Monday, September 26, 2016

መልሱ ላይ ጥያቄ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


ሰኞ መስከረም 16 ቀን 2009 የጸጋ ዓመት

‹‹ፍቅርም እውነትም ማን ነው?››

       ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመስቀል አደባባዩ ትልቁ ደመራ፤ ትንንሽ ደመራ ልጆች በየአካባቢው መታየታቸው እየተለመደ መጥቶአል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለበትን ብንመረምር ደግሞ ብዙ ምክንያቶችን ልናገኝ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰው በቀላሉ የሚያስተውለውን ለማየት ብንሞክር ሃይማኖታዊ መልክና ዓለማዊ መልክ ብለን በሁለት ልንከፍለው እንችላለን፡፡

      ከእምነት ጋር በተያያዘ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የመስቀሉን ቃል ይዞ ታሪካዊ የሆነውን ተዛምዶ በማስከተል በዓል የሚያደርጉትን ልብ ስንል፤ ከዚህ ውጪ የሆነው ደግሞ መጠጥ ማሻሻጫ፤ የሥጋን ጥያቄ በመንፈሳዊ ሽፋን ማርኪያ፤ ከአላፊ አግዳሚው ገንዘብ መሰብሰቢያ፤ መዝፈን መጨፈሪያ፤ ይህንንም የሚመስል ሁሉ ነው፡፡

      ለዚህ ጽሑፍ የመጻፍ ግፊት ኃይል የሆነኝ ዛሬ ማለዳ በተንቀሳቀስኩበት አካባቢ ዓይኖቼ የተመለከቱት ጽሑፍ ነው፡፡ ምሽት ሊለኮስ አንድ መጠት ቤት ፊት ለፊት የተደመረ ደመራ ጉልላት ላያ፤ የተመሳቀለውን እንጨትና ጉንጉን አበባ ታኮ በነጭ ወረቀት በጥቁር እስክርቢቶ የተጻፈ ‹‹ፍቅርም እውነትም ማን ነው?›› የሚል ትልቅ ጥያቄ ላይ ዓይኖቼ አረፉ፡፡ አሥር ደቂቃ ቆሜ ብዙ አሰብኩ፡፡ ነገር ግን ቀለል አድርጌ ላየው በሞከርኩ ቁጥር ዙር እየከረረ፤ ነገሩ እየከበደ መጣብኝ፡፡ እናም ውስጤ ‹‹መልሱ ላይ ጥያቄ›› የሚል ርዕስ ተፈጠረ፡፡

    ፍቅር እና እውነት በክርስትና ውስጥ እጅግ መሰረታዊ ነገሮች ናቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያው ጳውሎስ በኩል ‹‹ . . በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ›› ባለበት ክፍል ‹‹ . . እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ›› (ኤፌ. 4፡15) ይለናል፡፡ እውነት ያመንበት መሰረት ሲሆን፤ ፍቅር ደግሞ ያመነውን በተግባር የምንገልጥበት መንገድ ነው፡፡ እውነት ኖሯቸው ፍቅር የሌላቸው እውነቱን የብቻቸው ከማድረግ ጀምሮ ሌላውን ለመጉዳት ጭምር ሊያውሉት ይችላሉ፡፡ ፍቅር ኖሯቸው እውነቱ የሌላቸው ደግሞ ሚዛን በሌለው ፍቅር እውነትን እየረገጡ ይበድላሉ፡፡

      ሐዋርያው በኤፌሶን መልእክት በመጀመሪያዎቹ ሦስት ምእራፎች ስለ መሰረተ እምነት (ጥሪ) ካስተማረ በኋላ በቀጣይ ሦስት ምእራፎች ማለት ከምእራፍ አራት በኋላ ለጥሪው እንደሚገባ መመላለስን ይመክራል፡፡ እንዲሁ በእውነተኛ ክርስቲያን ሕይወት፤ መጀመሪያ መሰረተ እምነቱን መረዳት፤ ሲቀጥል ደግሞ ያ እምነት የሚጠይቀውን ኑሮ በተግባር መኖር የተገባ ነው (እምነት ያለ ሥራ እንዲል)፡፡

      ቅደም ተከተላዊ ፍሰቱ መቼም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ከዚህ የተነሣ በእያንዳንዱ በሚመጣው ዛሬ በእምነት የምናደርጋቸው ነገሮች በግድ የለሽነት የሚከወኑ ሊሆኑ ፈጽሞ አይችልም፡፡ ዳሩ ግን ተግባራዊ እውነታው በእኛ ዘንድ እንዲህ ነውን? የሚለው ጥያቄ የአንባቢውን መልስ በትህትና ይጠይቃል፡፡

     ‹‹ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ›› (ገላ. 6፡14) ተብሎ እንደተጻፈ፤ እውነትና ፍቅር በክርስቶስ መስቀል ተገልጧል፡፡ እርሱ መድኃኒታችን ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤›› ብሎናል፤ ደግሞ ‹‹ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም›› (ዮሐ. 15፡13) ተብሏል፡፡ የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ (1 ዮሐ. 4፡3) ጠላት ዲያብሎስ ግን ዛሬም መልስ በሆነው ክርስቶስ ላይ ጥያቄን ይለጥፋል፡፡ መልሱን እንዲያደበዝዙ ልዩ ልዩ ብልሐቶችንም ይጠቀማል፡፡


        ‹‹ . . ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ፡፡›› (ፊል. 2፡8) ተብሎ እንደተጻፈ፤ በዔደን ገነት ለእይታ እንኳ መልካም በሆነው ሥፍራ (ዘፍ. 2፡8-17) ባለመታዘዝ (ዘፍ. 3፡1-8) ለወደቀው ሰው፤ ክርስቶስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ እርግማን በመሆን (ገላ. 3፡13)፤ በክቡር ደሙ ዋጅቶናል (1 ጴጥ. 1፡18፤19)፡፡ መስቀልን ከክርስትናው ጋር ያያዘው እውነትና ፍቅር ይህ ነው፡፡ እኛ ለእግዚአብሔር ያደረግነውን ሳይሆን እርሱ ለእኛ ያደረገውን የምናስተውልበት ነው፡፡ ከእኛ ያላይደለ ከእርሱ የሆነው ደግሞ ጸጋ ነው፡፡ የሰው የጽድቅና የሕይወት ትልቅ ጥያቄ ምላሽ ያገኘበት መንገድ መስቀል ላይ የሞተው ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡

    ክርስቶስ ያልተሰቀለበት፤ እሾሁ ወርዶ አበባ የተጎነጎነበት፤ ሐሞቱ ተረስቶ የማር ጠጅ የፈሰሰበት፤ በጅራፍ ጎመዱ ፈንታ ወርቅ ብር ያረፈበት፤ እውነት ተከልሎ ሥጋ የሚታይበት ይህ የሰው መስቀል ነው፡፡ ሐዋርያው ‹‹ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር . . ›› እንዳለ ልብ በሉ፡፡ እንዲህ ያለው መስቀል ላይ ዛሬም መልስ ሳይሆን ትልልቅ ጥያቄ አለ፡፡ ሰላም ማነው? እረፍት ማነው? ጽድቅ ማነው? ፍቅር ማነው? እውነት ማነው? . . ማነው? . . ማነው? . . ማነው? 

       ተወዳጆች ሆይ፤ አትሳቱ! ክርስቶስ የሌለበት መስቀል ጥያቄ ነው፡፡ ጠላት ክርስቶስን እያወረደ ዋጋ ተከፍሎ እንዳልተከፈለ የሚያኖርበትን ብልሐት ንቁበት፡፡ መልሱ ላይ ጥያቄ የሚያኖርበትን አመፁን በጽድቅ ተቃወሙት፡፡ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የተገለጠው የእግዚአብሔር ጸጋ ሰዎችን ሁሉ ያድናል (ቲቶ 2፡11)፡፡ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን!                  
             



No comments:

Post a Comment