችልም፡፡ በአንድ መንገድ ጉድለታችሁን የሞላ ቢኖር፤ እርሱ ራሱ በሌላ ነገር ጎድሎ ታገኛላችሁ፡፡ ሐኪሙ የመሐንዲሱን እርዳታ እንደሚፈልግ፤ መሐንዲሱም የሐኪሙን እርዳታ ይፈልጋል፡፡ ትልልቅ የሚባሉ ተግባራትን የሚያከናውኑ ሰዎች የቤታቸውን በር እጀታ ብልሽት መጠገን አይችሉም፡፡ ደካማና የተናቀ የሚመስለው ሰው ግን ያንን ያስተካክለዋል፡፡

        ስለዚህ ምድራችን የምንፈልገውን ሁሉ የምናገኝበት አንድ ቦታና ሰው የላትም፡፡ ዳሩ ግን ሁሉንም የሚያስፈልገንን መልካም የምናገኝበት አንድ የት ይሆን ያለው? ቤተ ሰዎቼ፤ ከእግዚአብሔር በተደረገልን የሚረካ ልብ ሊኖረን ያስፈልጋል (1 ዜና. 16፡10)፡፡ ‹‹በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና›› (ቆላ. 2፡9) ተብሎ እንደ ተጻፈው፤ ‹‹ . . ክርስቶስ ሁሉ ነው፤ በሁሉም ነው›› (ቆላ. 3፡11)፡፡     

        ጥበብ፡

        እኛና የአሁኑ ዓለም በእያንዳንዱ ዛሬ ‹‹ሞኝ›› እየተባባልን መኖራችን በቃሉ የተገለጠ እውነት ነው፡፡ ‹‹የዚህች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነውና›› (1 ቆሮ. 3፡19-20)፤ እንዲሁም ‹‹ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና›› (1 ቆሮ. 2፡14) ተብለናል፡፡ ዓለም እግዚአብሔር ፊት እና እግዚአብሔር በአሁኑ ዓለም ፊት በመካከላቸው ያለውን ግልጽ ልዩነት ማስተዋል ያስፈልጋል (ዮሐ. 17፡16)፡፡

        ለሰው እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ጥበብ ነው፡፡ በንግግር ቢሆን በማድረግ ጥበብ ልንሻው አስፈላጊያችን ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ኢዮብ ‹‹ጥበብ የምትገኘው ወዴት ነው? የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው?›› (ኢዮ. 28፡12) የሚል ትልቅ ጥያቄ ያነሣል፡፡ ፍለጋውን አቀርቅሮ ይጀምራል፤ ‹‹ . . በሕያዋን ምድር አትገኝም፡፡›› የፍለጋው የመጀመሪያ ውጤት ነበር፡፡ ደግሞ ቀና ብሎ ፍለጋውን ይቀጥላል፤ ‹‹ቀላይ፡- በእኔ ውስጥ የለችም ይላል›› በማለት ደግሞ የተባለውን ያስተጋባል፡፡

        በምዝምዝ ወርቅ፤ በሰንፔር፤ በአልማዝ . . ጥበብ እንደማትገመት የሚነግረን ኢዮብ፤ በመጨረሻ ‹‹የጥበብ ዋጋ ከቀይ ዕንቁ ይልቅ ይበልጣል›› (ኢዮ. 28፡18) ይለናል፡፡ በዚህም እውነተኛ ጥበብ፤ ሰው እጁ ላይ ባለው ቁሳዊ ነገር፤ አልያም በራስ ድካምና ጥረት እንደማትገኝ እንረዳለን፡፡ አገልጋዩ ‹‹አይቴ ብሔራ ለጥበብ››፤ የጥበብ አገሯ ወዴት ነው? እያለ ይዞራል፡፡ ይወጣል ይወርዳል፤ ይቧጥጣል ይምሳል፤ ሽቅብ ቁልቁል፤ ቀኝ ግራ ብሎ ማረፊያ ያገኛል፡፡ ‹‹ጥበብሰ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ››፤ ጥበብ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ‹‹ . . የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው›› (1 ቆሮ. 1፡24)፡፡

        ‹‹ጥበበኞች ነን ሲሉ . . ›› (ሮሜ 1፡22)፤ ሰው እግዚአብሔር ጥበብ ያደረገው ‹‹ጥበብ ነው›› ብሎ ካላመነ ውጤቱ ‹‹ . . ደንቆሮ ሆኑ›› የሚል ነው፡፡ ምድር በደምና በሥጋ ብልሃት ጭንቅን አትርፋለች፤ በልቡ የላይኛውን ጥበብ የሚከተል ግን እርሱ ምስጉን ነው፡፡ የሰውን ውድቀት ተከትሎ ሰው ያጣው አንዱ የእግዚአብሔር መልክ እውቀት/ ጥበብ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ላጣነው ጥበብና እውቀት መለኮታዊ መፍትሔ ነው፡፡

        ተወዳጆች ሆይ፤ ‹‹ . . ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች . . ›› (1 ቆሮ. 1፡21) ተብሎ እንደተጻፈው፤ ከሰማይ የሆኑ መለኮታዊ ምክሮችን በራስ ማስተዋል፤ ከዚህም ዓለም በሆን እውቀት መረዳት አይቻልም፡፡ ይህንን ጥበብ ስለ ማግኘትና በዚህ ጥበብ ስለ መመላለስ የሚያስብ ማንም ቢኖር ‹‹የጥበብ ዋጋ ከቀይ ዕንቁ ይልቅ ይበልጣል›› የተባለውን ልብ ይላል፤ እንግዲህ ይህ ጥበብ እንዴት ሊገኝ ይችላል? መልሱ፡- ‹‹በስብከት ሞኝነት . . ›› የሚል ነው፡፡ ‹‹እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? . . እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው፤ መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው›› (ሮሜ 10፡14-17)፡፡

         ተወዳጆች ወዳጆቼ ሆይ፤ ለጉብዝናችሁ ቢሆን፤ ለትዳራችሁ፤ ለግንኙነቶቻችሁ ቢሆን፤ ለአገልግሎታችሁ፤ ክርስቶስ ጥበብ ነው፡፡ እምነት ደግሞ የዚህ ጥበብ ተጠቃሚዎች የምንሆንበት መንገድ ነው፡፡ የምናምንበት መሠረት ደግሞ ቃሉ ነው (የስብከት ሞኝነት)፡፡ ጥበብ የምትገኝበት መንገድ ለምን እንዲህ ብቻ ሆነ? ብሎ ለሚጠይቅ አእምሮ፤ መልሱ ‹‹ . . ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ፡፡›› (1 ቆሮ. 129) የሚል ነው፡፡

                                                                        ይቀጥላል -

                               ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment