ከበርሃማው የመልክዓ ምድር ክልል አንዱ፤ ከጥቂት መልካሞች እንደ
እድለኛ ያደኩበትን የድሮውን ሳስታውስ ከማረሳቸው ሰዎች መካከል የድጓ
መምህር የኔታ ብርሃኑ አንዱ ነበሩ፡፡ ሰው ለእግዚአብሔር በማይታጭበት፤ በልዩ ልዩ ሱስ መጠመድ እንደ ነቄ በሚያስቆጥርበት፤ ለሕያው
አምላክ ማድላት ፋራና ፈሪ በሚያሰኝበት መዝሙረ ዳዊት ሁለቴ ዘልቆ ማጠናቀቅ እንደ ብርቅ በሚታይበት ማኅበረሰብ፤ እንደተረዱት መጠን
ለእግዚአብሔር አገልግሎት ወንዶችን ያቀርቡ ዘንድ የኔታ በትጋት ያስተምሩን ነበር፡፡
አንድ ቀን የሰኞ መስተጋብ ላዜም በተለመደው ሰዓት ወደ መቃብር
ቤታቸው ስሄድ፤ በበሩ ትይዩ ባለው ሽቦ አልጋቸው ላይ በቁጭ አቀርቅረው ትልቅ መጽሐፍ ያነባሉ፡፡ ወደ ውስጥ ለመዝለቅ ፈቃዳቸውን
በሚጠይቅ ዜማዊ አነጋገር የኔታ . . የኔታ . . እያልኩ በተደጋጋሚ ከስተውጪ ወደ ውስጥ ገርበብ ባለው ብረት በር በኩል እጣራለሁ፡፡
መልስ ለመጠበቅ በቂ እንደ ሆነ ያሰብኩት ሰዓት ሲያበቃ፤ ዝምታውን
አቋርጬ፤ በሩን በትህትና ከፍቼ ወደ ውስጥ ገባሁ፡፡ የኔታ የእኔን እግር ተከትሎ እየጨመረ እየጨመረ የመጣውን የፀሐይ ብርሃን ሽቅብ
እያዩ፤ ቁጭ እንድል በእጃቸው ጠቅሰውኝ ጥቂት ማንበባቸውን ቀጠሉ፡፡ የኔታን ከቁንጥጫና ከልምጭ ጋር ያያያዘው የልጅ አእምሮዬ ዓይኔን
ቀና እንዲል ማዘዝ እየተሳነው አቀርቅሬ ቆየሁ፡፡
የኔታ ጉሮሯቸውን ጠርገው መጽሐፌን እንድገልጥ ትእዛዝ ሲሰጡ፤ ድምፃቸውን
ተከትሎ ያሻቀበው ዓይኔ ሁለት ጆሮአቸው ላይ አረፈ፡፡ በዚያው ተመሳሳይ ጊዜ ሁለት እጆቻቸውን አንሥተው ከሁለት ጆሮአቸው ዘይት
የተነከረ ጥጥ አወጡ፡፡ ጥያቄ ላዘለው ቁልጭ ቁልጭ የሚል ዓይኔ ምላሽ ሲሰጡ ‹‹ቅድም ያልሰማሁህ፤ መስሚያዬ ጥጥ ስለነበረ ነው›› አሉኝ፡፡ ቀበል አድርጌ፤ ‹‹ምነው!
ታመው ነው?›› አልኳቸው፡፡ ‹‹አየህ ልጄ! ስታነብ ከልብህ አትሰማም፤ ስትሰማ ደግሞ ከውስጥህ አታነብም፡፡ ጥጡን ያደረኩት አሞኝ
አይደለም፤ የታመመ ወሬ እንዳልሰማ ብዬ እንጂ፡፡ የማነበው መልካሙን
ስለሆነ ክፉው እንዲሻማኝ አልፈቅድም፡፡
ጥጡን ዘይት ስለነከርኩት ደግሞ እምቢታዬ ተጨምሮ ምንም ሌላ አልሰማም፡፡
አንተም ነገ ታድጋለህ፡፡ መርጠህ መስማትን ዛሬ ጀምረህ ልብ አድርግ፡፡ በጆሮ የገባም ያረክሳል፡፡ አንተ ጮኸህ እያዜምክ እኔ ማረም
ብጀምር አንተ ፈጥነህ ታቆማለህ፤ እንደዚያ ባይሆን ግን ስህተቱን
ስትጮህ ትኖራለህ፡፡ . . ›› በመሐል የዘገዩት ተማሪዎች ወደ ውስጥ ሲገቡ እነርሱን እያዩ ‹‹እግዚአብሔር ከወሬ ስስትና
መስገብገብ ይጠብቅህ፡፡›› ብለው መረቁኝ፡፡ በዚያው መማር ማስተማሩ ቀጠለ፡፡ /የኔታ እዚህ አዲስ አበባ መጥተው እንጦጦ ማርያም
በድጓ መምህርነት ተቀጥረው ሲያገለግሉ ዓይናቸው ደክሞ ታመው ሞተዋል፤ ምክራቸው ግን ዛሬም ይታወሰኛል/፡፡
እንዲሁ ከሁለት ዓመት በፊት የስነ ልቦና ማማከር ሁለተኛ ድግሪ
ትምህርቴን ስከታተል በክፍለ ጊዜው ሁሉ ‹‹ጥሩ አድማጭ ያልሆነ፤ መፍትሔ ፈላጊውን አይረዳውም›› የሚል ተደጋጋሚ አሳብ ወደ እኛ
ሲወረወር ይታወሰኛል፡፡ እኔም እንደ ጌታዬ እንዲህ እል ነበር ‹‹ሰሚዎች ብዙዎች ናቸው፤ አድማጮች ግን ጥቂቶች››፡፡ ተወዳጆች
ሆይ፤ መንደርደሪያው እንዳልረዘመባችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ደግሞ ቢሆንም በረራው ረዥም ስለሆነ በመልካም ትታገሱታላችሁ፡፡
ምድራችን ከአየር ብክለት ያልተናነሰ በድምጽ ብክለቶች እየተናጠች
ነው፡፡ ዓለም በሰፋፊ መንገዶች ግን በጠበቡ አመለካከቶች፤ በተዋቡ ሕንጻዎች ግን ደግሞ በወየቡ አመሎች ተጨንቃለች፡፡ ሰዎች ብዙ
ሰብስበው ጥቂት የማይደሰቱበት፤ ብዙ አውቀው ያነሰ የሚተገብሩበት፤ ብዙ ሙያ ጥቂት መፍትሔ የጠፋበት የዘመን ጭራሽ ላይ ነን፡፡
ሁሉም ‹‹ማጣሪያ›› የሚል የተለጠፈበት ይመስላል፡፡ ሰዎች ጨርሰው አውርተው ወሬ የሚዋሱበት ጊዜ ይመስላል፡፡ ጠቢቡ ‹‹ . .
ዓይን ከማየት አይጠግብም፤ ጆሮም ከመስማት አይሞላም›› (መክ. 1፡8) እንዲል፡፡
ጠቢቡ
በሌላ ስፍራ ‹‹ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል›› (መክ. 7፡5) ይለናል፡፡ በዚህ ክፍል
ከሰነፎች ዘንድ ከሚመጣው የሚስብ ዜማ ይልቅ፤ ከጠቢባን የሆነው መራራ ተግሣጽ ሚዛን ደፍቷል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለማናደርገው ሲነግረን፤
እንዲሁ ስለምናደርገው ደግሞ ይነግረናል፡፡ ሽሹ ሲለን ቅረቡት የሚለንን ማስተዋል አለብን፡፡
ታዘዙት ሲለን ደግሞ የምንቃወመውን መረዳት አለብን፡፡ በእግዚአብሔር
ቃል ውስጥ አሉታውያን የሆኑ ግን መታዘዞች የሆኑትን ልብ እንላለን፤ ነቢዩ ‹‹በጽድቅ የሚሔድ . . ›› ብሎ ‹‹ . . ከመስማት
ጆሮቹን የሚያደነቁር . . ነው›› (ኢሳ. 33፡15-16) ይላል፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ለእግዚአብሔር መታዘዝ (በጽድቅ መሔድ) መስማት
ሳይሆን አለመስማት ነው፡፡ በምንሰማው ውስጥ መታዘዝ እንዳለ ሁሉ ባለ ማድመጥ ውስጥም መታዘዝ አለ፡፡
በነቢዩ
በኤርምያስ ደግሞ ‹‹እነሆ፤ ጆሮአቸው ያልተገረዘች ናት፤ ለመስማትም አይችሉም፡፡ እነሆ የእግዚአብሔር ቃል ለስድብ ሆኖባቸዋል፤
ደስም አያሰኛቸውም›› (ኤር. 6፡10) ተብሎ እናነባለን፡፡ እግዚአብሔርን መስማትን እምቢ ማለት ውድቀቱ በዘላለም ሞት የሚሰላ
ነው፡፡ ከእግዚአብሔር የሆነውን ባለ መስማት ውስጥ በእያንዳንዱ ጊዜ ጥፋት አለ (ሐዋ. 3፡23)፡፡ መስማት እምነትን ያመጣል
(ሮሜ 10፡17)፤ ትክክለኛውን እምነት በውስጣችን የሚያመጣው ግን እግዚአብሔርን ብቻ መስማት ነው፡፡
ሐዋርያው
እውነተኛ የእምነት ልጁን ሲመክረው ‹‹ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ
ስለ ሆነ . . እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ›› (2 ጢሞ. 4፡4) ብሎታል፡፡ ጢሞቴዎስን
በተመለከተ ጨምሮ ሲናገር ‹‹አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፤ መከራን ተቀበል የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ አገልግሎትህን
ፈጽም፡፡›› ይለዋል፡፡ ይህ ምንኛ የተወደደ በጽድቅ ያለ ምክር ነው!
እንግዲህ መስማትና አለመስማት ማስተዋልን የሚጠይቅ ነገር ሆኖ በቃሉ
ውስጥ ቀርቦአል፡፡ ቤተ ሰዎቼ፤ ስለምትሰሙት ጠንቃቆች ልትሆኑ ያስፈልጋችኋል፡፡ በምታደምጡት እውነት ያልሆነ ላለመወሰድ ንቁዎች
ሁኑ፡፡ በሐሰት ወሬ ነፋስ አትነዋወጡ፡፡ ክርስቶስ ‹‹በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ ይከተሉኝማል . . ›› (ዮሐ.
10፡27) እንዳለ፤ እውነተኛ በጎች የእረኛቸውን እውነተኛ ድምጽ የመለየት ችሎታ ያላቸው ናቸው፡፡ ከዚህ ውጪ ለሆነው ግን እንደ
የኔታ ጥጥ አርጉበት፤ ደግሞ ዘይት ይኑረው፡፡ በደንብ! በደንብ!
የማይረባንን የምናስቀርበት፤ ከሰማይ በሆነው ላይ ትኩረት የምናደርግበት፤
ወደ ቀኝም ወደ ግራም ላንል የምንጸናበት የጥጡ ላይ ዘይት በውስጣችንና በዘንዳችን የሚሠራው ‹‹ወደ እውነት ሁሉ የሚመራን መንፈስ
ቅዱስ›› ነው (ዮሐ. 16፡13)፡፡ ጥጡ ደግሞ የቀለሙን ንጣት ወስደን ከቅድስና ጋር ልናያይዘው ይቻለናል፡፡ ‹‹በእውነትህ ቀድሳቸው፤
ቃልህ እውነት ነው›› (ዮሐ. 17፡17) እንደተባለ፤ የሚቀድሰውን እውነት በጆሮአችሁ ተቅጥቁት፡፡ ቃሉና መንፈሱ አይነጣጠሉም!
መልካሙን የምስራች የሚያነቡ ሁሉ እንደዚህ ዓለም ለሆነው ከንቱ መለፍለፍ
‹‹መስሚያቸው ጥጥ›› ነው፡፡ ወደ ውስጥ እንዲዘልቅ እንዲቆጣጠራቸው፤ በጎውን እንዲጋፋው፤ ቅዱሱን እንዲያረክሳቸው አይፈቅዱም፡፡
እንደነዚህ ያሉቱ ዘወትር የሚሰሙት ዓላቸው በዋጋ ከገዛቸው በቀር ማንም በቀላሉ ትኩረታቸውን አያገኝም፡፡ ኑሮአቸውም ከክፉው ሽሽግ
ነው፤ የእጁም ዝርጋታ አይነካቸውም፡፡
መጽሐፍ
‹‹ከጋለሞታ ሴት ከንፈር ማር ይንጠባጠባልና . . ›› (ምሳ. 5፡3) እንደሚል፤ ‹‹ቃልህ ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ
ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ፡፡›› (መዝ. 118፡103) ደግሞ እንደተባለ፤ ያኛው ማር፤ ይህን ወለላ ሊያራክሰው፤ አቻው ሆኖም ሊተካከለው፤
እውነቱን አሽሾ እርሱ ሊጣፍጥ እንደማይችል፤ ከሕያው እግዚአብሔር መስማትን አታስታጉሉ፡፡ ቤተ ሰዎቼ፤ ቃሉና መንፈሱ በሙላት ይኑርባችሁ!
ይቀጥላል -
‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!
‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!
No comments:
Post a Comment