በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
እሑድ መስከረም 1 ቀን 2009 የጸጋ ዓመት
ቀጣዩን (የሚሆነውን)
የማወቅ ጉጉት በማንኛውም ሰው ውስጥ ያለ የጋራ ፍላጎት እንደ ሆነ ይስተዋላል፡፡ ምንም እንኳ ‹‹ነገ ለራሱ ይጨነቃልና፤ ለነገ
አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል›› (ማቴ. 6፡34) ተብሎ በቅዱሱ መጽሐፋችን የተጻፈ ቢሆንም፤ ምድር ብርቱ ሠልፍ አላትና በክርስትናችንም
እንዲህ የምናውቀውን ቃል መታዘዝ ጭንቅ ይሆናል፡፡ ደግሞ ቀጣዩ ምን ይሆን?፤ ኖሬ ምን ይገጥመኛል? የሚሉ ጥያቄዎች፤ ‹‹አይመጣምን
ትተሽ ይመጣልን አስቢ›› አይነት አባባሎች . . ወዘተ፤ ሰው በቀጣዩ ላይ ያለው ሥጋት ከፍተኛ መሆኑን ያሳብቃሉ፡፡
በመጽሐፍ ቅዱሳችን የመጀመሪያ ክፍል ‹‹ያዕቆብ ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ
አለ፡- በኋለኛው ዘመን የሚያገኛችሁን እንድነግራችሁ ተሰብሰቡ፡፡›› (ዘፍ. 49፡1-28) ተብሎ ተጽፎአል፡፡ የብዙዎች አባት አብርሃም፤
ሳቅ የሆነውን ይስሐቅን ወለደ፤ እርሱ ደግሞ አሰናካይ የሆነውን ያዕቆብን ወለደ፡፡ ያዕቆብ ከእርሱ ከራሱ በሆነው ብልጣ ብልጥነት
ብዙ ዘመኑን የደከመ ቢሆንም በጎልማስነቱ ጊዜ ከአምላክ ጋር ታገለ፤ አልቅሶም ለመነው (ሆሴ. 11፡4)፡፡ እግዚአብሔር ያዕቆብን
ስሙን ለእግዚአብሔር የሚዋጋ ሲል እስራኤል አለው፡፡ ያዕቆብ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ወደ ማድረግ የመጣው ከስሙ መቀየር
ጋር ተከትሎ ሆነ፡፡ ይህም በቀጣይ ኑሮው ላይ ግልጽ ለውጦችን አምጥቶአል፡፡
መድኃኒታችን ኢየሱስ ለአገልግሎቱ ሾሞ፤ ታማኝ አድርጎ የቆጠረውን ሐዋርያ
ጳውሎስ (1 ጢሞ. 1፡12) አስቀድሞ የነበረውን ስም በመቀየር (ሐዋ. 9)፤ ታናሽ የሚለውን የስም ፍቺ ይዞ ለጌታ ምርጥ ዕቃው
ሆኗል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስምን ከተግባራዊ ባህርይ ጋርም ያያይዘዋል፡፡ በእርግጥም ዙሪያችንን አጥርተን ብናይ ስም በባህርይ ላይ
ያለውን ተጽእኖ በግልጽ ልናይ እንችላለን፡፡ ሰው ዘመኑን በብዛት የሚሰማው የራሱን ስም ነውና፡፡ ወላጆች ለልጆች የስም ስያሜ ሲያወጡ፤
ልጆችም በወጣላቸው ስያሜ ሲጠሩ ማስተዋልና ለዚያ መጠንቀቅ ተገቢ ይሆናል፡፡